አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር በተገነቡት 10ሩም የክፍለ ከተማ ጽህፈት ቤት ህንጻዎች ላይ የአደጋ ጊዜ መውጫ አለመዘጋጀቱ አሳሳቢ ችግር መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ስራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮንስትራክሽን ቢሮ በበኩሉ ለህንጻዎቹ መደበኛ አገልግሎት የሚያገለግሉት እና በህንጻው የውስጠኛ ክፍል ግራ እና በቀኝ በኩል የተገነቡት ደረጃዎች ለአደጋ ጊዜ መውጫ በቂ በመሆናቸው ተጨማሪ መውጫ እንደማያስፈል ገልጿል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ስራ አመራር ኮሚሽን የአደጋ ስጋት ጥናትና ትግበራ ዳይሬክተር ወይዘሮ ሒሩት ሽፈራው እንደገለጹት፤ በህንጻዎች ላይ አስፈላጊውን የአደጋ ጊዜ መውጫ በማዘጋጀት ችግር ከመድረሱ በፊት ቀድሞ በመጠንቀቅ የሚደርሰውን አደጋ መቀነስ ይቻላል። በመሆኑም ማንኛውም ህንጻ ለአደጋ ጊዜ መውጫ የሚሆኑ መወጣጫዎች በህንጻው የውጭኛ ክፍል ሊዘጋጅላቸው ይገባል። በዚህ ረገድ የአዲስ አበባ ክፍለ ከተሞች ህንጻዎችም የውስጥ መመላለሻ ደረጃዎች ስላሏቸው ብቻ የአደጋ ጊዜ መውጫ አያስፈልጋቸውም ብሎ ማሰብ ተገቢ አይደለም።
የኮሚሽኑ የአደጋ ደህንነት ሙያ ምስክርና ቴክኒክ ድጋፍ ከፍተኛ ባለሙያ ወይዘሮ የውብዛፍ ዳምጤ እንደተናገሩት ደግሞ፣ የከተማዋ 10ሩም የክፍለ ከተማ ህንጻዎች ከመገንባታቸው በፊት ከኮሚሽኑ ባለሙያዎች ጋር በመነጋገር የአደጋ መውጫዎቹ ስለሚገነቡበት ሁኔታ መነጋገር ይቻል ነበር። በህንጻዎቹ በርካታ ሰዎች በየቀኑ የሚንቀሳቀሱ በመሆኑ ድንገተኛ አደጋ ቢከሰት እንኳን በደረጃዎቹ ብቻ ተጠቅሞ ለመውጣት አስቸጋሪ በመሆኑ ጉዳዩ አሳሳቢ ነው።
እንደ ወይዘሮ የውብዛፍ ገለጻ፤ ህንጻዎቹን ያለአደጋ ጊዜ መውጫ መገንባቱ ስህተት መሆኑ እሙን ነው። በመሆኑም አሁንም ቢሆን የአደጋ መውጫዎቹን መገንባት ያስፈልጋል። በእያንዳንዱ ህንጻ ላይ ቢያንስ ሁለት እና ሶስት የአደጋ ጊዜ መውጫዎችን በውጭኛው የህንጻዎቹ አካል መገንባት ካልተቻለ ጉዳዩ አሳሳቢ ነው። በዚህ ረገድ ወደፊት አስገዳጅ ህግ መውጣቱ ስለማይቀር ቀድሞ ማሰቡ ተገቢ ነው።
የአዲስ አበባ ኮንስትራክሽን ቢሮ የፕሮጀክት ጥናትና የዲዛይን ክትትል ዳይሬክተር አቶ ዳዊት ለሜሳ በበኩላቸው እንደተናገሩት፣ የክፈለ ከተሞች ህንጻ በአጠቃላይ ዲዛይናቸው ጸድቆ የግንባታ ፈቃድ ወጥቶላቸው የተሰሩ ናቸው። ህንጻዎቹም በግራና በቀኝ በኩል ሰፊና አደጋ ቢደርስ ታሳቢ ተደርጎ ለመውጫ የሚሆኑ እና በተመሳሳይ ደግሞ ለማንኛውም ቀን የሚያገለግሉ ደረጃዎች አሏቸው። በመሆኑም ህንጻዎቹ የግድ የአደጋ ጊዜ መውጫ ያስፈልጋቸዋል የሚለው ሃሳብ ተቀባይነት የለውም ብለዋል።
እንደ አቶ ዳዊት ከሆነ፣ በዲዛይን አሰራሩ መሰረት በሁለት አቅጣጫዎች የተገነቡ መወጣጫ ደረጃዎች ካሉ ተጨማሪ የአደጋ ጊዜ መውጫ መገንባት አያስፈልግም። እንደ አጋጣሚ የእሳት አደጋ ቢነሳ እንኳን ተገልጋዩ ሁለቱን ደረጃዎች ተጠቅሞ ለመውጣት እንደማይቸገር ታሳቢ ተደርጎ የተገነባ በመሆኑ ህንጻዎቹ ላይ ችግር የለም።
እንደ የየአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ስራ አመራር ኮሚሽን መረጃ መሰረት፤ ተቋሙ ፍተሻ በሚያደርግባቸው በርካታ የመዲናዋ ህንጻዎች ላይ የአደጋ ጊዜ መውጫዎች የሉም። አንዳንዶቹም በብረት የተሰሩ መውጫዎችን ቢያዘጋጁም ወደ ደረጃዎቹ የሚያስወጣውን በር በመቆለፍ ከታሰበላቸው አላማው ውጪ ለአደጋ ጊዜ መውጫነት እንዳያገለግሉ ሆነው ተቀምጠዋል። በመሆኑም በጉዳዩ ላይ ሰፊ የግንዛቤ ትኩረት ማነስ ይስተዋላል፣ ተቋሙም አስገዳጅ ህግ ስላልወጣለት ሙያዊ ምክር ከመስጠት ባለፈ የቁጥጥር ተግባራትን ማከናወን አልቻለም ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ህዳር 6/2012
ጌትነት ተስፋማርያም