አዲስ አበባ፡- ‹‹የኢህአዴግ ውህደት የጋምቤላ ክልል ራሱን በራሱ በትክክል የማስተዳደሩን መብትና በክልሉ የሚገኘውን ሀብት የመጠቀም መብት እንደሚያጎናፅፈው አምናለሁ›› ሲሉ የቀድሞው የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት ገለፁ።
የቀድሞው የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ኦኬሎ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፤ በአሁኑ ወቅት ኢህአዴግ ውህደት በመፍጠር አገርን በአንድነት እንምራ ማለቱ ቀደም ሲል በክልሉ የነበረውን ሳንካ ያስወግዳል የሚል እምነት አላቸው። ውህደቱ ከተተገበረ ክልሉ ለይምሰል ብቻ ራሱን በራሱ ያስተዳድር የነበረበትን ስርዓት ቀይሮ በትክክል ያለጣልቃ ገብ ለማስተዳደር ያግዘዋል። የክልሉም ህዝብ በክልሉ በሚገኘው ሀብት መጠቀም እንዲችልም ይረዳዋል።
‹‹እስካሁን ድረስ የክልሉ ፕሬዚዳንት ሆነው ያገለገሉ የጋምቤላ ተወላጆች ሁሉ በህዝብ ፍላጎት ተመርጠው የመጡ አይደሉም። እኔ ወደ ፕሬዚዳንትነት ከመምጣቴና በተፎካካሪ ፓርቲ ውስጥ በነበርኩበት ወቅት በህዝብ ተመርጬ ነበር። ይሁንና የነበሩት የህወሓት ካድሬዎች አንድን አካል ስልጣን ላይ እንዲቀመጥ የሚያደርጉት የጋምቤላ ህዝብ ስለፈለገው አይደለም።›› ያሉት አቶ ኦኬሎ፣ ‹‹ክልሉን ሲያስተዳድሩ የነበሩ ፕሬዚዳንቶች በራሳቸው ሐሳብና ፈቃድ ሳይሆን ሞግዚት ተቀምጦላቸው ነበር ማለት ይቻላል። ምክንያት ቢባል ደግሞ ከሁሉም ጎን የህወሓት አማካሪዎች በመኖራቸው ነው።
ፕሬዚዳንቶቹ ከላይ የተቀመጡ ይምሰሉ እንጂ ክልሉን ለማስተዳደር በራሳቸው የሚወስኑት አንዳች ነገር አልነበረም። ክልሉን የተመለከተም ይሁን ሌላውን ነገር ከመወሰናቸው በፊት በአማካሪ ስም በዙሪያቸው የተቀመጡ የህወሓት ካድሬዎች ከተወያዩና የሚከናወነው ጉዳይ በምን መልኩ መሄድ እንዳለበት ሐሳብ ከሰጡ በኋላ ነው። በዚህም ጣልቃ ገብነቱ ከፍ ያለ ነበር ማለት ነው።›› ሲሉ አክለው ተናግረዋል።
እንደ አቶ ኦኬሎ ገለፃ፤ የክልሉ ህዝብ በህወሓት ካድሬዎች አማካይነት በማማከር ስም ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱን እንዳይጠቀም ከመደረጉም በተጨማሪ የክልሉ መሬትም በኢንቨስትመንት ስም በመሸጥ አልቋል። በተለይ መሬቱን በማስያዝ ከልማት ባንክ ገንዘብ እየወሰዱ ተጫውተውበታል። በክልሉ ያለውን ሀብት የክልሉ ህዝብ እየተጠቀመበት አይደለም፤ በባለሀብት ስም ክልሉ ተወሯል። በአብዛኛው ደግሞ የተያዘው ከህወሓት ጋር ተያያዥነት ባላቸው ባለሀብት ነን ባዮች ነው።
ምንም ገንዘብ የሌለው ሁሉ እየተጠቀመ ያለው ከልማት ባንክ የጋምቤላን ክልል መሬት አስይዞ ነው። የክልሉን ህዝብ ከመሬታቸው በማፈናቀል ጭምር ነው መሬቱን ለባንክ በማስያዝ ገንዘቡን ሲጠቀሙበት የነበረው። እነዚህም አካላት ሀብታም የሆኑት እያየናቸው ነው እንጂ እንዳሉት ኢንቨስተር ሆነው አልነበረም። በክልሉ የተካሄደው ዝርፊያ ሲሆን፣ የሚቀናቀናቸውን እነሱን መሰል ሰዎች ከክልሉ እንዲሰደዱ አድርገዋቸዋል። ከዚህም በላይ በተለይ በርካታ ቁጥር ያላቸው አኝዋኮችን ለሞት ዳርገዋል፣ ንብረታቸው ተቃጥሏል፤ ብሎም ከአገር ተሰደዋል።
‹‹በአሁኑ ሰዓት ግን ተስፋ ሰንቀናል። ምክንያቱም ውህደቱ ሲመጣ ጋምቤላ በትክክል ራሱን በራሱ ማስተዳደር እንደ ሚችል እምነቱ አለኝ። በአንድነትና በኢትዮጵያ ህዝብ የሚያምን መንግስት ከመጣ የተወረሰው መሬት እንደሚመለስልን እናምናል። ከዛም ቀጥሎ ለክልሉ በሚመች መንገድ እንደምናደርግ እናውቃለን። ከዚህም የተነሳ ውህደቱ ትልቅ ተስፋ የተጣለበት ነው። እኛም የውህደቱ አንድ አካል እስከሆንን ድረስ መድረኩን እናገኛለን ብለን እናምናለን።›› ብለዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ህዳር 6/2012
አስቴር ኤልያስ