አዲስ አበባ፡- አላስፈላጊ የስብሰባ ወጪን በመቀነስ በአንድ ዓመት ብቻ 600 ሚሊዮን ብር ማዳን መቻሉን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሃጂ ኢብሳ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል እንደተናገሩት፤ ቀደም ሲል ከስብሰባ ጋር ተያይዞ ይዘጋጁ የነበሩ ኮፍያዎችና ቲሸርቶች ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ቆመዋል። ተቋማት በ2009 የወጣውን መመሪያ ተከትለው አላስፈላጊ ወጪዎችን በመቀነሳቸው ከያዙት የ2010 በጀት ውስጥ 600 ሚሊዮን ብር ወደገንዘብ ሚኒስቴር ተመላሽ ተደርጓል።
ዳይሬክተሩ፤ እንደነዚህ ዓይነት ወጪዎችን በአንድ ጊዜ ሙሉ ለሙሉ ማስቆም ባይቻልም በሂደት ለውጥ እየመጣ መሆኑን አመልክተው፤ በተለይ በዓመት መጨረሻ ከአዲስ አበባ ውጪ በአዳማ፤ በቢሾፍቱ እና በሐዋሳ ይካሄዱ የነበሩ ተደጋጋሚ ስብሰባዎች መቀነሳቸውን ተናግረዋል። አንዳንድ ተቋማት ትንንሽ ስብሰባዎችን ሳይቀር በሆቴል የሚያካሂዱበት ሁኔታ መኖሩን በማስታወስ፤ እርምት እንዲያደርጉና በጀታቸውን አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ብቻ እንዲያውሉ ግፊት መፈጠሩ ወጪ እየቀነሰ መሆኑን አመልክተዋል።
እንደአቶ ሃጂ ገለፃ፤ ገንዘብ ሚኒስቴር የተቋማት በጀት አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ብቻ እንዲውል ከማሳሰብ ውጪ 187 መስሪያ ቤቶች የሚያካሂዱትን ስብሰባ መቆጣጠር አይችልም። ሆኖም፤ “ወጪያችሁን ቀንሱ” በማለቱና 120 መስሪያ ቤቶች የመስተንግዶ ወጪያቸውን በመቀነሳቸው በሰኔ ወር ካስገቡት የበጀት ጥያቄ 600 ሚሊዮን ብር ማትረፍ በመቻሉ ለሌላ ጉዳይ ውሏል።
በሌላ በኩል፤ “የውጪ ጉዞን በመሚ ለከት የየትኛውም መስሪያ ቤት ሰራተኛ በፈለገው ጊዜ ተነስቶ ወደ የትኛውም አገር መሄድ አይችልም።” የሚሉት አቶ ሃጂ፤ ጥያቄው ለጠቅላይ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት ቀርቦ የጉዞው አስፈላጊነት፣ ተጓዡ ማን መሆኑ፣ ወጪው በማን እንደሚሸፈን፣ ምን ያህል ጊዜ እንደሚፈጅ ተረጋግጦ አስፈላጊነቱ ሲታመንበት ብቻ ጉዞ የሚካሄድ መሆኑም በወጪ ቅነሳ ላይ ከፍተኛ ሚና እንዳለው አመልክተዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ህዳር 6/2012
ሶሎሞን በየነ