በሰው ልጅ ታሪክ ፅንፈኝነት፣ ዋልታ ረገጥነትና አክራሪነት የሚጠቅመው ለዛውም በጊዜአዊነት ጥቂት ፓለቲከኞችንና አክቲቪስቶችን እንጂ ሀገርንና ሕዝብን አይደለም። ሀገርን የሚጠቅመው በጥሞና በእርጋታ መመካከር ማንሰላሰል ነው። ዜጎች እርስ በእርሳቸውም ሆነ ከመንግስት ጋር ያላቸውን ማንኛውንም ልዩነት ተቀራርቦ በመነጋገር መፍታት ይችላሉ። በቀደመው ሆነ በቅርቡ ታሪካችን ልዩነታችን በኃይል ለመፍታት ለማፈን ያደረግነው ጥረት ልዩነታችንን ይበልጥ አንቦረቀቀው እንጂ አላጠበበውም፤ አልፈታውም። የለውጥ ኃይሉ ልዩነትን እና አለመግባባትን በውይይት ለመፍታት የሚያደርገው ጥረት እንዳለ ሆኖ ውጤታማነቱን ግን ቆም ብሎ መፈተሽ ያስፈልጋል።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አንዳንድ ከተሞች የጥቅምት 12ቱን እና ተከታታይ ቀናትን ግፍ አስመልክቶ ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር ከ20 በላይ ስብሰባዎችን እንዳካሄዱ ገልፀውልናል። ይህ መጣጥፍ ለህትመት እስከሚበቃበትም ሆነ ከዚያ በኋላ ከላይ ከተጠቀሰው ቁጥር በብዙ እጥፍ የሚልቁ ስብሰባዎች ይካሄዳሉ ብዬ አስባለሁ። እዚህ ላይ ” ስብሰባዎች ” የሚለውን ቃል ያዙልኝ። ለውጡ ከመጣ ካለፉት 20 ወራት ወዲህ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የሚያዘጋጃቸውን የ”አዲስ ወገ ” ስብሰባዎች ጨምሮ በሌሎች የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ በፌዴራል ተቋማት፣ በክልሎች፣ እንደ ማህበራዊ ጥናት መድረክ ባሉ ሀገር በቀል መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና በአለም አቀፍ ተቋማት እንዲሁም ‘ EBC ‘ “በልቦና ውቅር”፣ “በወቅታዊ”ና “በካስማ”፣ ወዘተ .፤ ፋና ” በዙሪያ መለስ “ሰላምን፣ መቻቻልን፣ ፓለቲካዊ ምህዳርን፣ ለውጡን፣ ውህደቱን፣ የህዳሴ ግድብን እና ተያያዥ የሆኑ ሀገራዊ ርዕሰ ጉዳዮችን በተመለከት ቢያንስ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ስብሰባዎች በመላ ሀገሪቱ ተካሂደዋል።
ሆኖም እነዚህ ስብሰባዎች የሚመለከታቸውን አካላት ስለ ማሳተፍ አለማሳተፋቸው፤ አወያዮች ከርዕሰ ጉዳዩ ጋር አግባብነት ያለው ልምድና የትምህርት ዝግጅት ይኑራቸው አይኑራቸው፤ ርዕሰ ጉዳዮች ወቅታዊና ችግር ፈቺ ይሁኑ አይሁኑ፤ የተግባቦቱ አግባብ ስብሰባ ይሁን ምክክር ወይም ማንሰላሰል፤ ወዘተ. እርግጠኞች ስለመሆናቸው መረጃም ማስረጃም የለኝም። ምክንያቱም” ስብሰባዎች “ያመጡትን የአመለካከት ለውጥ ያስመዘገቡትን ውጤት የሚለኩበትን ስርዓት ወይም ግብረ መልስ የሚተነትኑበትን ስነ ዘዴ አልያም አስተያየት የሚሰበስቡበትን መንገድ አልገለፁልንም።
ሆኖም መሬት ላይ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ብዙዎቹ አልያም ሁሉም ” ስብሰባዎች” በቅድመ ፍላጎት ዳሰሳ፣ በቅድመም ሆነ በድህረ አስተያየት ስብሰባ፣ በግብረ መልስ ከፍ ሲልም በጥናት የሚካሄዱ አለመሆናቸውን መገመት እችላለሁ። የተሰብሳቢዎች ስብጥርም ሆነ የጥናታዊ ፁሑፍ አቅራቢዎች አመራረጥ ሳይንሳዊ አለመሆኑን ለመናገርም ሞራ ማንበብ አያሻም። በእርግጥ ካለፉት 20 ወራት ወዲህ አዳዲስ ተሰብሳቢዎችን እና ሰብሳቢዎችን በአዲስ አቀራረብ ማየቴን አልክድም። ሆኖም ካስመዘገቡት ውጤት አንጻር ሲመዘኑ ዛሬም ብዙ እንደሚቀራቸው ማሳሰብ ያስፈልጋል።
ላለፉት 50 ዓመታት መዋቅራዊና ተቋማዊ ሆኖ ሲሰራበት የኖረ የፈጠራ ትርክት፣ ልዩነት፣ ጥላቻ፣ መጠራጠር፣ ወዘተ . ለውጡ በባ’ተ ማግስት በአንድ ጀምበር ይወገዳል የሚል ቅዠትም የለኝም። ስብሰባም ሆነ ሌላ ተቀራርቦ የመወያያ የመነጋገሪያ መንገድ ብቻውን እንደ ቋጥኝ የተጫኑንን ችግሮች ሁሉ ከላያችን አንከባሎ ይጥላል የሚል ገራገር ዕምነትም አልሰነቅሁም። ከዚህ ጎን ለጎን ለውጡን ተቋማዊ የማድረግ በዚህ ዙሪያ በአንድነት መሰባሰብ እና የሕግ የበላይነትን በራሱ በመንግስት መዋቅርም ሆነ በገዥው ፓርቲና በመላ ሀገሪቱ ማረጋገጥን እንዲሁም ችግርና ቀውስ የመፍታት አተያያችን አንድ በአንድና ተናጠላዊ ሳይሆን ሁለንተናዊ ምልከታን (wholistic approach) እንደሚጠይቅ ተገንዝበን በቅንጅት መስራት እንዳለብን ማጤን ይጠይቃል።
ይሁንና ላለፉት 27 ዓመታትም ሆነ ከለውጡ ወዲህ ከፌዴራል እስከ ጎጥ፣ ከከፍተኛ እስከ ዝቅተኛ አማራር የተሳተፈባቸው ” ስብሰባዎች፣ ኮንፈረሶች፣ አውደ ጥናቶች ጉባኤዎች፣ ወዘተ.” የሚፈለገውን ያህል ውጤታማ ናቸው የሚል ዕምነት የለኝም። ይህን ድምዳሜዬን የሚያረጋግጥልኝ የግብረ መልስ ወይም የሕዝብ አስተያየት ጥናት እጄ ላይ ባይኖርም ተደጋጋሚና ተከታታይ ስብሰባ የተደረገባቸው ርዕሰ ጉዳዮች ማለትም ሰላም፣ አብሮነት፣ አቃፊነት፣ ሆደ ሰፊነት፣ ይቅርባይነት፣ ልማት፣ ዕድገት፣ ወዘተ. በሚፈለገው መጠንና ጥልቀት እየተዋሀዱን ከፍ ሲልም በዕለት ተዕለት ኑሮአችን እየተገለጡ እየታዩ አለመሆናቸው ከጥናቱ በላይ ትልቅ ግኝት ነው። መሬት ላይ ያለውን በአይኔ በብረቱ እያየሁት እየሰማሁት ስለሆነ። ለዚህ ጥሩ ማሳያው ከሁከት፣ ከግዕብታዊነት፣ ከአጉራ ዘለልነት፣ ከቀውስ፣ ከብጥብጥ፣ ከመግደል፣ ከመሞት ወዘተ. አዙሪት መውጣት አለመቻላችን ነው።
ከዚህ በላይ በዘመናዊው የሀገሪቱ ታሪክ ኢትዮጵያውያን እንደዚህ በፓለቲካ፣ በማንነት፣ በተረክ፣ በሰንደቅ አለማ፣ በጀግኖች፣ ወዘተ. እንዲህ ተከፋፍለን፣ በትንሹ በትልቁ ተለያይተን፣ ሆድና ጀርባ ሆነን አናውቅም። ለነገሩ በልዩነትና በጥላቻ ላይ ላለፉት 27 ዓመታት ተቋማዊና መዋቅራዊ ሆኖ ሲሰራ በኖረ ሀገር ሳንለያይ ብንቀር ነበር የሚገርመው። በተቀናጀና ስትራቴጂካዊ በሆነ መንገድ ባይሆንም ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ይሄን ልዩነት ለማጥብ ጥረት እየተደረገ መሆኑን መካድ አይቻልም።
ይሁንና በልዩነቶቻችን፣ በግጭታችን፣ በሞታችን ነግደው የሚያተርፉ ቡድኖች ይህን ቀለበት ሰብረን እንዳንወጣ በተደጋጋሚ እንቅፋት ሲሆንብን በመንገዳችን ሲቆሙ እየተመለከትን ነው። እነዚህን እንቅፋቶች በጥበብ በማስተዋል ከመሻገር ጎን ለጎን ለውጡ ገዥ ሀሳብ ሆኖ ልዕልና እንዲያገኝ ከተግባቦት ስርዓታችን አንዱ የሆነውን ውይይት፣ ስብሰባ፣ ምክክርና ማንሰላሰል እንዴት ቢካሄድና ቢመራ ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል ቆም ብለን ማሰብ ማንሰላሰል አለብን። ከፍ ብዬ እንደገለፅሁት ልዩነታችን በውይይት፣ በመነጋገርና በመመካር ካልሆነ በኃይል መፍታት እንደማንችል ውድቀታችን ታሪካችን አስተምሮናልና።
በነገራችን ላይ መለያየቱ፣ መከፋፈሉ፣ መጠላላቱ፣ መጠራጠሩ፣ አለመደማመጡ የእኛ የኢትዮጵያውን እጣ ፈንታ ብቻ ተደርጎ መታየት የለበትም። ከ2ኛው የአለም ጦርነት ወይም ካለፉት 70 ዓመታት ወዲህ የፕሬዚዳንት ትራምፕን ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ አሜሪካውያንና አውሮፓውያን እንዲህ አንድነታቸው ላልቶ፣ ተከፋፍለው አይውቅም። አሜሪካ በታሪኳ እንዲህ ተከፋፍላ፣ ሆድና ጀርባ ሆና፣ ፅንፍና ፅንፍ ረግጣ፣ ሪፐብሊካኖችና ዴሞክራቶች እንዲህ ሆድና ጀርባ ሆነው እንደማያውቁ የCNNኑ የGLOBAL PUBLIC SQUARE / GPS / አዘጋጅና የWASHINGTON POST ቋሚ አምደኛ ፋሪድ ዘካርያን ይናገራል።
ዴሞክራቶች ትራምፕ ላይ የጀመሩት ክስ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው። አጎት ሳም / አሜሪካ/ ሲያነጥስ በጉፋን የሚያዘው የተቀረው አለምም መከፋፈሉ ፅንፍና ፅንፍ መርገጡ አልቀረለትም። ተጋብቶበታል። ብዙኃን መገናኞዎች ይህን አደገኛ ክስተት በአለማችን አራቱ ማዕዘናት እየዘገቡት ይገኛል። ከላቲን አሜሪካ እስከ ሰሜን አሜሪካ፣ ከምዕራብ አውሮፓ እስከ ምስራቅ አውሮፓ፣ ከሎንደን እስከ ብራስልስ፣ ከሞስኮ እስከ ሎንደን፣ ከመካከለኛው ምስራቅ እስከ ሩቅ ምስራቅ፣ ከዶሀ እስከ ሪያድ፣ ከቴህራን እስከ መካ፣ ወዘተ . ልዩነት ግዘፍ ነስቶ እንደ ጅብራ ተገትሯል።
የ ” The Square and The Tower “መጽሐፍ ደራሲና በስታንፎርድ የሁቨር ተቋም ባልደረባ የሆኑት ኔል ፈርጉሰን ዳግማዊ ቀዝቃዛ ጦርነት እየተስተዋለ እንደሆነ ይሞግታሉ። ሩሲያዊው የቼዝ ግራንድ ማስተርና ተሟጋች ጋሪ ካስፓሮቭ የፈርጉሰንን ሀሳብ ይጋራል። ጉምቱ የአለም አቀፍ ጉዳዮች እና የሚዲያ ልሒቃን አዲስ አይነት ዳግማዊ ቀዝቃዛ ጦርነት በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፉክክር፣ በንግድ ውድድር ሰበብ እንደባ’ተ በመለፈፍ ሙግቱን ያፀኑታል። ለአብነትም የቻያናንና የአሜሪካንን የንግድ ጦርነት ያነሳሉ። 5Gን ተከትሎ የገቡበትን እሰጥ አገባ እዚህ ላይ ልብ ይሏል። እንዲሁም የኔቶንና የሩሲያን ግብግብ፣ የእንግሊዝን ከሕብረቱ የመነጠል እሰጥ አገባ፣ የሕዝበኛ እና የሊበራል ፓርቲዎችን ሙግት፣ የግራ ዘመምና የቀኝ አክራሪዎች ገመድ ጉተታን፣ ወዘተ.ን ያነሳሳሉ።
ሀገራችንም በራሷ አውድ በልሒቃኖቿ እየተመራች እንበለው እየተነዳች የዚህ የሰው ልጅ የታሪክ ምዕራፍ አካል ለመሆን የወሰነች ይመስል እየተፍገመገመቸ ትገኛለች። በኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነትና በንዑስ ብሔርተኝነት፣ በዜግነት ፓለቲካና በማንነት ፓለቲካ፣ በግለሰብና በቡድን መብት፣ በመዋሀድና በአለመዋሀድ፣ በመደመርና ባለመደመር፣ በፅንፈኝነትና በለዘብተኝነት፣ በታሪክ ብያኔ ወዘተ. መካከል እየተንጠራወዝች፣ እየተወላከፈች ትገኛለች። የአሜሪካው የቀድሞ ፕሬዚዳንት አይዘን አወር ምክረ ሀሳብ እንደሆነ የሚነገርለትን ሶስተኛውን፣ አማካኙንና መሀለኛውን አማራጭ በጀ ያለችው አትመስልም። ሁለቱም ጫፎች ወደ ገደል እንደሚገፏት ልብ ማለት ተስኗታል።
ይህን የመለያየት፣ የመከፋፈል፣ የፅንፈኝነት አባዜ ምዕራባውያንም ሆነ አሜሪካውያን ምን ይደረጋል ብለው እጃቸውን አጣጥፈው አልተቀመጡም። በሚዲያዎቻቸው፣ በሲቭል ተቋማትና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ይህን አደገኛ አዝማሚያ ሽንጣቸውን ገትረው እየሞገቱት ይገኛሉ። የስታንፎርድ ዩኒቨርስቲው ጄምስ ፊሽኪን እና የቴክሳሱ ዩኒቨርሲቲ ሮበርት ሉስኪን በዚህ ረገድ ችግር ፈቺ መፍትሔ በማፍለቅ በፋና ወጊነት ይጠቀሳሉ። የእነዚህ አሜሪካውያን ሀሳብ ” አሜሪካውያን በአንድ ጣራ ስር ” ይሰኛል። ይህ ሀሳብ አዲስ መንገድ የሚመራ እና አቅጣጫ ጠቋሚ ሆኖ ስለአገኘሁት ” በዚህ በኩል” ብየዋለሁ።
መንገድ የሳቱ ስብሰባዎቻችንን ወደ ትክክለኛው መንገድ የሚመልስ፣ የሚመራ ስለሆነ። በዜጎች መካከል ያለን ፅንፍ የረገጠ የተካረረ ልዩነት፤ ከመንግስት ጋር ያላቸውን የማይታረቅ ተቃርኖ፤ በፖሊሲዎች ላይ የያዙትን የተለያየ አቋም፤ ወዘተ. በጥሞና በመመካከር በማንሰላሰል ለማጥበብ፣ ለማስታረቅ የሚያስችለው ይህ አዲስ ዕይታ Delibrative Democracy / የምክክር ዴሞክራሲ / ይባላል። ይሄን ተከትሎ በታዳሚዎች መካከል የተደረገው ምክክርና ማንሰላሰል ምን ያህል ልዩነታቸውን እንዳጠበበ እና አቋማቸውን እንዳለዘበ ወይም እንዳስቀየረ ለማወቅ የሚሰበሰብ አስተያየት ደግሞ Deliberative Pool/ የምክክር አስተያየት/ይሰኛል።
በዚህ በኩል
/ /
የስታንፎርድ ዩኒቨርስቲው ጄምስ ፊሽኪን እና የቴክሳሱ ዩኒቨርሲቲ ሮበርት ሉስኪን በ109 ሀገራት 28 የምክክር አስተያየት ሰብስበው ተንትነዋል። አስተያየቱን ያሰባሰቡት የየሀገራቱን ዜጎች ለሁለት ከፍለው በሚያወዛግቧቸው ኢኮኖሚያዊ ወይም ፓለቲካዊ አልያም ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ከመወያየታቸው በፊትና ለሳምንት በገለልተኛ ባለሙያዎች እየታገዙ በጥሞና ከተመካከሩ በኋላ ነው። የምክክር አስተያየት ከተጠናቀረባቸው ሀገራት መካከል ሀንጋሪ አንዷ ናት። በዚህች ሀገር በጥሞና ምክክር የተደረገው እንደ ሁለተኛ ዜጋ በሚቆጠሩትና መገለልና መድልዎ በሚደርስባቸው ሮማኖች ላይ ነው። ከምክክሩ በፊት የሮማኖች ጉዳይ ብዙ ግድ የማይሰጣቸው ሀንጋሪያውያን ከምክክሩ በኋላ ብዙዎቹ ሀሳባቸውን በመቀየር ሮማኖችን እንደ ሁለተኛ ዜጋ መቁጠሩም ሆነ አድልዎና መገለል መፈፀሙ ተገቢ እንዳልሆነ አስተያየት ሰጥተዋል።
እነ ፊሽከን ያካሄዱት ሌላው ምክክራዊ ዴሞክራሲ በአሜሪካ ዳላስ ነው። በዚህ ምክክር 523 ዴሞክራቶች፣ ሪፐብሊካኖች፣ ቀኝ አክራሪዎች፣ ግራ ዘመሞችና ሌሎች የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ስለስደተኞች፣ ስለውጭ ጉዳይ ፓሊሲ፣ ስለጤና፣ ስለኢኮኖሚ እና ሌሎች ጉዳዮች በየዘርፉ ገለልተኛ ባለሙያዎች እየታገዙ ለሳምንት ከተመካከሩ፣ ካንሰላሰሉና በቡድን በቡድን ከተወያዩ በኋላ በተሰበሰበ የምክክር አስተያየት የሚያስደንቅ ውጤት ተገኘ። ለመተያየት ለመጨባበጥ እንኳ ፈቃደኛ ያልነበሩ ተሳታፊዎች በመከሩባቸው ርዕሰ ጉዳዮች ከተጠበቀው በላይ መግባባትና መቀባበል ቻሉ።
እንደ ማጠቃለያ
ልዩነቶችን አለመግባባቶች በኃይል ሳይሆን በጥሞና ሳይንሳዊና ገለልተኛ በሆነ አግባብ በመወያየት፣ በመመካከርና በማሰላሰል ማጥበብ እንደሚቻል ከላይ በተመለከትናቸው ግኝቶች አረጋግጠናል። ይህ እንዲሆን” ስብሰባዎች” ን የምናካሂድበትን ስልትና ወጤታማ መሆናቸውን የምንመዝንበት አሰራር ሊኖር ይገባል። ተወያየን፣ ተነጋገርን፣ ተመካከርን፣ ወዘተ. ለማለት ብቻ ስብሰባ ማድረግ የለብንም። እንደነ ፊሽከን ስብሰባዎቻችንን በጥሞና በጥልቀት ወደ መመካከር ማንሰላሰል መቀየርና ውጤታቸውን መለካት አለብን። ይህን የስታንፎርድ እና የቴክሳስ ዩኒቨርቲዎችን ልሒቃንን ግኝት ከሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር ቀምረን ልንጠቀምበት ይገባል። ስብሰባዎችን የምናካሂድባቸውና የታለመላቸውን ግብ ማሳካት አለማሳካታቸውን የምንመዝንበት ሀገራዊና ወጥ የሆነ አሰራርና አደረጃጀት ስለመዘርጋትም አበክሮ ማሰብ ያስፈልጋል።
ኢትዮጵያ ሀገራችን በዜጎቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!!
ሀገራችንን ፈጣሪ አብዝቶ ይባርክ!!!
አሜን ።
አዲስ ዘመን ጥቅም6/2012