ዓለም ዘወርዋራ፤ ዓለም ባለተራ ናት። አንዱ ገበታው ሞልቶ ተትረፍርፎ ህይወትን በቅንጦት ሲመራ ሌላው ከመሶቡ ምንም ሳይኖር ህይወቱን ለማቆየት የሌሎችን ፍርፋሪ ይፈልጋል። አንዱ በጭስ ታፍኖ በእሳት ተፈትኖ ምርጥ አንጥርኛ ሲሆን ሌላው አንጥረኛው በለፋበት በጌጣጌጦቹ ይዋብበታል። አንዱ ከእፊያው ሲቀምስ ሌላው ፍቅፋቂም ይናፍቀዋል። ጥቂቱ ትኩስ ፉት ሲል፤ በርከት ያሉቱ ዕድሜ ዘመናቸውን ቀዝቃዛውም ይናፍቃቸዋል።
አዎ! በዓለም ዘወርዋራ ናት። አንዱን በደስታ ስታስፈነድቅ ሌላውን በሐዘን ማቅ ልቡን ትሰብራለች። አንዱን በውሃ ሙላት ሌላውን በውሃ ጥማት ትፈትናለች። ሌሎች የባህር እንስሳትንና በሚቀልብ ትርፍ ምርት ሲንበሸበሹ በሌላ ጎራ ሉት አንበጣ መጣብን ብለው ይጨነቃሉ። ዓለም በበይዎችና በተበይዎች የተሞላች፤ የፈታኝና ተፈታኝ ተምሳሌት ናት። ዓለም ዘዋርዋራዋ ከቆላ ደጋ ትወስዳለች፤ እንደ ወተት እየናጠች እንደ ቅቤ ከአናት ላይ ትወጣለች።
እኔም ሰሞኑን በማለዳ ከአራዳው ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ዘቅዘቅ ብሎ ወደ መርካቶ ከሚወስደው አትክልት ተራ ጎራ አልኩኝ። አካባቢው ጉራማይሌ ገፅታ የተላበሰ ነው። ውስጥ ለውስጥ ዞር ዞር ብሎ ለተመለከተው ሰው ብዙ አስገራሚትዕይንቶችን ይመለከታል። በአረጁ ህንጻዎች ጥግ የተቆለለው ቆሻሻ ይሰነፍጣል፤ ሽታው አፍንጫ ይቆርጣል። ግራ ቀኝ ያለው ግፊያ ትንፋሽ ያሳጥራል። ግን ሁኔታውን ለተላመዱ ሰዎች ብዙም ደንታ የሚሰጣቸው አይመስልም፤ ጉዳያቸው ከሽታው ጋር ሳይሆን ከዕለት እንጀራቸው ጋር ስለሆነ የዕለት ተዕለት ሥራቸውን ያለመታከት ይከውናሉ።
በጭንቅላታቸው ላይ ቅርጫትና ዘንቢል ተሸክመው የኑሮን ቀዳዳ ለመድፈን ቱር! ቱር! የሚሉ ወጣቶች፣ ግራ ቀኝ እየተወራጩ ‹‹ፌስታል ያስፈልጋል በማለት በጥያቄ የሚያካልቡ ታዳጊዎች፣ የማለዳ ቁርሳቸውን ለማግኘት ከአንዱ ተሽከርካሪ ላይ ፊጥ ብለው የሚታዩ ጫኝና አውራጆች፣ የሚሸጡትን ከመንገድ ዳር ዘርግተው ገዢ የሚቀላውጡ ነጋዴዎች፣ አትክልት ተራን የሚያደምቁ አትክልት ተራም የምትደምቅባቸው ባለዥንጉርጉር ቀለም ተዋናየች ናቸው። በዚህች ሩጫ በበዛባት ዓለም የአትክልት ተራ የማለዳ ገፅታ እጅጉን ያስደምማል፤ ያሳዝናል፤ ያስቃል።
ወይዘሮ መሠረት መምሩ እና በላይነሽ አበራ ጓደኛሞች ናቸው። ሁለቱም ማልደው ከፈረንሳይ አካባቢ ወደ አትክልት ተራ እንደመጡ አወጉኝ። ሁለቱም ልጅ አዝለዋል። ዕድሜያቸው በ30ዎቹ መጀመሪያ ላይ ነው። በዚህ ሥፍራ የዕለት ጉርሳቸውን ለመሸፈን ደፋ ቀና የሚሉበት መደበኛ ሥራ ነው። ያገኙትን አትክልትና ፍራፍሬ ሁሉ ይለቅማሉ። የሚፈልጉት ነገር ከሆነ ከደረቅ ቦታም ሆነ ርጥብ ቆሻሻ ላይ ያነሳሉ። የቻሉትን ያክል ከለቀሙ በኋላ ከአትክልት ተራ በቅርብ ርቀት ሄደው የቁጥ! ቁጥ! ይሸጣሉ። ቋሚ ደንበኛ ባይኖራቸውም ኑሮ የደቆሳቸው ሰዎች ግን አያልፏቸውም። አልሸጥ ብሎ የተረፈውን ደግሞ ተሸክመው ወደ አካባቢያቸው ይመለሳሉ።
ምንም እንኳን ጉሯሯቸውን በዚህ ለመድፈን ይሞክሩ አንጂ ስራው አስከፊ ነው። የሚለቅሙት ፍራፍሬ አንዳንዴ ጊዜ ሊጠፋ ይችላል። መሰረትም ሆነች በላይነሽ ወደ አትክልት ተራ በሌሊት ለመምጣት የልጆቻቸው ነገር ችግር ሆኖባቸዋል። ልጆችን ተሸክሞ ማልደው አትክልት ተራ መገኘት ደግሞ ልጆቹን ከእንቅልፍ መቀስቀሱ አስቸጋሪ ከመሆኑም በሻገር የእናት አንጀት ነውና ብርድ ቢመታብኝስ የሚልም ስጋት አለ። ስለዚህ አትክልት ተራ የሚደርሱት የወዳደቁት አትክልቶች ማልደው በመጡ ለቃሚዎች ተሰብስበው ካለቁ በኋላ ነው። ሌላ ሥራ ቢኖር ለመስራት ፈቃደኛ ቢሆኑም ልጆቻቸውን አደራ የሚሰጡት ሰውም የላቸውም።
መሰረትም ሆነች በላይነሽ ከአትክልት ተራ የሚለቅሙት ውድቅዳቂ አቮካዶ፣ ቀይ ሽንኩርት፣ ፓፓያ፣ ማንጎ፣ ነጭ ሽንኩርት በብዛት የሚያገኙ መሆኑን ይናገራሉ። በቆሻሻው መሀል ለዕለት የሚሆናቸውን ጉርስ እየፈለጉ ኑሯቸውን ይገፋሉ። አንዳንዴም ሙሉ ቀን ሲንከላወሱ ውለው አንዳችም ነገር ሳያገኙ ወደ ቤታቸው የሚመለሱበት ክፉ ቀን ያጋጥማቸዋል።
ፈተናው ይህ ብቻ አይደለም አትክልት ተራ የወደቀ ነገር ፍላጋ ሲንከራተቱ ዘወር በሉ ከዚህ ብለው የሚያሳድዷቸው ሰዎች አሉ። በተለይም በአካባቢው የጥበቃ ሥራ የሚሰሩ ሰዎች ወደዚህ ሥፍራ አትምጡ ብለው ይቆጧቸዋል፤ ያባርሯቸዋል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የለቃቀሙትን አትክልትና ፍራፍሬ ይቀበሏቸዋል። በዚህን ጊዜ አይቀበሏቸው ነገር አቅም የላቸው፤ ትተው እንዳይሄዱ ችግሩ ቀን አይሰጣቸው። ስለዚህ ስደቡንና ግልምጫውን ችለው እንዲሰጧቸው ጥበቃዎቹን ይማፀናሉ። በዚህ ሂደት ውስጥ አሁናዊ ሕይወታቸውን እየመሩ ሲሆን፤ ስለነገ ግን እንዲህ ነው ብለው በእርግጠኝነት የሚናገሩትና ተስፋ የሚያደርጉት ነገር የለም፤ ሁሉን ነገር ለፈጣሪ ከመስጠት በዘለለ።
አቶ ዓባይ አመሃ በአትክልት ተራ ላለፉት አምስት ዓመታት በጥበቃ ሥራ ላይ ቆይተዋል። በዚህ ጊዜ ብዙ ነገሮችን ታዝበዋል። አንዳንድ ጊዜ የሚመለከቱትን ነገር ማመን ይከብዳቸዋል። አንዳንዴ ደግሞ ኑሮ በዘዴ የሚሉት ብሂል በእጅጉ ያስገርማቸዋል።
ከአትክልት ተራ የወዳደቁ የፍራፍሬ ዓነቶችን እየለቀሙ የሚመገቡ ሰዎችን ሲመለከቱ ወይ ‹‹ችግር ክፉ›› ብለው እጃቸውን አፋቸው ላይ ያሳርፋሉ። በተለይም ደግሞ ሰዎች ከመጠን በላይ የበሰሉትን(በአካባቢው አጠራር ማርች ይባላል) አሊያም ደግሞ እጅግ ጥሬ የሆነ ፍራፍሬ ሲበሉ ተመልክተዋል። እርሳቸውን የሚያስገርማቸው ነገር እንደምን አድርገው ጥሬ ፓፓያ፣ አቮካዶ እና ሌሎች ፍራፍሬዎችን እንደሚያጣጥሙ ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ ከቆሻሻ ላይ እየለቀሙ ሳያጥቡ የሚጠቀሙ ሰዎች ሲመለከቱ የሰው ከንቱ ብለው ታዝበዋል፤ ወዲህ ግን ኑሮን የመጋፈጥ ድፈረታቸውን አድንቀዋል።
እኝህ ሰው የኑሮ መሠረታቸውን ከአትክልት ተራ አድርገው ዛሬም ስለቤተሳባቸው እየተጨነቁ ነው። በጎልማሳነታቸው ከሰቆጣ ከወጡበት ጊዜ ጀምሮ ነገሮች እንደፈለጉት ባይሆኑላቸውም ከአትክልት ተራ ጋር ከተገናኙ ጀምረው የፍራፍሬ ፍቅር ወጥቶላቸዋል። ሰዎች ይጠሯቸውና ቆንጆ ሙዝ አሊያም ደግሞ ብስል አቮካዶ ይሰጧቸዋል። በተለይም አቮካዶና ሙዝ ሲያገኙ ወዲያውኑ ላጥ! ላጥ! አድርገው ከዳቦ ውስጥ ወሸቅ አድርገውት ይሰለቅጡታል። በሚገባ ካጣጠሙት በኋላ በሁለት ብር ሻይ ፉት አድርገው ቀኑን ቀና አድርግልኝ ብለው ይውላሉ።
በአቶ ዓባይ አመሃ እይታ አትክልት ተራ በረከት የበዛበት በዚያው ልክ ደግሞ የሚያሳቅቁ የህይወት ቅኝቶች የተካተቱበት መሆኑን ታዝበዋል። በእርሳቸው ትዝብት አትክልት ተራ የህይወትን መራራነት አፍ አውጥተው የሚናገሩ በርካታ ትእይንቶች እንዳሉ ሁሉ ኑሮን በትዕግስትና በታታሪነት ማሸነፍ እንደሚቻል ምስክር የሚሆኑ ብርቱዎች የሞሉበት አካባቢ መሆኑን ይናገራሉ።
ወጣት አቡዱራዛቅ ኑረዲን በአትክልት ተራ ልዩ ስሙ ‹‹ፍሪጅ ተራ›› ለአንድ ዓመት ተቀጥሮ ሲሠራ ቆይቷል። ገና መጀመሪያ ላይ ሥራ ሲጀመር ብዙ ነገሮች ግር ይሉት ነበር። ወዲህ ደግሞ ከፍራፍሬ በየዓይነቱ እየበላ ምቾት ቢጤም ተሰምቶት ነበር። እየቆየ ሲሄድ አካባቢውን፣ አትክልትና ፍራፍሬ ሥራውንና ደንበኞችን ተላመደ። ግን ደግሞ ለአትክልት ያለው ፍቅር በመቀነሱ ወደ ሌላ ምግብ ማተኮር ጀምሯል። ምናልባትም ‹‹በእጅ የያዙት ወርቅ ›› ይሉት ብሂል ሳይዋሃደው አልቀረም። ወይ ደግሞ በብዛት አትክልት ከመጠቀሙ የተነሳ ሌላ ምግብ አምሮት ይሆናል።
አብዱራዛቅ በስራው ቦታ በርካታ አግራሞት የሚያጭሩ ብሎም ልብ የሚሰብሩ ሁነቶችን መመልከቱን ይናገራል። እርሱ ተቀጥሮ ከሚሰራበት ቦታ ሙዝ፣ ፓፓያ፣ ሙዝና ሌሎች ፍራፍሬዎች ትንሽ ብልሽት ቢጤ ሲገጥማቸው ሌላውን እንዳይመርዙ ወይንም እንዳያበሰብሱ ተመርጠው በቆሻሻ መልክ ይጣላሉ። ነገር ግን ይህ ቆሻሻ ብለው እነርሱ የሚጥሉትን ሌሎች ሊጠቀሙበት ይሻማሉ። አቅም ያላቸው በርከት አድርገው ያጠራቅማሉ። በለስ ያልቀናቸው ደግሞ ቁልጭ ቁልጭ እያሉ የዕድላቸውን በተስፋ ይጠባበቃሉ።
አብዱራዛቅና ጓደኞቹ በብዛት ወደ ሥራ የሚያመሩት ከሌሊቱ ዘጠኝ ሠዓት ነው። ታዲያ በዚህ ጊዜ እርሱንም የሚያስገርመው ነገር አለ። ልክ ሌሊት ከባልደረቦቹ ጋር ሥራ ሲጀምሩ በእኩል ሰዓት የወዳደቀ ፍራፍሬ እና አትክልት ለመለቃቀም የሚያሰፈስፉ ወጣቶችና ሴቶች አብረው እኩል ይንቀሳቀሳሉ። በዚህም እስከ 50 ኪሎ ፍራፍሬ የሚለቅሙ መኖራቸውን ይናገራል። ይህንንም መልሰው በመሸጥ ዕለታዊ ኑርዋቸውን የሚገፉ በርካቶች እንደሆኑ ተገንዝቧል። ግን ይህ ሁሉ ፍራፍሬ ለመልቀም ያለውን ድካምና ውጣ ውረድ ሲመለከት በእጅጉ ያዝንላቸዋል፤ ወዲህ ኑሮን ለማሸነፍ የዘየዱትን መላ በአግራሞትና በአድናቆት ይመለከተዋል።
አትክልት ተራ በዓይነቱ የበዛ ፍራፍሬ እንደያዘ ሁሉ መልከ ብዙ ሕይወትን ቀይጦ ይዟል። ብቻ ‹‹እንዲህም ይኖራል›› ወይ የሚያስብሉ አግራሞትና አድናቆት የሚያጭሩ አያሌ ውጥንቅጦችን ይዟል- አትክልት ተራ።
አዲስ ዘመን ጥቅም6/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር