በዓለም ላይ ተወዳጅ ከመሆኑ ባለፈ በታላላቅ የውድድር መድረኮች ላይ ፍልሚያ ይደረግበታል። በተለይ በበጋ በሚደረገው ኦሎምፒክ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1964 ጀምሮ ከሌሎች ስፖርቶች ጋር በቀዳሚነት እውቅና አግኝቶ በሴቶችና ወንዶች ውድድሩን ያደምቁታል። የቡድን ጨዋታ ነው። ልብ አንጠልጣይ እና አይን የሚያቅበዘብዝ ፉክክር ሁሌም አይጠፋውም። ሰርቡ፣ ቀበራው፣ መከላከሉና ማጥቃቱ፣ የኳስ ቅብብሉና ምልልሱ ስሜትን ቆንጥጦ የመያዝ አቅም አለው። የቮሊቦል ስፖርት።
ቮሊቦል በኢትዮጵያ እውቅና የተሰጠው የስፖርት አይነት ነው። ሆኖም ግን በሚፈለገው ደረጃ እድገት አሳይቶ አገሪቷን ወክሎ በአህጉርም ሆነ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ውጤታማ የሚሆን ብሄራዊ ቡድን መፍጠር አልተቻለም። የውድድር መድረክን ማመቻቸት ህብረተሰቡ በስፖርቱ ያለውን ፍላጎቱ የሚጨምሩ ብቁ ስፖርተኞች የሚፈጠሩበት መንገድን ማመቻቸት አለመቻል ከሚጠቀሱት ችግሮች መካከል ነው።
በመግቢያችን ላይ እንደጠቀስነው በስፋት የቮሊቦል ስፖርት ችግሮች ላይ አናተኩርም። ይልቁንም በዛሬው የእሁድ አምዳችን በትኩረት ቢሰራበት ብዙ እንቁ ስፖርተኞችን ማፍራት እንደሚቻል ምሳሌ መሆን የምትችል ፕሮፌሽናል የቮሊቦል ተጫዋች እንግዳችን አድርገናል። የእርሷን የህይወት ገፅ እየገለጥን እና በስፖርቱ ያሳለፈችውን በጎና አስቸጋሪ ጊዜያት እየዳሰስን ቆይታ እናደርጋለን።
ዮዲት አዲስ ፕሮፌሽናል የቮሊቦል ተጨዋች ነች። ላለፉት 20 ዓመታት በዚሁ ስፖርት ላይ ቆይታለች። ለቮሊቦል ልዩ የሆነ ፍቅር እና ፍላጎት አላት። ይህ ብቻ ሳይሆን በርካታ እንቅፋቶች ባለበት ስፖርት ላይ ነጥራ መውጣት የቻለች ተምሳሌት ናት።
አሁን በቮሊቦል ታሪክ የመጀመሪያዎቹ ኢንተርናሽናል ሴት ተጫዋቾች መካከል አንዷ መሆን ችላለች። «የሲሸልሱ ፕራስሊን የሴቶች ቮሊቦል ክለብ» ውስጥ ተሰልፋ መጫወት ከጀመረች 5 ወራትን አስቆጥራለች። በቆይታዋም ስኬታማ ጊዜያትን አሳልፋ መጥታለች። እኛም «እንኳን ደህና መጣሽ» ብለን ስለዛሬ ስኬቷ ብቻ ሳይሆን ወደ ስፖርቱ የገባችበትን ጥንስስ ጭምር እንድታወጋን ጋበዝናት።
ቴዎድሮስ አደባባይ
ጊዜው 1974 ዓ.ም ነው። ቦታው ደግሞ ቴዎድሮስ አደባባይ። ቸርቸር ጎዳና። ዮዲት የተወለደችበት የአራዶቹ ሰፈር። ፒያሳን ሽቅብ እያየች ስታዲዮምን ቁልቁል እየተመለከተች በፍል ውሃ ተፈጥሯዊ ውሃ ተንቦጫርቃ በአያቷ ወይዘሮ ዘውዲ ሃጎስ እቅፍ ውስጥ ነው ያደገችው። በልጅነቷ ዝምተኛ ባህሪ የነበራት ቢሆንም ግን ከመንደር ልጆች ጋር ተቀላቅላ ለመጫወት የሚከብዳት አይነት አልነበረችም።
ቴዘር እና ሱዚ በነብስ የምትወዳቸው የልጅነት ጨዋታዎች ናቸው። በተለይ ደግሞ ከወንዶች ጋር መጫወትን ታዘወትራለች። ሁለቱም ጨዋታዎች እግር ማንሳት እና ዝላይ የሚበዛባቸውና በወቅቱ በልጆች በእጅጉ የሚወደዱ ነበሩ። አያቷ ቢንከባከቧትም «የአያት ልጅ ቅምጥል» እንደሚባለው ብሂል በበዛ መሞላቀቅ ውስጥ አላሳደጓትም። እራሷን እንድትሆን፣ ለሰው ክብር ያላትና ስራ ወዳድ፣ ጠንካራና በመልካም ስብዕና የታነፀችውን ዮዲትን ቀርፀዋል።
የቀለም ትምህርትን አሃዱ ያለችው በጆን ኦፍ ኬኔዲ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ነበር። ልጅነቷን ትወደዋለች። ከትምህርት መልስ ከጓደኞቿ ስፖርት ነክ በሆኑ ጨዋታዎች ላይ ታሳልፍ ነበር። «በመንደራችን ውስጥ ወንዶች ስለሚበዙ ከነርሱ ጋር ጠንከር ያሉ ጨዋታዎች ላይ እሳተፍ ነበር። ይሄ ባህሪዬ ወደ ትምህርት ቤትም ሄዶ ስፖርት እንድወድ አደረገኝ» ትላለች ያለፈው ዘመኗን መለስ ብላ እያስታወሰች።
ቀስ በቀስ በስፖርታዊ ጨዋታዎች ላይ መሳተፍ ጀመረች። በትምህርት ቤት የሚደረጉ የሩጫ እና የቮሊቦል ጨዋታዎች ትኩረቷን ይስቡት ጀመር። በትምህርቷ እየተቀዛቀዘች ወደ ፈቀደችው መክሊቷ አዘነበለች። ስምንተኛ ክፍል ስትደርስ ቮሊቦል ስፖርት ላይ ትምህርት ቤቷን መወከል እና መጫወት ቻለች።
ቁመቷ ረጅም ነው። በዚያ ላይ ደግሞ ችሎታዋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። ፍሏጎቷም ንሯር። በዚህ ሁኔታ እያለች ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ለመማር ወደ ጥቁር አንበሳ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተዘዋወረች። በዚያ ከቀለም ትምህርት ይልቅ ቮሊቦል ትኩረቷን ወሰደው። ያን ጊዜ አዲሷ ዮዲት እንደገና ተወለደች።
ቮሊቦል የዮዲት የህይወት መስመር
ጆን ኦፍ ኬኔዲ እየተማረች አትሌቲክስ ላይም ውጤታማ ነበረች። በአጭር ርቀት የመቶ ሜትር ሩጫ ትምህርት ቤቷን ወክላ በተዘጋጀ ውድድር አሸናፊ ሆና ነበር። አዲስ አበባንም የመወከል እድል አግኝታ ነበር። ሆኖም በአያቷ ተፅኖ ምክንያት ሳይሳካ ቀረ። ጥቁር አንበሳ በ1991 ዓ.ም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ስትጀምር ግን ዮዲት ሙሉ ትኩረቷን ወደሳበው ቮሊቦል ስፖርት ላይ አደረገች። ምክንያቱ ደግሞ ግልፅ ነው። ልዩ ችሎታ ነበራት። በዚያ ላይ ደግሞ ፍቅሯ ከቮሊቦል ጋር የተቆራኘ ነው።
ተሾመ ለማ እና ፍፁም ኪሮስ በትንሿ ስታዲዮም የቮሊቮል ፕሮጀክት አሰልጣኞች ነበሩ። እዚያ በታዳጊ ፕሮጀክቱ ከጓደኞቿ ጋር የመስራት እድል ገጠማት። በዚያ ላይ የጥቁር አንበሳን ትምህርት ቤት በመወከል ውድድሮች ታደርግ ነበር። ስፖርት አስተማሪዋም ብቃቷን በመመልከት ያበረታታት እና ይደግፋት ጀምሯል። ይሄ መልካም አጋጣሚ ደግሞ ከምርጥ ብቃቷ ጋር ተደምሮ «ለቡና ገበያ የቮሊቦል ስፖርት ክለብ» እንድትታጭ አደረጋት። ዮዲት እና ቮሊቦል አሁን አንድ ቋንቋ መናገር ጀምረዋል። ልብ ለልብ እንደተገናኙ ጓደኛሞች። ለክለቡ በፈረመች በዚያው ዓመት በኢትዮጵያ ሻምፒዮና አዲስ አበባን ወክላ ለመመረጥ በቃች። ውድድሩ አዲስ አበባ በበላይነት አጠናቆ ዋንጫ መብላት ቻለ።
በዚህ ጊዜ የኢትዮጵያ ቮሊቦል ስፖርት አዲስ ኮኮብ አገኘ። የውድድሩ ምርጥ ተብላ ፕሮፌሽናል በሆነች በዚያው ዓመት ድል መቀዳጀት ቻለች። የውድድር ኮሚቴውም ብቃቷን ተረድቶ ቢመርጣትም ለርሷ ግን ግራ የሚያጋባ ነበር። ቡና ገበያ ከማረሚያ ቤት ባደረጉት ፍልሚያ ላይ ቡና አሸናፊነቱን ሲቀናጅ የእርሷ ድርሻ ጉልህ ነበር። «በችሎታዋ የማደንቃትን አበበች አሻግሬን ጨምሮ በርካታ ተጫዋቾች እያሉ እኔን ሲመርጡኝ ትንሽ ግራ የሚያጋባ ስሜት ውስጥ ገብቼ ነበር»ትላለች ስለሁኔታው መለስ ብላ ስታስብ።
በወቅቱ በቮሊቦል ስፖርት የሚሳተፉ ክለቦች አነስተኛ ነበሩ። እህል ንግድ፣ ማረሚያ ቤት፣ ቡና ገበያ እንዲሁም ሙገር ብቻ ነበሩ። ስፖርቱ ትኩረት አለማግኘቱ እና በርካታ ፕሮጀክቶች አለመኖራቸው እንደ አገር ጉዳት የነበረው ቢሆንም እርሷን ግን ከውድድር ቦታ እንድትርቅ አላደረጋትም። ይበልጥ እየተበረታታች በምታመጣቸው ውጤቶች እራሷን እየለካች እና ክለቧን እያገዘች የህይወት መስመሯን ጠብቃ መጓዝ ጀመረች።
ዮዲት የቮሊቦልን ታክቲክና ቴክኒክ፣ ማጥቃት መከላከል እንዲሁም ከጓደኞቿ ጋር ተጋግዛ የባላጋራን ክልል በኳስ ማስጨነቁን ስራዬ ብላ ያዘችው። የስፖርቱ ፍልስፍና በውስጧ ሰረፀ። ለቡና ገበያ ለሁለት ዓመታትም ተጫወተች። በኋላም በራሷ የግል ምክንያት ወደ እህል ንግድ ተዛወረች። በዚያ የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኟን አሚና ሽኩር አገኘች። አሁን በራስ መተማመኗ ጨምሯል። በክለቡ ደግሞ ጓደኞቿ አሉ። ሁኔታው ጥሩ እድል ፈጠረላት።
የብሄራዊ ቡድን ተሳትፎ
ከስፖርቱ ጋር ጥብቅ ወዳጅነት የፈጠረችው ዮዲት ዓመት አልፎ ዓመት ሲተካ ስኬታማ ጊዜያትን ማሳለፍ ጀመረች። ደጋፊዎች እርሷ ስትጫወት መመልከት ያስደስታቸዋል። ያበረታቷታል። ይሄ ለርሷ ጥሩ የሞራል ስንቅ ነው። አጋጣሚው ደግሞ የኢትዮጵያ የቮሊቦል ብሄራዊ ቡድን ላይ ተመራጭ አደረጋት 1993 ዓ.ም አገሯን ወክላ ለመላው አፍሪካ ጨዋታ ወደ ግብፅ አመራች።
ቡድኑ በተለያየ ምክንያት ስኬታማ ባይሆንም ወደ ውጭ በመውጣት ውድድሮችን ማድረግ አዲስ ምእራፍ የከፈተላት አጋጣሚ ነበር። ከዚያን ጊዜ አንስቶ ኢትዮጵያ በምትሳተፍባቸው የቮሊቦል ውድድሮች ላይ ዮዲት ቀዳሚ ተመራጭ መሆን ቻለች። ግብፅ፣ ኬንያን ጨምሮ ብዙ የአፍሪካ አገራት ጋር የመጫወት እድል አጋጠማት።
ዮዲት ብሄራዊ ቡድኑን ወክላ ከተለያዩ አገራት ጋር ብትወዳደርም በውጤቶቹ ግን ብዙም ደስተኛ አይደለችም። ምክንያቷ ደግሞ አገሯ ውስጥ ለስፖርቱ የሚሰጠው ትኩረት እና ተፎካካሪዎች ያሉበት የእድገት ደረጃ የማይመጣጠን መሆኑን በመገንዘቧ ነበር። የተሟላ የመወዳደሪያ ስፍራ፣ በቂ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ እና የአሰለጣጠን ዘዴ ከበቂ በጀት ጋር ያጣመሩት ተፎካካሪዎች ብልጫ መውሰዳቸው ያበሽቃታል። ኢትዮጵያ ውስጥ ይህ ሁኔታ አለመኖሩን እንደ ዋንኛ ድክመት ታየዋለች።
ከ1993 ዓ.ም በኋላ ዮዲት የብሄራዊ ቡድኑ ቀዳሚ ተመራጭ ሆና ቀጠለች። ግብፅ ፣ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ አልጄሪያን ጨምሮ በርካታ አፍሪካ አገራት ቡድኑን ወክላ መሳተፏን ቀጠለች። ለዓመታት ከዘለቀው የቡድኑ ተሳትፎዋ ግን የ1999 ዓ.ም ለዮዲት ልዩ ስፍራ አለው። ለመላው አፍሪካ ጨዋታ በምስራቅ አፍካ ምድብ ኢትዮጵያ ባዘጋጀችው የማጣሪያ ውድድር ድል በመገኘቱ በቀጥታ ቡድኑ ለአልጄሪያው ውድድር ማለፍ ቻለ።
«የወቅቱ የብሄራዊ ቡድኑ ስብስብ ጠንካራ ነበር» በማለት ጊዜውን መለስ ብላ የምታስታውሰው ዮዲት ለመጀመሪያ ጊዜ በተወዳደሩበት የመላው አፍሪካ ጨዋታ ላይ «ኮኮብ ሰርብ» በሚለው ዘርፍ አሸናፊ መሆን ችላ እንደነበር ትናገራለች። በኋላም ለመጨረሻ ጊዜ በ2006 ዓ.ም ቡድኑን በአንበልነት በመምራት ወደ ኡጋንዳ አቅንታ ነበር።
ወደ ኡጋንዳ የሄደው ብሄራዊ ቡድን እርሷን፣ ፋናዬ ከበደ፣ የሺ ዳኜ ጨምሮ 12 ልኡክ ነበረው። የማረሚያ ቤቱ አሰልጣኝ ተሾመ ለማ እና የውሃ ስራዎች አሰልጣኝ ሰልማን ኢብራሂም ደግሞ ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት እየመሩ ሄደዋል። በዚህ ውድድር ላይ ኢትዮጵያ ሶስተኛ ሆና አጠናቃለች።
«ብሄራዊ ቡድኑ ወደ ውጭ ወጥቶ ስኬታማ የማይሆነው ታዳጊዎች ላይ ስለማይሰራ እና ተተኪ ስለማይኖር ነው» የምትለው ዮዲት ሁሌም አገሪቷ ላይ አቅም ያላቸው በርካታ ተጫዋቾቸን ማፍራት እየተቻለ ይህ አለመደረጉ ይቆጫታል። ከዓመት ዓመት የሌሎች አገራት አዳዲስ ተጫዋቾችን ሲያፈሩ ኢትዮጵያ ግን በዚህ አልታደለችም ትላለች። ለመጨረሻ ጊዜም በ2006 ዓ.ም ኡጋንዳ ላይ ከተደረገው ኢንተርናሽናል ጨዋታ ውጪ ብሄራዊ ቡድኑ ውድድር አለማድረጉን ትናገራለች።
ዮዲት በሜዳ እና ከሜዳ ውጪ
ለነገሮች ቁጥብ ነች። ስትናገር ረጋ ብላ ነው። መቸኮል አይታይባትም። ትንሽ አይናፋርም ትመስላለች። ይሄ ሁሉ ግን ከቮሊቦል ስፖርት ሜዳ ውጪ ነው። ዮዲት ኳስ ስትይዝ እና ሜዳ ውስጥ ስትገባ ሌላ አስገራሚ ባህሪ ነው ያላት። እጇን ታወናጭፋለች። በተቃራኒ ቡድን ላይ መጮህ እንዲሁም የስነ ልቦና ብልጫ መውሰድ ትችልበታለች።
«ለኔ እራሱ ግራ ይገባኛል» ትላለች ዮዲት ይሄን ባህሪዋን ምን እንደፈጠረው ስትናገር። ምናልባትም ለስፖርቱ ሙሉ ትኩረቷን መስጠቷ እና ስሜታዊነቷ ሊሆን እንደሚችል ትገልፃለች። በዚያ ላይ በጨዋታ እና ልምምድ ወቅት ደሟ ይሞቃል። ይቺኛዋን ዮዲትን ግን በፍፁም ከሜዳ ውጪ አናገኛትም። ሁለት በሀሪ። ዮዲት በሜዳ እና ከሜዳ ውጪ።
ጊዜው 1996 ዓ.ም ነው። ተመልሳ ቡና ገበያ ክለብ የገባችበት ወቅት። አንድ ዓመት እንደተጫ ወተች አመራሮቹ ክለቡን እነርሱ በማያውቁት ምክንያት አፈረሱት። ይሄ ለዮዲት እና ለጓደኞቿ አስደንጋጭ ነበር። ሆኖም አሜን ብላ አልተቀበለችም። ከቡድኑ አባላት ጋር በመሆን ፍርድ ቤት ድረስ በመሄድ መብቷን አስከብራለች። የፍርድ ቤት ህግ ባታውቅም ለስፖርቱ ፍቅር እና ለመብቷ ስትል ሌላኛዋን ዮዲት ከውስጧ አውጥታ ሽንጧን ገትራ ተከራክራለች።
ከቡና ገበያ ጋር መለያየቷ ከአሰልጣኝ ጌታ ዘሩ ጋር በድጋሚ አገናኝቷታል። የምትወደውን ክለብ ብትለቅም ጥረቷ ለሌላ ድል አብቅቷታል። ከፍርድ ቤት ውሳኔ በኋላ ወደ ስፖርቱ ተመልሳ ለውሃ ስራዎች ፈርማለች። እንቅፋት ቢያጋጥማትም እጅ አልሰጠችም። በክለብ የዙር ውድድርም ዋንጫን አንስታለች። በ1998 ደግሞ ክለቡን ወክላ ግብፅ በመሄድ ከ18 አገራት የተውጣጡ ቡድኖች ጋር ተፋልማለች። ከዚያ አልፎ በቱኒዚያ፣ ማዳጋስካር እንዲሁም ኬንያ የክለብ ውድድሮች ላይ ተሳትፋለች። በ2003 ዓ.ም ትልቁ ስኬት ኬኒያ ላይ ከ18 ክለቦች አምስተኛ ወጥተዋል። ይሄ እውነታ ዮዲት ለምታምንበት እና ለምትወደው ስፖርት ምን ያህል ዋጋ ለመክፈል ቁርጠኛ እንደሆነች የሚያሳይ ነበር። በአገር ውስጥ በክለቦች ውድድር ላይ በምታሳየው ምርጥ ብቃትም ከ10 ጊዜ በላይ ኮኮብ ተጫዋች መሆን ችላለች። ለመጨረሻ ግዜ በአገር ውስጥ ኮኮብ የተባለችው በ2010 ዓ.ም ነበር።
ሲሼልስ አዲሱ የዮዲት ክለብ
ዮዲት በቮሊቦል በአገር ውስጥ ትልቅ ስኬት ማስመዝገብ ችላለች። በተለይ በ2010ዓ.ም የነበረው የዙር ውድድር ላይ «ኮኮብ ኳስ አከፋፋይ» እና የዓመቱ ምርጥ ኮኮብ ተጫዋችነት ማእረግን መደረብ ችላለች። ይሄ ደግሞ ለአንድ ሌላ ትልቅ እድል እንድትታጭ አደረጋት። ከአገሯ አልፎ በቮሊቦል ስፖርት ውጤታማ ወደ ሆነችው ሲሸልስ ተጉዛ ፕሮፌሽናል የምትሆንበትን ትልቅ እድል እንድታገኝ ፈር ቀዶላታል። ከመጣችበት መንገድ እና ለስፖርቱ ከከፈለችው ዋጋ አንፃር ይሄ ለርሷ ትልቁ ስኬት ነው።
የሲሼልሱ «ፕራስሊን ገርልስ» የቮሊቦል ክለብ ከኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን ጋር ግንኙነት በመፍጠር ሀምሌ ሰባት 2010 ዓ.ም ለአንድ ዓመት የሚቆይ ኮንትራት ፈረመች። ከጥቁር አንበሳ ትምህርት ቤት የጀመረው የዮዲት የቮሊቦል ጨዋታ የህይወት መስመር ሲሼልስ ደረሰ።
«በምወደው ስፖርት ስኬታማ የሚያደርገኝን የፕሮፌሽናል ተጫዋችነት እድል ማግኘቴ አስደስቶኛል» በማለት፤ ከዚህ ቀደም ይህን እድል መፍጠር ቢቻል ኖሮ በርካታ ተጫዋቾችን ኢትዮጵያ ማፍራት ትችል ነበር ትላለች። በተለይ የርሷ አርአያ የነበሩት እነ አበበች አሻግሬ፣ ገነት ጴጥሮስ እንዲሁም አመልማል ተስፋዬን የመሳሰሉ ተጫዋቾች ይህን መሰል እድል አለማግኘታቸው እንደሚያስቆጫት ትገልፃለች።
በ«ፕራስሊን ገርልስ» መጫወት ከጀመረች አምስት ወራት ሆኗታል። በአገሪቷ ቦሊቦል ስፖርት ልዩ ትኩረት ይሰጠዋል። ተወዳጅም ነው። በተለይ ታዳጊዎች ላይ የሚሰሩ በርካታ ፕሮጀክቶች አሉ። በአንደኛ ዲቪዚዮን እና በሁለተኛ ዲቪዚዮን በጥቅል 18 ክለቦች ይገኛሉ። እርሷ በአንደኛ ዲቪዚዮን ነው የምትጫወተው።
ዮዲት ለክለቡ ከፈረመች ጀምሮ ሰባት ጨዋታዎች ላይ ተሰልፋ ተጫውታለች። ከሰባቱ በአንዱ ብቻ ሲሸነፉ ስድስቱን ደግሞ ድል አድርገዋል። የእርሷ ድርሻ ትልቅ ነበር። አሁን በ28 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። በጥሎ ማለፉ ጨዋታ ደግሞ «ፕራስሊን ከካስካድ» ጋር ተገናኝቶ 3ለ1 በሆነ ድምር ውጤት በማሸነፍ ዋንጫ ማንሳት ችሏል። ማዳጋስካር የካቲት ላይ ለሚካሄደው ኢንዲያን ኦሽን የዞን ሰባት ውድድርም አልፈዋል። ዮዲት በአምስት ወር ቆይታዋ ቡድኑን ውጤታማ ማድረግ ችላለች።
ተሻጋሪ ህልሞች
በቮሊቦል ስፖርት ላለፉት 20 ዓመታት ስኬታማ ቆይታ አድርጋለች። ስፖርቱ በሚፈለግው መጠን እድገት እያሳየ ባይሆንም የግል ጥረቷ ከአገሯ አልፎ ለፕሮፌሽናል ተጫዋችነት አብቅቷታል። አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ቮሊቦል የሚገባውን ትኩረት አግኝቶ እድገት እንዲያመጣ ጥረት የማድረግ ትልም አላት።
«በአገር ውስጥ ከሰባ በላይ የታዳጊ ፕሮጀክቶች እንዳለ ይነገራል። ሆኖም ግን ተተኪ ማፍራት እየተቻለ አይደለም። አሁን አሁን ስፖርት አካዳሚ እየሰራ ያለው ስራ ጥሩ ነው» በማለት በቂ ትኩረት አግኝቶ አቅም ያላቸው ተጫዋቾችን ለማፍራት ጥረት መደረግ አለበት ትላለች። እርሷም ባካበተችው ልምድ የበኩሏን ለማበርከት ትፈልጋለች።
ከስፖርቱ መራቅ ባትፈልግም ለረጅም ዓመት የመጫወት እቅድ የላትም። ለሁለት ዓመት በፕሮፌሽናል ተጫዋችነት የመቆየት ሃሳብ አላት። አገር ውስጥ የለመደችውን ኮኮብ ተጫዋች የመሆን ድል በሲሼልስም መድገም ትፈልጋለች። ለዚያ ደግሞ በእረፍት ጊዜዋም ልምምዶችን ትሰራለች። «አቋሜን ጠብቄ በቀረኝ ግዜ ውስጥ መጫወት እፈልጋለሁ» በማለት ምን ያህል ከስፖርቱ ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዳላት ትገልፃለች።
የዮዲት ዋልታዎች
1996 ዓ.ም ከጓደኛዋ አፍኒን ማሩ ጋር በትዳር ተጣምራ በ2001 ዓ.ም ረድኤት አፍኒን የተባለች ሴት ልጅ አፍርተዋል። ለልጇ የተለየ ፍቅር ቢኖራትም ከስፖርቱ ጋር በተገናኘ ለረጅም ጊዜ ሳይተያዩ ይቆያሉ። ውድድር እና የልምምድ ሰዓት ለቀናት አንዳንዴም ለወራት ያለያያቸዋል። አራስ ቤት ሆና ብሄራዊ ቡድኑ ጨዋታ ስለነበረው ልጇን ጥላ ኬንያ ሄዳ ተጫውታለች። በዚህ ጊዜ የቀድሞ ጓደኛዋ አፍኒን እናት ወይዘሮ ራሄል መላኩ የልጃቸውን ልጅ አደራ ተቀብለው የዮዲት ህልም እውን እንዲሆን አድርገዋል።
«አሁን የእረፍት ጊዜዬን ከልጄ ጋር ነው ማሳለፍ የምፈልገው። የቮሊቦል ተጫዋች ብትሆንልኝ ደስ ይለኛል ሆኖም ግን በፍላጎቷ ገብቼ አላስገድዳትም» የምትለው ዮዲት የቀድሞ ጓደኛዋ ቤተሰቦች እርሷ ባልነበረችበት ወቅት ልጇን በመንከባከብ ትልቅ እገዛ እንዳደረጉላት ነው የምትገልፀው። ልጇም እሷ ስፖርተኛ መሆኗን እንደምትወድላት ትናገራለች። የእናቷን ሰባት ቁጥር ያለበት መለያ ቲሸርት በመልበስ ሁሌም ፍቅሯን ትገልፅላታለች።
ዮዲት ስፖርተኛ ባትሆን ኖሮ ጥሩ ነጋዴ ይወጣት ነበር። አሁንም ቢሆን የወደፊት ፍሏጎቷ ከስፖርቱ ጎን ለጎን በንግዱ ዓለም ላይ መሰማራት ነው። ይህ አይነት አመለካከት እንዲቀረፅባት እና በስራ እንድታምን አድርገው ያሳደጓት አያቷ ናቸው። ለርሳቸው ልዩ ፍቅር እና ምስጋና አላት። አሰልጣኞቿ ተሾመ ለማ፣ አበበ ዘውዴ እና ፍፁም ኪሮስ ዮዲት ማንነቷን ስትገነባ ከጎኗ ነበሩ። ውለታቸውን ሳትዘነጋ «ዛሬ ላይ የደረስኩበት የልቤ መሻት እንዲሳካ ከጎኔ ስለነበራችሁ ምስጋናዬ ይድረሳችሁ» ትላለች።
አዲስ ዘመን ታህሳስ21/2011
ዳግም ከበደ