ስለ ኤች አይ ቪ ቫይረስ ግንዛቤ የሌላቸው እጅግ ጥቂት ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ነገር ግን በጭራሽ ስለዚህ ቫይረስ ምንም መረጃ አልሰማሁም የሚል ሰው አለ ለማለት ይከብዳል:: ነገር ግን ማንኛውም ሰው ምንም ያክል ስለዚህ ቫይረስ ያነበበ እንኳን ቢሆን በዕለት ተዕለት ኑሮው ውስጥ የቫይረሱን መተላለፊያ መንገዶችና የሚያስከትላቸውን ጉዳቶች እያገናዘበ ካልሄደ ማወቁ ብቻ የሚሰጠው ጥቅም የለም። ምክንያቱም እኛ ብንረሳውም ቫይረሱ ግን በየቀኑ የሰውን ህይወት እየቀጠፈ ይገኛል። አሁን ያለንበት ሁኔታ ስለ ኤች አይ ቪ ቫይረስ ከመርሳታችን የተነሳ ቫይረሱ ጥንቃቄ በጎደለው የግብረ ስጋ ግንኙነት እንደሚተላለፍ እንኳን የዘነጋነው ይመስላል፤አሊያም ደግሞ ቫይረሱ ቀደም ሲል የነበረውን የጉዳት መጠን አሳንሰን ያየነው ይመስለኛል።
የኤች አይ ቪ ኤድስ በሽታ በሰው ልጅ ሰውነት ውስጥ ከተገኘበት ጊዜ ጀምሮ ከ75 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን እንደያዘ እና 32 ሚሊዮን ሰዎችን ደግሞ ህይወታቸውን እንደቀጠፈ ይታወቃል። በ2018 እ.ኤ.አ. 38 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ከኤች አይ ቪ ቫይረስ ጋር እየኖሩ ነው ፤ ሁልጊዜም እንደምናነሳው ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው ባደገችው አሜሪካ አገር ውስጥ ይሁን እንጂ አሁን በስፋት ቫይረሱ እያጠቃ ያለው የአፍሪካ ሀገሮችን በተለይም ከ ሰሀራ በታች የሚገኙ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራትን ነው።
የዓለም አቀፍ የጤና ድርጅት እንደ ዘገበው በአንዳንድ ቦታ የኤች አይ ቪ በሽታ ስርጭት ከሀገር ሀገር እንዲሁም አንድ ሀገር ውስጥም ሆኖ ከቦታ ቦታ ልዩነት ያለው ቢሆንም በአፍሪካ አህጉር ውስጥ ከ25 ሰዎች ውስጥ አንዱ በኤችአይቪ በሽታ ጋር የሚኖር ነው፣ ይህ ቁጥር የቫይረሱ ስርጭት አስፈሪ ደረጃ ላይ መገኘቱን ያሳያል።
ወደ አገራችን ኢትዮጵያ ስንመለስ በዚሁ ዓመት ማለትም በ2018 እ.ኤ.አ. 700,000 (ሰባት መቶ ሺህ) የሚሆኑ ከኤች አይ ቪ ቫይረስ በሽታ ጋር የሚኖሩ ሲሆን 23,000 (ሃያ ሶስት ሺህ) ሰዎች ደግሞ በየዓመቱ በዚህ በሽታ እንደ አዲስ ይያዛሉ። ባለፉት 10 ዓመታት ውስጥ ይህ ቁጥር በተወሰነ መልኩ የቀነሰ ቢሆንም የቫይረሱ ስርጭት አሁንም በየእለቱ ከሰዎች ወደ ሰዎች እየተላለፈ ነው፣ ህይወት እየቀጠፈ ነው፣ ህፃናቶችን ወላጅ አልባ እያደረገ እና ጎዳና ላይ እንዲቀሩ እያደረገ ነው።
ከኤች አይ ቪ ቫይረስ ጋር እየኖሩ ነገር ግን በቫይረሱ መጠቃታቸውን የማያውቁ በርካታ ሰዎች አሉ። ይህ ደግሞ በሽታው በስፋት እንዲሰራጭና በቀላሉም ከአንዱ ወደ ሌላው እንዲተላለፍ በር ከፍቷል። በአብዛኛው ከገጠሪቱ የአገራችን ክፍል በበለጠ ከተሞች በኤች አይ ቪ ቫይረስ በብዛት የሚጠቁ ሲሆን በክልሎች ደረጃ ካየን ደግሞ አብዛኞቹ ክልሎች ተመሳሳይ ገጽታ ያላቸው ቢሆንም የጋምቤላ ክልል ከሁሉም ክልሎች በበለጠ ቫይረሱ የሚገኝበት መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ።
ቀደም ባሉት ዓመታት በኢችአይቪ ላይ የተሰሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ውጤት ያመጡና ስርጭቱንም በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ ያስቻሉ ነበሩ። አሁን ላይ ግን ስለ ኤች አይ ቪ ቫይረስ እየተረሳ የመጣ ይመስላል። መዘናጋቱ እና ግዴለሽነቱ ጨምሯል። ሰዎች ያለምንም ጥንቃቄ ያሻቸውን ሲያደርጉና ስለጉዳዩም ሲነሳ ሲደነግጡ አይታዩም። ሚዲያዎችም ሆኑ ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት መንግሥትን ጨምሮ ጆሮ ዳባ ልበስ ያሉ ይመስላሉ። ችግሩ ገዝፎ እየመጣ መሆኑ እየታወቀ አላየንም አልሰማንም ማለትን መርጠናል።
ስለዚህም ከትላንቱ የከፋ እንጂ የቀነሰ ችግር አለመኖሩን ተረድተን ትኩረታችንን ዛሬም በኤች አይቪ መከላከሉ ላይ ልናደርግ ይገባል። ድምጹን አጥፍቶ ዛሬም ኤች አይቪ ቫይረስ የነገ ሀገር ተረካቢዎችን እያሳጣን ይገኛል። ስለዚህም ዛሬም ቢሆን እንደ ከዚህ ቀደሙ ግንዛቤ በመፍጠር ሰዎች ህይወታቸውን እንዲጠብቁና ሌሎችን ሰዎች እንዲታደጉ በኩላችንን ጥረት ሁላችንም ልናደርግ ይገባል። ስለ ቫይረሱ በአንድ ፅሁፍ ማጠናቀቅ ባንችልም አንዳንድ አንኳር አንኳር የሆኑ ነጥቦችን እናስታውስ ብለን ያዘጋጀነውን አብረን እንመልከት።
በሰውነታችን ካሉት ፈሳሾች ኤች አይ ቪ በየትኛው ውስጥ ይገኛል?
በሰውነታችን ውስጥ ካሉት ፈሳሾች የኤች አይ ቪ ቫይረስ የሚገኘው፡ በደም፣ በወንድ ልጅ ዘር ውስጥ ባለው ፈሳሽ ፤ከሴት ማህጸን ውስጥ ከሚወጣው ፈሳሽ እና በጡት ውስጥ ከሚገኘው ወተት ውስጥ ነው። የኤች አይ ቪ ቫይረስ ለመተላለፍም ከቫይረሱ ጋር ከሚኖረው ሰው ወደ ጤነኛ ሰው ለመተላለፍ ይህ ፈሳሽ ወደ ጤነኛ ሰው አካል መግባትና ከደም ጋር መቀላቀል አለበት።
የዚህን በሽታ መተላለፍን አስመልክቶ እንደሚታወቀው ጥንቃቄ የጎደለው የግብረ ስጋ ግንኙነት የመጀመሪያው መንገድ ነው፣ በአጠቃላይ ኤች አይ ቪ ቫይረስ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፈው ከ95% በላይ በግብረ ስጋ ግንኙነት ነው። ከዚህም ውጪ ከእናት ወደ ልጅ በወሊድ ጊዜ ይተላለፋል። ስለት ባላቸው መሳሪያዎች በመጠቀም ሊተላለፍ ይችላል፣ ያልተመረመረ ደም በመውሰድ እና በመሳሰሉት መንገዶች ሊተላለፍ ይችላል።
የኤች አይ ቪ ቫይረስ አነስተኛ በሆነ መጠን (የመተላለፍ እድሉ ዝቅተኛ በሆነ ደረጃ) በጥልቅ ከንፈር ለከንፈር መሳሳም (Deep mouth kissing) ሊተላለፍ ይችላል። ቫይረሱ ሊተላለፍ የሚችለው የሚሳሳሙት ፍቅረኛሞች አፋቸው ላይ ቁስል ወይም የጥርስ ድዳቸው የሚደማ ከሆነ ብቻ ነው። እንዲሁም የጤናማ ሰው አካል ቁስል ክፍት ሆኖ ቁስሉ ላይ የተጠቀሰው ፈሳሽ ከዚህ ከቫይረሱ ጋር የሚኖር ሰው ጋር ከተቀላቀለ ኤች አይቪ ቫይረስ የመተላለፍ እድሉ በጣም አነስተኛ በሆነ ደረጃም ቢሆን ሊተላለፍ ይችላል።
የኤች አይ ቪ ቫይረስ ደም ያልተቀላቀለበት እምባ እና ላብ ቫይረሱን አያስተላልፉም። ቁስል የሌለበት ሰውን ቆዳ በስቶ መግባትም አይችልም። አንድን ሰው የነደፈች የወባ ትንኝ ወደ ሌላ ሰው ማስተላለፍም አትችልም። በተመሳሳይም ከቫይረሱ ጋር የሚኖር ሰው የተጠቀመበት እቃ በመጠቀምና ኤች አይ ቪ ኤድስ ያለባቸው ግለሰቦች አካል በመሳም በሽታው ወደ ጤነኛው ሰው አይተላለፍም።
መመርምር ለምን ይጠቅማል
የኤች አይ ቪ ቫይረስ ወደ ሰውነት አካል ከገባ በኋላ እንደሚታወቀው የሰውነት የመከላከል አቅምን ጎድቶ የተለያዩ ምልክቶች እስኪያሳይ ድረስ ከ7- 10 ዓመት ድረስ ሊቆይ ይችላል፤ ይህ ማለት ቫይረሱ በሰውነት ውስጥ ካለ ህክምና አይፈልግም ማለት አይደለም። ምልክቶች የሚያሳየው የሰውን አካላት ከጎዳ በኋላ የሰውነት የመከላከል አቅምን ካዳከመ እና ለተጨማሪ በሽታ ካጋለጠ በኋላ ነው በሽታው መከሰቱን የምናውቀው።
እዚህ አስከፊ ደረጃ ላይ ሳይደርስ ተመርምሮ መድኃኒት በመውሰድ ኑሮአችንን በጥሩ ሁኔታ መቀጠል እንችላለን። የኤች አይ ቪ ቫይረስ መድኃኒት በወቅቱ ከተጀመረ ለረጅም ዓመታት ከቫይረሱ ጋር ተስማምቶ መኖር ይቻላል:: ምርመራ ሳይደረግና የቫይረሱን በአካል ውስጥ መኖር ሳይታወቅ ለረጅም ዓመታት ከቆየን ሰውነታችን በቫይረሱ ስለሚዳከምና ለተለያዩ በሽታዎች በቀላሉ ስለምንጋለጥ ቶሎ ለማገገም እንቸገራለን። ስለዚህም ተመርምሮ በጊዜ ውጤትን ማወቅ ቫይረሱን ወደ ሌሎች እንዳይተላለፍ ለመጠንቀቅ ከማስቻሉም በላይ በወቅቱ የሰውነትን አቅም የሚገነቡ ህክምናዎችን ለማግኘት ያስችላል።
የሆነ ሆኖ አንድ ጊዜ ብቻ ተመርምሮ ነጻ መሆን ዋስትና ሊሆን አይችልም። ምርመራ ተደርጎ ቫይረሱ በሰውነታችን ውስጥ ከሌለ ባለው ሁኔታ ላይ በመመስረት ዳግም ከ3 ወር በኋላ ምርመራ ማድረግ ግዴታ ነው። ምክንያቱም ይህ ቫይረስ የሰውነት አካል ውስጥ ከገባ በኋላ ለ3 ወራት ያህል በምርመራ ላይታይ ይችላል። ምርመራ ከተደረገ በኋላ የኤች አይ ቪ ቫይረስ በሰውነታችን ውስጥ ከሌለ ከዚህ በኋላ በቀጣይ ህይወታችን ከዚህ ቫይረስ እራሳችንን መጠበቅ እና ተመሳሳይ ጥንቃቄዎችን እስከ ህይወታችን ፍጻሜ ድረስ ማድረግን ባህላችን ልናደርገው ይገባል ።
ግብረ ስጋ ግንኙነት ከማድረግ መቆጠብ (Abstinence) መወሰን እና እርስ በርስ መወሰን (መተማመን) ይህ የማይቻል ከሆነ ሁልጊዜም ኮንዶም በአግባቡ በመጠቀም ከዚህ ቫይረስ መጠበቅ ይቻላል። ስለት ያላቸው መሳሪያዎች እንደ ጥፍር መቁረጫ፣ መርፌ በጋራ መጠቀም መተው ግዴታ ነው። የኤች አይቪ ቫይረስን አስከፊነት በዕለት ተዕለት ህይወታችን ውስጥ መርሳት የለብንም፤ እሱ አይረሳንምና !!!።
- Joint United Nations Programme on AIDS (UNAIDS): Ethiopia 2018
- World Health Organization: Health Information; HIV/AIDs Fact Sheets.
- Center for disease control and prevention (CDC); Basics of HIV/AIDS and HIV prevention
ዶ/ር ጉርሜሳ ሁንኬሳ
አርሲ ዩኒቨርስቲ
ሁራ ቡላ
አዲስ ዘመን ጥቅም6/2012