እስኪ ጎበዝ ከሀሜት ወጣ እንበልና ደግሞ ስለሀገር ዕድገትም እናውራ! ዝም ብዬ ሳየው አገራችን አድጋለች፤ አድጋለች ብያለሁ አድጋለች (መንግስት ብቻ ነው እንዴ ስለሀገር ዕድገት መመስከር ያለበት?) ይሄ እኔ የምነግራችሁ የአገራችን ዕድገት ግን በ‹‹ጂ ዲ ፒ›› የሚለካው አይደለም፡፡ የእኔ ጥናት (ደግሞ እውነት እንዳይመስላችሁ) በግለሰብ ላይ ያተኮረ ነው፡፡
በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ካፒታሊዝም ናት ወይስ ሶሻሊዝም? ይሄ ጥያቄ ከባድ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ለዚህ ጽሑፍ ግን ኢትዮጵያ የካፒታሊዝም ሥርዓት ተከታይ ናት (ኧረ ምን አስፈራኝ በትክክልም የካፒታሊዝም ሥርዓት ተከታይ ናት)፡፡ ትንሽ እንደ ኢኮኖሚ ተንታኝ ልሁንና፤ የካፒታሊዝም ሥርዓት ማለት ከአንድ ትልቅ ፎቅ አጠገብ ማደሪያ አጥተው ዝናብ ላይ የሚያድሩ የኔ ቢጤዎች ያሉበት ማለት ነው፡፡ ከአንድ ትልቅ ሆቴል ውስጥ ለቁርስ ብቻ ብዙ ሺህ ብር ተከፍሎ ሲበላ፤ ራት ሳይበላ ያደረ የኔ ቢጤ በርሃብ አንጀቱ ታጥፎ የሚለምንበት ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም የካፒታሊዝም ሥርዓት ማለት የግድ ሁሉም ሀብታም የሆነበት ማለት አይደለም፡፡
እንግዲህ እንዲህ ከሆነ አገሪቱ ውስጥ ብዙ ሀብታም መኖሩን የሚያሳይ የተዛነፈ ጥናት መሥራት ይቻላል፤ እንዲያውም እኮ የብዙ ጥናቶች ችግር ይሄው ነው፡፡ በተለይ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ደግሞ ይሄ ችግር ጎልቶ ይታያል፡፡ ጥናት የሚሰራው የሚፈልጉትን ነገር ለማሳየት እንጂ ትክክለኛ ጥናት አይደለም፡፡ ለምሳሌ በኢትዮጵያ ውስጥ ሀብታም መኖሩን ለማሳየት ከሆነ የጥናቱን ተሳታፊዎች ሀብታሞችን እየመረጡ ማካተት ነው፡፡ ከውጭ አገር የሚመጡ መሪዎች አገሪቱን አድንቀው የሚሄዱት ለምን ይመስላችኋል? ቦሌን እና ቤተ መንግስቱን እኮ ነው ጎብኝተው የሚሄዱት! እንግዲያው የኔን ቤት አያዩትም ነበር?
ወደ ሀሜት አልገባም ብዬ ገባሁ አይደል? (አመል ነው እንግዲህ ምን ይደረጋል!) ግዴለም አሁን ወደ እኔ ጥናት እንገባለን፡፡ ባደረኩት የመንደር ለመንደር ጥናት መሰረት ኢትዮጵያ ድሃ ናት የሚለው ውድቅ ነው፡፡ ምን ዋጋ አለው! ችግሩ ኢትዮጵያ ሀብታም ናት የሚለውም ውድቅ ነው (ግራ የገባው ጥናት!) ኢትዮጵያ ድሃም ናት፤ ሀብታምም ናት፡፡
አዲስ አበባ አያሳየው የለውም፡፡ ‹‹አዲስ አበባ ሁሉም ነገር ብዙ ነው›› የሚለው ዓረፍተ ነገር በጣም ገላጭ ነው፡፡ ስለድህነትና ጎዳና ላይ ስለወደቁ ሰዎች ብዙ ብለናል፡፡ እስኪ ደግሞ ስለሀብታም ልጆችም እናውራ፡፡
ፒያሳ ነው፡፡ ከጓደኞቼ ጋር በወርም ይሁን በሁለት ወር፤ ብቻ በተገናኘንበት አጋጣሚ የምንገባበት አንድ ካፌ አለ፡፡ ካፌው ውስጥ የሚገቡት የሀብታም ልጆች ናቸው፤ እኛ የምንገባው የሀብታም ልጅ ሆነን አይደለም፡፡ በሁለት ምክንያት እንለያያለን፡፡ አንደኛው እኛ የምንገባው በጣም ከፈጠነ በአሥራ አምስት ቀን ሲዘገይም እስከ ሁለትና ሦስት ወርም ልንቆይ እንችላለን፡፡ ሁለተኛው እኛ የምናዘውና እነርሱ የሚያዙት ያለው ልዩነት ሰፊ ነው፡፡ ‹‹ቆይ ግን ካፌ ውስጥ ይህን ያህል ልዩነት አለ እንዴ?›› የሚል አይጠፋም፡፡ እኔም የገረመኝ ካፌ ውስጥ ያን ያህል ልዩነት መኖሩ ነው፡፡ ልዩነቱ የአንድ በርገር ወይም ፒዛ ዋጋ አይደለም፤ ልዩነቱ ሌላ ነው፡፡
በተደጋጋሚ የታዘብኩት ነገር ነው፡፡ ይህ የሚሆነው ሁለት ወይም ሦስት ብቻ ሆነው ነው፡፡ ፒዛ ይታዘዛል፡፡ ፒዛው እስከሚደርስ ድረስ በርገር ይታዘዛል፡፡ ቀድሞ ከመጣው በርገር ላይ የተረፋቸው ሁለት የራበው ሰው አጥግቦ ይሸኛል (እኔማ ሄደህ አንሳው አንሳው ይለኛል)፡፡ በርገሩ ትንሽ ትንሽ ተቀምሶለት እንደተቀመጠ ፒዛው ይመጣል፡፡ ፒዛውም እንደዚሁ ነው፤ ትንሽ ተበልቶለት ነው የሚመለሰው፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ እኔ ስማቸውን የማላውቃቸው ብዙ አይነት የሚበሉና የሚጠጡ አሉ፡፡ አንዳንዱ በስትሮ የሚመጠጥ፣ አንዳንዱ ዕቃው በእጅ እየተጨመቀ የሚጠጣ፣ አንዳንዱ በማንኪያ የሚጠጣ(የሚበላም ማለት ይቻላል)…ኧረ ስንቱ!
ይሄ ሁሉ ሲሆን እኔ ውስጤ ይስቃል፡፡ የምስቀው በራሴ ነው፡፡ እነዚህ ልጆች የአራዳነት ጣሪያ ላይ ነን ብለው የሚያስቡ ናቸው፤ እኔ ደግሞ የፋራነት ጣሪያ ላይ ነኝ፡፡ ፋራነቴ ያንን በማድረጋቸው ከመደነቄ ይጀምራል፡፡ እውነቱን ስነግራችሁ ያንን ሁሉ ሳይ በፍጹም ሳላስነቃ ነው(ኧረ እንዲህም አራዳ ነኝ)፡፡ ይሄን ሁሉ ትዝብት ስነግራችሁ እኮ አይኔን ላያቸው ላይ ተክዬ አይደለም፡፡ አንዴ ባየሁት ብቻ ብዙ ነገር አስተውላለሁ፡፡ በዚያ ላይ ከፊቴ ነው ያሉት፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ ሴቶቹ በጣም ቆንጆ ናቸው(ለካ የሀብታም ልጅ ቆንጆ ነው)፤ ጓደኞቼ በቁንጅናቸው ተማርከው ፊታቸው ላይ ሲያፈጡ እኔ የሚበሉት ላይ (አይ የሆዳም ነገር!)፤ በእርግጥ እግረ መንገዴን ውበታቸውንም አያለሁ፡፡ በነገራችን ላይ ቢያዩኝ ራሱ በቁንጅናቸው እንደሆነ ስለሚያምኑ አይነቁብኝም፡፡
ውይ! አሁንስ ፋራነቱን አበዛሁት! ሒሳብ ሲከፍሉ ነው ደግሞ ልብ ብዬ የማያቸው፡፡ ያው እንግዲህ የተጠቀሙትን ነገር ስጠቃቅስላችሁ ነበር አይደል? ለመሆኑ የዚህ ሁሉ ዋጋው ስንት ይሆን? ብዬ ሳይ ከሀገር ሊወጣ ሲል ተያዘ እየተባለ በፌስቡክ የሚዘዋወረውን ብር ያክላል፡፡ ያው እንግዲህ ፋራ ከተባልኩ አይቀር ብዬ የሚተውትን ‹‹ቲፕ›› ሁሉ ሳይቀር ነው የማየው፡፡ እነርሱ የሚተውት ‹‹ቲፕ›› እኔ ለመዝናናት ይዤው የምገባው ነው(ኧረ እንዲያውም ይበልጣል)፡፡
ለምን ያን ያህል ‹‹ቲፕ›› ይሰጣሉ ብዬ እየተቃወምኩ አይደለም፤ የልጆቹ ሀብታምነት ነው ያስገረመኝ፡፡ በነገራችን ላይ እኔ ‹‹ቲፕ›› የምሰጠው (ሁለትም ይሁን ሦስት ብር) ደንብ ነው ብዬ አይደለም፤ አራዳ ለመምሰልም አይደለም፤ ወይም ደግሞ የቤቱ ደንበኛ ስለሆንኩም አይደለም፤ በቃ አስተናጋጆቹ ስለሚያሳዝኑኝ ነው፡፡ የዚያን ሁሉ ሰው ፀባይ ችለው፣ እግራቸው እስከሚንቀጠቀጥ ቆመው ስለሚሰሩ ነው፡፡
እነዚያ አሥር አይነት ምግብ ሲቀያይሩ የነበሩት ምን ሠርተው እንደሚያመጡት አይታወቅም፤ ይህኔ የሌባ ባለሥልጣን ልጆችም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ መቼም ሰርቶ ያገኘ ሰው እንደዚያ በብር አይጫወትም፤ ድካሙን ያውቀዋል፡፡ ሲጀመር ሰርቶ የሚያገኝ ሰው እንዲህ አይነት የተትረፈረፈ ጊዜም አይኖረውም፡፡ ይልቅ ሌላ ነገር ልገምት፤ ከሰውም እንደምሰማው ሊሆን የሚችለው ዳያስፖራ ቤተሰብ ያላቸው ልጆች ይሆናሉ፡፡
ታዲያ ከዚህ ተነስተን አገራችን አድጋለች ማለት አንችልም? እንዲያው አንድ ጉዳይ ላይ ላተኩር ብዬ ነው ካፌን የመረጥኩ እንጂ ሌላም እንዲህ አይነት ያየሁባቸው ብዙ አጋጣሚዎች አሉ፡፡ እነዚያን ነገሮች እኮ በአግባቡ ማድረግ ይቻል ነበር፡፡ ለምሳሌ ያንኑ የጀመርነውን የካፌውን እንውሰድ፡፡ ከታዘዙት የምግብ አይነቶች ውስጥ ከተበላው ይልቅ ሳይበላ የተመለሰው ይበልጣል፡፡ ሲጀመር ገና በበርገሩ ነው የጠገቡት፤ ስለዚህ ፒዛው የታዘዘው ለፕሮቶኮል መሆኑ ነው፡፡ በቃ ለእነርሱ ግዴታዊ ደንብ ነው፡፡ ስለዚህ ጉዳይ እነርሱ ጋ ማንሳት የለየለት ፋራነት ነው፡፡ ‹‹እንዲህ ስትጫወቱበት በሩ ላይ ደረቅ ዳቦ የራበው አለ›› ቢባሉ ‹‹ታዲያ ምን አገባኝ!›› ብለው ሊሳደቡም ይችላሉ፡፡ ከርሃብተኛው ይልቅ ይህንን ባለው ሰው ፋራነት ያዝናሉ፡፡
ነገሩን እንደ መብት ካየነው ምንም ክርክር የለውም መብት ነው፡፡ ገና ለገና ድሃ አለና በልክ እንመገብ ሊሉ አይችሉም፡፡ በዚያ ላይ ይሄ የግለሰብ ጉዳይ ነው፡፡ ነገሩን እንደ አገር ካየነውም ግን የዚህ አምሳል ነው፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ21/2011
ዋለልኝ አየለ