ከፍተሻው እንዳለፉ በነጭ ሸሚዝና ጥቁር ሰደርያ የደንብ ልብስ የለበሱና ጥቁር ኮፊያ አናታቸው ላይ ያደረጉ አስጎብኚ ወጣቶች አቀባበል ይደረግልዎታል። ከመካከላቸው አይኗ ጎላ ጎላ ያለው ፈገግታ ያላት ወጣት ናት ትምኒት ቢኒያም። ይህች ልጅ ጎብኝዎች ወደ አንድነት ፓርክ ዘልቀው ሲገቡ በፈገግታ ተቀብላ በቀላሉ የሚመሩበትን ‹ማፕ› ወይም ጠቃሚ መረጃ የያዘውን በምስል የተደገፈ ገላጭ ወረቀት በመስጠትና በማሳየት ታስጎበኛለች።
እንግዶችዋን በማስተናገድ ሥራ ተጠምዳ ያገኘኋት ወጣት ትምኒት በአንድነት ፓርክ በአስጎብኝነት ተቀጥራ ስትሰራ ገና የሁለት ሳምንት ዕድሜ ብቻ ነው ያላት። መስተንግዶዋ ግን በሥራው ላይ ልምድ ያላት ነው የምትመስለው። በአጭር ጊዜ እንዲህ ያለ ችሎታ ማዳበሯ፣ ታሪካዊ በሆነው አንድነት ፓርክ ውስጥ መስራትዋ ደግሞ የፈጠረባትን ስሜት እንድታጋራኝ ጠየኳት።
ወጣት ትምኒት እንዳጫወተችኝ ፓርኩ ያወጣውን የሥራ መስፈርት በማሟላቷና የቅጥር ፈተናውንም በማለፏ ነው የሥራ ዕድሉን ያገኘቸው። የተማረችው ትምህርት ግን ከሥራዋ ጋር አይገናኝም። በጠቅላላ ህክምና ነው ከሐያት ሜዲካል ኮሌጅ ከሁለት ዓመት በፊት የተመረቀችው። አሁን በምትገኝበት አንድነት ፓርክ ውስጥ ለመቀጠር የተለያዩ የታሪክ መጽሐፍትን በማንበብና ከታሪክ አዋቂዎችም መረጃዎችን በመውሰድ ዝግጅት አድርጋለች። ቅጥር ከፈጸመች በኋላም ስልጠና በማግኘቷ ሥራ ላይ አልተቸገረችም። ይህ ስራም ዋናው ፍላጎቷ እንደሆነም ትናገራለች።
በአንድነት ፓርክ ውስጥ መስራትዋ እራስዋን እንደ ታሪክ ባለቤት እንደምታይ የምትናገረው ወጣት ትምኒት የኢትዮጵያን ታሪክ ለማወቅ ዕድል እንደፈጠረላትና ሥራውን ከጀመረች በኋላም ታሪክን ለማወቅ ያላት ፍላጎት መጨመሩን ገልጻለች። ፓርኩ ከምድረ ግቢው አቀማመጥ ጀምሮ በውስጡ ተሰንዶ የሚገኘው ታሪክ ግንዛቤን የሚያስጨብጥና ትውልድን የሚያኮራ ሆኖ አግኝታዋለች። ወጣቱ እንዲህ ያሉ ታሪካዊ ቦታዎችን ቢጎበኝ ነገሮችን በተለይ ደግሞ ታሪክን ለማመዛዘንና ለባለታሪኮችም ዋጋ ለመስጠት እንደሚረዳው ሀሳብዋን አካፍላለች። ትናንት በተሰራው ታሪክ የዛሬ ወጣቶች የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸው ስለታሪካቸው እያወቁ መተዳደሪያ የሚያገኙበት የሥራ ዕድል መፈጠሩንም ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል ብላለች።
ስለኢትዮጵያ ታሪክ የማስተዋወቅ ሥራ ባለመሰራቱ ወጣቱ በውጭው ታሪክ እንዲሳብ እንዳደረገውና በተለይ የውጭዎቹ ታሪኮቻቸውን ወጣቱን በሚስብ በፊልም በማቅረብ እንደሚበልጡ ታስረዳለች። ‹‹ድንቅ የሆነና የምንደመምበት ታሪክ እያለን በውጭው ላይ ትኩረት ማድረጋችን የቆጨኝ አንድነት ፓርክን ካየሁ በኋላ ነው›› የምትለው ወጣት ትምኒት ‹እባካችሁ ኑና ታሪካችሁን አንብቡ› ስትል ጥሪዋን አቅርባለች።
ከትውልድ አካባቢው ነቀምት በሥራ ኑሮውን አዲስ አበባ ያደረገው ወጣት ዓለሙ ጥላሁን ‹ራማ ኮንስትራክሽን› በተባለ የግል ድርጅት ውስጥ የፍሳሽ ማስወገጃ (ሳኒተሪ) መሀንዲስ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል። አንድነት ፓርክ የሚገኝበትን ታላቁ ቤተመንግሥት ለማየት የበቃው በሙያው አማካኝነት ነው። ወጣት ዓለሙ በትውልድ ሥፍራው ሙዚየሞችና የነገሥታት መኖሪያዎችን እንኳን ጎብኝቶ አያወቅም። ትኩረት ካለመስጠት እንጂ ሌላ ምክንያት እንደሌለው ይናገራል። በአንድነት ፓርክ ውስጥ መስራቱ ለታሪክ ቦታ እንዲሰጥ እንዳደረገውም ይናገራል።
ወጣት ዓለሙ በሥራው ገንዘብ ቢያገኝበትም አሻራውን አሳርፏል። በቤተመንግሥት ግቢው ውስጥ መገኘትም ትልቅ ነገር እንደሆነ ይገልጻል። ወጣቱ የታሪክ ባለቤት መሆኑን የማወቅ ግዴታ እንዳለበትም ይናገራል። ቤተሰብና መንግሥት ግን ትልቁን ድርሻ ይይዛሉ ይላል። እርሱም ታናናሾቹን በማስጎብኘት የድርሻውን እንደሚወጣ ቃል ገብቷል። በስሜታዊነት እየተገፋፉ ለጥፋት የሚሯሯጡ ወጣቶችም ታሪካቸውን ቢያውቁ ሰከን ሊሉ እንደሚችሉ መልዕክቱን አስተላልፏል።
ከቤተሰቦችዋ ጋር አንድነት ፓርክን ስትጎበኝ ያገኘኋት በአዲስ አበባ ከተማ ፈረሳይ ለጋሲዮን ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪ የሆነችው ወጣት አይዳ ለማ ባየችው ሁሉ መደሰቷን ትናገራለች። በአዲስ አበባ ውስጥ ከሚገኙ ሙዚየሞች የተወሰኑትን ብትጎበኝም አንድነት ፓርክ ለየት ያሉ ታሪኮችን በመያዙና የመጎብኘት ዕድሉንም አገኛለሁ ብላ ባለማሰቧ ተደስታለች።
ወጣት አይዳ ፓርኩን ከመጎብኘቷ በፊት እና ከጎበኘች በኋላም ያላትን ስሜት እንደገለጸችልኝ ጉብኝቱ ከሶስት ሰዓት በላይ ይወስዳል ብላ አልጠበቀችም። በነገሥታቱ ዘመን የተገነቡ ቤቶችን ብቻ እንደምታይ ነበር የገመተችው። ከጠበቀችው በላይ በመሆኑ ተደስታለች። በፓርኩ ውስጥ ትኩረቷን ከሳቡት መስህቦች መካከልም አጼ ምኒልክ ይጫሙት የነበረውን ወርቃማ ጫማና የእጅ ጭራቸው ሳይጉላላ አዲስ መሆኑ፣ የእቴጌ ጣይቱ የመኝታ ክፍል ዘመናዊነት መሆን ይጠቀሳሉ።
አብዛኞቹ ወጣቶች ታሪካዊ ቦታዎችን የማየትም ሆነ በታሪካቸው መኩራት ላይ ግድ ያለመስጠታቸው ጉዳይ በእርሷም ስሜት ውስጥ እንዳለ አይዳ ትናገራለች። እርሷ እንዳለችው አንድነት ፓርክ ሥራውን ከመጀመሩ በፊት ጀምሮ የቅስቀሳ ሥራ ተሰርቷል። ይሄ ደግሞ ሰው ለመጎብኘት ጉጉት አሳድሯል።
እንዲህ አይነት ነገር ባለመለመዱ እና ታሪክ ላይ ትኩረት ያደረጉ ዘጋቢ ፊልሞች አለመኖራቸው፣ በአጠቃላይ ወጣቱም ሆነ ሌላው ህብረተሰብ ታሪክን ለማወቅ ጉጉት እንዲኖረው የሚያደርግ ሥራ ባለመሰራቱ ለታሪክ ግድ እንዳይኖር አድርጓል የሚል እምነት አላት። ወጣት አይዳ ታሪክን ለወጣቱ ማሳወቅ አሁንም አልረፈደም ትላለች። ሰዎች የተለያየ ሙያ ቢኖራቸውም ታሪካቸውን ከማወቅ የሚያግዳቸው ነገር መኖር እንደሌለበትም ትገልጻለች።
‹በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ› እንደሚባለው አይነት እየሰሩ ታሪክንም እያዩ ተጠቃሚ ከሆኑትና በጉብኝትም ታሪካቸውን ለማወቅ ጥረት ካደረጉ ወጣቶቹ ጋር በአንድነት ፓርክ እንዲህ ነበር ቆይታችን።
አዲስ ዘመን ጥቅም4/2012
ለምለም መንግሥቱ