ቅዳሜ ጥቅምት 7 ቀን 1963 ዓ.ም የወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ 30ኛ ዓመት ቁጥር 240 እትም በሌሊት ያለሰፈሯ ስትዞር በመገኘቷ በፍርድ ቤት ቅጣት ስለተላለፈባት እንስት ተከታዩን ዘገባ አስነብቦ ነበር፡፡
ፋንቱ ያለሰፈሯ ሌሊት ስትዞር ተይዛ ታሰረች
ወይዘሮ ፋንቱ ወልደማሪያም የተባለች በንፋስ ስልክ አካባቢ የምትኖር ሴት ያለሰፈሯ ከሌሊቱ በ10 ሰዓት በየካቲት 12 አደባባይ ስትዘዋወር በመገኘቷ ተይዛ የሶስተኛ ወረዳ ፍርድ ቤት የአንድ ወር እስራት የቀጣት መሆኑን አስታውቋል። ስትዘዋወር መገኘቷንና ተላላፊ መኪናዎችንም አድርሱኝ በማለት ማስቸገሯን ፖሊሶች መመስከራቸው ታውቋል፡፡
ተከሳሿም ፍርድ ቤት ቀርባ በተጠየቀች ጊዜ በአድራጎቷ ጥፋተኛ መሆኗን ስላመነች ፤ ፍርዱ ተሸሽሎላት በ30 ብር መቀጫ ወይም በአንድ ወር እስራት እንድትቀጣ ተደርጎ መቀጫውን መክፈል ስላልቻለች አንድ ወር እንድትታሰር ወደ ወህኒ ወርዳለች ሲል ከአንደኛ ፖሊስ ጣቢያ አካባቢ ከሶስተኛ ወረዳ ፍርድ ቤት የተገኘ ዜና ያስረዳል፡፡
*****************
ቅዳሜ ነሐሴ 9 ቀን 1945 ዓ.ም የወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ 13ኛ ዓመት ቁጥር 17 እትም “ፉጨት የብልግና መጀመሪያ ነው” በሚል ርእስ አንድ ግለሰብ ለጋዜጣው የላኩትን ጽሑፍ አስነብቦ ነበር፡፡
ፉጨት የብልግና መጀመሪያ ነው
ፉጨት የብልግና መጀመሪያ ነው የሚል አርዕስትን መነሻ አድርጌ ለአንባቢዎች ለማሳሰብ የተነሳሁበት ዋናው ምክንያት በአንዳንድ ስፍራዎች በፉጨት ብልግና የሚፈጸመውን መጥፎ ምግባር በመመልከቴ ነው፡፡
የፉጨት ስሜት ሊነሳ የሚችለው በኦርኬስትራ ወይም በዳንስ ቤቶች በሚደረገው የጨወታ ጊዜ እንጂ በሆስፒታልና በአድሚኒስትራሲዮን በመሳሰሉት ጸጥታ በሚያስፈልግባቸው ስፍራዎች አይደለምና ይህን የመሰለ ምግባር የሚታይባቸው አንዳንድ ወጣቶች ቢታረሙ በተመልካች ዘንድ የሚያስነቅፋቸው አይሆንም፡፡
ነሐሴ 4 ቀን 1945 ዓ.ም አንድ የታመመ ሰው ለመጠየቅ ወደ ሆስፒታል ሄጄ ነበር፡፡ በማስታመሚያ ክፍል ብዙ የጸናባቸው ታካሚዎች ተኝተዋል፡፡ እንደኔው አንዱን ታማሚ ለመጠየቅ ወደ ክፍሉ የገባ አንድ አለባበሱና ቁመናው ደስ የሚያሰኝ ወጣት የብልግና መንፈስ በጋረደው ስሜት ባርኔጣውን ከራሱ ላይ ጋደል አድርጎ በሩን በኃይል ከፍቶ መግባቱ ሲገርመኝ የባሰውን ይግረምህ ብሎ ፉጨቱን ለቀቀው፡፡ ይህ ወጣት በሽተኛውን ለማበሳጨት እንጂ ለመጠየቅ አልመጣም በማለት ከሐሳቤ ጋር ከተፈታተንኩ በኋላ ሕመምተኛውን እግዚአብሔር ይማርህ ብዬ ወደ ጉዳዬ ሄድኩኝ፡፡
ይህም ብቻ ሳይሆን በየስፍራው የሚታየው የአንዳንድ ወጣቶች የብልግና ስሜት ያልታረመ ሆኖ በመገኘቱ በብዙ ተመልካቾች ዘንድ ቅሬታን ያስከተለ ስለሆነ ይህን ከመሰለ ከሚያስነቅፍ ተግባር ለመዳን መታረም ያስፈልጋል፡፡
አገኘው ገብሬ ዘብሔረ የጁ
*****************
ረቡዕ ታህሳስ 21 ቀን 1946 ዓ.ም የወጣው ሰንደቅ ዓላማችን ጋዜጣ 13ኛ ዓመት ቁጥር 37 እትም “በገዛ እጁ” በሚል ርእስ ስለ አንድ ጀርመናዊ መሐንዲስ ተከታዩን ዘገባ አስነብቦ ነበር፡፡
በገዛ እጁ
እግሮቹን የቅዝቃዜ (ሪህ) በሽታ ሲያሰቃያቸው የኖረው አንድ የጀርመን መሐንዲስ በአዲስ አይነት ብልሃት የተፈለሰፈ የሙቀት ማቀበያ ዲናሞ ሰርቶ ከህመሙ በገዛ እጁ ለመዳን ችሏል፡፡ ይህም መሐንዲስ ምን አደረገ ቢባል ከመጫሚያዎቹ ተረከዞች ጋር የሚገናኝ አንድ አነስተኛ ዲናሞ ሰርቶ እግሮቹ በተራመዱ ቁጥር ዲናሞው በሚያደርገው መንቀሳቀስ የኤሌክትሪክ ሙቀት ይሰጠው ስለነበር ከሕመሙ በገዛ እጁ ለመታገስ ባወጣው አዲስ ዓይነት ብልሐት ታክሞ ለመዳን ችሏል፡፡
አዲስ ዘመን ኅዳር3/2012
የትናየት ፈሩ