የዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ልጅ ልዑል ዓለማየሁ ወደ እንግሊዝ አገር ተወስዶ 12 ዓመታት በዚያ ከኖረ በኋላ በ19 ዓመቱ ህይወቱ ያለፈው ከ 140 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ህዳር 5 ቀን 1872 ዓ.ም ነበር።
ጳውሎስ ኞኞ የአፄ ቴዎድሮስን ታሪክ በተረከበት መጽሐፉ እንዳሰፈረው አለማየሁ በደብረ ታቦር ከተማ በ1853 ዓ.ም ሚያዝያ አምስት ቀን ሲወለድ አፄ ቴዎድሮስ መድፍና ጠመንጃ አስተኩሰዋል። 500 ያህል እስረኞችንም ፈትተዋል። ቴዎድሮስ ከአለማየሁ ጋር ሲጫወቱ መዋል በጣም ያስደስታቸው ነበር። ተናደውና ተበሳጭተው በሚመለሱበት ጊዜ እንኳን አለማየሁን ታቅፈው ሲስሙ ንዴታቸውም ሆነ ብስጭታቸው ይጠፋላቸው ነበር ይባላል።
አፄ ቴዎድሮስ መቅደላ ላይ እጄን ለእንግሊዞች አልሰጥም ብለው ሽጉጣቸውን ጠጥተው ህይወታቸው ካለፈ በኋላ ልዑል አለማየሁም በእንግሊዞች እጅ ወደቀ። እንግሊዞች ከመቅደላ ጦርነት በኋላ በርካታ ቅርስና ሀብት ወደ አገራቸው ሲያግዙ የሰባት ዓመት እድሜ የነበረው ልዑል አለማየሁም ወደ እንግሊዝ ተወሰደ።
ልዑል ዓለማየሁን ከአፄ ቴዎድሮስ የወለዱት እቴጌ ጥሩ ወርቅ ናቸው። እንግሊዞች ልዑሉን ከእነ እናቱ ይዘው ነበር ወደ እንግሊዝ መጓዝ የጀመሩት። ጀነራል ናፒየር አማርኛ ቋንቋ አቀላጥፎ የሚናገረውን ካፒቴን እስፒዲን የአለማየሁ ሞግዚትና ኃላፊ አድርጎ ሾመው። በቴዎድሮስ ቤተ መንግስት የታወቁት አለቃ ዝርአትና አቶ ገብረ መድኅን የተባሉ ሁለት ሞግዚቶችና አጫዋቾችም ተመረጡለት።
እቴጌ ጥሩ ወርቅ በሞት አፋፍ ላይ ሆነው ካፒቴን እስፒዲን አስጠርተው እጁን ይዘው “ልጄ አባት የለውም። እኔም እናቱ ልሞት ነው። በሚሄድበትም አገር ዘመድ ስለሌለው አንተ ዘመድ ሁነው። ይሄን ያልኩህን ሁሉ እንደምታደርግለት በእግዚአብሔር ማልልኝ” አሉት። እስፒዲም የጠየቁኝን ሁሉ እፈጽመዋለሁ ብሎ ማለላቸው።
ተክለጻድቅ መኩሪያ “አፄ ቴዎድሮስና የኢትዮጵያ አንድነት” በተሰኘ መጽሐፋቸው እቴጌ ጥሩ ወርቅ በጉዞ ላይ እያሉ ህመም ጸንቶባቸው ሰውነታቸው እየተዳከመ ሄዶ ትግራይ ሲደርሱ ግንቦት ሰባት ቀን አረፉ። ናፒየር በተባለው የእንግሊዝ ጀነራል ፈቃድ አስክሬናቸው ወደ ሸለቆት ሄዶ እናታቸውና ዘመድ አዝማድ እየተላቀሰ ከስመ ጥሩው የትግሬ መስፍን ከራስ ወልደሥላሴ መቃብር ጎን በክብር ተቀበሩ። የእቴጌ ጥሩወርቅ እናትም ዓለማየሁ ያገሩን አማርኛ ቋንቋ እንዳይረሳ አደራ በማለት እንግሊዞችን ተማጽነው ተሰናበቱት ይላሉ።
ልዑል አለማየሁ እንግሊዝ አገር ከደረሰ በኋላ ከእንግሊዝ ንግስት ቪክቶሪያ ጋር ተገናኘ። ንግስቲቱ ለአለማየሁ ማንኛውም ጥንቃቄ እንዲደረግለት አዘዙ። የፍርሃት ነገር ከአእምሮ እንዲጠፋ ሐኪሞች ሁሉ ተባብረው እንዲያድኑት አሳሰቡ። ንግስት ቪክቶሪያ አለማየሁን በተቀበሉበት ወቅት ስለነበረበት ሁኔታ ማስታወሻ ደብተራቸው ላይ “ምስኪኑ ልጅ (ፑር ቻይልድ) አሁንም ፍርሃቱ አለቀቀውም። መቅደላ በተያዘ ጊዜ በዚያ የነበረውን እልቂትና የአባቱን ሞት ስላየ ያ ነገር በአእምሮው ይመጣበታል። …” ብለው ጽፈዋል።
ተክለጻዲቅ የልዑል አለማየሁ አያት ላቂያዬ (ታላቄ) ስለልጅ ልጃቸው ስጋት ገብቷቸው ለእንግሊዝ ንግስት ቪክቶሪያ ተከታዩን ያደራ ደብዳቤ ስለመላካቸውም ጽፈዋል። “በስመ አብ … ከወይዘሮ ላቂያዬ የእቴጌ ጥሩወርቅ እናት ፣ የደጃዝማች ዓለማየሁ እሜታ (አያት) የተላከ። ይድረስ ለንግስት እንግሊዝ። አንባቢው እጅ ይንሳልኝ ፤ መድኃኔ ዓለም ጤና ይስጥልኝ ፤ መንግስትዎን ያስፋ ፤ ጠላትዎን ያጥፋ።
ሦስት ደጃዝማቾች አራተኛ እቴጌ (ጥሩ ወርቅ) ሞተውብኝ የቀረኝ ደጃዝማች ዓለማየሁ ነው። አደራዎን ይጠብቁልኝ። እግዚአብሔር አባቱንና እናቱን ቢነሳው እርስዎን ሰጥቶታል። እኔም ካላየሁት ከሞቱት ቁጥር ነኝ። እርስዎን እናቴ ይላል እንጂ እኔን እናቴ አይለኝም፤ አላሳደግሁትምና። እርስዎ ያሳድጉት ስለ እግዚአብሔር ብለው።” በኋላም የዓለማየሁ አያት በስደት የነበረው የልጅ ልጃቸው ልዑል ዓለማየሁ ናፍቆት ቢበረታባቸው ጥር 4 ቀን 1862 ዓ.ም. የጻፉለት ደብዳቤ አሁንም ድረስ በብሪታንያ ግምጃ ቤት ይገኛል።
የልዑል አለማየሁ የስደት ህይወት አሳዛኝ ነበር። ልዑሉ በብቸኝነት ሲሰቃይ ቆይቶ በ18 ዓመቱ እንደሞተ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ። የእውቁ ታሪክ ጸሐፊ ሪቻርድ ፓንክረስት ልጅ አሉላ ፓንክረስት በመጨረሻ ከልዑል አለማየሁ አንደበት “ተመርዣለሁ” የሚል ቃል ስለመደመጡ ጽፏል።
አለማየሁ በጠና ታሞ ምግብም ሆነ መድኃኒት መውሰድ የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሶ ህዳር 5 ቀን 1872 ዓ.ም ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ከሩብ በተወለደ በ19 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ። በንግስት ቪክቶሪያ ትዕዛዝ ዊንድሰር በሚገኘው የነገስታት መቀበሪያ በቅዱስ ቤተ ክርስቲያን ተቀበረ። በመቃብሩም ላይ “የአበሻው ልዑል አለማየሁ አፕሪል 13 ቀን 1861 ተወለደ ኖቬምበር 14 ቀን 1879 አረፈ” የሚል ጽሑፍ ሰፈረ። ንግስት ቪክቶሪያም ከዚህ ጽሑፍ በታች “እንግዳ ሆኜ መጣሁ ተቀበላችሁኝም” የሚለው የወንጌል ቃል እንዲጻፍ አደረጉ። ንግስት ቪክቶሪያ ስለ ልዑሉ እረፍት የተሰማቸውን ሀዘን በዕለት ማስታወሻቸው ሲገልጹ “በሰው ሃገር ባይተዋር ሆነህ ደስተኛ ሳትሆን በመሞትህ አዝናለሁ” ብለዋል።
አፅሙ አገሩ እንዲያርፍ ለእንግሊዝ መንግሥት በተደጋጋሚ ጥያቄ የቀረበ ቢሆንም እስካሁን ምላሽ አላገኘም። እንግሊዞች ከኢትዮጵያ የመዘበሯቸውን ቅርሶች እንዲመለሱ በተለያዩ ምሁራን፣ አገር ወዳድ ግለሰቦችና በመንግስት ደረጃ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል።
በቅርቡ የአፄ ቴዎድሮስ ቁንዳላ በተመለሰበት ወቅት የባህልና ቱሪዝም ሚንስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ የልዑል አለማየሁን አፅም ለማስመለስ ያለሰለሰ ጥረት እየተደረገ ስለመሆኑ ተናግረዋል። የልዑሉን አጽም እንግሊዞች ለኢትዮጵያውያን ይመልሳሉ ብለው እንደሚያምኑ ገልጸው ይህን ለማሳካት በእንግሊዝ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበው ነበር። ሚንስትሯ የልዑሉ አፅም ቢመለስ የሚቀመጥበት ቦታ መዘጋጀቱንና ለዚህም ታላቁ ቤተ መንግሥት መመረጡን አስታውቀዋል።
በ2007 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ጥበባት ኮሌጅ ዲን በነበሩት ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ አዘጋጅነት “ልዑል አለማየሁ” የተሰኘ የልዑሉን ታሪክ የሚዳስስ ሙዚቃዊ ተውኔት በዩኒቨርሲቲው የቴአትር ጥበባት ተማሪዎች ተሳትፎ ለእይታ በቅቶ ነበር።
አዲስ ዘመን ጥቅም3/2012
የትናየት ፈሩ