የፌዴራል የኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከል እና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት በ2030 ኤድስን ማቆም የሚል ራዕይ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። የጽ/ቤቱም ተልዕኮ ለዘርፈ ብዙ ጸረ-ኤች አይ ቪ ኤድስ ምላሽ ስኬታማነት ህብረተሰቡን፣ አጋሮችንና ሁሉንም ዘርፎች በማስተባበር፣ ሀብትን በማሰባሰብና አቅምን በመገንባት የወረርሽኙን ስርጭት መከላከል መቆጣጠርና የሚያስከትለውን ተጽእኖ መቀነስ እንዲሁም ለምላሹ የሚውለውን ሀብት በአግባቡ መዋሉንና ውጤታማ መሆኑን መከታተልና ማረጋገጥ የሚል ነው።
ከፌዴራል ኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት ራዕይ እና ተልዕኮ መረዳት እንደሚቻለው በ2030 እ.ኤ.አ ኤች አይቪ ኤድስን ለማቆም በሚደረገው እንቅስቃሴ በተለይም ያሉትን ወቅታዊ የስርጭቱን ሁኔታ የሚያሳዩ መረጃዎች ለህብረተሰቡ ተደራሽ ማድረጉ አስፈላጊ ነው። ስርጭቱን ከመከላከል እና አስፈላጊውን የትምህርት ሁኔታ ተደራሽ ለማድረግም ባለድርሻ አካላት በተለይ ለህብረተሰቡ ቅርበት ያላቸው አርቲስቶችና የጥበብ ባለሙያዎች፣ በየትምህርት ተቋማት ያሉ መምህራንና፣ ክበባት እንዲሁም የሚዲያ አካላት፣ በየመስሪያ ቦታዎች ያሉ አካላት እንዲሁም ሁሉም ዘርፎች ተሳትፎ ማድረጋቸው ተገቢ ነው።
የዚህው ኤች አይ ቪ ኤድስ የመከላከል አካል የሆነው እና አርቲስቶችን እና የጥበብ ሰዎችን ባሳተፈ መልኩ ታህሳስ 11 ቀን 2011 ዓ.ም በካፒታል ሆቴል «አሁንም ትኩረት ለኤች አይ ቪ መከላከል በሚል» በዋፋ እና በፌዴራል ኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት ትብብር ኤች አይ ቪ ኤድስ በዘመናት መካከል ያለውን ሁኔታ የሚያሳይ መረጃ ቀርቧል።
በዚህም የፌዴራል ኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት ዘርፈ ብዙ ምላሽ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ክፍሌ ምትኩ ባስተላለፉት ጥናታዊ መረጃ መሰረት በተለያዩ ወቅቶች ቫይረሱ የተለያየ የማህበረሰብ እይታ እና ውጤቶች እንደነበሩት አብራርተዋል።
በመሆኑም ከ1972-1982 ዓ.ም ያለው ዘመን የመጀመሪያው ኤች አይ ቪ የተከሰተበት ሲሆን፣ ይህም ጊዜ የዝምታ ጊዜ በመባል ይታወቃል። በዚህ ወቅት ቫይረሱ ውስጥ ለውስጥ የተስፋፋበት፣ መረጃዎች ተደራሽ ያልሆኑበት፣ ችግሩ በቸልታ የሚታይበት፣ አድሎና መገለል የበዛበት እንዲሁም ፍርሃት የሰፈነበት ወቅት ነበር።
ሁለተኛው (ከ1982-1992 ዓ.ም ) ያለው ወቅት የኤች ኤይ ቪ ወረርሽኝ ወደ ኤድስ ደረጃ የደረሰበት ሲሆን፣ በዚህም ጊዜ አድሎና መገለል በስፋት ጎልቶ የተንፀባረቀበት፤ የወቅቱን ተግዳሮት ለመመከትና ለመቀበል በአመራሩም ይሁን በአጋር ድርጅቶች ቁርጠኝነት ያልታየበት ወቅት በመሆኑ ችግሩ ውስብስብ ወደ ሆነ ደረጃ የደረሰ ጊዜ እንደነበር አውስተዋል።
በሶስተኛነት ያለው ዘመን(1887-1992) ሲሆን፣ ወቅቱም ዘርፈ ብዙ ምላሽ የተጠናከረበት ጊዜ እንደሆነ ተገልጿል። በዚህም ጊዜ ችግሩ ብዙ ምላሹም ዘርፈ ብዙ መሆኑ መግባባት የተደረሰበት፣ የሁሉንም ርብርብና የማህበረሰቡ ተሳትፎና ባለቤትነት ያስፈለገበት፣ የጸረ-ኤች አይ ቪ መድኃኒት በነፃ የተጀመረበትና የመከላከሉ ተግባር ከፍተኛ ትኩረት ያገኘበት ወቅት እንዲሁም ወረርሽኙ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገሮች የከፋ መሆኑ የታወቀበት ነበር።
አራተኛው (ከ1992-2002 ዓ.ም) የስርጭቱ ሁኔታ መቀነስ የታየበት ነው፤ በዚህም ጊዜ ተስፋ የፈነጠቀበት እና የጤና መሻሻል የታየበት እንዲሁም አንጻራዊ የስርጭት መጠን መቀነስ የታየበት ወቅት እንደነበር ተገልጿል።
በአምስተኛነት የተቀመጠው(ከ2002-2012 ዓ.ም) ያለው ሲሆን ይህም ጊዜ፣ ኤድስን የማቆም ግስጋሴ እና ሌላኛው ገፅታ የሚል ሲሆን በዚህም ወቅት ሁለት ገፅታዎች የተንፀባረቁበት ነው። ይህም አንደኛው አዲስ በኤች አይ ቪ የመያዝ ምጣኔ እና ሞት የቀነሰበት እና ሁለተኛው ከፍተኛ የሆነ የመዘናጋት እና መቀዛቀዝ የታየበት መሆኑን በውይይቱ ላይ ቀርቧል።
አሁን ላይ ያለውን የኤች አይ ቪ ወቅታዊ መረጃን በምናይበት ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ኤች አይ ቪ መከሰቱ ከታወቀበት ከ1973 ዓ.ም ጀምሮ ከ39 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በኤድስ ምክንያት ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን ከ16 ሚሊዮን በላይ ሕፃናትም ወላጆቻቸውን አጥተዋል፤ 36.9 ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ በአሁን ጊዜ ኤች አይ ቪ በደማቸው እንደሚገኝ ይገመታል። በየዓመቱ ከ2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች አዲስ በኤች አይ ቪ እንደሚያዙ እና 1.2 ሚሊዮን ሰዎች ለህልፈት እንደሚዳረጉ መረጃዎች ያሳያሉ።
እ.ኤ.አ በ2016 በተሰራው የኢትዮጵያ ጤናና ስነ-ህዝብ ጥናት መሰረት ያለውን የስርጭት ሁኔታን በምናይበት ወቅት እንደሀገር ያለው የኤች አይ ቪ የስርጭት ምጣኔ 0.9 በመቶ ሲሆን ከፍተኛው የስርጭት ምጣኔ በጋምቤላ ክልል 4.8 በመቶ ሲሆን ዝቅተኛው በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል ከ0.1 በመቶ ያነሰ ነው። በአገራችን የሚገኙ ኤች አይ ቪ በደማቸው ይገኛል ተብሎ ከሚገመተው ከ610 ሺ 335 ሰዎች ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት ማለትም 379ሺ251 ሴቶች ሲሆኑ የተቀሩት 231ሺ084 ወንዶች ናቸው። በዚህም መሰረት የኤች አይ ቪ ስርጭት በጾታ ሲታይ የሴቶች 62 በመቶ ሲሆን የወንዶች ደግሞ 38 ነው። ይህም ሴቶች ከወንዶች ይልቅ በተለያዩ ምክንያቶች ተጋላጭ እንደሆኑ ይጠቁማል።
የስርጭቱ ምጣኔ ከክልል ክልል፣ በክልል ውስጥም ከቦታ ቦታ በከተማና በገጠር እንዲሁም በተለያዩ የህበረተሰብ ክፍሎች በከፍተኛ ደረጃ ይለያያል፡፡ በሌላ በኩል አዳዲስ በሚፈጠሩ ከተሞች በትላልቅ የልማት ተቋማት አካባቢ ስርጭቱ ከጊዜ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
የኤች አይ ቪ ሥርጭት ምጣኔ በክልል ደረጃ ስናይ አዋቂ እድሜ (15-49) ጋመብላ 4.8 በመቶ በመሆን ከፍተኛውን ደረጃ ይዞ እናገኘዋለን፤ በመቀጠል አዲስ አበባ 3.4 በመቶ የሥርጭት ምጣኔ አለው፡፡ በሶስተኛ እና በአራተኛ ደረጃ ከፍተኛ የሥርጭት ምጣኔ ያለባቸው ድሬዳዋና ሀረሪ ሲሆኑ 2.5 እና 2.4 በመቶ በተከታታይ ሆነው እንደሚከተሉ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ የተቀሩትን ክልሎች ኤች አይ ቪ ኤድስ የስርጭት ምጣኔ ስንመለከት አፋር 1.4 በመቶ፣ ትግራይ እና አማራ በተመሳሳይ 1.2 በመቶ ቤንሻንጉል ጉሙዝ 1 በመቶ ፣ ኦሮሚያ 0.7 በመቶ ደቡብ ብ/ብ/ህ 0.4 በመቶ፣ ኢትዮጵያ ሱማሌ 0.1 በመቶ በታች ሆነው እናገኛቸዋለን። በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለው የቫይረሱ የስርጭት ምጣኔ ደግሞ በአጠቃላይ 0.9 በመቶ መሆኑን መረጃዎች አመልክተዋል።
በሌላ በኩል ኤች አይ ቪ በደማቸው ያለባቸውን ሰዎች በክልል ደረጃ ስንመለከት አማራ 194 ሺ 673፣ ኦሮሚያ 179ሺ 229 በመሆን እንደ ህዝብ ብዛቱ ከፍተኛውን ቁጥር ይዞ እናገኘዋለን። በሶስተኛነት ኤች አይ ቪ በደማቸው ያለባቸው ሰዎች በክልል አዲስ አበባ ሲሆን 105ሺ 899 ሰዎች እንደሆኑ መረጃዎች አመልክተዋል። በቀጣይነት ያሉ ክልሎችን ስናይ ደቡብ ብ/ብ/ህ 56ሺ71፣ ትግራይ 49ሺ672 አፋር 14ሺ 421 ሰዎች ኤች አይ ቪ በደማቸው የሚገኙ ሰዎች አሉ፤ እንዲሁም በተመሳሳይ በድሬዳዋ 9ሺ121 ቤኒንሻንጉል 7ሺ160 ሀረሪ 4ሺ 487 ሱማሌ 4ሺ139 ኤች አይ ቪ በደማቸው የሚገኙ ሰዎች አሉ። እ.ኤ.አ በ2018 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለው አጠቃላይ 613ሺ 825 ሰዎች ኤች አይ ቪ በደማቸው መኖሩን የቅርብ ጊዜ መረጃዎች ያሳያሉ።
እ.ኤአ በ2018 ሰዎች ላይ መሰረት አድርጎ በሀገራችን በከተሞች በተደረገ ጥናት የስርጭት ምጣኔው በክልል በከተሞቻቸው የስርጭት ምጣኔ ሲታይ ጋምቤላ 5.7 በመቶ፣ ሀራሪ እና ድሬዳዋ በተመሳሳይ 4.6 በመቶ እንዲሁም አፋር እና አማራ በተመሳሳይ 4.1 በመቶ ነው። በአዲስ አበባ ያለው የስርጭት ምጣኔ 3.1 በመቶ ሲሆን በኦሮሚያ ክልል በከተማ ያለው የስርጭት ምጣኔ ደግሞ 3 በመቶ ነው። በተቀሩት ክልሎች በከተማ ያለው የስርጭት ምጣኔ በትግራይ 2.7 በመቶ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ 2.4 በመቶ፣ ደቡብ ብ/ብ/ህ 1.8 በመቶ እና ሱማሌ 0.8 በመቶ ነው። በዚህም መረዳት እንደሚቻለው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የስርጭት ሁኔታ ሲታይ የኤች አይ ቪ ስርጭት ከገጠር ይልቅ በከተማ ከፍ ያለ መሆኑ ይስተዋላል።
የኤች አይ ቪ ስርጭትን ለመግታት ለወደፊቱ በተለይ ሀገራችን ያሏትን መልካም ባህሎች ጠብቆ በየሃይማኖት ተቋማቱ በሚደረገው የባህሪ እና ዓላማ ላይ ትኩረት እንዲደረግ የሚሰጡ ትምህርቶች ያስፈልጋሉ። ከዚህ ጎን ለጎን ኮንደምን በጥንቃቄ በመጠቀም እና ከአንድ ከቫይረሱ ነጻ ከሆነ ሰው ጋር ብቻ የግብረስጋ ግንኙነት በማድረግ ኤች አይ ቪን መከላከል እንደሚቻል ግንዛቤ ያላቸውን ሰዎች አሁን ካለበት 69 በመቶ ወንዶች እና 49 በመቶ ሴቶች ግንዛቤ ያላቸውን ሰዎች ብዛት ማሳደግ እንደ አቅጣጫ መቀመጡ አስፈላጊ ነው።
አዲስ ዘመን ታህሳስ21/2011