አገራት አነጋጋሪ የሕግ ክልከላዎችን ያደርጋሉ ። የስልጣኔ ተምሳሌት ተደርጋ በምትወሰደው አሜሪካ አንዳንድ ግዛቶች ውስጥ እንኳን እጅን በአፍ የሚያስጭኑ የህግ ክልከላዎች አሉ ። ባገለገለ የውስጥ ሱሪ መኪና ከማጽዳት ጀምሮ ሁሉም የመኝታ ቤት መስኮቶች ጥርቅም ብለው ካልተዘጉ በስተቀር ማንኮራፋትን እንዲሁም በፖሊስ ላይ ማፍጠጥን የሚከለክሉ ህጎች ስራ ላይ ውለዋል ። ታይላንድ ውስጥ ደግሞ የውስጥ ሱሪ፣ የውስጥ ልብስና የጡት ማስያዣ ሳያደርጉ ከቤት መውጣት ክልክል ነው ። በዚምቧቤ ፕሬዚዳንቱን ያጀበው መኪና ሲያልፍ ደስ የማይል የፊትና የሰውነት ንቅናቄ ወይም እንቅስቃሴ ማድረግ የተከለከለ ነው ። ቻይና አገር ያለመንግስት ፍቃድ ከሞት መነሳት ክልክል ነው ።
የሕግ የበላይነት በሰፈነበት አገር ሰዎች ሁሉ ከሕግ በታች ናቸው ። የሚወጡት ሕጎችም ከሞላ ጎደል ምክንያታዊ ናቸው ። በሕግ የሚቀመጡ ክልከላዎችም ይከበራሉ ። ሲጣሱም ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ተጠያቂነት አለ ። የሰው የበላይነት በነገሰበት አገር ግን አንዳንድ ሰዎች ከሕግ በላይ ይሆናሉ ። የሚደነገጉ ሕጎችም እነዚህን ሰዎች ላይመለከቱ ይችላሉ ። ጭራሽ የጥቂቶችን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲባል በብዙኃኑ ላይ የሚጫን ሕግ ስራ ላይ ሊውል ይችላል ። የሰው የበላይነት በነገሰበት አገር ሕግ መጣስ ብቻውን ተጠያቂ አያስደርግም፤ ጥሰቱን ማን ፈጸመው ተብሎ ይጠየቃል ። ተጠያቂ መሆንና አለመሆን ሕግጋትን በተላለፈው ሰው ማንነት ይወሰናል ።
ሕግ አውጪው አካል ያጸደቃቸው ሕጎች ነፍስ የሚዘሩት አሊያም በድን የሚሆኑት በየደረጃው ባሉ ሰዎች ይሁንታ ነው ። ከሕግ በላይ የሆኑ ሰዎች ከሕገ መንግስትም ሆነ ከሕገ ልቦና በላይ ስለሆኑ ከአፋቸው የሚወጣ ቃል ሁሉ ሕግ ነው ። ደስ ያሰኛቸውን ነገር ይፈቅዳሉ፤ ያልጣማቸውን ደግሞ ይከለክላሉ ። ባሻቸው ጊዜ የራሳቸውን ሕግ አርቅቀው ተግባራዊ እንዲሆን ትዕዛዝ ሊሰጡም ይችላሉ።
በአገራችን ከሕግ በላይ የሆኑ ሰዎች የበዙ ይመስለኛል ። ለዚህ አባባሌ አብይ አስረጅ አድርጌ የምጠቅሰው በረባ ባልረባው አንዳንድ ጊዜም ያለበቂ ጥናት የሚከለከሉ ነገሮች መብዛታቸውን ነው ። ተከለከለ በሚል ማሰሪያ አንቀጽ የሚቋጩ ዜናዎች በርክተዋል ። እከሌ ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳይሰጥ ተከለከለ፤ ጾታዊ ጥቃትን በመቃወም ሊደረግ የነበረው ሰልፍ ተከለከለ፤ የጭነት መኪና በቀን እንዳይንቀሳቀስ ተከለከለ፤ እከሌ የተባለ ሙዚቀኛ የሙዚቃ ዝግጅት እንዳያቀርብ ተከለከለ፤ እከሌን በመቃወም (በመደገፍ) ሊደረግ የታቀደው ሰልፍ ተከለከለ … ሌላም ሌላም ።
በዕውቀቱ ስዩም ይህን የክልከላ ቀለበት አጢኖ ይመስላል ተከታዩን ስንኝ የቋጠረው።
ክልክል ነው!
ማጨስ ክልክል ነው!
ማፏጨት ክልክል ነው!
መሽናት ክልክል ነው!
ግድግዳው በሙሉ ተሠርቶ በክልክል
የቱ ነው ትክክል?
ትንሽ ግድግዳ እና ትንሽ ኃይል ባደለኝ
“መከልከል ክልክል ነው፤” የሚል ትእዛዝ አለኝ።
ወጣቱ ገጣሚ ጥሩ ታዝቧል ። ታክሲ ውስጥ ብትገቡ እንኳን “ሹፌሩን በፍቅር ማሣቅ እንጂ በነገር ማሣቀቅ ክልክል ነው “ የሚል ጥቅስ ታነባላችሁ ።
ዴሞክራሲን ኢትዮጵያ ውስጥ አላራምድ ያለው በፖለቲካ ውሳኔ የሚደረግ ክልከላ ይመስለኛል ። የዜጎች ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ከሕግ በላይ በሆኑ ሰዎች እዚህም እዚያም ውሃ በማይቋጥሩ ምክንያቶች ክልከላ እየተደረገባቸው ይገደባሉ ። በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያሉ ጉልበተኞች ለአንድ አገር ዜጎች በተለያየ ቁና ይሰፍራሉ ። የተቃውሞ ድምጾችን በክልከላ ለማፈን ይራወጣሉ ። መከልከል ማስተዳደር ካለመቻልና ሕጋዊ በሆነ መንገድ የሚቀርቡ ጥያቄዎችን ከመፍራት የሚመረጥ አቋራጭ መንገድ ነው ። ከወረዳ ጀምሮ ያለ አመራር አንድ ችግር በተከሰተ ቁጥር ክልከላን ሁነኛ መፍትሔ አድርጎ የመውሰድ አባዜ ተጠናውቶታል ።
ከአምስት ቀናት በፊት ድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ለሴት ተማሪዎቹ በገደምዳሜው ማርገዝ ክልክል ነው የሚል ሕግ ማውጣቱን አስታውቆ ነበር ። እንዲህ ይላል “በ48 ሰዓታት ውስጥ ከመንግስት ሆስፒታል የእርግዝና ምርመራ አድርጋችሁ የምርመራ ውጤቱን ለፕሮክተራችሁ እንድታስገቡ። ማሳሰቢያ፡- ይህንን ሳያደርግ የቀረ ተማሪ ለሚመጣበት ችግር ራሱ ኃላፊነቱን ይወስዳል ።”
ማስታወቂያው በማህበራዊ ድረ ገጾች የብዙዎችን ትኩረት ማግኘቱን ተከትሎ ብዙም ሳይቆይ ዩኒቨርሲቲው ሴቶች የእርግዝና ምርመራ እንዲያደርጉ የተጠየቀው “በስህተት “ መሆኑን አስታወቀ ። የዩኒቨርሲቲው የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር በአንድ ሬዲዮ ጣቢያ ቀርበው “ለሴት ተማሪዎች በሙሉ በሚል ማስታወቂያ የወጣው በስህተት ነው፤ ለተፈጠረው ስህተትም ዩኒቨርሲቲው ይቅርታ ይጠይቃል” አሉ ። በኋላ የወጡ መረጃዎች እንዳመላከቱት ማስታወቂያው የተለጠፈው አንዲት ተማሪ የወለደችውን ልጅ ጥላ በመጥፋቷ ነው።
መከልከል ለችግሮች ሁሉ መፍትሄ አይሆንም ። ችግሮችን በክልከላ አድበስብሶ መክደን ሌላ ችግር እንዲረገዝ እንጂ መፍትሄ እንዲወለድ አያደርግም ። መንግስት ጠዋት ማታ የሚደግመውን ዲሞክራሲ ለማስፈን ቁርጠኛ ከሆነ የሚጣፍጠውን ብቻ ሳይሆን የሚመረውንም ማጣጣም አለበት ። ዳንኤል ክብረት “በሕግ የተሰጠን መብት ማገድ ወደማንፈልገው ሥርዓት ይወስደናል። ሰላማዊ ሰልፍን መፍቀድ የሰልፉን ዓላማ መፍቀድ አይደለም። ለመብት መከበር መቆም እንጂ” እንዳለው መንግስት ለሕግ መከበር ደጀን በመሆን ኃላፊነቱን መወጣት አለበት ።
በሌላ በኩል የመንግስት አመራሮችን የመከልከል አባዜ መጠቀሚያ የሚያደርጉ አካላት አሉ ። እነዚህ ወገኖች አንዳንድ ጊዜ መከልከልን ግብ አድርገው ይነሳሉ ። ከዚያም የማያደርጉትን ነገር እናደርጋለን ብለው ፕሮፖጋንዳቸውን ሲነፉ ይከርማሉ ። ከቀናቸው ከሕግ በላይ ከሆኑት የመንግስት ሰዎች በአንዱ እጅ ላይ ወድቀው መከልከላቸው በይፋ ይነገራል ። ዕድል ፊቷን አዙራባቸው በይፋ መከልከላቸውን የሚገልጽ አካል ካልተገኘም ራሳቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ጠርተው እንዲህ እንዳናደርግ ተከለከልን ይላሉ።
እዚህ ሰፈር ደግሞ ክልከላ ሁነኛ ትኩረት ማግኛና መግነኛ መንገድ ነው ። አንዳንዶቹ ማናቸውንም አይነት እንቅስቃሴ ለማድረግ ወጥነው ለሚመለከተው አካል ጥያቄ ሲያቀርቡ ፍቃድ ማግኘትን ናፍቀው አይደለም ። በጉጉት የሚጠብቁት ምላሽ ክልከላ ነው ። ፍቃድ አግኝተው በሚሰሩት ስራ የሚያገኙት ትኩረት በመከልከላቸው ምክንያት በሚሰጣቸው ሰፊ የሚዲያ ሽፋን ከሚገኘው ትርፍ ጋር ሊወዳደር አይችልም ።
ከአንድ ወር በፊት የ71 የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች አዲሱን የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የስነ ምግባር አዋጅን በመቃወም የረሃብ አድማ ለመምታት መወሰናቸውን አስታውቀው ነበር። ፓርቲዎቹ ለ 48 ሰዓታት የሚቆይ የረሃብ አድማ ለማድረግ እንደዋዛ የያዙት ቀነ ቀጠሮ ከች ሲል የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ አስታከው በአንድ ወር አራዘሙት። ቀድሞውንም ቢሆን የማይደፍሩትን የረሃብ አድማ ስም ደፍረው መጥራት አልነበረባቸውም ። ቀጠሉና አንቡላንስ ይመደብልን፤ የሚጠብቀን የጸጥታ አካል ይላክልንና አራት ኪሎ አደባባይ እንድንራብ ይፈቀድልን ብለው ጥያቄ አቀረቡ ። ሶስት ጥያቄዎች ያቀረቡት ቢያንስ አንዱ ጥያቄ ተገቢ መልስ አላገኘም ብለን የረሃብ አድማውን መሰረዝ እንችላለን በሚል ተስፋ ይመስላል ።
የተቃዋሚ ፓርቲዎቹ አመራሮች ሰሞኑን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቦታ እንድንቀይር ሲጠይቀን “አይ እኛ ቦታ አንቀይርም፤ በያዝነው ቦታና ፕሮግራም እንድንራብ ሊፈቀድልን ይገባል” በማለታችን የረሃብ አድማውን እንድናደርግ ፍቃድ አላገኘንም አሉ ። የረሃብ አድማውን ሰርዘው በምትኩ በሰሞኑ ሁከት ለተጎዱ ወገኖች የሚውል የደም ልገሳ ለማድረግ ማቀዳቸውንም ገለጹ።
ይገርማል እኮ! ዋናው ጉዳይ የረሃብ አድማው መሆኑ ቀርቶ መራቢያ ቦታው ሆኖ አረፈ ። አንድ ሰው ልራብ ካለ ማን ሊከለክለው ይችላል? አክቲቪስትነትና ጋዜጠኝነት ተምታቶ ችግር ውስጥ ከረምን። አሁን ደግሞ ፖለቲከኛነትና ኮሜዲያንነት ተቆላልፎ አረፈው። በበኩሌ የከበበንን የሀዘን ድባብ ክብደት ተረድተው በዚህ ወቅት እንዲህ ያለ የተዋጣለት ኮሜዲ ተውኔት ላዘጋጁት ፖለቲከኞች ከፍ ያለ ከበሬታ አለኝ ። ሰው አንድን ሙያ በአግባቡ ለመካን መከራውን በሚያይበት ዘመን በሁለት የተለያዩ መስኮች የተዋጣላቸው ስኬታማዎች በመሆናቸው ቀናሁባቸው i
አዲስ ዘመን ጥቅም3/2012
የትናየት ፈሩ