አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ ለሰላም የሰጠችው ከፍተኛ ዋጋ ከሁሉም በላይ በተለያዩ ተቋማትና አገራት ለሚሠጡ ወታደራዊ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናዎች ተመራጭ እንድትሆን ማስቻሉ ተጠቆመ፡፡
የጃፓን መንግሥት ከኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር ሠላም ማስከበር ዋና መምሪያ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው በግጭት አፈታት ላይ ትኩረቱን ያደረገው ስልጠና ትናንት በተጀመረበት ወቅት ንግግር ያደረጉት በሚኒስቴሩ የሠላም ማስከበር ዋና መምሪያ ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ድሪባ መኮንን እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ቀዳሚና ተመራጭ በመሆን በተለይ በአፍሪካ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን በበርካታ አገራት ከፍተኛ መጠን ያለው ሰራዊት አሰማርታለች፡፡
አገሪቱ ለሰላም የምትሰጠው ከፍተኛ ትኩረትና እየከፈለች ያለችው መስዋእትነት ለተለያዩ ግዳጆች ተመራጭ እንድትሆን ማድረጋቸውን የጠቆሙት ሜጀር ጄኔራሉ፣ ‹‹አገሪቱ ለሰላም የምትሰጠው ዋጋ ከሁሉም በላይ በተለያዩ ተቋማትና አገራት የሚሠጡ ወታደራዊ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናዎች ማእከል እንድትሆን አስችሏታል›› ብለዋል፡፡
ስልጠናዎቹም በተለይ በሰላም ማስከበር ተልእኮ ሰላማዊ አገርና አህጉር ለመፍጠር ወሳኝ የሆኑ የተደራጀ የሲቪል፣ የፖሊስና የወታደራዊ ክህሎቶች ባለቤት የሚያደርጋትን አቅም ለመገንባት ወሳኝ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
ከጃፓን መንግሥት ጋር በመተባበር የተዘጋጀው ግጭትን መቆጣጠር ላይ ትኩረቱን ያደረገው ይህ ስልጠናም በአገር ውስጥም ሆነ በተለያዩ የውጭ አገራት ተልእኮዎች ላይ ኃይልን አማራጭ ከማድረግ ይልቅ የውይይት አማራጭን ለማስቀደም በቂ አቅም እንደሚፈጥር ተናግረው፣ ልምድ በመለዋወጥ በሰላም ላይ የጋራ ትብብርን ለማጠናከር እንደሚያግዝ አስገንዝበዋል፡፡
በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሚስተር ዳይሱኬ ማትሱናጋ በበኩላቸው፣የአፍሪካ ደህንነት ከመቼውም ጊዜ በላይ መሻሻሉን ጠቁመው፣ ኢትዮጵያም በሰላም ማስከበር ተልዕኮ በብቃትና በጀግንነት አኩሪ ተግባሮችን እያከናወነች መሆኗን ጠቅሰዋል፡፡
አሁንም ቢሆን ሀገሪቱ ሰላምና ደህንነትን በማረጋገጥ ረገድ በንቃት መስራት የሚገባት የቤት ሥራዎች እንዳሉባት የጠቆሙት አምባሳደሩ፣የጃፓን መንግሥትም ኢትዮጵያ ከራሷ አልፎ ለሌሎች ሰላም የምታደርገውን ጥረት ለማገዝ ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
መንግሥታቸው በኢትዮጵያ እስካሁን 11 የሚሆኑ ስልጠናዎችን መስጠቱን ጠቅሰው፣ግጭትን በጋራ ለመቆጣጠርና ለመፍታት በሚቻልበት አግባብ የሚሰጠው የአሁኑ ስልጠናም ‹‹የአፍሪካን የሰላም እና ደህንነት ተግዳሮቶች ለመፍታት ከፍተኛ አስተዋፆኦ ያበረክታል›› ብለዋል፡፡
በስልጠናው ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከቡሩንዲ፣ ኮሞሮስ፣ ጅቡቲ፣ኡጋንዳ፣ ሞሮኮ፣ ሩዋንዳ፣ ሶማሊያ፣ ታንዛኒያ፣ ቱኒዚያ፣ ኡጋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን እንዲሁም ሱዳን የተውጣጡ ሰልጣኞች እየተካፈሉ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ስልጠናው ለ10 ተከታታይ ቀናት ይሰጣል።
አዲስ ዘመን ህዳር 2/2012
ታምራት ተስፋዬ