የፀረ ተሕዋስያን መድኃኒት መላመድ በዓለም ላይ ከአየር ንብረት ቀጥሎ አሳሳቢ ደረጃ መድረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በአፍሪካም ችግሩ እየተባባሰ መሆኑን እነዚሁ መረጃዎች ያመለክታሉ። በፀረ ተሕዋስያን መድኃኒት መላመድ ምክንያት በዓለም በቀን 750 ሺ በላይ ሰዎች ለሞት የሚዳረጉ ሲሆን፣ ይህም ወደ ቀን ሲመነዘር ወደ 2 ሺህ 55 ሰዎች በቀን ሕይወታቸውን ያጣሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ ትልቁን ድርሻ የምትወስደው አፍሪካ ናት፡፡ የአፍሪካ ድርሻ 41ነጥብ 1 በመቶውን ትወስዳለች፡፡ በሰዓት ወደ 86 ሰዎች በዓለም ላይ ሲሞቱ 36ቱ ከአፍሪካ የሚሞቱ ናቸው፡፡
ሰሞኑን በቢሾፍቱ በጸረ ተህዋሲያን መድኃኒቶች መላመድ ላይ በተካሄደ ስልጠና ላይ እንደተጠቆመው፤ ከአፍሪካ 1ነጥብ 2 ቢሊዮን ህዝብ ውስጥ 100 ሚሊዮኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ በጸረ ተህዋስያን መድሐኒት መላመድ ሳቢያ ወደ 3ነጥብ5 ሰዎች በሰዓት ለሞት ይዳረጋሉ፡፡ ይህም በቀን ወደ 85 ሰዎች እንደሚሞቱ ያመለክታል። ችግሩ በዓለም ደረጃ ስለታወቀ ድምፅ አልባው ሱናሚ በሚል እየተጠራ ነው፡፡
ጉዳዩ በሰው ጤና ላይ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን በእንስሳት እና በአካባቢ ላይም ችግር መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት እንዲሁም የምግብና እርሻ ድርጅት ባለ አምስት ነጥብ ስልታዊ ግብ አውጥተው ችግሩን ለመፍታት እየሰሩ ይገኛሉ ፡፡
በጸረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ላይ በምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን የፀረ ተህዋስያን መድኃኒት መላመድ መከላከልና መቆጣጠር አማካሪ አቶ ወንዴ ዓለሙ እንደገለጹት፤ የፀረ ተህዋስያን መድኃኒቶች ማለት በሽታ አምጪ ተህዋስያንን የሚገድሉ ወይም ደግሞ መራባታቸውን የሚያቆሙ ንጥረ ነገሮች ናቸው፡፡ እነዚህ ፀረ ተህዋስያን መድኃኒቶች በሽታ አምጪ ተህዋስያኖቹን ገደሉ ማለት ከበሽታ መፈወስ ማለት ነው፡፡ ዕድገታቸውን መራባታቸውን አቆሙ ማለት ተፈወስን ማለት ነው፡፡
እነዚህን መድኃኒቶች በተደጋጋሚ ስንጠቀምባቸው በተለይ አላግባብ ስንጠቀምባቸው በሽታ አምጪ ተህዋስያኖቹ መድኃኒቶቹን ይለምዷቸዋል ያሉት አቶ ወንዴ፣ መዳህኒቶቹን አላግባብ ከተጠቀምንባቸው የፈውስነት ደረጃቸው በመላመድ ይቀንሳል ይላሉ። አላግባብ የመድኃኒት አጠቃቀም መድኃኒት በሚያዘው፣ በሚያድለው እና በሚጠቀመው ሰው ሊከሰት እንደሚችል ተናግረው፣ ስለዚህ ከሦስቱ አንዱ ጋ ችግር ከተፈጠረ፤ ሀኪሙ በሽታውን በትክክል ካላወቀው ወይም ለበሽታው ትክክለኛውን መድኃኒት ካላዘዘ ወይም ደግሞ መድኃኒት የሚያድለው ትክክለኛውን መድኃኒት መጠን ካላደለ ወይም ካልሰጠ፣ ተጠቃሚው በትክክል ካልተጠቀመ አላግባብ የመድኃኒት አጠቃቀም እንደሚከሰት ያብራራሉ፡፡
ችግሩን ለመፍታት ዓለም ተግባብቶ ባለ አምስት ነጥብ ስልታዊ ግቦች ማዘጋጀቱን አቶ ወንዴ ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያም ከዚሁ ጋር የሚሄድ ባለ5 ነጥብ ስልታዊ ግብ አዘጋጅታ እየተገበረች መሆኗን ይጠቅሳሉ፡፡
በጤና ሚኒስቴር የፀረ ተሕዋስያን መድኃኒት መላመድ ብሔራዊ አስተባባሪ አቶ ይድነቃቸው ደገፋው ችግሩ ሰዎችን ብቻ ሳይሆን ግብርናውንም እንደሚመለከት ጠቅሰው፣ ችግሩን የመከላከል ስራዎች በሀገር ደረጃ እንዴት ተቀናጅተው መሄድ አለባቸው በሚል ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ እንደ ሀገር መዋቅሩ መሰራቱን ጠቅሰው፣ መሥሪያ ቤቶች ተቀናጅተው በጋራ ይሄን ችግር ይቀርፋሉ በሚል በቅርቡ በሚኒስትሩ ተፈርሞ ወደ ስራ እንደሚገባ ይናገራሉ። በአጠቃላይ የሚመለከታቸው ሴክተር መሥሪያ ቤቶች በየሦስት ወሩ በጤና ሚኒስቴር በኩል በጉዳዩ ላይ እንደሚወያዩም ተናግረዋል፡፡
እንደ አስተባባሪው ገለጻ፤ ሥራው የጤና ብቻ ሳይሆን የአካባቢ ጥበቃ፣ የፋይናንስ፣ የትምህርት፣ የሁሉም ሚኒስቴሮች ነው፡፡ ለዚህም ሚኒስትሮችን ያካተተ ኮሚቴም ተቋቁሟል፡፡ በኮሚቴው ላይ አጀንዳዎች እየተነሱ ውይይት ይደረጋል፡፡ ሁሉም ያገባናል ብለው በጋራ እንዲሠሩም እንደ ሀገር መዋቅር ተሠርቷል፡፡ ይህን ችግር በማሰብ በጤና ሚኒስቴር ውስጥ ይህን ሥራ ብቻ የሚሠራ አንድ ኬዝ ቲም ተቋቁሟል፡፡ በሀገር ደረጃ ሥራዎችን እያቀናጀ ሆስፒታሎችን እየተከታተለ እንዲህ ዓይነቶቹ ተግባራት እንዲከናውኑ ኬዝ ቲሙ ይሠራል። የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችም የማነቃቃት ሥራዎችን እንዲሠሩ ይጠበቃል፡፡
በሀገር ደረጃ ጤና ሚኒስቴር ከባለድርሻ መሥሪያ ቤቶች ጋራ ለተሻለ ውጤት እየሰራ መሆኑን አቶ ይድነቃቸው ጠቅሰው፣ በሆስፒታሎች ላይም የፀረ ተህዋስያን ቡድኖች ተመሥርተው ሆስፒታሎች የመድኃኒት በጀት አጠቃቀማቸውን የሚገመግሙበት ተጠቃሚው እንዴት እየተጠቀመ ነው የሚለውን የሚያዩበት አሰራር መዘርጋቱንም ይጠቁማሉ ፡፡
እንደ አስተባባሪው ገለጻ፤ ችግሩ በሁሉም የግልና የመንግሥት ህክምና ተቋማት ላይ ይስተዋላል። መድኃኒትን በአግባቡ በተቋማቸው እንዲጠቀሙ የሚያደርግ ቡድን አለ፡፡ አሁን 12 ሆስፒታሎች ይሄንን ቡድን አቋቁመዋል፡፡ እንደ ሀገር በዚህ ዓመት በ30 ሆስፒታሎች ቡድኖቹ ይቋቋማሉ፡፡ እነዚህ ሆስፒታሎች በተቋሙ ውስጥ ያለውን የመድኃኒት አጠቃቀም ይቆጣጠራሉ። የፀረ ተህዋስያን ዕጣ ፋንታ እጃችን ላይ እስካለ ድረስ የመቆጣጠር ሥራዎችና ችግሮች ሲኖሩ የሚያስቆም ይሆናል፡፡ ይሄንን መድኃኒት ማዘዝ ያለበት ሀኪም ነው፡፡ ይሄንን ደግሞ ስፔሻሊስት ነው የሚል ቲም እየተቋቋመ ይገኛል፡፡ የጸረ ተህዋሲያን መድኃኒት ጉዳይ በስርአተ ትምህርቱም ውስጥ ሊገባ የሚችልበት ሁኔታም እየተመቻቸ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ካስቀመጠችው የፀረ ተሕዋስያን መከላከል ግቦች አንዱ መድኃኒት በሚያዘው በሚሰጠውና በሚጠቀመው ሕብረተሰብ ላይ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ መስራት የሚለው ነው። ለኅብረተሰቡ በተቻለ መጠን በማስታወቂያዎች በሬዲዮ ፕሮግራሞች በመሳሰሉት ለመድረስ እየተሞከረ ነው። ለሥልጠና ለሚመጡ ጤና ባለሙያዎችም በጉዳዩ ላይ ግንዛቤ በመስጠት እንዲሰሩ ይደረጋል፡፡
አዲስ ዘመን ኅዳር 2 /2012
ኃይለማርያም ወንድሙ