አዲስ አበባ፡- በመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አዳዲስ የተመደቡ ተማሪዎች በሙሉ ተመዝግበው መደበኛ የመማር ማስተማሩ ተግባር በተያዘለት መርሐ ግብር መሰረት እየተካሄደ መሆኑ ተገለጸ።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እንደገለጸው በሁሉም የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የተመደቡ ተማሪዎች በሙሉ ገብተውና አስፈላጊውን የምዝገባ ሂደት አጠናቅቀው መደበኛውን የትምህርት ፕሮግራም እየተከታተሉ ይገኛሉ።
በሚኒስቴሩ የከፍተኛ ትምህርት የተማሪዎች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ደጀኔ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት ሚኒስቴሩ ባዘጋጀው የምደባ መመሪያ መሰረት ከሁሉም የአገሪቱ ክልሎች የማለፊያ ውጤት ያመጡና በአርባ አምስቱም የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የተደለደሉ ተማሪዎች በየተመደቡባቸው ተቋማት በመገኘት ትምህርታቸውን መከታተል ጀምረዋል፡፡
በወጣው ፕሮግራም መሰረት ከመስከረም 19 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ የነባር፤ ከመስከረም 26 ጀምሮ የአዲስ ተማሪዎች ቅበላና ምዝገባ የተደረገ መሆኑን የሚገልጹት አቶ ብርሃኑ በተለያዩ ምክንያቶች ዘግይተው የደረሱ ተማሪዎችም ችግራቸው ታይቶ እንዲመዘገቡ መደረጉን ተናግረዋል።
በያዝነው የትምህርት ዘመን በአርባ አምስቱም ዩኒቨርሲቲዎች በአጠቃላይ 142 ሺህ 943 አዲስ ገቢ ተማሪዎች መመደባቸውን የሚናገሩት ዳይሬክተሩ ሁሉም በየተመደቡባቸው ተቋማት ተገኝተው መመዝገባቸውንና በትምህርት ገበታቸው ላይ እንደሚገኙ ከየዩኒቨርሲቲዎቹ የደረሱ ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱም ተናግረዋል።
መደበኛ ትምህርቱም በተያዘለት ፕሮግራም መሰረት ተጀምሮ በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ ይገኛል የሚሉት አቶ ብርሃኑ የፀጥታ ችግር አለ በሚባልበት ኦሮሚያ ክልልም የመማር ማስተማሩ ተግባር ያለምንም መስተጓጎል እየተከናወነ እንደሆነ ይናገራሉ።
በየዩኒቨርሲቲዎቹ ማናጅመንትና ማህበረሰብ ከሚደረጉ ሰላምን የማስፈንና ጤናማ የመማር ማስተማር ድባብን የመፍጠር ተግባር በተጨማሪ የየዩኒቨርሲቲዎቹን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴና አጠቃላይ ሁኔታ የሚከታተል ግብረ ኃይል ተቋቁሞ የየተቋማቱን ውሎና አዳር እየተከታተለ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ እስከአሁን ምንም ዓይነት ችግር እንዳላጋጠመም ተናረዋል፡፡
ቀደም ሲል የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ተማሪዎቹ ወደአማራ ክልል ሄደው እንዳይመዘገቡ ጥሪ ማስተላለፉ ትክክል እንዳልነበር የጠቆሙት አቶ ብርሃኑ እነሱ ይህን የማለት ኃላፊነት እንደሌላቸውም ተናግረዋል።
“ይህን የማድረግም ሆነ ያለማድረግ ኃላፊነት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ነው” ያሉት አቶ ብርሃኑ “ቢሮው አትመዝገቡ የሚል ጥሪ ቢያቀርብም ሁሉም ተማሪዎች ተመዝግበው ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ናቸው” ሲሉ ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 1/2012
ግርማ መንግሥቴ