• የመምህራንን ጥቅማጥቅም ለማስጠበቅ እየሠራሁ ነው አለ
አዲስ አበባ፡- የትምህርት ጥራት ችግርን ለመፍታት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በርብርብና በጋራ ሊሠሩ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡ ማህበሩ የመምህራንን ጥቅማጥቅም ለማስጠበቅ እንደሚሠራም አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ የመምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዮሐንስ በንቲ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት ተማሪዎች በዕውቀት፣ በክሂሎትና በአስተሳሰብ ልቀው በመገኘት ለራሳቸውም ሆነ ለአገራቸው አለኝታ ሊሆኑ እንጂ በኩረጃ ላይ ሊንጠለጠሉና የወደፊት ህይወታቸውን ሊያበላሹ አይገባም፡፡
የትምህርት ጥራት ችግር የማንኛውም አገር ችግር ነው የሚሉት ዶክተር ዮሐንስ እኛም ጋር በስፋት የሚታይ በመሆኑ እሱን በመሰረታዊነትና በዘላቂነት መፍታት ላይ መሥራት ይገባል የሚል እምነት ተይዞ እየተሠራ ነው ብለዋል።
የትምህርት ጥራትን ከመጠበቅ አኳያ የመምህራን ድርሻ እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ የጠቆሙት ዶክተር ዮሐንስ በቅርቡ የተካሄደው መምህራን ጉባኤ አቋምም ይህንኑ እንደሚያመለክት ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንቱ እንደጠቆሙት በማህበሩ ምክርቤት የተነሳውና ሰፊ ውይይት የተደረገበትን የመምህራን ጥቅማጥቅም በተመለከተ ማህበሩ እስከአሁን በተቻለ አቅምና ፍጥነት ሲሠራ የነበረ ሲሆን እስከአሁንም ከ54ሺህ በላይ ለሆኑ መምህራን የቤት ችግር ማቃለሉን እና ወደፊትም በዚሁ ጥረቱ እንደሚቀጥል ተናግረዋል:: የመምህራን ችግሮች በዓይነትና አካባቢዎች ተለይተው የታወቁ መሆኑንና ማህበሩም በዚሁ መሰረት እንደሚሠራም ጠቅሰዋል።
ማህበሩ የትምህርት ዓለም አቀፍ ቦርድ አባልና የአፍሪካ ተወካይ መሆኑንና የሴት አመራር ቡድን (ኮከስ) መስርቶ ሥራ መጀመሩንም ፕሬዚዳቱ ጠቁመዋል።
የኦሮሚያ ክልል መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንተ አቶ ዋቅወያ ቶሌራ በበኩላቸው የዘንድሮ የመምህራን ማህበር ጉባኤ በጥሩ ሁኔታ ተሳትፎ የታየበት፣ ባለቤትነትና ተቆርቋሪነት የተንፀባረቀበት ሲሆን መድረኩም ፍፁም ዴሞክራሲያዊና አሳታፊ እንደነበር ገልጸዋል።
በመድረኩም ላይ “እንችላለን”፣ “አመራር እና የአመራር ሚና” እና ሌሎች ወጣቶችን የተመለከቱ የማንቂያ አጫጭር ስልጠናዎች በጎንዮሽ መሰጠታቸው እንደትልቅ ተሞክሮ ሊወሰድ የሚችል እንደሆነ አቶ ዋቅወያ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር (ኢመማ) በ32 መምህራን አማካኝነት የካቲት 1941 ዓ.ም በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት የተመሰረተ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም ከግማሽ ሚሊዮን በላይ አባላትን ያቀፈ የሙያ ማህበር ነው። ማበሩ የራሱን ባለ 32 ፎቅ ዘመናዊ ሕንፃ ለማስገንባትም በሜክሲኮ አካባቢ መሬት ተረክቦ ለመገንባት ሚያስችለውን የዲዛይን ሥራ እንደጀመረ ለማወቅ ተችሏል።
አዲስ ዘመን ህዳር 1/2012
ግርማ መንግሥቴ