የልጅ አዋቂ፣ ምሁር ደግሞ ሩህሩህ መሆናቸውን ብዙዎች ይመሰክራሉ:: ከታመመው ጋር ታመው፤ ስቃዩንም ተካፍለው የሚኖሩ ናቸው። ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የሚለፉ፣ እንደባለሙያ፣ እንደ እናት፣ ቤተሰብ ሆነው የተጨናቂዎችን ጭንቀት ይካፈላሉም። በሙያቸው ምስጉንና ለተቸገሩ ደራሽም ናቸው። ይህ ባህሪያቸው በተለይ ለኩላሊት ህመምተኞች ተስፋ ሰጪ ከመሆን ጋር ተያይዞ ከአገር ቤትም አልፎ በውጭ አገራት ሳይቀር ‹‹ልዩ ነሽ›› ተብለው የተለያዩ ሽልማቶችን አግኝተዋል::
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምና ማዕከል መስራችና ሜዲካል ዳይሬክተር የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት፤ የኩላሊት ሰብ ስፔሻሊስት፣ የንቅለተከላም ዶክተር የሆኑት ዶክተር ሞሚና አህመድ:: ስለሆነም የዛሬዋ የ”ህይወት እንዲህ ናት” አምድ እንግዳ አድርገናቸዋልና ከእሳቸው ልምድን ትቀስሙ ዘንድ ያደረግነው ቆይታ እነሆ።
በልጅነት ኃላፊነት
በአማራ ክልል ከባህርዳር በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው የገዳማት መናኸሪያ በሆነችውና ክርስቲያን ሙስሊሙ ተዋዶና ተከባብሮ በሚኖርባት ዘጌ በምትባል ቦታ ነው የተወለዱት:: ለቤተሰቡ ደግሞ የበኩር ልጅ በመሆናቸው በልዩ እንክብካቤ አድገዋል:: በዚያውም ልክ ብዙ ኃላፊነቶች ተሰጥቷቸው ተወጥተውታል። ቤታቸውን ከእናታቸው በላይ ይመራሉ፤ ታናናሾቻቸውንም ይቆጣጠራሉ:: ብዙ የቤት ውስጥ ሥራዎችን በማከናወንም ማንም አያክላቸውም:: ውሳኔ የሚያስፈልጋቸው ነገሮች ካሉም መጀመሪያ የሚጠየቁት እርሳቸው ናቸው::
“በልጅነቴ ብዙ የቤት ውስጥ ሃላፊነት ቢኖርብኝም ነገሮችን የማከናውነው በፕሮግራም ነው። ቤተሰቦቼ በንግድ ዘርፍ የተሰማሩ በመሆናቸው ብዙ ጊዜ ሱቁን የምጠብቀውም ሆነ የማስተዳድረው እኔ ነኝ:: ቤተሰቡን በሁሉም መልኩ አግዛለሁ። በቤት ውስጥ የሚሰራ ነገር ካለ እሰራለሁ:: ትምህርት ቤትና የእምነት ቦታ የምሄደውም እንዲሁ በፕሮግራም ስለሆነ ሳልሰራ የምንቀሳቀስበት ሁኔታ የለም::”ይላሉ።
እንደልጅ ሳይጫወቱና ሳይቦርቁ ያደጉት እንግዳችን፤ የበኩር ልጅ በመሆናቸው ሁሉንም ተግባራት በኃላፊነት ይወጣሉ:: በቤት ውስጥ እንዲህ ሁኚ፤ እንዲህ አድርጊ፤ ይህ ለምን አልሆነም የሚባል ነገር ስለማይገጥማቸውም በመሰላቸውና ውጤታማ እሆንበታለሁ ብለው በሚያስቡት መልኩ ነበር የተለያዩ ተግባራትን የሚከውኑት:: ይሄም ውጤታማ እንዳደረጋቸው ይናገራሉ::
‹‹ሥራ በአቅሜ ተለክቶ አይሰጠኝም፤ነጻነት ስላለኝ አላደርገውም የምለውም የለም:: ሳላደርገው የቀረሁትም አለ ብዬም አላስብም::›› የሚሉት ባለታሪኳ፤ የቤት ውስጥ የሥራ ጫና አይደረግባቸውም:: ቤት ውስጥ ድግስ ካለ ብቻ ነው እንደሴቶቹ ኩሽና ገብተው የሚንጎዳጎዱት:: በዚህም በራስ ፍላጎት ስራ መስራታቸው ስራ እንዲወዱ አድርጓቸዋል::
‹‹በልጅነቴ በጣም የሚቆጨኝ እንደልጅ ተጫውቼ አለማደጌ ነው:: ትምህርት ቤት እንኳን ሄጄ ልጆች ሲጫወቱ ሳይ አብሬ ለመጫወት አልደፍርም:: ምክንያቱም በተግባር አልለማመደውም:: በዚህም ብጫወት ተሳስቼ ሊሳቅብኝ ይችላል ያስብለኛል:: ስለዚህ ምርጫዬ ልጆች ሲጫወቱ ማየት ብቻ ነው›› ብለውናል::
ዶክተር ሞሚና በልጅነታቸው መሆን የሚፈልጉት መምህር ነበር:: ሆኖም ከፍ እያሉና ውጤታማነታቸውን ሲያረጋገጡ ሌላ ሙያ ተመኙ:: የወቅቱ የማህበረሰብ ትልቅ ግምት የሚሰጠውን ኢንጅነርና ዶክተር ለመሆን አብልጠው ያነቡ ጀመር:: ለዚህ ደግሞ ቤተሰቦቻቸው የሚሰጧቸው ነጻነት እንዳበረታቸው ይናገራሉ::
‹‹ብዙ መምህራን በባህሬዬ ጭምት እንደነበርኩ ይነግሩኛል:: ከሰዎች ጋር ቶሎ የመግባባት ልምድም የለኝም:: መናገር ሲኖርብኝ ብቻ ነው ድምጼ የሚሰማው። በዚህ ደግሞ አንድ የአማርኛ መምህራችን ግጥም ጽፎልን ክፍል ውስጥ ያነበበልንን አረሳውም::›› የሚሉት ዶክተር ሞሚና፤ ሁሉም ሰው ማድረግ ያለበትን ማድረግ አለበት ብለው ያምናሉ:: በዚሄሜ በልጅነታቸው ማድረግ ያለባቸውን አድርገው ነው ያለፉት::
ሃይማኖት ያልገደበው እድገት
‹‹የቅርብ ወዳጅና የቤተሰብ ተጠሪ ጥቀሽ ብባል ቅድሚያ የምሰጠው ክርስቲያን ጎረቤታችንን ነው:: በእነርሱ ቤት አድጌያለሁ:: ቤተሰቦቼ ብቻ እንዳሳደጉኝ አይደለም የሚሰማኝ:: የእነርሱ ቤተሰብም በእኛ ቤት ከሥጋ በቀር እየተመገቡ አድገዋል:: ስለዚህ አካባቢያችን የእምነት ገደብ የለበትም:: በጋራ መብላት፣ መጠጣትና ማህበራዊ ኃላፊነትን መወጣትን ብቻ የሚያውቅ ነው›› ይላሉ ስለ አስተዳደጋቸው ሲያጫውቱን::
በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ትልቁ የሃይማኖቱ ልዩነት ተደርጎ የሚታሰበው ሥጋ ነው:: ስለዚህም በዓል በመጣ ቁጥር የክርስቲያን ስጋ የሙስሊም ሥጋ እየተባለ ይከፈልና ለሙስሊሙ ሙስሊም ለክርስቲያኑ ክርስቲያን ያርዳል:: ከሙስሊም አራጆች መካከል ደግሞ በዋናነት የሚጠራው አባቴ ነው:: ለመስራት ደግሞ እናቴ ትሄዳለች:: በዚህም የአካባቢያችን ሰዎች ሁሉ ሙስሊም ክርስቲያን ሳይሉ በአንድነት መኖርን አለማምደውኛል:: ሌሎቹም ልጆች እንደኔ አይነት ስሜት እየተሰማቸው ያደጉ ናቸው ብዬ አስባለሁ:: ምክንያቱም አንድም ቀን ክፉ ንግግር እንኳን ተነጋግረን አናውቅም::
የሰፈሩ የህብረት ሥራና አብሮ መብላት በስፋት የሚታየው በአል ላይ እንደሆነ የሚናገሩት ዶክተር ሞሚና፤ ሥጋ ብቻ ለየብቻቸው አንስተው ሌሎች ምግቦችን በጋራ እንደሚጠቀሙ፤ ካነሱ በኋላ ደግሞ በአንድ ማዕድ ላይ ተሰባስበው በመቀመጥ እንደሚመገቡ አውግተውናል:: ይህ ስሜት ዛሬ ድረስ ከውስጣቸው እንደማይጠፋም ይገልጻሉ::
ክርስቲያንና ሙስሊም የሚባል መገፋፋት አለመኖሩን አስታውሰው አሁን ምነው ያ ጊዜ በመጣ ያሰኘኛል የሚሉት እንግዳችን፤ አሁን ባህላችንን ማን እንደቀማን በማናውቀው መንገድ እየተጠላላን ነውና ቆም ብለን እናስብ ይላሉ::
ዶክተር ሞሚና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እየተማሩ የገጠማቸውን እንዲህ ሲሉ ያነሳሉ:: የትምህርት ቤታቸው ዳይሬክተር ነው:: ልጆቹ ደግሞ በጣም የሚጠበቁና ትምህርት ቤቱን የሚያስጠሩ ናቸው:: ግን መሸፋፈናቸው ያንን ቦታ እንዳያሳጣቸው ይፈራል:: እናም አንድ ቀን ደፈር ብሎ የተከናነቡትን ሻርፕ ይቀማቸውና በተማሪዎች ፊት ያቃጥለዋል:: በጊዜው እነዶክተር ሞሚና በጣም ተበሳጩ። ሆኖም ለምን እንዳደረገው ሲነግራቸው ግን ተረዱት::
እንደሚወዳቸውም አወቁ:: ከዚያ ጀምሮም ክርስቲያን ሙስሊም የሚለው ለእርሳቸው ከሥጋ ምግብ ውጪ ልዩነት የሌለው ሆኖ ተሰማቸው:: ዛሬም ቢሆን ያው ስሜት እንዳላቸው ይናገራሉ:: ሙስሊም ወገኖቻቸውንም ማህበረሰቡ ለእኛ ሲል የሚያደርገው ብዙ መልካም ነገር እንዳለ ማሰብ ይጠበቅብናል ሲሉ ይመክራሉ:: ስናድግ ብዙ የተጋራናቸውን ባህሎች በመጤ ተንኮል ልንሸረሽራቸው አይገባምም ይላሉ::
ሴትን ማን ለትምህርት አጫት
አባት እናት ያልተማሩ ቢሆኑም ልጃቸው ተምራ ለቁም ነገር እንድትበቃ ይሻሉ:: ስለዚህ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ ከማሟላት ወደኋላ አይሉም:: በትምህርታቸው ጎበዝ እንዲሆኑና የደረጃ ተማሪ ሆነው እንዲቀጥሉ የቻሉትም ለዚህም ነው:: በትምህርት ቤታቸው ካሉት አምስት ሴቶች አንዷና በራሳቸው የሚተማመኑ ሆነው ለውጤት የበቁትም ነጻ በመሆናቸ|ው ነው::
‹‹ሴት ልጅ ዩኒቨርሲቲ ገብታ ለቁምነገር ትደርሳለች›› የሚል ግምት በማይሰጥበት፤ ብዙዎች በተለይም ሙስሊም ሴቶች ያለፍላጎታቸው በሚዳሩበት አካባቢ ያደጉ ቢሆንም ከግል ጥረታቸው ባለፈ የቤተሰቡ እገዛ ታክሎበት 12ኛ ክፍል አጠናቀዋል:: እዚህ ደረጃ ለመድረስ ግን ብዙ ፈተናዎች እንደነበሩ ዶክተር ሞሚና በትዝታ ወደኋላ መለስ ብለው ያስታውሳሉ::
ትዳር ፈላጊው ናላቸውን ያዞረው ነበር:: ቅድሚያ ለልጃቸው ፍላጎትና ለትምህርቷ የሚሰጡት ቤተሰቦችም የሽማግሌው ጋጋታ አላስቆም አላስቀምጥ ቢላቸው ከ12ኛ ክፍል በኋላ ውጤት ካልመጣላት እንድራለን በሚል እንዲወስኑ ሆኑ:: ይሁንና በብቃታቸው የሚተማመኑት ዶክተር ሞሚና ግን እንደማይሆን ያውቃሉና ቤተሰቡን ወደማረጋጋቱ እንደገቡ ይናገራሉ:: ብዙ ጓደኞቻቸው ጎበዝና ለትልቅ አገራዊ ኃላፊነት መብቃት ቢችሉም በወላጆች ጫና የቤት እመቤት መሆናቸውን ያውቃሉና ይህ በእርሳቸው ላይ እንዳይተገበርም ጉብዝናቸውን ለማሳየት በሚገባ ያነቡ እንደነበር ይገልጻሉ::
ዶክተር ሞሚና ትምህርትን የጀመሩት በሃይማኖት ትምህርት ቤት ቁራን በመቅራት ነበር:: ዘመናዊ ትምህርትን ደግሞ በዚያው በትውልድ ቀያቸው ዘጌ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ‹‹ሀ›› አሉ:: እስከ ሰባተኛ ክፍል ትምህርታቸውን በዚያው ከተከተተሉ በኋላ ቤተሰብ ከዘጌ ወደ ባህርዳር በማምራቱ በባህርዳር ሰርጸ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ስምንተኛ ክፍልን ተማሩ:: ከዘጠኝ እስከ አስራ ሁለት የተማሩበት ደግሞ ጣና ሀይቅ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው::
በጣና ሀይቅ ሲማሩ የልዩ ክፍል/ ስፔሻለ ክላስ/ ተማሪ እንደነበሩ የሚያነሱት ባለታሪኳ፤ ወደ ዩኒቨርሲቲ የገቡት አራት ነጥብ በማግኘት ነበር:: በዚህ ውጤት ወደ ጎንደር ሜዲካል ኮሌጅ አቅንተው በህክምና ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በከፍተኛ ማዕረግ ማግኘታቸውን ይናገራሉ:: ሴትን ለትዳር እንጂ ማን ለትምህርት አጫት የሚለውን ሰብረው በመውጣት ጥንካሬያቸውን አስመስክረዋል። ከዚያ ለተወሰኑ ዓመታት በፖሊስ ሆስፒታል ጠቅላላ ሀኪም ሆነው ካገለገሉ በኋላ ሙያውን ለማሻሻል ‹‹ኢንተርናሽናል ሶሳይቲ ኦፍ ሞርኮሎጂ›› የተባለ ድርጅት እድል ሰጣቸውና ወደ ደቡብ አፍሪካ አቀኑ:: እዚያም በኩላሊት ህክምና ተምረው ወደ አገራቸው ተመለሱ::
በመንግስት ሆስፒታል እየሰሩ በተለያዩ አገራት በርካታ ስልጠናዎችን ወስደዋልም:: በተመሳሳይ አብረዋቸው ከሚሰሩ የውጭ ዜጎች ልምድ ቀስመዋል:: የሥራ ላይ ቆይታ በራሱ ትምህርት ቤት እንደሆነም ይናገራሉ:: ስለዚህ የእርሳቸው ትምህርት ዲግሪ፣ ማስተር፣ ፒኤች ዲ በሚል የሚቆጠር አይደለምና ሁሌም ይማራሉ።
የህክምና ሙያ ሲገለጥ
በአዲስ አበባ የሚገኘው ፖሊስ ሆስፒታል የመጀመሪያው የሥራ ቦታቸው ነበር::እዛ ራሳቸውን ለማሻሻል ምቹ ሁኔታ አላገኙምና
መስሪያ ቤታቸውን ቀይረው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የጥቁር አንበሳ ሪፈራል ሆስፒታል ገቡ:: እዚህም ቢሆን ብዙ አልቆዩም በቀጥታ የሚፈልጉትን ሙያ ለመማር ቤተል ሆስፒታልን ተቀላቀሉ:: በዚህ ሆስፒታልም ለዛሬ ያበቃቸውን ትምህርት አገኙ:: ብዙ ልምዶችንም ቀሰሙ:: የኩላሊት እጥበት ማድረግንም ያስተማራቸው ይሄ የስራ ቦታቸው እንደነበር ያነሳሉ::
መጀመሪያ አካባቢ መሳሪያዎችን ለመጠቀም ከብዷቸው እንደነበር፤ ታካሚዎችን ምን ማድረግ እንዳለባቸው ግራ ሲጋቡ እንደቆዩም ያስታውሳሉ። ከብዙ ልምምድና ትምህርት በኋላ ግን የተሻለ አቅም እንደፈጠሩ ይናገራሉ:: የኩላሊት ህመምተኞች ሰው እንደሚያስፈልጋቸው የተረዱትም ከዚህ በኋላ ነው። ምክንያቱም ህመሙ ብቻ ሳይሆን የሚወጣው ገንዘብ ሌላ ጠባሳን ይጥላልና::
ስለኩላሊት ህመምተኞች ሲያስቡ ሁልጊዜ ያዝናሉ። ህሙማኑ ህክምናውን በበቂ ሁኔታ ስለማያገኙ ሁልጊዜ ያሳስባቸዋል:: ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ገብተው በዚህ ዙሪያ መስራት እንዳለባቸውም ያመኑት ይህ ችግር መባባሱን ከተመለከቱ በኋላ እንደነበርም ይናገራሉ:: የታካሚው ሀዘን ሀዘኔ ነው ብለው ስለሚያምኑም በሙያው ሰዎችን ለመርዳት መሰማራታቸውን ያስረዳሉ::
በቤቴል ሆስፒታል እያሉ ሀኪሞች ኩላሊት ህሙማን ጋር በምንም ሁኔታ መጣላት እንደማይችሉ የነገሩን ባለታሪኳ፤ ዘወትር ግን እንዴት ማገዝ እንዳለባቸው ያስቡ ነበር። የገንዘብ ችግራቸውን ለመውጣትም ከኪሳቸው ሳይቀር ገንዘብ በማውጣት መደጎማቸውን ያስታውሳሉ። ይህም ቢሆን የመጨረሻ መፍትሄ ስላልሆነ ህሙማኑን ለማገዝ ሌላ አማራጭ እንደፈለጉ አጫውተውናል::
ዶክተር ሞሚና ይህንን ያደረጉት በሁለት ምክንያት ነበር:: የመጀመሪያው ብዙዎችን ማግኘት የሚችሉት በመንግስት ሆስፒታል በመሆኑ፤ ሁለተኛው ደግሞ በኮሌጁ በማስተማር ሌሎች ባለሙያዎችን ማፍራት ይቻላል ብለው ስለሚያምኑ ነው:: ስለዚህም በስራቸው ስኬታማ ለመሆን ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅን እንደመረጡ ይናገራሉ:: በሆስፒታሉ ሲገቡ የውስጥ ደዌ ህክምና ብቻ ነው የሚሰጠው:: የኩላሊት ህክምና የሚባል ክፍል አልነበረውም:: ሆኖም እርሳቸው ከመጡ በኋላ መስመር እንዲኖረው ጥረት አደረጉ፤ አሳኩትም::
‹‹እድለኛ ነኝ፤ እድሜ ለአባይ ግድብ። ተመርቄ ከመጣሁ በኋላ ትንሽ እንደሰራሁ አባይን ተከትሎ በመጣው እድል ለአገሬ የምደርስበትን መንገድ አገኘሁ›› የሚሉት እንግዳችን፤ ከመጡ ጀምሮ በማስተማርና የኩላሊት ህመም ታካሚዎችን በማየት ብቻ ተጠምደው ያሳልፉ ነበር:: ሆኖም የግብጽ መንግስት በአባይ ሰበብ ከአገሪቱ ጋር ለመቀራረብ በሚያደርገው ትብብር የኩላሊት እጥበት ማሽንና ሙያተኛ አመጣ:: ይህ ደግሞ ሰዎች ተስፋ እንዲያገኙበት አደረገ:: የተጨናቂዋ ዶክተር ሞሚናንም ደስታ አብሮ አለመለመ::
“የኩላሊት ቀዶ ህክምና ባለሙያም አልነበረንም፣ ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሚቺጋን ጋር ሆነን እንሰራ ነበር” ያሉት ዶክተሯ፤ አሁን ላይ የንቅለ ተከላ ሃኪሞች መኖራቸውንና ከነርሶችና ደጋፊ ባለሙያዎች ዙሪያ አቅም የመገንባት ስራ መሰራቱን ነግረውናል:: ይህ ደግሞ በራስ አቅም ለመስራት እንዳገዛቸው ነው ያጫወቱን :: ሆኖም አንዳንድ ጊዜ የሚከሰቱት ነገሮች በጣም ያበሳጯቸው እንደነበር ያነሳሉ:: በተለይ በአንድ ወቅት የገጠማቸውን መቼም አይረሱትም:: ነገሩ እንዲህ ነው::
እንዲያግዟቸው ከግብጽ የመጡት ባለሙያዎች ወደ አገራቸው ሊሄዱ ነው:: ሆኖም ለብቻቸው እንዴት መስራት እንደሚችሉ ለማሳየት ፈለጉ:: ከዚያም ሥራውን ጀመሩት:: በአጋጣሚ በመሀል አስገዳጅ የመንግስት ስብሰባ ተጠሩ:: ለመቅረት ቢፈልጉም አልቻሉም:: ስለዚህ የተጀመረውን ሥራ ትተው እንዲሳተፉ ተገደዱ:: ሁኔታው በጣም እያበሳጫቸውም ቢሆን ወደ ስብሰባው ገቡ:: በአካል ቢኖሩም በመንፈስ ከታካሚያቸው ጋር ሆነው ስብሰባውን አጠናቀቁ::
ዶክተር ሞሚና እንደሚናገሩት፤ የኩላሊት ህክምና ብዙ የሚያስደስቱ የህክምና ባህሪያት ስላሉት እንጂ ያ ሰው የመትረፉ ሁኔታ አጠያያቂ ነበር:: ህክምናው በሰዓት የሚከናወን ስለሆነ ሰዓቱን ተብቆ መገኘት ብቻ በቂ ነው:: በዚህም ከስብሰባ ስወጣ በሰዓቱ በመድረሴ ታካሚው ድኖ ወደ ቤተሰቡ እንዲቀላቀል ሆኗል:: ሁኔታው ግን ይህንን ባለመፍቀዱ በጣም ያበሳጫል::
ዶክተር ሞሚና በቋሚነት የኩላሊት ህክምና ማዕከሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ሆነው እያገለገሉ ቢሆንም በግል ሆስፒታሎችም ሆነ በመንግስት ሆስፒታሎች ውስጥ ተዘዋውረው ኩላሊት ነክ ህክምናዎችን ይሰጣሉ:: ስልጠናዎችንም በክልል ሆስፒታሎች ጭምር ይሰጣሉ:: በሆስፒታሉም ስፔሻላይዝድ የሚያደርጉ ዶክተሮችን ያስተምራሉ:: በአጠቃላይ ዶክተር ሞሚና መምህር፣ሀኪም፣ አሰልጣኝና አስተዳዳሪም ሆነው ሀገራቸውን እያገለገሉ ይገኛሉ::
ተስፋ ለመስጠት፣ተስፋ አለመቁረጥ
‹‹ልጅ ሆኜ ፣ ተማሪ ሆኜና በሥራ ላይ እያለሁ የደስታዬ ምንጭ የሚሆነው ጉዳይ ይለያያል:: ለአብነት ህክምና ውስጥ ገብቼ መስራት ከጀመርኩ በኋላ ህመምተኞች ድነው ሳይና ለቤተሰቦቻቸው ሲደርሱላቸው ስመለከት ከመቼውም የበለጠ ደስተኛ እሆናለሁ:: ምኞቴ ታካሚዎቼ ነጻ የኩላሊት እጥበት ሲያገኙ ማየት ነውና ይህ እንደተሳካልኝም ይሰማኛል:: የለፋሁበት ፕሮጀክት ዳዴ እያለነው ብዬም አስባለሁ::›› ይላሉ::
በዚህ ሥራ ውስጥ ትልቁ ፈተና ሴት መሆን የሚያመጣው እንደሆነ የሚያነሱት ዶክተር ሞሚና፤ ኩላሊት ቀዶ ማከም ከወንድ ውጪ ያልተፈቀደ ያህል ብዙዎች ይሰማቸዋል:: በዚህም ወንድ ቢሆን ኖሮ አይገጥመውም የሚባሉ ችግሮችን ገጥመዋቸው እንደነበር ያስታውሳሉ:: ሆኖም ተስፋ ሳይቆርጡ ችግሩን ተጋፍጠው ድል አድርገዋል:: በዚህም ደስተኛ እንደሆኑ ይናገራሉ::
ፕሮጀክቱ ሲጀመር በጣም ትልልቅ የሚባሉ ችግሮች እንደፈተኗቸው የሚያነሱት ዶክተር ሞሚና፤ ውጤቱ የላቀ በመሆኑና የህመምተኞች ተስፋ መተኪያ ስለሌለው በእነርሱ ድል እንደነሱት ያስረዳሉ:: ህመሙ ህፃን፣ ወጣት፣ ጎልማሳ፣ አዛውንት አይልም:: ስለዚህ ህጻኑ ሲያድግ፣ ወጣቱ ጉልበቱን ተጠቅሞ ለአገሩና ለቤተሰቡ ሲያገለግል፣ አዛውንቱ ደግሞ አገርን ሲመርቁ ማየትን የመሰለ ነገር በዚህች ምድር ላይ የለም:: ይህ የሆነው ደግሞ ተስፋ ሳልቆርጥ ተስፋ ለሚፈልጉ መኖር ስለቻልኩ ነው ይላሉ::
‹‹የህክምና ስርዓቱ ለጥቂቶች ደርሶ ተስፋ ቢሰጥም ለብዙዎች ባለመድረሱ አሁንም እያዘንኩ ወደ ቤቴ የምመለስበት ጊዜ ጥቂት አይደለም:: በዚህ ወቅት እኔን ጨምሮ ኩላሊቴ ቢደክም በሚከፈለኝ ደመወዝ የኩላሊት እጥበት ማድረግ ያስቸግራል:: በመሆኑም የብዙዎች እጣፋንታ መሞት አሊያም ጎዳና መውጣት ይሆናል›› የሚሉት እንግዳችን፤ ሁሌ ህመምተኞቻቸውን ሲመለከቱ በራሳቸው ውስጥ ያዩዋቸዋል:: ይህ ደግሞ ሁሌ ልባቸው በሀዘን እንዲሰበር ያደርገዋል:: በኩላሊት ህመም ዙሪያ የሚመጡ ታካሚዎች ታሪክን ሰምተው መልስ መስጠት አለመቻላቸው ዘወትር ያስለቅሳቸዋል፤ ያሳዝናቸዋል:: እናም ፈተናው ጥቂት ስላልሆነ የመፍትሄ አካል የሆነው ሁሉ ሊያግዛቸው እንደሚገባ ይናገራሉ::
ስኬት- ተተኪን ማፍራት
“ስኬት የሚመጣው ሌሎች እኔን መተካት ሲችሉና ሲያስቀጥሉ ነው:: በብቸኝነቴ እንዳልቀጥልና ያሰብኩት አላማ ከግብ እንዲደርስ ለማድረግ ተተኪዎችን በማስተማር እያፈራሁ ነው:: ለዚህ ደግሞ መሰረቴና አርአያዬ ፕሮፌሰር ሰናይት ፍስሃ ናት:: እርሷ አንድ ሰው ብቻውን አገር እለውጣለሁ ብሎ ከተነሳ የሚችለውን ያህል መራመድና ለስኬት መብቃት እንደሚችል አስተምራኛለች::እናም ሁልጊዜ እርሷን መምሰል እፈልጋለሁ::
በአገር ውስጥ ብዙ መሰራት ያለባቸው ነገሮች አሉ:: እናም ሌሎች እኔን እንዳበቁኝ ሁሉ እኔም መሰሎቼን ማፍራትና ለፕሮጀክቱ ማበርከት እፈልጋለሁ:: ይህንን ማድረግ ከቻልኩ የህክምና ባለሙያዎች ይበራከቱና የኩላሊት ታካሚ ቁጥር እንደሚቀንስ አምናለሁ:: ለዚህ ደግሞ የታካሚዎቼ ጸሎት ያግዘኛል:: እስከዛሬ ያለሁትና ለዚህ የበቃሁት አርአያዎችን በመከተልና በየቀኑ ከታካሚዎቼ በሚጎርፍልኝ ምስጋና ነው:: በብዙ ቦታዎች ላይ ሽልማቶችን ተቀብያለሁ:: የተለያዩ የምስክር ወረቀቶችንም አግኝቻለሁ:: ከሁሉም የሚልቀው ግን ታካሚዎቼ በየቀኑ የሚያደርጉልኝ ጸሎት ነው” ይላሉ:: በእርግጥ ለዚህ ሁሉ ውለታቸው የ2018 የዓመቱ ‹‹ውሜን ኦፍ ኤክሰለንስ›› በሚል ተመርጠው ሽልማት ተበርክቶላቸዋል:: በተመሳሳይ በአገር ውስጥም የበጎሰው ተሸላሚ ሆነዋል:: ግን ብልጫው የታካሚ ጸሎት እንደሆነ ይናገራሉ::
‹‹ሁሉም ሰው ተሰጥኦ አለው፤ ሁሉም ሰው ተሰጥኦውን በተግባር መተርጎምም ይችላል::›› የሚል እምነት ያላቸው ባለታሪኳ፤ ሰዎች በችግሮች ውስጥ ማለፍ ሲችሉ አመርቂ ለውጥ ያመጣሉ:: በአንዱ ስለወደቅሁ ሌላ መንገድ የለም ብለው ካሰቡ ግን ተሰጥኦውን ተጠቅመው ያሰቡት ደረጃ ላይ መድረስ አይችሉም:: እናም ተሰጥኦ ሲደመር ተግባርና ተስፋ አለመቁረጥ ስኬትን ያመጣል:: ስለዚህ ይህንን ታሳቢ ማድረግ ይገባል ይላሉ::
ቤተሰብ
ልጆች ሲኖሩ የበለጠ ጠንካራ መሆን ይቻላል:: ምክንያቱም ለእነርሱ አርአያ መሆን ብቻ አንዱ ለሥራና ለጥንካሬ ምንጭ ነው:: ልጆችን ቤት ውስጥ ማስጠናትና መንከባከብ ግዴታ ነው:: ከዚያ አልፎ እነርሱ ጠንካራ መሆን እንዴት እንደሚቻሉ ለማሳወቅ የሚሰራውን ሁሉ በእነርሱ ልክ ማስተማርና መንገር ለውጤታማነት ያበቃቸዋል:: ‹‹ጊዜ ባይሰጣቸውም በምን ምክንያት ይህ እንደሆነ ማስረዳት ስለሚኖር እዚያ መስመር ላይ እንዲገቡ እነግራቸዋለሁ:: የስራ ባህልንና ጥንካሬን ማሳየት የሚቻለው ደግሞ በሥራ ልቆ ወጥቶ እነርሱ ሲመለከቱት ነው:: እናም ልጆቼ ከእኔ እየተማሩ ነው ብዬ አምናለሁ›› ይላሉ::
ሁለት ወንድ ልጆች ያሏቸው ዶክተር ሞሚና፤ ቀንም ሌሊትም ሰዓት ሳይገድቡ ሥራቸውን ይሰራሉ:: ቀን ውለው አዳር ሙሉ የሚሰሩበት ጊዜም እንዳለ ይናገራሉ:: በዚህም ከልጆቻቸው ጋር በቂ ጊዜ ስለማያሳልፉ ምክንያቱ ምን እንደሆነ እያንዳንዱን ክስተትና ያደረጉትን ነገር ልክ እንደጓደኛ ይነግሯቸዋል:: እነሱም ይቀበላሉ ።ስለዚህ ደስተኛ ሆነው እንደሚኖሩ አጫውተውናል::
መልዕክት ከዶክተር ሞሚና
በሁላችንም ውስጥ ለኛ ብቻ የተሰጠ ስጦታ አለ፤ ይህን ስጦታ አውጥተን ሌሎች እንዲያዩት ማድረግ የምንችለው ውሳኔ መወሰን ስንችል ብቻ ነው። ውሳኔያችን ደግሞ መሆን የምንፈልገውን መሆን አለበት። ምክንያቱም ሙያችን እንዲሆን የምንመርጠው ነገር የምንወደው ነገር ከሆነ በዛ ነገር ላይ እውቀታችንን ለማዳበርም ሆነ ልምድ ለማግኘት ፍላጎት ይኖረናል። ለአብነት ሰውን መርዳት የማይወድ ወይም ስለሰው ግድ የለሌው ሆኖ የህክምና ባለሙያ ቢሆን፤ በሽተኞቹን እንደ ገንዘብ ማግኛ ከመቁጠር በቀር ለጤንነታቸውም ሆነ ለደስታቸው ዴንታ አይሰጠውም። ስለዚህ የምንሰራው ነገር ምን ያህል ደስታ ወይም እርካታ ይሰጠናል የሚለውን መመለስ ይኖርበታል ይላሉ::
እርሳቸው መሆን የሚፈልጉትን በመሆናቸው ዛሬ ለታካሚዎቻቸው የሚሆን ነገር ለማግኘት እየጣሩ ናቸው:: ስለዚህም ሰዎች ከእኔ ቢማሩ የሚሉት ላመንበት ነገር መቆምና መታገል ፣ከዚያም ለግብ ማብቃት ነው:: በተለይ ብቻዬን ምን ላመጣ የሚል መፈክር ከውስጣችን ሊጠፋ ይገባል:: አለምን የቀየሩት ግለሰቦች መሆናቸውን አምኖ መስራትም ያስፈልጋል::
‹‹ብቻዬን ነኝ ብዬ ይህንን ሥራ ባላስጀምረው የፍላጎቴን ማግኘት አልችልም፤ ለወገኖቼም እንዳልደርስ እሆናለሁ›› የሚሉት ዶክተር ሞሚና፤ ተስፋ መቁረጥና በሌሎች ላይ ጣት ቀስሮ ሥራ ማቆም ተገቢ እንዳልሆነ ሁሉም ሰው ሊያውቅ ይገባል:: ወደፊት መገስገስና አሸናፊ የሚኮነውም አቅዶና አልሞ ለግቡ መስራት ሲቻል ነው:: ስለዚህ አማራጮችን በመያዝ አንዱ ሳይሳካ አንዱ ላይ በመሻገር መስራት እንደሚገባ ይመክራሉ::
‹‹ግለሰቦች ኃላፊነታቸውን ሲወጡ አገር ታድጋለች፤ የራስ ብልጽግናም ይመጣል:: እናም እንደ ግል ኃላፊነትን መወጣት ገንዘብ እናድርግ›› መልዕክታቸው ነው:: እኛም ይህን እውነት በተግባር እንድናውለው በመመኘት ተሰናበትን:: ሰላም!
አዲስ ዘመን ጥቅም30/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው