‹‹ሥራ ፈጠራ ማለት ምን ማለት ነው?›› የሚል ጊዜያዊ ጥያቄ እንጠይቅ።የሚመጣልን መልስ ሳይንሳዊ ትንታኔ ያለው ትርጉም ነው።በቃ! ሥራ ፈጠራ ማለት አዲስ ነገር መፍጠር ማለት ነው (በተለመደው ትርጉም ማለቴ ነው)።ሥራ ፈጠራ ማለት የሆነ አዲስ ግኝት ማግኘት ማለት ነው።ከዚህም ከፍ ሲል ደግሞ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤት የሆነ ነገር መፍጠር ማለት ነው።ሥራ ፈጣሪ ተብለው ሰፊ ሽፋን የሚያገኙትም ከኤሌክትሮኒክስ ነገር ጋር የተገናኘ ነው።ይህ ዓይነት የሥራ ፈጠራ ትርጉም ከሳይንሳዊነቱ ይልቅ ልማዳዊነቱ ይበልጣል።
የሥራ ፈጠራ ትርጉም የግድ አዲስ ነገር (ከዚህ በፊት የሌለ ማለት ነው) መፍጠር ብቻ አይደለም።ያለውን ነገር ማስተዋወቅ ነው።ሰዎች አጠገባቸው እያለ ልብ ያላሉትን ነገር ልብ እንዲሉት ማድረግና ሥራው ምን ያህል ውጤታማ እንደሆነ ማሳየት ነው።በሥራ ፈጠራ ላይ የተሰሩ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ጥናቶችም የሚያሳዩት ይህንኑ ነው።ሰዎች ንቀው ወይም የሚጠቅም ሳይመስላቸው ቀርቶ የተውትን ሥራ ማስተዋወቅ ነው።‹‹ለካ እንዲህም መሥራት ይቻል ነበር›› እንዲሉ ማድረግ ነው።ያ! ሥራ ማንም ሰው የሚሰራው ሆኖ ግን ልብ ሳይባል ወይም በተለያየ አጋጣሚ የማይሰራበት ይሆናል፡፡
ነገሩን ወደ አገራችን እናምጣው። ‹‹ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብትና የሰው ኃይል እያላት ነው ድሃ የሆነች›› የሚለውን ገለጻ ለምደነዋል።የሥራ ባህላችን ስንፍናን የሚያበረታታ ነው።አኩሪ ባህል እንዳለን ሁሉ ለድህነት የሚዳርጉ አጉል ልማዶችም አሉብን።
በአገራችን ውስጥ በኋላቀር ልማድ ምክንያት ብዙ የማይሰሩ ሥራዎች አሉ።አንዳንዶቹ ፆታ የተለየላቸው ናቸው፤ አንዳንዶቹ ደግሞ የድሃ ሥራ እና የሀብታም ሥራ ተብለው የተለዩም ናቸው።ከልጅነቴ ጀምሮ የማውቀው በአካባቢያችን የነበረ አንድ ባህል ልንገራችሁ።በነገራችን ላይ የሁለተኛ ደረጃ እና የመሰናዶ ትምህርት ቤት ተማሪ እያለሁ በዚህ ጉዳይ ላይ ከቤተሰብና ከጎረቤት ጋር እከራከር ነበር።ለማስረዳትም እሞክር ነበር፤ አሁን ተሻሽሏል (በእርግጥ የተሻሻለው በእኔ ምክር ሳይሆን ችግር ሲቆነድዳቸው ነው)፡፡
ነገሩ እንዲህ ነው።ከአካባቢያችን አንድ የእጅ ባለሙያ ሰውየ ነበር።ከሸንበቆ የሚሰራቸው የመገልገያ ዕቃዎች ከፋብሪካ የተሰሩ ዘመናዊ ዕቃዎችን ያስንቃሉ።ይሄው ሰውየ ከብረታብረት፣ ከእንጨት፣ ከገመድ (ከቃጫ ማለት ነው)፣ ከማዳበሪያ… የሚሰራቸው ዕቃዎች ሁሉ ጥንካሬና ውበት ያላቸው ናቸው።በእንዲህ አይነቱ የሰብል መሰብሰቢያ ወቅት ደግሞ ከሸንበቆ ትልልቅ ቅርጫቶችን ይሠራል።ገበሬዎች ሁሉ እሱ ጋ እየሄዱ ነው የሚያሰሩት ወይም የሚገዙት፡፡
ልብ በሉ! ይሄ ሰውየ እየሰራ ያለው እነርሱ መሥራት ያልቻሉትን ነገር ነው፤ ግን በአካባቢው የሚሰጠው ክብር ዝቅተኛ ነበር።በልጅነት አዕምሯችን የሚነግሩን ሁሉ እውነት ይመስለን ነበር።‹‹ባለ እጅ ነው›› ይሉናል፤ እንዲህ አይነት ጥበብ ያላቸው ሰዎች ልጅ ካዩ ዓይናቸው ይበላችኋል ይሉናል (ሙያ እንኳን እንዳንማር)፣ ድሃ ናቸው ይሉናል፣ እንዲህ ዓይነት ሥራ የሚሰሩ ሀብታም አይሆኑም ይሉናል።የሚገርመው ይህን የሚሉት ሰዎች ከዚህ ሰውየ የሚበደሩ ድሃዎች ናቸው።
ይህ አይነት አጉል ልማድ ብዙዎችን ድህነት ላይ ጥሏል።በተለይም በሴት ልጆች ላይ የከፋ ነው።በየጎዳናው አስከፊ ሕይወት ሲኖሩ የምናየው አገሪቱ ውስጥ የሚሰራ ጠፍቶ አይደለም፤ ራሳቸውን እስከማጥፋት የሚያደርስ አስከፊ ሕይወት ውስጥ የሚኖሩት ከወንድ የተለየ አቅመ ቢስ ወይም መሥራት የማይችሉ ሆነው አይደለም።ይልቁንም የማህበራዊ ሕይወት አድሎ ነው።ለሴቶች ተብሎ በአጉል ልማድ የተገደመ የሥራ ዘርፍ መሆኑ ነው።
ይህንን አጉል ልማድ ጥሰው የወጡ ቆራጥ ሴቶች ደግሞ ለብዙዎች ምሳሌ ሆነዋል።እስኪ ለዛሬ በወንዶች ብዙ ሲሰራ የምናየውን አንድ ሥራ የሚሰሩ ሴቶችን እናስተዋውቃችሁ።ቀጥታ ወደ ባህርዳር እንሄዳለን፡፡
ይህ ለባህርዳር ከተማ ነዋሪዎች አዲስ ነገር አይደለም፤ ይህን ወሬ ቢሰሙ ‹‹ብርቅ ነው እንዴ ታዲያ!›› ሊሉ ይችላሉ።እንኳን ለነዋሪዎች ለእንግድነት ወደ ባህርዳር ለሄደ ሁሉ የተለመደ ነው።
ባህርዳር ከተማ ውስጥ ከገቡ ከአስፋልቱ ግራና ቀኝ የሚያዩት ሴት ጫማ ጠራጊዎችን ነው።አንድ ቦታ አይተው ተገርመው ከሆነ ከተማዋን ሲዟዟሩ ግርምቱ ይለቅብዎታል።የከተማዋ ነዋሪ ከሆኑ ደግሞ ወንድ ሊስትሮ ካዩ ነው የሚገረሙ።አንድ ነገር አዲስ የሚመስለን እስከሚለመድ ድረስ ነው።ባህርዳር ደርሰው የመጡ ሁሉ ሴት ሊስትሮ በማየታቸው ሲገረሙ ይሰማል።የገረማቸው ሊስትሮነት የወንድ ሥራ ብቻ ሆኖ ሳይሆን ሴት ሲሰራው አይተው ስለማያውቁ ነው።እርግጥ ነው አዲስ አበባ ውስጥም እጅግ በጣም አልፎ አልፎ ይታያሉ፤ ባህርዳር ከተማ ውስጥ ግን ብርቅ አይደለም።አዲስ አበባ የአገሪቱ ዋና ከተማ ሆና፤ ግን ይሄ አጉል ልማድ አለቀቃትም።ሴት የታክሲ ሾፌርም ሆነ ረዳት ብዙም አይታዩም።እስኪ ከባህርዳር ሴት ሊስትሮዎች ልምድ እንውሰድ!
አገሬ ገብሩ ትባላለች።በባህርዳር ከተማ ውስጥ በሊስትሮነት ሥራ የተሰማራች ናት።አገሬ በዚህ ሥራ ውስጥ ከተሰማራች ሁለት ዓመት ሊሆናት እንደሆነ ታስታውሳለች።ወደዚህ ሥራ ስትገባ ሴት መሆኗ ምንም ያስቸገራት ነገር የለም።ምክንያቱም ከእሷ በፊት ብዙ ሴቶች በዚህ ሥራ ውስጥ ተሰማርተው ነበር።አገሬ ከዚህ በፊት ሴት ሊስትሮ የምትሰራ አይመስላትም ነበር።ከገጠር ወደ ባህርዳር የመጣችውም ይህን ሥራ እሰራለሁ ብላ አልነበረም።እንደመጣች በሌላ ሥራ ብትቆይም በየመንገዱ የምታያቸው ሴቶች ግን በዚህ ሥራ የተሰማሩ ናቸው።ብዙ መሆናቸው ደግሞ ሥራው የሴት እስከሚመስል ድረስ በራስ መተማመን ፈጥሮባታል።አሁን ላይ በዚህ ሥራ ተሰማርታ ለወላጆቿም የምትልከው ብር ማግኘት ችላለች።
አንዳንድ ከሌላ አካባቢ የሚመጡ ሰዎች እንደሚገረሙ የምትናገረው አገሬ፤ በሌላ አካባቢዎች ሴት ሊስትሮ ያልተለመደ መሆኑን ታውቃለች።ወደዚህ ሥራ ከገባች በኋላ ግን ለምን የወንዶች ሥራ እንደመሰለ ይገርማታል።ሥራው የጉልበት ኃይል የሚፈልግ አይደለም፣ የትምህርት ደረጃ የሚጠይቅ አይደለም፣ በሌሊት ወይም በሌላ አስቸጋሪ ሁኔታ የሚሰራ አይደለም።ማንም በቀላሉ መሥራት የሚችለው ሆኖ ለወንዶች ብቻ የተሰጠ መምሰሉ ትክክል እንዳልነበር ታምናለች።
እንደ አገሬ ትዝብት፤ ሊስትሮ በመሆኗ ከወንዶች ይልቅ ሴቶች ሲገረሙ አስተውላለች።የብዙ ሴቶች ጥያቄም ‹‹ወንዶች ምን ይሉሻል?›› የሚል ነው። አንዳንዶቹም ወደዚህ ሥራ መግባት ይፈልጉና በራስ መተማመን ያጣሉ።ዳሩ ግን የሚሰሩት ሥራና የሚኖሩት ኑሮ ደግሞ ራሳቸውን እንኳን ለመቻል የማያስችል ነው።የዕለት ጉርስ እንኳን እያጡ ወደሌላ አልባሌ ነገሮች ይገባሉ።
ያም ሆኖ ግን የሚያበረታቷትና የሚያደንቋት እንዳሉም ትናገራለች።ምንም እንኳን በአካባቢው ብዙ ሴት ሊስትሮዎች ቢኖሩም አንዳንድ ሰዎች አሁንም ድረስ አዲስ እየሆነባቸው ያበረታቷቸዋል።‹‹እንዲህ ለሌሎች ዓርዓያ ሁኑ›› እያሉ ይነግሯቸዋል።
ሌላኛዋ ወጣት እመቤት አለሙ ትባላለች።እሷም እንደ አገሬ ሁሉ ወደዚህ ሥራ ስትገባ ቀድመው የነበሩ ሴት ሊስትሮዎችን አይታ ነው።የዚያው የባህርዳር ከተማ ነዋሪ ነበረች።እመቤት እንደምትለው፤ ሴት ሊስትሮ የበዛው አሁን አሁን ነው እንጂ በፊት እንደዚህ አይበዙም ነበር።በአንድ ሁለት ሴቶች ተጀመረ፤ ያኔ የባህርዳር ከተማ ነዋሪዎች ራሱ ነገሩ አዲስ ይሆንባቸው ነበር።እንዲህ እንዲህ እያለ ቁጥራቸው ከፍ እያለ መጣ።አሁን ላይ በየትኛውም የከተማዋ አካባቢ በብዛት የሚታዩት ሴት ሊስትሮዎች ናቸው።
እንደ እመቤት አስተያየት፤ ይህን ሥራ ሴቶች ሲሰሩ ባታይ ኖሮ በድፍረት አትጀምረውም ነበር።እንዲያውም እንኳን ብቻዋን ልትጀምረው ከጎኗ ሴቶች እያሉ ራሱ ገና የጀመረችው ሰሞን እየተሳቀቀች ነበር።ሥራውን በደንብ እየቻለችበት፤ ዳሩ ግን ‹‹ሰውነቴ ሁሉ ይንቀጠቀጥ ነበር›› ትላለች።አሁን ላይ ሆና ስታስበው ሥራውን ትታው ቢሆን ይቆጫት ነበር።
በነገራችን ላይ በዚህ ሥራ የተሰማሩት ሁሉም ውጤታማና ደስተኞች ናቸው ማለት አይደለም።አንዳንዶቹ የተሰላቹም ናቸው።የተሰላቹበት ምክንያት ደግሞ ሴት ሆነው ይህን ሥራ በመሥራታቸው ሳይሆን ሥራ ባለመኖሩ ነው።ከጀመሩት በኋላ የተውትም አሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ ዕድል የቀናቸው ለሌላ የንግድ ሥራ ወረት (መነሻ ገንዘብ) የሆናቸውም አሉ።
ብዙ ሴቶች ወረት (መነሻ ገንዘብ) ካገኙ ሌላ የንግድ ሥራ እንደሚጀምሩበት ነበር የነገሩኝ።እንደ ወንዶች ሥራው ላይ ረጅም ዓመታት አይቆዩበትም።የራሳቸው የንግድ ሥራ ይጀምሩና በሌላ ሥራ ይሰማራሉ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ወደ አረብ አገር ይሄዱበታል።ወደ አረብ አገር መሄድም ሆነ የራስን የንግድ ሥራ ለመጀመር የሚያስችል ወረት ማግኘት ያልቻሉት ደግሞ በዚህ ሥራ ይቀጥላሉ።እንደ አብዛኞቹ አስተያየት ግን ከሰው ቤት ተቀጥሮ ከመሥራት በብዙ እጥፍ የተሻለ ነው።ነፃነት አለው፤ በገንዘብም ቢሆን ሲያገኝ ሲያጣ ይሆናል እንጂ የተሻለ ነው፡፡
እነዚህ የባህርዳር ከተማ ሴቶች ለብዙ ነገር አርዓያ ይሆናሉ።ከዚህ መረዳት ያለብን ነገር ደፍሮ መጀመር ለብዙዎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ነው።ይሄኔ እኮ እዚያ ከተማ ውስጥ ይህን ሥራ የጀመረችው አንዲት ሴት ልትሆን ትችላለች።ዛሬ ላይ ግን ማንም አይገርመውም።የአጉል ልማዶችን ጎጂነት አሳይተዋል።እንግዲህ ከሊስትሮ ቀላል የሆነ ሥራ የለም ነበር፤ እንደ ትልቅ ጉዳይ የሚታይ አልነበረም፤ እንዲህ ጥቂቶች ሲጀምሩት ግን ቀላልነቱ ይታያል ማለት ነው።ብዙ እንዲህ ዓይነት ሥራዎች ሊለመዱ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት29/2012
ዋለልኝ አየለ