ኢትዮጵያዊነት ከደም ውስጥ የሚዋሀድ ማንነት በመሆኑ በቀላሉ ሊጠፋ አይችልም። መገለጫውም ቢሆን ለአመነበት መሞት ነው። ለዚህም ነው «ኢትዮጵያ በአህያ ቆዳ አልተሰራችምና ማንም በጩኸት ሊያፈርሳት አይችልም» የሚባለው።
ምክንያቱም ከ3ሺ ምናምን ዓመታት በላይ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ አያሌ ጊዜ ሞክሮ ተሳክቶለት የፎከረ የለምና። ሊያፈርሱት ሲያስቡ የሚበረታ፤ ሊለያዩት ሲቋምጡ የሚዋሀድ፤ ሊያዋርዱት ሲመጡ ፈጥኖ የሚያዋርድ ህዝብ ነው።
የኢትዮጵያ ህዝብ ሰላሙን ሊያውኩበት የሚፈልጉትን የሚታገስበት ልብም የለውም። በታሪካችን የምናውቀው የአንዱ ጫፍ ሰላም መናጋት ሁሉንም አካባቢ ሲያመው ነው። ዛሬ ግን እርስ በርሳችን እንድንጠላላና ጦር እንድንማዘዝ የሚያደርጉን ኃይሎች ተፈጥረዋል። ይህ ሃሳብ ህልም ሆኖ ይቀራል እንጂ ሃሳባቸው እንደማይሰምር ከታሪካችን ሊማሩ በተገባ ነበር።
ለዚህም ነው ‹‹ሊነጋ ሲል ይጨልማል›› እንዲሉ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ እንዲህ ያሉት «ዛሬ በየቦታው የሞትና የመፈናቀል ዜና እየሰማችሁ ይሆናል። ሊታደስ እየፈረሰ ያለ ቤት ፍርስራሽ ስለሚበዛው በአካባቢው አቧራ እና የሚያውክ ነገር መኖሩ አይቀርም። እናንተ ግን ማወቅ ያለባችሁ ይህ እድሳት ተጠናቆ ውብ የሆነ ቤትና ውብ የሆነች ኢትዮጵያን የምናስረክባችሁ መሆኑ ነው»
ሰሞኑን ብሌን ኪነጥበባዊ የሰላም ምሽት በኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ተዘጋጅቶ ነበር።
የኪነጥብብ ምሽቱ ዓላማ ሰላምን በጥበብ ለመስበክ ታስቦ የተዘጋጀ ነበር። «ለጠቢብ ጥበብ እንዲጨምር ምክንያት ጨምርለት» እንዲሉ በርግጥም መርሃ ግብሩ የተሳካለት ነበር። ከምንም ነገር በላይ ኪነ ጥበብ ለሰላም ያላትን ዋጋ ለማስረዳት የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ሳይቀሩ በቦታው መገኘታቸው ክብራቸውን ሊያሳዩ ሳይሆን በጥበብ ሊከብሩ መሆኑን መናገራቸው አስደናቂ ነበር።
በመርሃ ግብሩ ላይ የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚልና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው ተገኝተው ነበር።
የሰላም ሚኒስትሯ በርግጥም የጥበብን ኃያልነት ከመረዳት አልፈው በጥበብ መታከም እንደሚቻልና ከኪነጥበብ ባለሙያዎች ጋር ማሳለፍ ምንያህል መታደል እንደሆነ መረዳታቸውን አሳይተውናል። ጥበብን አክብረው በጥበበኞች ፊት ተከብረውበታል።
በተለይም ያስተላለፉት መልእክት የፖለቲከኛ ሳይሆን በጥበብ የታሸና የተዋዛ በመሆኑ ከቀረቡት የኪነጥበብ ስራዎች በላይ ቀልብን የገዛ ነበር። «አንደበቱ የቀና ተናግሮ የሚያሳምን እርሱ ጥበበኛ ነው» እንዲሉ በታዳሚው እንዲህ አይነት ጥበበኛ መሪዎችን ያብዛልን ተብለዋል።
መሪዎች አገልጋዮች ናቸው። አገልግሎታቸው ደግሞ በጊዜና በሁኔታ ያልተገደበ መሆን ይኖርበታል። ሁለቱ ሚኒስትሮች በክብር የቆረሱትን የሰላም ዳቦ ቆርሰው አልተቀመጡም። ይልቁንም የተቆረሰውን ዳቦ ለእድምተኛው በማዞር ዳቦ የመስጠታቸው ምስጢር የአገልጋይነት ስሜት መኖሩን የሚያመላክት ነው። ይህን በማድረጋቸውም አብዝተው አትርፈዋል «የአገልግሎት ዘመናችሁን ይባርከው» ተብለው ተመርቀዋል።
ይህ በሌሎችም ከፍተኛ ባለስልጣናት ሊለመድ የሚገባው ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፤ የግድም መሆን ያለበት ተግባር ነው። ምክንያቱም ከማገልገሉ ባለፈ ቅርበትን ይፈጥራልና። አገልጋይ ማለት ከተገልጋዩ ቅርበት ያለው ቅርበቱን ደግሞ ለታይታ ሳይሆን ለፍቅር የሚያደርገው መሆኑ የታመነ ነውና።
በየትኛውም መንገድ የምትቀርብ ጥበብ ወዳጅነቷ ከህሊና ጋር ነው። በጥበብ የሚነጋገር ትውልድ ለውጥ ያመጣል፣ በጥበብ የሚናገር መሪ ተወዳጅና ተሰሚ ይሆናል፤ የሚበጀውን የተናገረ እንደሆነ ማንም ሳያቅማማ ይቀበለዋል። ጥበብን የለበሰ ደግሞ አንድም ሰው ቢሆን አገር ይሸፍናል፤ ብቻውንም አገር ያክላል። በመሆኑም የጥበብን ፋይዳ የተረዳና ያመነ መሪ ሀገርንና ህዝብን በጥበብና በብቃት ይመራል።
የኪነ ጥበብ መለኪያው እውነትና ውበት ነው፤ ኪነጥበብ የሚያንፀባርቀው የሰው ልጅ በዘመኑና በታሪኩ የፊተኛና የኋለኛ ክፍሎች ያሰባሰባቸውን ሀቅ ነው፤ ኪነጥበብ ደምቆ የሚታየውና የሚኖረው በራሱ በህብረተሰቡ ውስጥ ነው፤ ያለ ህብረተሰብ ዋጋ የለውም፤ በነፃ ህብረተሰብ ውስጥ ኪነጥበብ ያድጋል ይመነደጋል።
ኪነጥበብ የሰላም፣ የልማትና የእድገት ማምጫ መሣሪያ ይሆናል፤ የህብረተሰብ ሃያሲ ከመሆኑም በላይ የጠንካራ ህብረተሰብ መሠረቱ ኪነጥበብ ይሆናል። እናም ሰላምን ለማስፈን የኪነጥበብ ሚና እጅጉን የገዘፈ ነውና የተጀመረው እንዲቀጥል፣ የሚቀጥለውም ፍሬያማ እንዲሆን መግባባትና ተባብሮ መስራት ከሁሉም ሀገር ወዳድ ይጠበቃል።
ኪነጥበብ ህዝብን ከፍርሃት የማላቀቅ ኃላፊነት አለበት። ኪነጥበብ ሰው የእውነትና የህብረተሰብ ወገንተኛ በመሆኑ የህብረተሰቡን ሰላም የሚያውኩትን በብእሩ ይሞግታል፤ አልፎም ይፋለማል። አሁን አሁን በአገራችን ውስጥ ፍርሃትና መጠላለፍ በዝቷል። በእጃችን የጨበጥነውን ሰላም ለቀን ብጥብጥና ጭንቀትን መስማት አንፈልግም፤ ሰላም በሌለበት ሀገር ውስጥ ኪነጥበብ ህልውና የለውም፡፡
በመሆኑም ሁሉም የጥበብ ወዳጅ ለሀገራችን ሰላም መስፈን ድርሻው ግዙፍ እንደሆነ በመረዳት ሚናውን ሊወጣ ይገባል። ምክንያቱም ኢትዮጵያዊው ፈላስፋ ወልደ ሕይወት «ለጠቢብ ጥበብ እንዲጨምር ምክንያት ጨምርለት» ብሎ ተናግሯልና፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 21/2011