የበርካቶችን ሠርግ በዲኮር ሥራቸው አድምቀዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ የመድረክ እና የአዳራሽ ዝግጅቶች ለዓይን ማራኪ እንዲሆኑ ለዓመታት ሠርተዋል። ከድግስ ዕቃዎች ጀምሮ የቡና ቤት እና የሆቴል ቤት ዕቃዎችን በማቅረብ ንግዳቸውን ያሳደጉ ብልህ ሰው ናቸው።
ባለታሪኩ አቶ ዳዊት ሙሳ ይባላሉ። በአዲስ አበባ መርካቶ አካባቢ ሰባተኛ በሚባለው ሰፈር ነው የተወለዱት። በልጅነታቸው የነበራቸው የወደፊት ህልም ሹፌር ወይንም ደግሞ አየር ወለድ ለመሆን ነበር። ግና ቅሉ ህይወት ባላሰቡት ዘርፍ በዝግጅት ማስዋብ እና የኪራይ ዕቃዎችን ወደማቅረቡ መርታቸዋለች።
አቶ ዳዊት አንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተስፋ ኮከብ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። በወቅቱ ከክፍላቸው የአንደኝነት ደረጃን ይዘው የሚያጠናቅቁ ጎበዝ ተማሪ እንደነበሩ የሚያውቋቸው ይመሰክራሉ። እርሳቸው ግን በትምህርታቸው ጎበዝ ቢሆኑም በጎን ደግሞ በአነስተኛ ንግድ ተሳትፈው ገቢ መሰብሰቡን ለምደውት ነበር።
ግማሽ ቀን ተምረው በሚኖራቸው የግማሽ ቀን ዕረፍት ጊዜ ‹‹ደርሶ መልስ ትኬት›› ብለው የሚጠሩትን የትርፍ ንግድ ጀመሩ። ደርሶ መልስ ማለት ለሁለት ጉዞዎች የሚያገለግል የደርሶ መልስ የአውቶቡስ ትኬት ሲሆን፤ ይህን ትኬት ከአንበሳ አውቶቡስ ቢሮዎች ቆርጦ አንድ ጉዞ ብቻ ከሄደ ሰው ላይ አቶ ዳዊት በዓይነት ማለትም በምላጭ እና በመርፌ ከፍለው ይገዙታል። ከዚያም አንድ የመመለሻ ጎዞ የሚቀረውን ትኬት ለሚፈልግ ሰው በመሸጥ ጥቂት ሳንቲሞችን ያተርፉ ነበር።
ስምንት ምላጭ ፣ ከረሜላ ወይንም መርፌ ከሱቅ በአምስት ሳንቲም ከገዙ አራቱን ምላጭ ወይም ከረሜላውን ደርሶ መልስ ቆርጦ አንድ ጉዞ ለሄደ ሰው ይሰጡትና ትኬቱን ተቀብለው እርሳቸው አምስት ሳንቲም አትርፈው ትኬቱን ይሸጡ ነበር።
ከዚህም አልፈው ሱቅ በደረቴ ጀምረው ሲጋራ፣ ማስቲካ እና የተለያዩ ምርቶችን በማዞር በልጅነታቸው የንግድን ጥቅም ተገነዘቡ። ይህ ሁሉ ሲሆን ግን አቶ ዳዊት ከትምህርታቸው ፈቀቅ አላሉም። በርካታ መጽሕፍትን ማንበብ የሚወዱት የንግድ ሰው ትምህርታቸውን በጥሩ ሁኔታ አልፈው የሁለተኛ ደረጃ የአስኳላን ለመከታተል በቀድሞው ልዑል መኮንን በአሁኑ አዲስ ከተማ ትምህርት ቤት ገቡ።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ሳለ ደግሞ ወደተሻለ የንግድ ሥራ የሚያሸጋግራቸው አጋጣሚ ተፈጠረ። በወቅቱ የእህል ነጋዴዎች አላዋጣ ቢላቸው ሱቃቸውን ለመሸጥ ያቅዳሉ። በዚህ ወቅት ለንግድ ድፍረት አለኝ የሚሉት አቶ ዳዊት ሱቆቹን ለመጠቅለል በማሰባቸው ወንድማቸው ሦስት ሺህ ብር አበደሯቸውና ሦስት አነስተኛ ሱቆችን ገዙ። ወዲያውም የተለያዩ የግብርና ምርቶችን በማስገባት በአካባቢው ታዋቂ የእህል መሸጫ ለማድረግ ጊዜ አልወሰደባቸውም።
ከባሌ፣ አርሲ፣ ጎጃም፣ ጎንደር እና ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚመጡ ምርቶችን በመቀበል መነገዱን ተያያዙት። በወቅቱ አቶ ዳዊት ሲያስታውሱ አንድ መኪና ሙሉ እህል ወደሱቃቸው ካስገቡ በኋላ ሸጠው እንደሚከፍሉ ተስማምተው ቃላቸውን ጠብቀው ገንዘቡን ለባለቤቶቹ ይመልሳሉ። ይህ የወቅቱ የንግድ አካሄድ ደግሞ አነስተኛ ካፒታል ላላቸው ሰዎች የሚያመች ነበርና በብድር ለጀመሩት አቶ ዳዊት አዋጭ ሆኖላቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።
ለአምስት ዓመታት በእህል ንግዱ እንደሠሩ ደግሞ ለተለያዩ ተቋማት አትክልቶችንና የተለያዩ ፍራፍሬዎችን ማቅረቡን ተያያዙት። ለመንግሥታዊ ተቋማት፣ ለዓለም አቀፍ እና የግል ተቋማት ጭምር የካፌ አገልግሎት የሚሆኑ ግብዓቶችን አቅርበዋል። በወቅቱ ደግሞ ንግዳቸው ከፍ እያለ ሲሄድ አትክልቶችን የሚያመላልሱበት ተሽከርካሪ ‹‹ጂፕ›› የተሰኘችውን መኪና በአምስት ሺህ ብር ገዙ። በሱቃቸው ሁለት ሠራተኞችን ቀጥረው እያሠሩ እራሳቸውም ደከመኝ ሳይሉ እየሠሩ ሰፋ ያለ ንግድ ለመጀመር ነበር እቅዳቸው። ይህን ሲያስቡ ግን ዘመኑ የሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም የተንሰራፋበት ነውና ብዙም ሊያንቀሳቅሳቸው አልቻለም።
ከንግዱ ጎን ደግሞ አቶ ዳዊት ከትምህርት ቤት ጀምሮ ጓደኛቸው የነበሩትን ሴት አግብተው፤ ትዳር መስርተው ኑሯቸውን ቀጥለዋል። ባለቤታቸው ደግሞ ለሥራ ያላቸው ፍቅር ጠንካራ የሚባል ነበርና ከእህል ንግዱ በተጨማሪ በሌሎች ዘርፎችም አቶ ዳዊት እንዲሰማሩ ጥረት ያደርጋሉ። ከዕለታት አንድ ቀን ወደአዕምሯቸው የመጣውን ሃሳብ ለባለቤታቸው አካፈሉ። ከ‹‹ማሞ ካቻ›› አካባቢ ያመጡትን አሮጌ ድንኳን ተጠቅመው የዲኮር እና የድግስ ዕቃዎች ኪራይ ንግድ ላይ መሰማራት እንዳለባቸው በመነጋገር ሥራውን ጀመሩት።
አቶ ዳዊት ከባለቤታቸው ጋር በመሆን አሮጌዋን ድንኳን በነጭ አቡጀዲ በማስዋብ እና ነጭ ወንበሮች በማዘጋጀት አነስተኛ አበባ እና ምንጣፎችን ጨምረው የሠርግ ዲኮር ሥራ ውስጥ ገቡ። በወቅቱ ማለትም ሥራውን በ1986 ዓ.ም ሲጀምሩት ሙያው ያልተለመደና በርካታ ዲኮሮችም ያልነበሩ ቢሆንም አቶ ዳዊት ግን ፈላጊ ለማግኘት ጊዜ አልወሰደባቸውም። በባለቤታቸው እገዛ አንድ ብለው የጀመሩት የዲኮር ሥራ በበርካታ ሠርጎች እና ዝግጅቶች ላይ ተፈላጊ እያደረጋቸው መጣ።
ቤተሰባቸውን ጭምር እያሳተፉ የተለያዩ ሠርጎችን ውብ እንዲሆኑ በአበባ እና የተለያዩ ጌጣጌጦች አሸብርቀው ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ምስጋናንም አተረፉ። ሥራው እየታወቀና እየተስፋፋ ሲመጣም ‹‹መድህን ዲኮር›› የተሰኘው የአቶ ዳዊት የማስዋብ ሥራ በአንድ ቀን ስድስት ሠርጎች ላይ እንዲሠሩ አደረጋቸው።
ሌሊትም ጭምር እስከ 10 ሰዓት ድረስ እየሠሩ ከአንዱ ሠርግ አዳራሽ ወደሌላው በመጓዝ ሁሉም እንደየፍላጎቱና ክፍያው እንዲስተናገድ በማድረግ እንደሚሠሩ አቶ ዳዊት ይናገራሉ። ከዲኮሩ ጎን ለጎን ደግሞ የተለያዩ የፕላስቲክ ወንበሮችን፣ የዲኮር ዕቃዎችን እና የተለያዩ ዕቃዎችን በመግዛት ለሚፈልጉት ማቅረብ ጀመሩ። በርካታ የቡና ቤት እና የሆቴል መቀመጫ ወንበሮችን በማቅረባቸውና በዲኮር ሥራቸው አማካኝነት ቢያንስ በአንድ ነገር እያንዳንዱ ቤት መድረሳቸውን ይገልጻሉ።
ከዲኮሩ ሥራ ጎን የተጀመረው የዕቃዎች ንግድ ከፍ እያለ ሲሄድ ደግሞ ከተለያዩ የውጭ ሀገራት ጭምር በማስመጣት ንግዱን ወደተሻለ ደረጃ አደረሱት። በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ ግን ከሁለት ሠራተኛ ተነስተው ከ100 በላይ ሠራተኞችን መቅጠር ችለው ነበር። ሠራተኞቻቸውንም በአበባ እና በተለያዩ የማስዋብ ፈጠራ ሥራዎች ላይ በማሰልጠን ጭምር ገቢ እንዲያገኙ በሩን ከፍተዋል።
ለ10 ዓመታት በዲኮር እና የድግስ ዕቃዎች ኪራይ ላይ እንደሠሩ ደግሞ ቃሊቲ አካባቢ ሰፊ መናፈሻ ያለው የሠርግ እና የተለያዩ ዝግጅቶች የሚያስተናግድ አዳራሽ ገንብተው ጨረሱ። ‹‹ስኖው ኋይት›› ብለው የሰየሙት የተንጣለለ አዳራሽ የልጃቸውን ሠርግ እና የእራሳቸውን ትዳር 34ኛ ዓመት ክብረ በዓል እንዲስተናገድበት በማድረግ አስመርቀውታል። ከዚያ በኋላ ደግሞ የበርካቶች የሠርግ አዳራሽ ምርጫ በመሆን እና የተለያዩ ስብሰባዎችን በማሰናዳት አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
ከአዳራሹ በተጨማሪ ደግሞ የምግብ ዝግጅት በማቅረብ ሙሉ አገልግሎትን መስጠት ችለዋል። በአዳራሹ ለመጠቀም የሚፈልግ ደንበኛ ምግብን ጨምሮ ለአንድ ሰው 600 ብር ያስከፍላሉ። ያለምግብ አዳራሹን ብቻ የሚከራይ ደግሞ በአንድ ሰው 150 ብር እያስከፈሉ ይሠራሉ። አዳራሹ 1000 ሰው ዘና አድርጎ ማስተናገድ የሚያስችል ሲሆን፤ መናፈሻው ደግሞ 3ሺ500 ሰው መያዝ ይችላል።
በዲኮር እና ዕቃ ኪራይ ሥራ ዘርፎች በተጨማሪ ደግሞ የምንጣፍ እና መጋረጃ ማምረቻ ክፍል በማቋቋም በርካታ ምርቶችን ወደገበያ በማቅረብ ዘርፈ ብዙ ሰው መሆናቸውን አቶ ዳዊት አሳይተዋል። መድህን የንግድ ሥራ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በሚል በተሰየመው ድርጅታቸው ስር የፒቪሲ ኮርኒስ አምርተው ይሸጣሉ። የኮርኒስ ምርቱንም በመላ ኢትዮጵያ በማቅረብ ተቀባይነትን አትርፈዋል።
በአሁኑ ወቅት 160 ሠራተኞችን ቀጥረው የሚያሠሩት አቶ ዳዊት፣ ‹‹ዋናው ትርፌ ዕቃዎቼ ላይ ያፈሰስኩት ሀብት ነው›› ይላሉ። በተለይ የብረት ወንበሮች፣ ሰፋፊ ድንኳኖች፣ በርካታ የዲኮር እና የምግብ ማቅረቢያ ዕቃዎች ዋነኛ ሀብቶቻቸው ናቸው። እነዚህን ሀብቶቻቸውን በማከራየት ቤተመንግሥትን ጨምሮ፣ የተለያዩ ትላልቅ ተቋማት እና የብሔር ብሔረሰብ በዓላት እና የመድረክ ዝግጅቶች ላይ ተሳትፈዋል።
ፈተናዎችን እያለፉ ሠርተው በማሠራት ትልቅ ደረጃ የደረሱት የመድህን ዲኮር ባለቤቱ አቶ ዳዊት በአምስት ተሽከርካሪዎች ገዝተው ሥራቸውን በየዕለቱ ያከውናሉ። ከአዳራሹ ውጪ አጠቃላይ ሀብታቸውም ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚሆን ይገመታል።
መድህን ዲኮር ከ10ሺ ብር ጀምሮ የሚመጡለትን የዲኮር አገልግሎት ይሰጣል። አቶ ዳዊትም በየቀኑም የሚያገኙትን ገቢ ለተጨማሪ የአገልግሎት መስጫ ዕቃዎች ላይ በማዋል ገንዘባቸውን ወደንብረት የመቀየር ልምድ አዳብረዋል። ይህ ሁሉ ሲሆን ግን አልጋ በአልጋ እንዳልነበረ አይዘነጉትም። በተለይ ከ500ሺ ብር በላይ የሚያወጡ ንብረቶቻቸውን ተከራይቶ የተሰወረ አንድ ግለሰብ ለማፈላለግ ብዙ እንደደከሙ አይረሱትም።
ንብረቶቻቸው እንደጠፉባቸው ለፖሊስ ካሳወቁ በኋላ ደግሞ ጨርቆስ አካባቢ በመገኘታቸው ከህግ አካላት ጋር በመሆን ማስመለስ እንደቻሉ ነው የሚናገሩት። ሥራው ትዕግስት እና ክትትልን የሚጠይቅ በመሆኑ ተከራይቶ የወጣ ዕቃ በአግባቡ ስለመመለሱ በማረጋገጥ ከተበላሸም በውል መሰረት እያስከፈሉ እንደሚሠሩ ያስረዳሉ።
ለ300 ተማሪዎች የሚሆን የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ እና በቡታጅራ የሚገኙ የልማት ሥራዎችን በመደገፍ የሚያወቁት አቶ ዳዊት፤ ‹‹ብዙሃኑ ሠርቶ የሚኖርበትን ንግዳቸውን ማስፋፋት ነው አላማዬ ›› ይላሉ። ከደርሶ መልስ እና ሱቅ በደረቴ የተነሳው የንግድ ህይወታቸው ለሚሊየነርነት ቢያበቃቸውም ሠርቶ ማሠራትን ዓላማ አድርገው በየቀኑ የሠራተኞቻቸውን ቁጥር በመጨመር ላይ ናቸው።
ማንኛውም ሰው በመጠነኛ ትርፍ እና ሐቀኝነት ላይ ከተመሰረተ እራሱንም ለውጦ ሃገሩንም መጥቀም ይችላል የሚል እምነት አላቸው፡፡ በተለይ ወጣቱ ሠርቶ የመለወጥን ልምድ በማዳበር የሚያገኛትን ገንዘብ ተጨማሪ ሀብት እንድታመጣለት በሚችለው የሙያ ዘርፍ መሰማራት ይችላል የሚለው ደግ ምክራቸው ነው።
አዲስ ዘመን ጥቅምት29/2012
ጌትነት ተስፋማርያም