የአገሪቱን ሁኔታ ያበለሻሸው የማህበራዊ ሚዲያ አክቲቪስት ነው። እርግጥ ነው ባለሥልጣናቱ አላበለሻሹም ማለት አይደለም። ዳሩ ግን ባለሥልጣናቱም እየተመሩ ያሉት በአክቲቪስት ነውና የአክቲቪስቶች ነገር እንደ ቀላል የሚታይ አይደለም።
ከአክቲቪስቶች እንቅስቃሴ ውስጥ ሁሌም የሚገርመኝ ‹‹የእገሌ ደጋፊ እና የእገሌ ተቃዋሚ›› የሚባለው ነገር ነው። ይሄ ማለት የሚነዱት በሃሳብ ሳይሆን በቲፎዞ ነው ማለት ነው። የሃሳብ ሰው ቋሚ ጥላቻም ሆነ ቋሚ ድጋፍ አይኖረውም። ብዙ ጊዜ ግን እንዲህ ዓይነቱን ሰው አቋሙ የሚዋዥቅ ይሉታል። ሃሳብ ተከትሎ መደገፍና መቃወም የአቋም መዋዠቅ ሳይሆን ሃሳባዊነት ነው። ከአቋሙ ዋዠቀ ይሉኛል ተብሎ አንድ ነገር ላይ ብቻ ሙጭጭ ማለት ደግሞ ግትርነትና ኋላቀርነት ነው። ይሄ ማለት ግን አቋምን መቀያየር ማለትም አይደለም። ዞሮ ዞሮ የአቋም ሰው ማለት ሃሳብን ብቻ መሰረት አድርጎ የሚሄድ ነው።
ለምሳሌ ‹‹ለውጥ›› የሚባለውን ነገር እንውሰድ። የለውጡ ደጋፊ እና የለውጡ ተቃዋሚ የሚባሉ አሉ። ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሰዎች የሚጠዛጠዙት የአብይ ደጋፊ እና የአብይ ተቃዋሚ በሚል ነው። አንድ የአብይ ደጋፊ የተባለ ሰው ሳት ብሎት ከተቃወመ አለቀለት! የአብይ ተቃዋሚ የተባለም ሳት ብሎ የደገፈ ዕለት የስድብ ናዳ ሲወርድበት ይውላል። እንግዲህ በእነዚህ ሰዎች እሳቤ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የደገፈ ሰው ምንም ጥፋት ቢሠሩ መተቸት የለበትም ማለት ነው። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቃዋሚ የተባለ ሰው የቱንም ያህል አኩሪ ሥራ ይሥሩ መደገፍ የለበትም ማለት ነው። ይሄ ግትርነት ነው ኋላቀር ያደረገን።
ጎበዝ! የማህበራዊ ሚዲያን ነገር ንቆ ማለፍ አይቻልም። ምክንያቱም አገር እየተበጠበጠች ያለው በማህበራዊ ሚዲያ ነው። መደበኞቹ የመገናኛ ብዙኃን እኮ ምንጫቸው የማህበራዊ ሚዲያ ነው። ልብ ብላችሁ ከሆነ ቃለ መጠይቅ ሲያደርጉ እንኳን ‹‹በማህበራዊ ገጽህ ላይ እንዲህ ብለሃል›› የሚል ነው። ባለሥልጣን ሲያናግሩም ‹‹ሰሞኑን በማህበራዊ ገፆች እንዲህ እየተባለ ነውና…›› ተብሎ ነው የሚጀመር። እና ታዲያ ይሄን ያህል ተፅዕኖ ያለውን ማህበራዊ ሚዲያ ንቆ ማለፍ ይቻላል? በእርግጥ ለማህበራዊ ገፆች መጠናከር ከፍተኛውን ሚና የተጫወተው የመደበኞቹ ሚዲያዎች መዳከም ነው።
የፌስቡክ አክቲቪስቶች የእገሌ ደጋፊ እና የእገሌ ተቃዋሚ ተባብለው መድበው ጨርሰዋል። ተደጋፊዎቹና ተተችዎቹ ደግሞ ባለሥልጣናት ናቸው። ከዚህ አለፍ ሲልም፤ አርቲስቶች፣ የድሮ ነገሥታት እና በተለያየ ሁኔታ ታዋቂ የሆኑ ሰዎች ናቸው። ከራሳቸው ከአክቲቪስቶቹም ተደጋፊ እና ተተችዎች የሆኑ አሉ። በጣም ብዙ ተከታይና ታዋቂ የሆኑት የራሳቸው ቡድን አላቸው። እንግዲህ የአንዱ ቡድን ሌላውን መደገፍ የለበትም ማለት ነው።
ትናንት ያደንቅኩትን ሰው ዛሬ ካጠፋ እልም አድርጌ እተቸዋለሁ። ትናንት የተቸሁትን ሰው ከጥፋቱ ተመልሶ ጥሩ ሥራ ከሠራ ድብን አድርጌ ነው የማደንቀው! ምክንያቱም መጀመሪያውኑም ያደነቅኩት ወይም የተቸሁት በሠራው ሥራ እንጂ በተፈጥሯዊ ማንነቱ አልነበረም።
አሁን አሁን ግን እየሆነ ያለው ነገር በሥራው ሳይሆን በተሰጠው ምድብ ብቻ ነው። ለምሳሌ የሰሞኑን ጉዳይ ብናይ፤ ታማኝ በየነ በአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ የዶክተር አብይን ሥርዓት በመተቸቱ ታማኝን ሲወርፉት ነበር። ምክንያታቸው ደግሞ ዶክተር አብይ ወደ ሥልጣን በመጡ ሰሞን ከእግራቸው ሥር ወድቆ አመስግኖ ነበር፤ ለምን አቋሙን ይቀይራል የሚል ነው። ሲወርፉት የነበሩም የዶክተር አብይ ተቃዋሚዎች ነን የሚሉት ናቸው። ታማኝ በየነን ምሳሌ አነሳሁ እንጂ ብዙ የዚህ ዓይነት መካረሮች አሉ።
ዶክተር አብይ የአገሪቱ ከፍተኛው ባለሥልጣን ናቸውና ደጋፊ ወይም ተቃዋሚ ብቻ ይኖራቸዋል ማለት አይቻልም። ዳሩ ግን ችግሩ ለምን ተቃዋሚና ደጋፊ አጋጠማቸው ሳይሆን ሁሉም አንዴ በሄደበት ብቻ ይቀጥል መባሉ ነው። ይሄ ነገር እኮ ሃሳብ እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ወይም ዶግማ አይደለም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚያኮራ ሥራ ሲሠሩ ይደነቃሉ፤ በተቃራኒው ደግሞ ጥፋት ከሠሩ የማይተቹበት ምንም ምክንያት የለም።
በነገራችን ላይ እንዲህ የሚያደርገን እኮ የሃሳብ ጥንካሬ ስለሌለን ነው። አብሮን የሚነዳ ሰው እንጂ ከእኛ ሃሳብ ተቃራኒ የሆነ ሰው አንወድም። ልብ ብላችሁ ከሆነ ሰዎች ፌስቡክ ላይ ‹‹ብሎክ›› የሚደርጉት ከእነርሱ ሀሳብ ተቃራኒ የሆነ አስተያየት የሚሰጣቸውን ነው። እውቀት ብንፈልግ ኖሮ ግን የሚጠቅመን ከእኛ ሃሳብ ጋር የሚመሳሰለው ሳይሆን ተቃራኒው ነው። ከእኔ ተመሳሳይ ሃሳብ ብቻ የምጠበቅ ከሆነ እኮ ያው የራሴው ሃሳብ እንደማለት ነው።
ይሄ ልማዳችን ካልተቀረፈ ችግር ነው። በአገሪቱ ውስጥ የሚፈጠረው የመንግሥት ወይም የጥቂት ፖለቲከኞች ሳይሆን የሁላችንም ነው። የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ሁሉ ነው። ምኑንም ሳታረጋግጥ የለጠፍከው ዜና ራሱን የቻለ የጥፋት አካል ነው። ተጠቃሚው ደግሞ እንደተገለጸው በቡድን የተከፋፈለ ነው። የእገሌ ደጋፊ የእገሌ ተቃዋሚ በሚል ነው የሚቀባበሉት።
ቆይ ግን በዚህ አካሄዳችን የደጋፊዎች እና የተቃዋሚዎች ማህበር እያልን ልናቋቁም ይሆን? ይሄ ማለት እኮ ያኛው ሰው አያገባኝም እንደማለት ነው። ለምሳሌ እኔ የቴዲ አፍሮ ደጋፊ ከሆንኩ የሌላ አርቲስት ጉዳይ አያገባኝም ማለት ነው? የቴዲ አፍሮ ተቃዋሚ ከሆንኩም ስለቴዲ አያገባኝም ማለት ነው? ይሄ ማለት እኮ ቴዲ አፍሮ የሆነ በጎ አድራጎት ነገር ቢያደርግ ማመስገንና ማድነቅ የለብኝም ማለት ነው። ምክንያቱም ደጋፊዎቹ ይሰድቡኛል። የሆነ ጊዜ እንዲህ ብለህ ነበርና ዛሬ ተገለበጥክ ሊሉኝ ነው ማለት ነው። በዚህኛው ሥራው ላላመሰግነው ነው ማለት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የኖቤል ተሸላሚ የሆኑ ሰሞን አንድ ጋዜጣ ላይ ያነበብኩት ትዝ አለኝ። ቃል በቃል ባላስታውሰውም ሃሳቡን ልንገራችሁ። ፀሐፊው የጻፈው የዶክተር አብይን መሸለም ለተቃወሙ ሰዎች ነው። ምክንያታቸው ደግሞ አገሪቱ ውስጥ መፈናቀልና ብጥብጥ እያለ እንዴት የሰላም ኖቤል ተሸላሚ ይሆናል የሚል ነው። የፀሐፊው አስረጂ ሃሳብ እንዲህ ነበር።
አንድ ሚስቱን በተደጋጋሚ የሚደበድብ ሰውዬ ለሆነ በሽታ መዲሃኒት አገኘ እንበል። ይሄ ሰውዬ በኬሚስትሪ የኖቤል ተሸላሚ ይሆናል። ሰውዬው ሚስቱን በመደብደቡ ብዙ ሰው ያወግዘዋል፣ ይተቸዋል፤ በዚህ በኩል ተቀባይነት የለውም ማለት ነው። ዳሩ ግን የተሸለመው ሚስቱን ስለደበደበ ሳይሆን ባገኘው መዲሃኒት ነው።
ስንተችም ሆነ ስንደግፍ ሃሳባዊ እንሁን!
አዲስ ዘመን ጥቅምት29/2012
ዋለልኝ አየለ