ወይ ጉድ ዛሬ ደግሞ ስለምን ልታወጋን ነው? ብላችሁ የምትጠብቁኝ አንባቢያን ሆይ!… ዛሬ ይቅርታ መጠየቅ ስለማያስፈልጋቸው ጉዳዮች ነው የማወጋችሁ:: አዎ ሰውን ይቅርታ የማንጠይቅባቸው ነገሮች አሉን::
በቅድሚያ ይቅርታ ልጠይቅበት ወይ ልትጠይቁበት አይገባችሁም ብዬ የምለው ነገር እናንተ ላወቃችሁትም ሆነ ላላወቃችሁት ነገር የምታሳዩት ፍቅር ነው:: ለምሳሌ ያህል ፣ አንድን ሰው መውደድ ወይም ማፍቀርን ልክ አይደለም ብሎ የሚሞግተኝ ወይም የምትሞግተኝ ሰው ካለች ፣ መውደዴ ሳይሆን ልክ ያልሆነው ወድጃለሁ ብዬ የምወስደው ያልተፈቀደ ዕርምጃ ነው፤ ብዬ ነው የምመልስላቸው::
ያልተገባ መሆኑን እያወቅሁ ካደረግኩት ውዴታና ፍቅር ወይም የተለየ ዝንባሌ ውጪ የሚያስከልክል ነገር እንዳለ ሳላውቅ መውደዴ በፍፁም ጥፋት ሆኖ ሊያስጠይቀኝና እኔም ይቅርታ እንድጠይቅበት አልገደድም::
ምናልባት የወደዳችሁት ሰው በሌላ ሰው የተያዘ የፈለጋችሁት ንብረትም ያልተገባ ሊሆን ይችላል ፤ መፈለጋችሁን ወይም መውደዳችሁን መግለጣችሁ ብቻውን ጥፋት ሆኖ ሊያስጠይቃችሁ ግን አይችልም:: ስለዚህ ነው፤ ይቅርታ አትጠይቁበትም የምላችሁ::
ሰው ስለወደደ ወይም ስላፈቀረ ሊጠየቅበት የሚገባ ጥፋት የለበትምና ይቅርታ ሊጠይቅ አይገባም:: የይቅርታ ጥያቄው ከተወደደውና ከተፈቀረው ሰው እንኳን መምጣት አይችልም:: ሌላው ቀርቶ እንዴት ልትወደኝ ደፈርክ አንተ ማነህና እኔን ተመኘህ ተብሎ አይጠየቅም::
ይህንን በተመለከተ በዩኒቨርሲቲ ሳለን የደረሰበትን ክፉ ያጫወተኝ የግቢ ጓደኛዬ ነበረና ታሪኩን ላጫውታችሁ:: በጣም በጥበብ ሥራዎች ሁለገብ የነበረ ወጣት ነው:: ልጁ ልጂትን ይወዳትና ፤ ፍቅሩን ይገልጽላታል:: የተስማማች ስለመሰለውም ሻይ ቤት ሲያገኛት ሊቃለዳት ይሞክራል፤ አንተ “እረፍ” ትለዋለች:: አላረፈም ፤ እንዲያውም የመግደርደሪያ መንገዷ ስለመሰለው ካፌም አካባቢ ሲያገኛት ይሁን ወደላይብረሪ ስትሄድም አስቁሞ ያወራታል:: ይህንን መታገስ ያቃታት ልጅ “ቆይ አሳይሃለሁ፤” ትለዋለች::
ቁጣዋን ያዩ የአካባቢዋ ልጆችም መጥተው፣ “በቃ ተዋት” ይሉታል:: አልፈልግህምን ቃል በቃል ትንገረኝ እንጂ ለምን አማላጅ ትልካለች፤ ሲላቸው እርሷ የትልቅ ባለስልጣን ልጅ ከመሆኗ ሌላ እዚህ ዩኒቨርስቲ መጥታ በመማሯ ሁሉ እያዘነች ነውና ተዋት ፤ አሉት::
አጅሬ ደግሞ ወደድኳት እንጂ ምን አጠፋሁ፣ ብሎ በሌላ ቀን ከግቢ ውጪ ባገኛት ስፍራ ሃገሩንም ግቢውንም እንድትወጂው ላደርግልሽ ቃል እገባለሁና አትበሳጪብኝ ይላታል:: ቆይ ትንሽ ጠብቀኝ፤ ብላው ትሄድና ስትመለስ ፣ “በሬ በኩርኩም የሚገድሉ” የሚያህሉ ሁለት ግዙፍ ሰዎች ይዛ መጥታ “ይኼ ነው” ትላቸዋለች:: ያንን በካፌ ምግብ የደቀቀ ምስኪን ወጣት እያካለቡና እያዳፉ በአንድ ታርጋ አልባ ቶዮታ መኪና ላይ ጭነውት ይሄዳሉ:: ማታ ላይ ወደ ሦስት ሰዓት ገደማ አምሽቶ ሲመጣ ያባበጠው ፊቱን በጃኬቱ ጠቅልሎ ነበር የመጣው::
ታሟል ተብለን ልንጠይቀው ወደዶርሙ ስንሄድ፣ ፊቱን ወደግድግዳው አዙሮ ድምፁን አስልሎ ፣ “ መውደድ ወንጀል ነው ወይ?” “በወደድኩኝ መደብደብ አለብኝ ወይ?” እያለ ደጋግሞ ሲናገር አሳዘነኝ:: መውደድ ወይም ማፍቀር ሴቷን ልጅ ሆነ ወንዱን ልጅ ሊያስቀጣና ሊያስቆጣ አይገባም:: ይሁንናም አንዳንዶች ከፍቅራቸው ይልቅ ጥላቻቸውን የሚሳዩበት ጉልበት ኃያል ምክንያት አልባ ነው::
ነገሮች ከተቀዛቀዙ በኋላ አንተስ ምነው ልክህን አላውቅ አልክ፤ ሌሎች ልጆችም አስጠንቅቀውህ አልነበረ? ለምን ችክ አልክ? ስለው ፣ ፊቷን እኮ ብታየው ይህን መሰል ጭካኔ አርግዞ የሚመላለስ አይመስልም:: ቆንጆና ደስ የምትል ልጅ እኮ ናት ሲል ነው ፤ የመለሰልኝ:: ለማንኛውም ወንበዴ መሳይ ፊት ያለው ሁሉ ጨካኝ፣ ለስላሳና ቆንጆ ፊት ያለው ሰው ሁሉ ደግሞ ሩህሩህ የሚመስለን ሰዎች ካለን ተሳስተናል:: ከዚያ ይልቅ ደግሞ ፣ እርሱን ተደብዳቢውን ልጅ ይቅርታ ጠይቅ መባሉ ደግሞ ድርብ ጥፋት ነው::
እንዲያውም የዘንድሮዎቹ ጨካኝ ሰዎች መልከ ቀናና አሳሳቾች ናቸው:: ስለዚህ መጠንቀቁ አይከፋም:: ለማንኛውም ግን በመውደዱ የተቀጣው ልጅ ይቅርታ እንዲጠይቅ አልመክርም:: ጥፋቱ ማፍቀሩ ነዋ::
ሁለተኛው ይቅርታ የማትጠይቁበት ነገር ደግሞ፣ ህልማችሁን መከተላችሁን ነው:: ህልማችሁ የህይወት ግባችሁ ነው፤ ታዋቂ ፖለቲከኛና የህዝብ እንደራሴ መሆን፣ ሐኪም መሆንና ማገልገል፣ ታዋቂ መሐንዲስ የመሆን ህልም ፣ አውቅ ነጋዴ ለመሆን መሥራት ፣ የሠዓሊነት ህልምህን፣ የደራሲነት ክህሎትህን ማሳደግና ተነባቢነትን ማዳበር፣ አገልጋይ የመሆን ስጦታህን ማዳበር፣ ወዘተርፈ… ለማሳደግ ስትጥር ምቾት ያልተሰማቸው ጓደኞችህን ይቅርታ መጠየቅ የለብህም::
እኔ ደራሲ ለመሆን በማደረገው ጥረት ውስጥ የማጠናቸውን ገጸባህሪያት ፣ ታሪኮችና ትልሞች ፣ ግጭቶችና ጭብጦች የማገኘው ከምንኖርበት ህብረተሰብ ነውና ለዚህ ስታትር የኔን መሰል ታሪክ ተጽፎብኛል የሚል ሰው ተነስቶ ከቶውም መንገዴ ላይ ቢንጫጫ ይቅርታ ልጠይቀው አልገደድም ፤ አልጠይቀውምም::
ታዋቂው ጋዜጠኛና ደራሲ በዓሉ ግርማ የሚጽፋቸውን ባለታሪኮች ገጽ የሚያገኘው ካጠገቡ እንደነበረ የሚያውቀው ደራሲ ስብሐት መጻፍህ መልካም ነው፤ ”ትንሽ ግን ብትቦርሻቸው፣ ደግመህ ብትጽፋቸው መልካም ነው፤” ይል እንደነበረ ጽፏል:: የማይካደው እውነት ገጸባህሪያቱ ከቅርብ የህወት ገጽ መቀዳታቸው ሲሆን የስፍራ፣ የዘመን ፣ የስም ለውጥ ይደረግባቸዋል:: ልክ ስብሐት ገ/ እግዚአብሔርን እምአእላፍ ብሎ እንደተረከው ማለት ነው:: ሰባኪያንም የስብከታቸው ዋና መነሻ ወንጌሉ ይሁን እንጂ ማበልጸጊያዎቻቸው፣ የግል ገጠመኛቸው፣ የተለወጡ ባለታሪኮችና የህይወት ተመክሯቸውና ልዩ ልዩ ክስተቶች ሁሉ ናቸው ማለታችን ነው::
ወደዚህ የህይወት ህልማችሁ ስትጓዙ ታዲያ ከቶውንም በገጠማችሁ ሳንካ ምክንያት ሌላውን ሰው ይቅርታ መጠየቅ አይጠበቅባችሁም:: እንዲያው አንዳንድ ደራሲያን ከድርሰታቸው መግቢያ አስቀድሞ፣ አንባብያን ሆይ! ከትረካው ፍሰት ውስጥ ራሳችሁን ካገኛችሁ ከቶውም ማንንም አትውቀሱ፤ ህይወት እንደዚህ ናትና፤ በድንገትም የተጻፈው የኔን ታሪክም ነው ብላችሁ እንዳትወቅሱኝ አደራ ሲሉ ይማጸናሉ:: ደራሲው ፣እንዲህ ብሎ ይቅርታ መጠየቅም መጥቀስም ግን አይገባውም ::
ህልማችሁን ስትከተሉ ባጣችሁት ነገር እንደማትቆጩ ሁሉ በገጠማችሁ ነገርም ማንንም ይቅርታ መጠየቅ የለባችሁም::
ሦስተኛው ይቅርታ የማትጠይቁበት ነገር ደግሞ፣ አምቢና አያስፈልገኝም ባላችሁበት ጉዳይ ነው:: ሰውየው ወይ ሴትየዋ የጠየቋችሁን ሥራ እንድትሠሩ ወይም እንድትቀጠሩ ወይም እንድታገለግሉና እንድትጠቀሙ ሊሆን ይችላል:: በዚህም ጉዳይ አውጥተውና አውርደው እምቢ ወይም አይሆንም ብለው መልስ በሰጡበት ጉዳይ ሰውየውም ሆነ ሴትየዋን ይቅርታ መጠየቅ የለብዎትም:: “አዝናለሁ” ሥራውን አልፈልገውም ማለት ይችላሉ፤ እንጂ ስላልፈለግሁት ይቅርታ ብለው ማንንም መጠየቅ አይገባዎትም::
አራተኛውና አስገራሚ የሚመስለው ይቅርታ የማይጠይቁበት ጉዳይ ደግሞ ፣ ለሰው የሰጡትን ጊዜ አስበው ወይም ከሰው ጠይቀው በወሰዱት ጊዜ ከቶውንም ይቅርታ መጠየቅ አይገባዎትም:: ምክንያቱም ጊዜውን ለመውሰድ ቀድመው ጠይቀዋልና ምን በወጣዎት እንደገና ይቅርታ ይጠይቃሉ::
ሁልጊዜ ስለዚህ ነገር ሳስብ የሩሲያዊው ደራሲ፣ አንቷን ቼኾቭ ፣ “የመዝገብ ቤቱ ፀሐፊ አሳዛኝ አሟሟት” የሚለው ድርሰት ነው:: ደራሲው፣ የሰውየውን የይቅርታ አጠያየቅ በሚያስገርም ሥነ-ልቡናዊ ትንተና አስቀምጦታል:: ሰው አንዴ የጠየቀውን ይቅርታ ደጋግሞ ሲጠይቅም ተጠያቂው ሌላ ነገር ሊያስብም ይችላል::
በወቅቱ የትራንስፖርት ሚኒስትር የነበሩት ሰው ከዚህ ሰው ፊት ለፊት ተቀምጠው፣ ትያትር እየተመለከቱ ነው:: ድንገት ሲያስነጥሰው፣ እንጥሻው በሚኒስትሩ መላጣ ላይ እርጥበት ያርከፈክፋል:: ሰውየውም ወደኋላቸው ገልመጥ አድርገው ካዩ በኋላ በመሐረብ እንጥሻውን ጠርገው፣ ወደትእይንት ምልከታቸው ይዞራሉ:: ትዕይንቱ ካለቀ በኋላም የመዝገብ ቤቱ ፀሐፊ መውጫው ላይ ይጠብቃቸውና በትህትና ቅድም አስቤው አላነጠስኩምና ይቅርታ ይላቸዋል:: ይቅር ብዬሃለሁ ብለውት ወደመኪናቸው ይገባሉ::
ቤት እንደደረሰም ጉዳዩን ለሚስቱ ሲነግራት እና መኪና ውስጥ ዝም ብለው ገቡ እንዴ፣ ስትለው ሃሳባቸውን ባላውቅም ይቅር ብየሃለሁ ብለው ሄደዋል ሲላት ፤ በእንጀራህ ቀለድክ ማለት ነው ብላ ፤ ነገ በጠዋት ቢሮ ከመግባታቸው በፊት አግኝተህ ሚኒስትሩን ቀድመህ ይቅር በሉኝ በላቸው፣ ስትል ሚስቱ ታስጠነቅቀዋለች::
“ሴት የላከው…” እንዲሉ ሚስቱ የነገረችውን ሳይጠረጥር የተቀበለው ባልም ፣ በጠዋት ተነስቶ ሚስቲቱ እንዳለችው ለማድረግ ማልዶ ቢሮ ተራ ጠብቆ ገብቶ ገና ….ትናንት ትያትር ቤት … ሲል ..
ትያትር ቤት ምን ፣ አሉት::
እ እ…ትያትር ቤት ያነጠስኩት እና መላጣዎ ላይ የሆነው የሆነብዎት …ከቶውኑ አውቄ ሳይሆን…. ሲል (አቋርጠውት ) የት ክፍል ነው የምትሠራው ሲሉ ጠየቁት:: መዝገብ ቤት ፀሐፊ መሆኑን ሲነግራቸው፣ ሥራ የለህም ማለት ነው? በረባ ባልረባው ምክንያት ቢሮ ለቢሮ የምትዞረው ብለው፣ ቢሮህ እያለህ ደብዳው ይደርስሃል ፤ ለማንኛውም፣ አሁን ውጣ ሲሉት፣ እንደውም ጌታዬ አክብሬዎት እና ከሥራዬም አስበልጬዎት እንጂ….በፍጹም ሥራዬን አክባሪ ሰው ነኝ:: እና….የእኔንስ የሥራ ጊዜ በማባከን የምለቅህ ይመስልሃል ሲሉት እያዞረው ወጣ….ከዚያን ቀን በኋላ ወደሥራውም ወደ ኑሮውም አልተመለሰም:: ከመ/ቤቱ ጀርባ ባለ አንድ ዛፍ ላይ፣ ራሱን ሰቅሎ ተገኘ::
አብዝተን ነገርን ማብሰልሰል የሚያደርሰን ወዳልተፈለገ ድምዳሜ ነው:: ድርሰቱ ድርሰት ይሁን እንጂ የኑሯችን ክፋይ ሰው የመሆናችን ዓይነትነት ገጽታ ነው:: ይቅርታ በማያስጠይቅ መጠይቅ ልባችን ሲሞላ የተጠየቀው ሰው ራሱ ጠያቂው የሚመዝንበት ዓይን የተለየ ይሆናልና፣ አያስፈልግም::
አምስተኛው ይቅርታ የማንጠይቅበት ጉዳይ ደግሞ፣ ቅድሚያ ልትሰጡት በምትፈልጉበት ጉዳይ ላይ ማንንም ይቅርታ ልትጠይቁ አይገባም:: በህይወታችሁ ቅድሚያ ልትሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮች ምን ምን ናቸው?
ልጆችህ፣ ሥራህ ፣ ህልምህ፣ ድርሰትህ፣ አገልግሎትህ፣ ባለቤትህ፣ እምነትህ ፣ ርእዮትህ ወይስ ምንህ? የሚያዛልቁህን ጉዳዮች የምታውቀው አንተ ነህ ፤ አንቺ ነሽ:: እንዲህ በጥቅሉ እናንሳቸው እንጂ ሙያህ ፣ ንባብህ ፣ የምረቃ ዝግጅትህ ፣ ሠርግህ ፣ የልጅህ ምርቃት፣ የታገልክለት ጉዳይ ….ወዘተ ሊሆን ይችላል:: እናም እነዚህን የህይወት ቅድሚያዎችህን ስትሠራ ማንንም ይቅርታ ልትጠይቅ አይገባህም ::
በመጨረሻም ካንተ ያልመጣ፣ ምክንያቱን ያልተረዳኸው የተበላሸ ግንኙነት ሲያጋጥምህና ስለጉዳዩ ማብራሪያ ስትጠይቅ መልስ በተነፈገህ ጉዳይ ላይ ይቅርታ መጠየቅ ጥፋቱን ወዳንተ ማሸጋገር ብቻ አይደለም:: አጥፊው ከስህተቱ እንዳይማር እያደረግህ ነው:: አንዳንዶች “ልክ ባለማድረጌ ልክ ሆንኩ” ሲሉ የሚናገሩት በዚህ ጊዜ ነው:: ስለዚህ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ላንተ የሚገባህን ያህል ዕርምጃ ከተጓዝክ በኋላ ጉዳዩ ማጣፊያ ባጠረው ሁኔታ ላይ ሲወድቅ ለራሱ ለጉዳዩ ጊዜ መስጠት እንጂ ሌላው ባጠፋው ይቅርታ ስትጠይቅ የሰውን ስህተት በልክነት እያደመቅክ መሆኑን አትርሳ›::
ክፉ ባል የገጠማት ሚስት ክፉውን የምታስጨንቀው በይቅርታና በመለማመጥ አይደለም:: በመነጋገርና በማብራራት እንጂ ይቅርታውን ባበዛች ቁጥር ተዓማኒነቷ በዚያው ልክ እየቀነሰ ነው የሚመጣው:: ነገርን እንዳመጣጡ መያዝ እንዳካሄዱ ለማስኬድ ይረዳል ::
አንድ ነባር ሃገር በቀል ትረካ ላክልላችሁና እንጨርስ:: ሰውየው ክፉ የሚባልና ለቀደሙት ሚስቶቹ ርህራሔ የሌለውና የማይመች ባል በመሆን ይታወቃል:: ሁለት ሚስቶቹ በብስጭት የሞቱበት ነውና ለእርሱ ፀባይ ምቹ የምትሆን ሚስት ሽማግሌዎች ፣ ቢያፈላልጉም ልትገኝ አልቻለችም:: ይህንን የሰማች አንዲት ብርቱ ሴት ግን እኔ አገባዋለሁ፤ አለች ፤ አሉ::
ሚስት መገኘቷን የሰማው ሰው ተገርሞ እንግዲህ ሙች ብሏት እንጂ በጤናዋ አልመጣችም ፤ ማን መሆኔን አሳያታለሁ ሲል ዛተ:: የሃገር ሽማግሌዎች ግን ይህችን ሴት ካበሳጨህ ሌላ እንደማናገኝልህ አውቀህ አብረህ በሰላም ለመኖር ሞክር ፤ ዛቻህንም ተው፤ ሲሉ ይመክሩታል ::
እንደተጋቡ 20 ቀን ሳይሞላም “ይህንን በግ አርደሽ ፤ ምግብ አሰናድተሽ ፣ ስመጣም በጉ ሳሩን እየበላ አስረሽው ደጅ ላይ እንዲጠብቀኝ” ሲል ነግሯት (አዝዟት) ይወጣል:: “ እሺ፣ የኔ ጌታ ፈጥነህ ናልኝ እንጂ ሁሉም እንዳዘዝከው ሆኖ ይጠብቅሃል” አለችው::
አመሻሽ ላይ አጅሬ ሲመጣ ወጡ ተሠርቶ የምግቡ ሽታ ግፍልፍል ከደጅ አወደው:: እየገረመው ወደግቢው ሲገባ በጉ ታስሮ ሳር እየበላ ነው:: የቤቱን ዙሪያ ሲያስጠብቅ መዋሉን ያውቃል ፤ ፈተናውን እንዴት ልታልፍ እንደቻለች ፤ ሲጠይቃት ግን አንተን ላገባ ወስኜ ወደዚህ ቤት ስገባ ቤቱ የሚፈልገውን ለማድረግ አስቤበት ነው የገባሁትና ይሄ ትዕዛዝህ ለእኔ ቀላል ነበረ:: የበጉን ላት ቆረጥኩና ምግብህን አዘጋጀሁ፤ በጉም አልሞተም፤ ምግብህም አልቀረም አለችው፤ ይባላል::
በቅድሚያ አስቸጋሪውን መንገድና ሰው የመረጠችው ራሷ ናት ፣ ያለፈችበትንም መከራ ያለፈችው ራሷ ናት:: መንገዷን ለመክፈት አማራጩን የወሰነችውም ራሷ ናት:: ይህች ሴት ወደግቧ ለመሄድና ወደዓላማዋ ለመድረስ የወሰነችውን ውሳኔ የሰሙ ቢያወግዟትም ከዚህ የተሻለ መፍትሔ ሊሰጧት አይችሉም ነበርና ፤ በድርጊቷ ማንንም ይቅርታ መጠየቅ አይገባትም ::
ይህንንም ሁሉ ስል ግን የይቅርታን ዋጋ አንኳስሼ ፣ ያለውን ማህበራዊ ፋይዳ አሳንሼ እንዳልሆነ እንድትገነዘቡልኝ እወዳለሁ:: ይቅርታ ፣ ለቤተሰብ ህይወት መነሻ፣ የሃገር ችግር ጋሻ፣ የጥላቻ ማርከሻ፤ የክፉ ሃሳብ ማስታገሻ፣ የቃልኪዳን ማደሻ መሆኑን ቀደም ባሉት ንግግሮቼም አስረግጬ ገልጫለሁ:: ያለቦታውና ሁኔታው ይቅርታን መጠየቅም ሆነ መስጠት ፤ ለተጠያቂው ማሳሳቻ፣ ለጠያቂውም ማምታቻ እንዳይሆን ሰግቼ ነው:: ስትናገሩም አስባችሁ ስታዳምጡም አስተውላችሁ ይሁን :: ይቅርታ ያለቦታው ፣ ኑሮ ያለአድራሻው እንዲሁ ነው፤ አንድም ያስጠረጥራል ፤ አለዚያም ያስገምታል::
የምትናገሩትና የምታደርጉት በስፍራውና በጊዜው የሚሆንበት ሳምንት ይሁንላችሁ!!
አዲስ ዘመን ጥቅምት29/2012
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ