ማንነቱን የሚያውቁ ሁሉ ስለ አጉል ባህሪው ይመሰክራሉ። ሁሌም በእልህና ቁጣው ይታወቃል። ቶሎ መናደድና ትዕግስት ማጣት መለያው ነው። እሱ ነገሮችን በመነጋገር መፍታት፣በመግባባት አብሮ መኖር ይሉት ነገር ገብቶት አያውቅም። ይህን ከሚያደርግ ይልቅ ኃይልና ጉልበት ቢጠቀም ይቀለዋል። ደጋግሞ የሚፈጽማቸው የጭከኔ ተግባራት ደግሞ ብዘዎችን ዋጋ አስከፍሏል። ሳይቀደም ለመቅደም የሚያደርገው ውሳኔም የበርካቶችን ማንነት እንዳልነበር አድርጎ ታሪካቸውን ቀይሯል።
ሙስጠፋ ኑር ተወልዶ ባደገበት አካባቢ ልጅነቱን ከቤተሰቦቹ ጋር አሳልፏል። ዕድሜው ከፍ ሲል ደግሞ ራሱን ለማስተዳደር ያልሞከረው የለም። በሥራው አጋጣሚ የቀረባቸው ሁሉ ከእሱ ጋር በሰላም ለመቀጠል እንደተቸገሩ ቆይተዋል።
ሙስጠፋ ዘወትር ከብዙዎች ያለመግባባቱ ለተደጋጋሚ እስር ዳርጎታል። በተለያዩ የመግደል ሙከራዎች እየተከሰሰም ማረሚያ ቤቶችን ሲያዳርስ ቆይቷል። የእስር ጊዜውን ጨርሶ ከሌሎች ሲቀላቀል ግን የትናንቱን ችግር ለመርሳት ጊዜ አይፈጅበትም። ሁሌም ከጎኑ በሚሽጠው ጩቤ በርካቶችን አስፈራርቷል። ማንነቱን ሳይረዱ ጠብ የገጠሙት ደግሞ በስለቱ የመግደል ሙከራዎች ተፈጽሞባቸዋል።
ሙስጠፋ እንደማንኛውም የገጠር ልጅ በቀዬው ቦርቆ አድጓል። ከእኩዮቹ ጋር ከሜዳ ውሎም ከብቶችን አሰማርቶ በጎችን አግዷል። ከፍ እያለ ሲሄድ ግን ብላቴናው እረኛ ማንነቱ ይለወጥ ያዘ። በውስጡ ማደግ የጀመረው ክፉ ባህርይም እልህና ቁጣን እያላበሰ ከብዘዎች ያጋጨው ጀመር። ይሄኔ ላለመሸነፍ ጉልበትን መረጠ። በርካቶችን ጠልፎ መጣልም መለያው ሆነ። ብዙዎችን ማስፈራራት ባስ ሲልም በስለት ወግቶ መሰወር ልማዱ ሆነ።
ህዳር 1993 ዓ.ም
በዚህ ቀን ሙስጠፋ ሰላም ሲሰማው አልዋለም። ከቀናት በፊት ጠብ የገጠመውን ጎልማሳ እያስታወሰ በንዴት መጋም ጀምሯል። ዓይኖቹ ከወዲያ ወዲህ እየቃበዙ ነው። በዚህ ሰዓት ከሚፈልገው ሰው ሌላ የሚያስቀድመው አልተገኘም። ጥርሱን እያፋጨ እጁን በእጁ ሲደበድብ አንዳንዶች ሁኔታውን ተረድተው ለመራቅ ሞክረዋል። ማንነቱን የሚያውቁ ብዙዎችም ገና ሲያዩት የሚሆነውን ገምተዋል። ከእነዚህ መሀል የተወሰኑት ቀድሞ የፈጸማቸውን የጭካኔ ድርጊቶች እያስታወሱ በስጋት ተንሾካሽከዋል።
ሙስጠፋ ቀኑን ሙሉ በድብርት ውሎ በንዴት ብዛት እየቃበዘ ነው። ከማለዳው ጀምሮ ሲፈልገው የዋለውን ባለማግኘቱ የውሰጡ ትኩሳት ጨምሯል። ያሰበውን ሳይፈጽም ቀኑ መጋመሱ የተመቸው አይመስልም። ከጎኑ የሻጠውን ትልቅ የከብት ማረጃ ቢላዋ ደጋግሞ እየነካካ ዓይኖቹን ባሻገር ይልካል። ከሩቁ የሚያያቸውን ተጠግቶ እየለየና የለያቸውንም በይለፍ እያረጋገጠ በእልህ ይቁነጠነጣል። እስከአሁን የዓይኑ ርሀብ ባለመታገሱ ንዴት እየወረረው ነው።
ሙስጠፋ አንገቱን ዞር አድርጎ መለስ ከማለቱ ዓይኖቹ ከአንድ ስፍራ ተወርውረው የሚሻውን አሳዩት። ሙስጠፋ ያየውን ማመን አልቻለም። የተፈላጊውን ማንነት እንዳረጋጠ ግን መቀዝቀዝ የጀመረው ስሜቱ መጋል ጀመረ። ልቡ እየመታም ሰውነቱ በእልህ መንቀጥቀጥ ሲጀምር ከጎኑ የሻጠውን ቢላዋ መነካካት ያዘ።
ረጅሙን የከብቶች ማረጃ ቢላዋ ሲነካካ የተለመደው ማንነቱ ‹‹አይዞህ›› ሲል አጀገነው። አሁን ጊዜ ማጥፋት እንደሌለበት ወስኗል። ያሰበውን ካልፈጸመ ደግሞ ከራሱ እየተጣላ ከሌሎች ጋር ሰላም እንደማይኖረው ለራሱ ነግሮታል። ይህን እውነት ደጋግሞ ሲያስብ ውስጡ የዋለው ስሜት ይበልጥ እየገፋ ‹‹በል›› ሲል አበረታው።
ሙስጠፋ አሁን ልክ እንደ አዳኝ አውሬ መሆን ጀምሯል። በተጠንቅቅ የቆመው አካሉ በድንገት ለመወርወር እያኮበኮበ ነው። ሰውየውን ከመቅረቡ በፊት ዙሪያ ገባውን ደጋግሞ ቃኘ። እሱ የቆመበትንና ታዳኙ ያለበትን ስፍራ ገምቶም ወደፊት ተራመደ። ካለበት እየተጠጋ ወደሰውየው ሲቃረብ ወደኋው ተገላምጦ ለድርጊቱ ምቹነት የሚሻለውን አመቻቸ።
ይህ ሁሉ ሲሆን ሰውዬው ፈጽሞ አላየውም። ቀድሞ ካየውና መሸሸ ከጀመረ ነገር እንደሚበላሽ ገምቷል። ጉዳዩን ጠርጥሮ ሮጦ ካመለጠው ደግሞ ለራሱ ይቅርታ አያደርግም። ይህ እንዳይሆን ስጋት ገባው። ጥንቃቄውን አክሎም ወደሰውዬው ተጠጋ። እየቀረበው አካባቢውን በትኩረት ቃኘ። ይህኔ ቂም ቋጥሮ የቆየው ልቡ በትኩስ ደም ተሞልቶ ዘና ሲል ተሰማው።
አሁን ማንም ቢያየው ግድ አይሰጠውም። ያሰበውን ማድረግ እንዳለበት ከፈጣን ውሳኔ ደርሷል። በእጁ የገባው ከማምለጡ በፊት ሲነካካው የቆየውን ቢላዋ ከጎኑ መዠረጠ። አንዴ ብቻ ተገላምጦም ስል ቢላዋውን በሰውዬው ሽንጥ ላይ አሳረፈው።
ሰውዬው በከባድ ስቃይ እያቃተተ ከመሬት ሲዘረር ሙስጠፋ በአካሉ የተሻጠውን ቢላዋ ነቅሎ ዳግም በሌላኛው ጎኑ ላይ ሰካው። ስፍራው በደም ርሶ ሰዎች መድረስ ሲጀምሩ ሙስጠፋ የእጁን ቢላዋ በቅርበት ወርውሮ ‹‹ እግሬ አውጪኝ›› ሲል ተፈተለከ።
አሯሯጡ በተለየ ፍጥነት ነበር። እንዳሰበው ግን ርቆ መሄድ አልቻለም። በስፍራው በነበሩና ድርጊቱን ባስተዋሉ ሰዎች ጥረት በቁጥጥር ስር ዋለ። ወዲያውም ለህግ ተላልፎ ተሰጠ። ሙስጠፋ በቂም በቀል መነሾ የፈጸመው አሰቃቂ ድርጊት ብዙዎችን ሲያሳዝንና ሲያስገርም ከረመ።
ቆይታ በማረሚያ ቤት
ሙስጠፋ በአንድ ግለሰብ ላይ በፈጸመው አሰቃቂ ወንጀል ተከሶ በማረሚያ ቤት ውሎ ማደር ከጀመረ ወራት ተቆጥረዋል። ጉዳዩ በህግ ውሳኔ አግኝቶ ቅጣት አስኪሰጠውም በጊዜ ቀጠሮ ሊቆይ ግድ ብሎታል። ማረሚያ ቤትን ከዚህ ቀድሞ ያውቀዋል። በድብደባና በመግደል ሙከራዎች ተከሶ ጊዜያትን ቆጥሮበታል።
በእስር ላይ ሳለ ከቆይታው በኋላ ሰላማዊ ሰው እንደሚሆን ለራሱ ቃል መግባትን ለምዷል። ጊዜውን ጨርሶ ኑሮን መቀጠል ሲጀምር ግን ቃሉን ሽሮ ዳግም በሌላ ወንጀል ውስጥ ይገኛል። ሙስጠፋ የአሁኑ ድርጊት ከሌሎቹ ጊዜያት እንደሚለይ አልጠፋውም። የፈጸመው ወንጀል የዓመታትን እስር እንደሚያስከፍለው ጠንቅቆ ያውቃል።
በዚህ ስፍራ እሱን መሰሎችን ተዋውቋል። የብዙዎችን የወንጀል ድርጊት ሰምቶም የራሱን ጭምር አካፍሏል። በርካቶቹ በጊዜ ቀጠሮ ላይ በመሆናቸው ነገን ከእስር ለመውጣት ‹‹ይበጀናል›› የሚሉትን ይመክራሉ። የመከላከያ ሃሳባቸውን እያውጣጡም ከልምዳቸው ይቆነጥራሉ። እያንዳንዳቸው ከፍርድቤት ሲመለሱ በቀን ውሏቸው ላይ መነጋገርን ለምደዋል። ብዙዎቹ የራሳቸውን የእስር ውሳኔ ቆርጠው የሌሎችን ጭምር ይተነብያሉ።
ከእነዚህ መሀል ጥቂቶቹ ደግሞ የነገን ከእስር መፈታት በተስፋ እየጠበቁ ራሳቸውን ያበረታሉ። የሙስጠፋ ሃሳብ ግን ከእነዚህ ሁሉ ይለያል። የእርሱ ውስጠት ሁሌም ሹክ የሚለው ክፉ የሚባሉ ሃሳቦችን ብቻ ነው። አንድ ቀን ደግሞ የዘወትር ዕቅዱ ዳር ይዞለት ከነበረበት የዝዋይ ማረሚያ ቤት ለማምለጥ ቻለ።
ሙስጠፋ ለጥቂት ጊዜያት ማንነቱን ደብቆ ቆየ። ራሱን አረጋግቶም በቀን በለሊት እያሳበረ ናዝሬት ገብቶ መኖር ጀመረ። ሳምንታት በወራት እየተተኩ ጊዜው መርዘም ሲጀምር ከሌሎች ተቀላቅሎ በቀን ሥራዎች ውሎ ተሰማራ። ሁሌም ሰላም የሌለው ሙስጠፋ ኮሽታ እያስደነበረው አተኩሮ ያየውን ሁሉ መጠርጠሩ አልቀረም። ያም ሆኖ ግን በዚህ ስሜቱ እምብዛም አልቀጠለም። ነገሮችን እያቀለለ የሆነውን ሁሉ ለመርሳት ሞከረ። እንዲህ ማድረጉ የተሳካለት ሲመስለው ደግሞ ራሱን ነፃ አድርጎ እንደሌሎች መሆኑን ገፋበት።
ሙስጠፋ የናዝሬት ኑሮው እየተመቸው ነው። በድንገት ያወቃት ሴትም ለትዳር አጋርነት መርጣው አብሯት መኖር ጀምሯል። በጎጆ ሲጠቃለል ደግሞ ይበልጥ መረጋጋት ያዘ። ባለትዳር መባሉ ለሠራው ወንጀል ከለላ ሆኖትም ያለስጋት ውሎ ማደር ጀመረ። ይህ ሁሉ ሲሆን የፖሊስ ማደኛ ወጥቶበት በህግ እንደሚፈለግ ጠንቅቆ ያውቃል። ምስጢሩን ሌሎች እንዳያውቁበትና አሳልፈው እንዳይሰጡትም ጥርጣሬው የበዛ መሆ ን ጀምሯል።
ሙስጠፋ ናዝሬት ከተማ ገብቶ የመሰረተው ትዳር በፍቅር መዝለቅ አልቻለም። መከለያ የደረገው ጎጆ በጠብና ንዝንዝ ታጅቦ ማዝመም ሲጀምር በእሱና በሚስቱ መሀከል የነበረው ፍቅር በጥላቻ ተተካ። ሰላም የራቀው ጎጆ መቀዛቀዝ ሲጀምር የሙስጠፋ የበቀል ስሜት አገርሽቶ ክፋትን መዝራት ቀጠለ።
ከሁሉም ግን አንድቀን ሙስጠፋ የፈጸመው ድርጊት የጅምሩ ትዳር ማጠናቀቂያ ሊሆን ግድ አለው። በእሱና በባለቤቱ መካከል የቆየውን አለመግባባት በኃይል ለመፍታት ያደረገው ሙከራ የህይወት ዋጋ አስከፈለ። ሙስጠፋ ክፉ ደጉን አብራው ያሳለፈች ሚስቱን በጭካኔ ገድሎ እንደለመደው ከስፍራው ተሰወረ።
ከናዝሬት ከተማ በፍጥነት ወጥቶ አዲስ አበባ መኖር የጀመረው ሰው ሁሉን ረስቶ ከሌሎች ለመግባባት ጊዜ አልፈጀበትም። ሆደ ሰፊዋ ከተማ ወንጀል ፈጻሚውን ሸሽጋ ለመያዝ ተባባሪ ብትሆነው ራሱን ለእይታ ሳያጋልጥ ቀናትን ቆጠረ። በዕርምጃው ሁሉ እየተጠነቀቀም ከአካባቢው ተላመደ።
ጥቂት ቆይቶ የአገሩን ልጅ ዘይኑን አገኘው። ከእሱ ተግባብቶና ተለማምጦ ሊኖር ወሰነ። ዘይኑ ባለትዳርና የልጆች አባት ነው። ሙስጠፋ አብሮ የመኖር ፍላጎቱን ሲነግረው ቤት ይጠበኛል ሲል ሊገፋው አልፈለገም። በእንግድነቱ አክብሮ ተቀበለው። ከቤተሰቡ ተቀላቅሎ እንዲኖርም ፈቀደለት።
ሙስጠፋ የሆዱን በሆዱ አድርጎ በሰላም ለመኖር አዲስ ህይወት ጀመረ። ያፈሰሰው የሁለት ሰዎች ደም እየጮህ ሰላም ቢነሳውም ጆሮ መስጠት አልፈለገም። ያጠፋቸውን ነፍሶች ዳግም ላለማሰብ ወስኖ በአዲስ ኑሮ መንገዱን ቀጠለ።
አካባቢውን አጥንቶ የጀመረው የጫኝና አውራጅ ሥራ በቂ ገንዘብ ማስገኘት ሲጀምር በቀን ውሎው የሚያገኘውን እያጠራቀመ ለዘይኑ ጭምር ተረፈ። አባወራው እጁ ባጠረና ገንዘብ ባስፈለገው ጊዜ ከእሱ መበደርን ለምዷል። ባገኘ ጊዜ ብድሩን እየመለሰም በቸገረው ቀን ዳግም ይጠይቃል።
አንድቀን ግን ዘይኑ ከሌሎች ቀናት በዛ የሚል ብድር ጠየቀው። ሙስጠፋ ጥቂት ካንገራገረ በኋላ የጠየቀውን አስር ሺ ብር ቆጥሮ በፈለገው ቀን እንዲመልስ አሳሰበው። ዘይኑ ገንዘቡን ተቀብሎ በተባለው ቀን እንደሚመልስ ቃሉን ሰጠ።
ቀናቶች አልፈው ወራቶች መተካት ሲጀምሩ ሙስጠፋ ያበደረውን ገንዘብ አስታውሶ እንዲመልስለት ጠየቀ። ዘይኑ በተባለው ቀን ባለመመለሱ ሐፍረት እየተሰማው ጥቂት ቀናት ብቻ እንዲሰጠው ተማጸነ። የተባለው ቀን ሲደርሰ ሙስጠፋ አሁንም ዳግመኛ የገንዘቡን ጉዳይ አነሳበት።
ዘይኑ በተባለው ቀን ብድሩን መመለስ አልቻለም። በሁለቱ መሀል እያደር ጭቅጭ መጀመሩ ደግሞ አርፎ የተኛ የሚመስለውን የሙስጠፋን ቂመኛ ልብ ይቀሰቅሰው ጀምሯል። አሁን አበዳሪና ተበዳሪ የጎሪጥ መተያየት ጀምረዋል። የጓደኛውን ድርጊት ከንቀት የቆጠረው ሙስጠፋ ግን ትዕግስቱ መሟጠጡን በምልክት ማሳየት ከጀመረ ቆይቷል።
ሀምሌ 23 ቀን 2007 ዓ.ም ምሽት
ሙስጠፋ ባበደረው ገንዘብ ምክንያት ከዘይኑ ጋር ተቀያይሟል። ባገኘው ቁጥር ስለብድሩ እያነሳ ያስጠነቅቀዋል፤ከእሱ በኩል የሚያየው ግዴለሽነት ግን ቁጣን አላብሶ ንዴቱን ይቀሰቅስበት ጀምሯል። በዚህ ቀን ምሽት እንደለመደው ወደ አንድ መጠጥ ቤት አመራ። ብስጭቱን በብርሌ ጠጅ ሊያወራርድ እያሰበ ነው።
ወደውስጥ ዘልቆ የፈለገውን እንዳዘዘ ዓይኖቹ ከወዲያ ወዲህ ቃብዘው ከጓደኛው ዘንድ አደረሱት። እሱን እንዳየው ከተቀመጠበት ተነስቶ ገንዘቡን እንዲመልስለት ጠየቀው። ዘይኑ በተለመደው ስሜት ሆኖ የሰሞኑን ዓይነት ምላሽ ሰጠው። ሙስጠፋ በንዴት እንደጋመ ደጋግሞ ጠየቀው። ጭቅጭቁ ያመጣው ለውጥ አልነበረም።
ሙስጠፋ በእጁ የያዘውን በቁሙ ጨልጦ ለሽንት ወደ ጓሮ አመራ። ካሰበው ከመድረሱ በፊት ግን ፈጣን ዓይኖቹ ከቤቱ ደረጃ ላይ ከተቀመጠ አንድ የሽንኩርት ቢላዋ ዘንድ አደረሱት፤ሙስጠፋ ሳያመነታ ቢላዋውን በጎኑ ሸሽጎ ወደ ጠጅ ቤቱ ተመለሰ። እግሩ እንደደረሰም ዘይኑን ተመለከተው። ለአፍታ ማወላወል አልፈለገም። ቢላዋውን አውጥቶ ሆዱ ላይ ደጋግሞ ወጋው። በዚህ ሳይመለስ የሰካውን እየነቀለ አንጀቱ ድረስ ዘለቀ። እምብርቱን ሆዱንና ጎኑን አዳርሶ ሲበቃው ፊቱ በእልህ ሲግም ታየ። ማንም ከድርጊቱ ያስቆመው አልነበረም።
ሁኔታውን ያስተዋሉ ሮጠው ሲደርሱ ዘይኑ ክፉኛ ተጎድቶ እያቃተተ ነበር። ትንፋሹ መኖሩን ሲረዱ ሆዱን በጨርቅ አስረው አንጀቱን ሊታደጉት ሞከሩ። ሁሉም ከንቱ ልፋት ቢሆንባቸው ሙስጠፋን ለመያዝ ተጣደፉ። አላመለጣቸውም። እምብዛም ሳይርቅ ለህግ አሳልፈው መስጠት ቻሉ።
የፖሊስ ምርመራ
ፖሊስ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ልዩ ቦታው ሃምሳ ስምንት በተባለው ስፍራ ደርሶ የወንጀሉን ድርገት አጣራ። የዓይን እማኞችና ሙስጠፋን ጠይቆም እውነታውን ተረዳ። የመዝገብ ቁጥር 112/08 ላይ በቂ መረጃዎችን ከማስረጃዎች እያጣቀሰ ማስፈር የጀመረው ምክትል ኢ/ር ታሪኩ ኢርኮ ከተጠርጣሪው የቀደመ ታሪክ በነፍስ በማጥፋት ወንጀሎች ተከሶ ከማረሚያ ቤት ማምለጡንና በህግ ሲፈለግ መቆየቱን አረጋገጠ። ፖሊስ ምርመራውን እንዳጠናቀቀ በዓቃቤ ህግ ክስ እንዲመሰረትበት መዝገቡን አሳልፎ ሰጠ።
አዲስ ዘመን ጥቅምት29/2012
መልካምስራ አፈወርቅ