በእግር ኳስ ስፖርት ሁለት ተቀናቃኝ ክለቦች የሚገናኙበት ግጥሚያ ደርቢ በሚል አጠቃላይ መጠሪያ ይታወቃል። ደርቢዎች በስፖርቱ ታሪክ እና ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳላቸው አሁን ላይ እግር ኳሳቸው የተመነደገ አገራትን መመልከት በቂ ነው። ደርቢዎቹ በተለይም የአንድ ከተማ ክለቦች ከሆኑ ፉክክሩ ከመጋጋል ባለፈ የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ትኩረት በመሆን በየውድድር ዘመኑ እጅግ ተጠባቂ መርሃግብር እስከመሆን ይደርሳል።
የደርቢ ጨዋታዎች ስቴድየሞችን በመሙላት፤ ከፍተኛ የትኬት ሽያጭ በማስመዝገብ፤ በማልያ ሽያጭ፤ በቴሌቭዥን የስርጭት መብት በሚያስገኙት ከፍተኛ ገቢ እና ትርፋማነታቸው ይታወቃሉ፡፡ በየደርቢ ጨዋታዎቹ የሚመዘገቡ ውጤቶች በየክለቦቹ በሚገኙ አሰልጣኞች፤ ተጨዋቾች፤ አመራሮች እና ቀንደኛ ደጋፊዎች እጣ ፋንታ ወሳኝነትም ሲኖራቸው መመልከት የተለመደ ጉዳይ ነው።
አንዳንድ ደርቢዎች ከጨዋታ ተቀናቃኝነትና ከአንድ ከተማ ክለብነት ባሻገር በፖለቲካዊ፤ በኢኮኖሚያዊ እና ሌሎች የውዝግብ አጀንዳዎች የሚታመሱ፤ ሌሎች ደግሞ በየጊዜው በከፍተኛ ውጥረት የሚካሄዱ እና ከፍተኛ የደጋፊዎች አመፅ የሚነሳባቸው ሆነው ይታያሉ።
በዘመናዊ የእግር ኳስ ታሪክ ግን ሌሎች የተለያዩ የደርቢ አይነቶች ተፈጥረዋል፡፡ ሁለት ተቀናቃኝ ከተሞች የሚፋጠጡባቸው፤ በየጊዜው በሚመዘገቡ የውጤት ታሪኮች ተፎካካሪዎች የተፈጠሩባቸው፤ በውጤት የበላይነት የሚያስተናንቁ ብዙ ዓይነት ደርቢዎች በመላው ዓለም ይካሄዳሉ፡፡
በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከሚፋለሙ ክለቦች መካከል ከፍተኛ ደጋፊ ያላቸውና በከፍተኛ የፉክክር ስሜት ታጅቦ የሚካሄደው ጨዋታ የኢትዮጵያ ቡና እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ነው። ሁለቱ ክለቦች ያላቸው የውጤት ተቀናቃኝነት ለውድድር የሚቀርብ ባይሆንም ባላቸው የደጋፊ ብዛት እና የቡድን ስብስብ ጥልቀት የተነሳ ጨዋታው ከፍተኛ ትኩረት የሚደረግበት የደርቢ ጨዋታ ነው። ጨዋታውንም በርካታ ደጋፊ በስቴድየም ተገኝቶ የሚከታተለው ሲሆን የመግቢያ ካርድ በማጣት በካምቦሎጆ ዙሪያ ገባ የሚኮለኮለው ደጋፊ ብዛትም የትየለሌ ነው።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ትልቁ ደርቢ የሚባለው የሁለቱ ክለቦች ፍልሚያ ሸገር ደርቢ በሚል ስያሜው ይበልጥ የሚታወቅ ሆኗል፡፡ ከአርባ ጊዜ ያላነሰ የደርቢ ጨዋታ ያደረጉት ሁለቱ ክለቦች በርካታ ጊዜ በማሸነፍ የፈረሰኞቹ ውጤት ጎልቶ የሚጠቀስ ቢሆንም ቡናማዎቹ በተለያዩ አጋጣሚዎች ያልተጠበቁ ድሎችን ሲያጣጥሙ መመልከት የተለመደ ነው።
ፈረሰኞቹ 1950 እኤአ ጀምሮ 28 ጊዜ የሊግ ቻምፒዮን፤ በጥሎ ማለፍ ከ1952 እኤአ ጀምሮ 10 ጊዜ አሸናፊ እንዲሁም በሱፐር ካፕ ከ1994 እኤአ ጀምሮ ስምንት ጊዜ በማሸነፍ በድምሩ46 ዋንጫዎችን ሰብስቧል። በአፍሪካ የክለቦች ውድድር አስቀድሞ ካፕ ኦፍ ቻምፒዮን ክለብስ በሚባለው ውድድር ለ10 ጊዜያት፤ በአፍሪካ ክለቦች ቻምፒዮንስ ሊግ 9 ጊዜያት፤ በአፍሪካ ክለቦች ኮንፌደሬሽን ካፕ 1 ጊዜ፤ በካፍ ካፕ 1 ጊዜ እንዲሁም በካፍ ካፕዊነርስ ካፕ 3 ጊዜ ለመሳተፍ ችሏል፡፡
ኢትዮጵያ ቡና ከተመሰረተ ከ40ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ሲሆን የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን ለሁለት ጊዜያት፤ የጥሎ ማለፍ ዋንጫን ለ5 ጊዜያት፤ የሱፐር ካፕ ለ4 ጊዜያት እንዲሁም የራን አዌይ ሊግን ለ1 ጊዜ በማሸነፍ 12 ዋንጫዎችን ሰብስቧል፡፡ በአፍሪካ የክለቦች ውድድር ደግሞ በአፍሪካ ክለቦች ቻምፒዮንስ ሊግ 2 ጊዜያት፤ በአፍሪካ ክለቦች ኮንፌደሬሽን ካፕ 1 ጊዜ፤ በካፍ ካፕ 2 ጊዜ እንዲሁም በካፍ ካፕዊነርስ ካፕ 3 ጊዜ ለመሳተፍ ችሏል፡፡
ይህን ታሪክ ይዘው ነገ በአዲስ አባባ ስቴድየም የሚገናኙት ሁለቱ ክለቦች በዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ባለፈው ረቡዕና ሐሙስ ተስተካካይ ጨዋታዎችን አድርገው ተጋጣሚዎቻቸውን በረቱበት ማግስት ነው። ማክሰኞ እለት ቡናማዎቹ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲን አስተናግደው አንድ ለዜሮ በሆነ ውጤት በመርታት በፕሪሚየር ሊጉ ደረጃቸውን አሻሽለው በሰባት ጨዋታ ከሐዋሳ ከተማ ጋር እኩል አስራ አራት ነጥብ በመያዝ በግብ ተበልጠው ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። የዛሬው የደርቢ ጨዋታም ቡናማዎቹ ፕሪመየር ሊጉን ለምምራት በሚያደርጉት ጉዞ ወሳኝ ይሆናል።
የፕሪሚየር ሊጉ የአስራ አራት ጊዜ ቻምፒዮኖች ፈረሰኞቹ ከሦስተኛው ሳምንት የተላለፈው ተስተካካይ ጨዋታቸውን ሐሙስ እለት ከቻምፒዮኑ ጅማ አባ ጅፋር ጋር አድርገው ከሦስት ጨዋታ በኋላ ወደ ድል የተመለሱበትን የሁለት ለምንም ውጤት አስመዝግበዋል። አጀማመራቸው እንደ ወትሮው በስኬት ያልታጀበው ፈረሰኞቹ ነገ በአሸናፊነት መንፈስ የደርቢውን ጨዋታ ማድረጋቸው ጨዋታውን ተጠባቂ አድርጎታል። በስድስት ጨዋታዎች ስምንት ነጥብ ብቻ በመሰበሰብ መጥፎ አጀማመር ያሳዩት ፈረሰኞቹ ካሉበት ሰባተኛ ደረጃ ከፍ ብለው በቀሪዎቹ መርሐግብሮች የለመዱትን የዋንጫ ፉክክር ለማድረግ ከነገው ጨዋታ ሙሉ ሦስት ነጥብ ይፈልጋሉ።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 20/2011
ቦጋለ አበበ