ያጠናቀቅነው 2018 የፈረንጆች ዓመት በአትሌቲክሱ ዓለም በርካታ የዓለም ክብረወሰኖች የተሰበሩበት ነበር። ከአጭር ርቀት አንስቶ እስከ መካከለኛና ረጅም ርቀት እንዲሁም ማራቶን ውድድር በርካታ የዓለም ክብረወሰኖች የተሰበሩ ሲሆን በሜዳ ተግባራት ውድድሮችም የተለያዩ ክብረወሰኖች ተመዝግበዋል። በአጠቃላይ በውድድር ዓመቱ ከተሰበሩ የዓለም ክብረወሰኖች መካከል የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ለሃያ አንዱ እውቅና ሰጥቷቸዋል።
ያለፈው የውድድር ዓመት በአስገራሚ ሁኔታ ከሌላው ጊዜ በተለየ በአማካኝ በየወሩ አንድ የዓለም ክብረወሰን የተመዘገበበት ሲሆን የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር በውድድር ዓመቱ ባካሄዳቸው አምስት ታላላቅ ውድድሮች በሦስቱ የዓለም ክብረወሰኖች ተመዝግበዋል። ቀሪዎቹ ክብረወሰኖች ደግሞ ትልቅም ትንሽም በሚባሉ ውድድሮች የተመዘገቡ ናቸው። እነዚህ ክብረወሰኖች መቼ፤ የትና በማን ተሰበሩ የሚለውን የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የስታስቲክ ባለሙያዎች ዳሰሳ አድርገዋል።
በውድድር ዓመቱ የተመዘገበው የመጀመሪያ የዓለም ክብረወሰን የሴቶች የቤት ውስጥ አራት በስምንት መቶ ሜትር ውድድር ነው። አራት አትሌቶች ስምንት መቶ ሜትርን ተቀባብለው የሚሮጡበትና ብዙ ጊዜ ፉክክር ሲደረግበት በማ ይታየው ርቀት ኒውዮርክ ከተማ ላይ በተካሄ ደው ሚልሮስ ጨዋታዎች ላይ እኤአ የካቲት ሦስት ነበር ክብረወሰኑ የተመዘገበው። 8፡05፡89 የሆነውን ክብረወሰን ያስመዘገቡትም አሜሪካውያኑ አትሌቶች ክሪሹና ዊሊያምስ፤ ሬቨን ሮጀርስ፤ ቻርሊን ሊፕሴይና አጄ ዊልሰን ስማቸው አፅፈዋል። በዚህ ውድድር ከዚህ ቀደም ተይዞ የነበረው ክብረወሰን 8፡06፡24 ሲሆን ሩሲያውያኑ አትሌቶች አሌክሳንድራ ቡላኖቫ፤ ዬካተሪና ማሪይኖቫ፤ ይሌና ኮፋኖቫ እንዲሁም አና ባላክሺና ሞስኮ ላይ በተካሄደ ውድድር እኤአ የካቲት አስራ ስምንት ነበር ያስመዘገቡት።
የፈረንጆቹ የካቲት አስራ አንድ ቀን በውድድር ዓመቱ ሁለተኛው ክብረወሰን የተመዘገበበት እለት ሲሆን በቤት ውስጥ ከሃያ ዓመት በታች ምርኩዝ ዝላይ ውድድር ግሪካዊው ወጣት አትሌት ኢማኑኢል ካራሊስ 5ነጥብ 75 ሜትር መዝለል ችሏል። በዚህ ውድድር ቀደም ሲል ተይዞ የነበረው ክብረወሰን 5ነጥብ 75 ሲሆን ስዊድናዊው አርማንድ ዱፕሌንቲስ እኤአ የካቲት አስራ አንድ ኒውዮርክ ላይ ያስመዘገበው ነበር።
የካቲት አስራ ስምንት ተከታዩ ክብረወሰን የተሻሻለበት ሲሆን በቤት ውስጥ የወንዶች ስልሳ ሜትር ውድድር አሜሪካዊው ክርስቲያን ኮሊማን 6፡34 ያጠናቀቀበት ነው። ይህ አትሌት በውድድር ዓመቱ ርቀቱን 6፡37 በማጠናቀቅ የጀመረ ሲሆን ክብረወሰኑን ማሻሻል የቻለው በአሜሪካ የቤት ውስጥ ቻምፒዮና ላይ ነበር። ይህ ክብረወሰን ቀደም ሲል ተይዞ የቆየው በሌላኛው አሜሪካዊ አትሌት ሞሪስ ግሪን ሲሆን 6፡39 የገባበት ሰዓት ነው። ይህ አትሌት ይህን ሰዓት ለመጀመሪያ ጊዜ በስፔን ማድሪድ እኤአ የካቲት 3/1998 ያስመዘገበ ሲሆን በቀጣይ አትላንታ ላይ መጋቢት 3/2001 ላይ ተመሳሳይ ሰዓት ማስመዝገብ ችሏል።
በፈረንጆቹ የካቲት አስራ አንድ ተመዝግቦ የነበረው የወንዶች የቤት ውስጥ ከሃያ ዓመት በታች ምርኩዝ ዝላይ ክብረወሰን ዳግም ለመሰበር ከሁለት ሳምንታት በላይ አልፈጀም። በዚህ ውድድር ቀደም ሲል የካቲት ሦስት ላይ ግሪካዊው ኢማኑኢል ካራሊስ 5ነጥብ 78 ሜትር በመዝለል ያስመዘገበው ክብረወሰን ከሁለት ሳምንት በኋላ በስዊድናዊው አርማንድ ዱፕሌንቲስ 5ነጥብ 81 እና 5ነጥብ 88 በመዝላል በአንድ ጊዜ ሰባብሮታል።
ልክ እንደ ሴቶቹ ሁሉ የወንዶች የቤት ውስጥ አራት በስምንት መቶ ሜትር ውድድርም በተመሳሳይ ወር የካቲት ሃያ አምስት ላይ ተሰብ ሯል። አሜሪካውያኑ አትሌቶች ጆይ ማክኤሴይ፤ ክሪስ ጊስቲንግ፤ ካየል መርበር፤ ጂሴ ጋርን 7፡11፡30 በሆነ ሰዓት ክብረወሰኑን በጥምረት ይዘውታል። ቀደም ሲል በዚህ ውድድር ተይዞ የነበረው ክብረወሰን 7፡13፡11 ሲሆን እኤአ የካቲት 8/2014 ቦስተን ላይ አሜሪካውያኑ ሪቻርድ ጆንስ፤ ዴቪድ ቶረንስ፤ ዱአን ሶሎሞን፤ ኤሪክ ሶውንስኪ የተያዘ ነበር።
የፈረንጆቹ መጋቢት አራት በርሚንግሃም ላይ በወንዶች የቤት ውስጥ ውድድር የአራት በአራት መቶ ሜትር ክብረወሰን ተሰብሯል። 3፡01፡77 የሆነው አዲስ የርቀቱ ክብረወሰን በፖላንዳውያኑ ካሮል ዜልውስኪ፤ ራፋል ኦሜልኮ፤ ሉካዝ ክሮውዙክ፤ ጃኩብ ከርዝዊና ሊመዘገብ ችሏል። የዚህ ርቀት ክብረወሰን ቀደም ሲል በአሜሪካውያኑ ካየል ክሊሞንስ፤ ዴቪድ ቨርበርግ፤ ኪንድ በትለር፤ ካልቪን ስሚዝ መጋቢት 9/2014 ፖላንድ ሶፖት የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና ላይ ነው የተመዘገበው።
መጋቢት ሃያ አራት በውድድር ዓመቱ በረጅም ርቀት ውድድሮች የመጀመሪያው የዓለም ክብረወሰን የተመዘገበበት ሲሆን ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ነፃነት ጉደታ በግማሽ ማራቶን አዲስ የዓለም ክብረወሰን ከረጅም ዓመት በኋላ ሳትጠበቅ ማሳካት ችላለች። የስፔኗ ከተማ ቫሌንሲያ ባስተናገደችው የዓለም ግማሽ ማራቶን ቻምፒዮና ይህ ክብረወሰን ይሰበራል ተብሎ ሳይጠበቅ 1፡06፡11 በሆነ ሰዓት ነፃነት ጉደታ ልታሻሽለው ችላለች። የዚህ ርቀት ክብረወሰን ቀደም ሲል ትውልደ ኬንያዊቷ የኔዘርላንድስ አትሌት ሎርናህ ኪፕላጋት እኤአ 2007 ላይ ተይዞ የነበረ ሲሆን ሰዓቱም 1፡06፡25 ነበር።
የፈረንጆቹ መጋቢት ወር የመጨረሻ ቀን በዓለም ከሃያ ዓመት በታች የምርኩዝ ዝላይ ውድድር ታሪክ አስደናቂ ክስተት የተስተናገደበት ነበር። ከዚህ ወር በፊት በቤት ውስጥ ውድድር ሁለት ጊዜ ክብረወሰን ማሻሻል የቻለው ስዊድናዊው አርማንድ ዱፕሌንቲስ ከቤት ውጪ ውድድርም 5ነጥብ 92 ሜርት በመዝለል ከሃያ ዓመት በታች ሌላ የዓለም ክብረወሰን መጨበጥ ችሏል። ይሄ አትሌት ቀደም ሲል ይህን ክብረወሰን ከዓመት በፊት 5ነጥብ 90 ሜትር በመዝለል እንደያዘው ይታወሳል። ይህም ስኬቱ በቅርቡ ተካሂዶ በነበረው የዓመቱ ምርጥ ታዳጊ አትሌቶች ሽልማት አሸናፊ ሊያደርገው ችሏል።
ባለፈው ሚያዝያ ወር በአትሌቲክሱ ዓለም አንድ ክብረወሰን ብቻ ተመዝግቦ ነው ያለፈው። ይህም የሴቶች የዓለም ከሃያ ዓመት በታች የቤት ውስጥ ውድድር አራት መቶ ሜትር መሰናከል ነው። ልክ እንደ ምርኩዝ ዝላዩ ስዊድናዊ አርማንድ ዱፕሌንቲስ የዓመቱ ምርጥ ታዳጊ አትሌት ሽልማት አሸናፊ የሆነችው አሜሪካዊቷ ሲድኒ ማክላህሊን የውድድር ዓመቱን በስኬት ያሳለፈው ሲሆን በአራት መቶ ሜትር መሰናክል ውድድር 52፡75 በማስመዝገብ የዓለም ከሃያ ዓመት በታች ክብረወሰን ባለቤት ሆናለች። ቀደም ሲል የነበረው ክብረወሰን 53፡82 ሲሆን 2017 ላይ በራሷ በሲድኒ የተያዘ ነበር።
ሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ የተመዘገበው የሴቶች ሃምሳ ኪሎ ሜትር እርምጃ ውድድር የዓለም ክብረወሰን ሆኖ እውቅና አግኝቷል። በዚህ ርቀት ቻይናዊቷ ሊንግ ሩይ 4፡04፡36 በመግባት አዲስ ክብረወሰን ያስመዘገበች ሲሆን ቀደም ሲል በርቀቱ የተመዘገበው ክብረወሰን 4፡05፡56 በፖርቹጋላዊቷ ኢንስ ሄንሪኩዊስ 2007ላይ ተይዞ የነበረ ነው።
2018 የውድድር ዓመት ከምንም በላይ ከሃያ ዓመት በታች ያሉ አትሌቶች በአዳዲስ ክብረወሰኖች የተንበሸበሹበት ነው። ለዚህም ማረጋገጫ ሐምሌ ወር ላይ በመቶ አስር ሜትር መሰናክል ውድድር ጃማይካዊው ዳሚየን ቶማስ 12፡99 በሆነ ሰዓት የዓለምን ከሃያ ዓመት በታች ክብረወሰን መጨበጡ አንዱ ማሳያ ነው። የዚህ ርቀት የቀድሞ ክብረወሰን በፈረንሳዊው ዊልሄም ቢሎሲያን 12፡99 ሆኖ በ2014 የተመዘገበ ሲሆን አዲሱ ክብረወሰን በ0ነጥብ 2 ማይክሮ ሰከንድ የተሻለ ነው።
በዚያው በሐምሌ ወር መጨረሻ በወንዶች መቶ ኪሎ ሜትር ውድድር ጃፓናዊው ናኦ ካዛሚ ከሃያ ዓመት በኋላ አዲስ ክብረወሰን ማስመዝገቡ ልዩ ክስተት ነበር። ይህ አትሌት ቀደም ሲል በአገሩ ልጅ ታካሂሮ ሱናዳ ከሃያ ዓመት በፊት ተይዞ የነበረውን 6፡13፡33 ከአራት ደቂቃ ባላነሰ ጊዜ በማሻሻል አዲስ ክብረወሰን በስሙ አስፍሯል።
ነሐሴ ወር መጀመሪያ ላይ በሞናኮ ዳይመንድ ሊግ ኬንያዊቷ የሦስት ሺ ሜትር መሰናክል አትሌት ቢትሪስ ቺፕኮይች ያስመዘገበችው የዓለም ክብረወሰን በውድድር ዓመቱ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው። ቺፕኮይች የርቀቱን የዓለም ክብረወሰን በስምንት ሰከንድ ያሻሻለች ሲሆን ቀደም ሲል የነበረው ክብረወሰን በሌላኛዋ ኬንያዊት ሩዝ ጂቤት 8፡52፡78 የተያዘው በ2016 ነበር። ከነሐሴ ወር መጨረሻ እስካለፈው ጥቅምት ወር ድረስ የተሻሻሉት ሦስት የዓለም ክብረወሰኖች ከቀደሙት ወራት የበለጠ ትልቅ ትኩረት የተሰጣቸውና ብዙ መነጋገሪያ የነበሩ ናቸው።
ኢትዮጵያዊው አትሌት ሰለሞን ባረጋ መስከ ረም ከመጥባቱ አስቀድሞ በብራሰልስ የዓመቱ ዳይመንድ ሊግ ውድድሮች መቋጫ አምስት ሺ ሜትር ላይ ያስመዘገበው 12፡43፡02 ሰዓት የዓለም ከሃያ ዓመት በታች ክብረወሰን ሆኗል። ከዚህ ባሻገር በርቀቱ ከምን ጊዜም ፈጣን አራት ሰዓቶች አንዱ ለመሆን በቅቷል። ቀደም ሲል ይህ ክብረወሰን ተይዞ የቆየው በኢትዮጵያዊው አትሌት ሃጎስ ገብረህይወት ሲሆን 12፡47፡53 በሆነ ሰዓት እኤአ 2012 ፓሪስ ላይ የተመዘገበ ነበር። የፈረንጆቹ መስከረም አስራ ስድስት በዓለም አትሌቲክስ ታሪክ ትልቁ የማራቶን ክብረወሰን የተመዘገበበት ስኬታማ ጊዜ ሆኖ ይታወሳል። ኬንያዊው የኦሊምፒክና የዓለም ቻምፒዮን ኢሉድ ኪፕቾጌ በበርሊን ማራቶን 2፡01፡39 በማስመዝገብ በሰባ ስምንት ሰከንዶች የቀድሞውን ክብረወሰን ማሻሻል ችሏል። ይህም በማራቶን ታሪክ እኤአ ከ1967 ወዲህ ትልቅ መሻሻል የታየበት ነበር። ቀደም ሲል ይሄ ክብረወሰን በሌላኛው ኬንያዊ ዴኒስ ኪሜቶ 2014 ላይ እዚያው በርሊን ማራቶን የተመዘገበ ሲሆን ሰዓቱም 2፡02፡57 ነው። በተመሳሳይ ጥቅምት ወር ላይ በቫሌንሲያ ግማሽ ማራቶን የወንዶች የዓለም ክብረወሰን በኬንያዊው አብረሃም ኪፕተም 58፡18 በሆነ ሰዓት ሊሰበር ችሏል። ይህ ክብረወሰን ቀደም ሲል በኤርትራዊው የርቀቱ ስኬታማ አትሌት ዘረሰናይ ታደሰ ሊዘበን ላይ እኤአ በ2010 የተያዘ ሲሆን ሰዓቱም 58፡23 ነበር።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 20/2011
ቦጋለ አበበ