‹‹ለውጡ ከመምጣቱ በፊት እኮ ይች ሀገር የግለሰቦች ንብረት ነበረች። በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጁ፤ ስራ ይፈጠርላችኋል እየተባልን በተደጋጋሚ ተቀልዶብናል። ስልጠና ሰጥተው ጠብቁ ይሉናል፤ እውነት እየመሰለን ስንጠብቅ ብዙ አመታት ያልፋሉ። ሌሎች ቅድሚያ ይስተናገዳሉ፤ እኛ ከወጣቶች እኩል ፣ከሰው እኩል ያልተፈጠርን ያህል የስነልቦና ጫና ያሳድሩብናል። ይንቁናል፤ ጠንከር ያለ የመብት ጥያቄ ካነሳን ‹‹ከርቸሌ›› ይወረውሩናል።
‹‹ከመንግስት አካላት ጋር አይጥና ድመት ሆነን ነው የኖርነው። በጥርጣሬ ያዩናል። በዚህ የተነሳ ከቤታችን ወጥተን ስራ መስራት እንዳንችል በማግለል ሀገራችንን ጠልተን ለስደት እስከመዳረግ ደርሰናል። በሚፈጠርብን ቂምና ጥላቻ ምክንያት የተለያዩ ወንጀሎች እስከመፈጸም ደርሰናል። ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም ያልተሰራብን ግፍና መከራ የለም።›› ሲል በስደት ወቅት ጓደኞቹን የበረሃ ረሃብና ባህር የነጠቃቸውን እያስታወሰ ወጣት ፈይሰል መሐመድ ይናገራል።
ኢትዮጵያዊ ማንነቱን ማግኘት የቻለው ሁለት አመት ባልሞላው ለውጥ ምክንያት መሆኑን በመግለጽ በዚች ሀገር ዜጎች በተለይም ወጣቱ እኩል መታየትና እኩል ሰርቶ መጠቀም እንዲሁም በሀገሩና በመሪዎቹ ላይ ተስፋ ማሳደር የጀመረው ለውጡ በፈጠረው የእኩልነት ስሜት መሆኑን ያነሳል፤ወጣት ፈይሰል።
‹‹ዛሬ ከወደቅንበትና ከተናቅንበት ተነስተን 40 ወጣቶች ተደራጅተን ራሳችንን እና ቤተሰቦቻችንን በተገቢው መመገብ ችለናል፤ ልጆቻንን ማስተማር ችለናል፤ጥሩ ገቢ ማግኘት ከቻሉ ሞዴል ወጣቶች ተመድበናል፤ አንገታችንን ያለ ሀፍረት ቀና ማድረግ ችለናል፤ያለመሽቆጥቆጥ እና ያለመሸማቀቅ ሀሳባችንን ያለ ከልካይ ተንፍሰናል። ሰበብ እየተፈለገ ቂሊንጦ፣ዝዋይ፣ሸዋ ሮቢት፣ደዴሳ ተወርውረን በሚሰራብን ግፍ አስፈሪው ሞት ጭምር ምርጥ መፍትሄ ሆኖ እንዲገላግለን በፍቅር እንለምን ነበር›› ወጣት ፈይሰል ይናገራል።
‹‹ወጣቱን ከወጣት፣ ብሔርን ከብሔር፣ ክልልን ከክልል፣ እና በተገኘው ቀዳዳ ሁሉ አንዱን ከአንዱ በማጋጨት የእሱን ደስታ የሚፈጥርና ስልጣኑን የሚያራዝም ቡድን ሀገሪቱንና ዜጎቿን ለማኝ፣ ወጣቶቹ ደግሞ ሱሰኛና ዘራፊ እንዲሆኑ ሲያደርጋቸው ቆይቷል። መስራት የሚችል ወጣት ኢትዮጵያዊ መሆን ብቻ መስፈርት ሆኖ ስራ መያዝ ችለናል›› የሚለው ሌላው የማህበሩ አባል ወጣት ዳዊት ከበደ ነው።
በሀገሪቱ የተገኘውን አጋጣሚ ተጠቅሞ እውነትም ወጣቱ ሀገር ተረካቢ መሆኑን በተግባር ካላስመሰከረ አሁንም የወጣቱን ጭንቅላት የሚበርዙና የሚሰልቡ ወሬዎችና ትርክቶች ቀጥለዋል። ለዚህም ማህበራዊ ሚዲያ ስራ በማስፈታት፣ ወጣቱን በማወናበድ፣ ጥላቻና መከፋፈልን በማስተማር፣ ለጥፋት በማደራጀት፣ወጣት ከወጣት፣ ማህበረሰብ ከማህበረሰብ እንዳይተማመን ስራዬ ተብሎ እየተሰራ ነው ሲልም ወጣት ዳዊት ይወቅሳል።
የአዲስ አበባ ወጣት በምንም ተአምር ቦታ ሊሰጥ አይገባውም። አዲስ አበባ የኢትዮጵያውያን ነች፤ ወጣቱም አለም የደረሰበትን አይቶ ለመረዳት ቅርብ ነው። ሥለዚህ ከኋላ ቀር አስተሳሰብና ተግባር ታጥረን ሰው መሆንን መድፈቅ አይገባም፤ የሚለው ወጣት ዳዊት የሀሪቱ ወጣት በሚመቻችለት ወሬ እየተጠለፈ፣ በሚያበጁለት ወጥመድ እየገባና በሚያሳፍር ምክንያት በረባ ባረባው እርስ በርስ እየተናከሰ የሚቀጥል ከሆነ የሶሪያውያን እጣ ፋንታ ለእኛም እሩቅ አይሆንም በማለት ወጣቱ ስጋቱን አስቀምጧል።
‹‹ የመርካቶ ልጅ ጠጠር መወርወር ቀርቶ ስራ የሚያበላሽና የሚያስተጓጉል እንዲሁም ማንነት የሚነካ የቃላት መወራወር ሰምተን ወጣቶች ዝም የምንል አይምሰልህ። መጥቶ የሄደው ሁሉ የጥላቻ ዱላውን አሳርፎብናል በዚህ የተነሳ በድህነት ችግር ውስጥ መከራችንን አይተናል፤ መሮናል። አሁን ላይ እኩል ሰርተን እኩል መኖርና እኩል መታየት ጀምረናል ይሄን እድልና ይሄን አጋጣሚ ማጠናከር እንጂ በከንቱ የምናበላሽ አይምሰልህ›› በማለት የለውጡን ፈተናዎች ለመታገል ቃል ገብቷል።
ወጣት መሐመድ ስንታየሁ በበኩሉ ‹‹ለውጡ የተረሱ ዜጎችን ያስታወሰ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። ፍጹም እንከን የለሽ እንዲሆንለት የሚመኝ አካል ካለም ተሸውዷል። ደምና ሕይወት የከፈልንበት የለውጥ ሂደት በአንጻራዊነት ሲታይ በአጭር ጊዜ ከ28 አመት ጭቆና እንድንላቀቅ አድርጓል። የምጽዋት እንጀራን በፌስታል ትሪ ከመሻማት አላቅቆናል፤ ›› ሲል አብራርቷል።
በተጨማሪም ወጣቱ ‹‹ኢትዮጵያዊነቱንና ሰው መሆኑን በተግባር በማረጋገጥ መንገድ ያሳየውን መልካም ሀገራዊ ጅምር የለውጥ ሂደት መደገፍ አለበት። መንገድ መዝጋት፣ ወንድም ወንድሙን መግደልና ብጥብጥ አንድ የጋራ ሀገር የሚፈጥር አይመስለኝም። ሀገራችን ሰላም እንድትሆን ወጣቶች የብሔር አስተሳሰባችንን አውልቀን ኢትዮጵያዊነትን መላበስ አስፈላጊና ግዴታችን ሊሆን ይገባል›› ብሏል።
‹‹ከለውጡ በፊት የነበረን የሕይወት ጣዕም በጣም አስቀያሚ ነበር። የመንግስት አካላት የሚያስቡንና የሚመለከቱን በወንጀለኛና በመጥፎ ባህሪ በመሆኑ ለረዥም አመታት ወጣትነታችንን በተስፋ መቁረጥ ውስጥ አሳልፈናል። ሀገራችንን እስከመጥላት ደርሰን ነበር›› የሚለው ወጣት ኤፍሬም ታሪኩ ነው።
‹‹በሀገሪቱ የመጣው ለውጥ እንደዜጋ እንድንቆጠርና ሐሳባችን መደመጥ እንዲችል እድል ሰጠን።በዚህ መነሻነት የነበርንባቸውን አስቀያሚ የሕይወት ምዕራፎች ዘግተን ከለውጡ የወረዳ አመራሮች ጋር በቅርበት መወያየት ቻልን። አሁን የስራ እድል ባለቤቶች ሆነናል። መጥፎ ስም የነበረን 40 ወጣቶች ተደራጅተን ተርሚናል የታክሲ ተራ ማህበር መስርተን ስማችንንም ኑሯችንንም ባንድ ላይ መቀየር ችለናል›› በማለትም ወጣት ኤፍሬም ማህበራቸው የደረሰበትን አሳይቷል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት27/2012
ሙሐመድ ሁሴን