የሌላውን ሀገር ባላውቅም በእኛ ሀገር ግን የማንተገብራቸው በርካታ አባባሎች አሉን። ምሳሌ ጥቀስ ካላችሁኝ ከመነሻዬ ሀሳብ ጋር ከሚቀራረቡት መካከል ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ፣ ሳይቃጠል በቅጠል፤ አስሬ ለካ አንዴ ቁረጥ፤ ሰዶ ማሳደድ ቢያምርህ….. ፤ ቀድሞ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ…..የሚሉት ከብዙ ጥቂቶቹ ናቸው። ብዙ አልተጠቀምንባቸውም እንጂ በየመስኩ በየጉዳዩ ብዙ ተረቶች ብዙ አባባሎችና ወጎች አሉን።
ያለሁት ኮተቤ ከአንድ የዘመዴ ቤት ነው የታመመች ልጇን ለመጠየቅ። ልጅቱ ደግሞ እግሯን በጀሶ ጠቅልላ መሬት ላይ የተነጠፈ ፍራሽ ላይ ተኝታለች። እንዴ? ምን ተፈጥሮ ነው? ጠየቅኩ፤ «ወለም ብሏት» ስትይኝ ቀላል መስሎኝ ነበር አልኩ ደንገጥ ብዬ። «እንዳትደነግጡ ብዬ ለሁሉም እንዲሁ ነው ያልኩት። ለነገሩ ዶክተሩ አጥንቷ ብዙም አልተጎዳ፤ በዛ ላይ ልጅ ስለሆነች ቶሎ ይስተካከላል ብሎኛል» አለች። ለመሆኑ ምን ሆና ነው?
እናቲቱ « አልሰማ ብላ» በማለት ጀምራ ባጭሩ ታሪኩን አወጋችኝ። በአካባቢው ረጅም ጊዜ የወሰደ ሰፊ የመንገድ ሥራ እየተከናወነ ነው። እናም በየቀኑ ወይ ይቆፈራል ወይ ይናዳል ይሄ ሲሆን ግን መንገዱ በከፊል ለመኪና ይዘጋል። እግረኛው በአንድ ጎን የግለሰብ አጥር በሌላ በኩል ደግሞ ገደል በሚያዋስኑት ጠባብ የግራና ቀኝ መንገዶች እየተጠባበቀ ነው የሚጓዘው። አንዳንድ ቦታ ገደሉ ረጅም ስለሚሆን እናት ልጇን በዛ መንገድ እንዳትሄድ ርቀት ቢኖረውም በአስፋልት ዞራ እንድትመጣ በተደጋጋሚ መክራት ነበር፤ ግን አልሆነም። ከጓደኞቿ መለየት ያልመረጠችው ልጅት ከጓደኛዋ ጋር እንደተያያዙ ተንሸራተው ከአንዱ ገደል ይወድቃሉ። እንደተነገረኝ ከሆነ ሁለቱም ለከፋ ጉዳት ባይዳረጉም ለቀናት ከትምህርት ገበታቸው መለየታቸው ግን አልቀረም።
እንደኔው ሊጠይቁ የመጡ አንዲት እናት «አሁንማ አስተካከሉት እኮ ትናንት የእከሌ አባት አሉ ስም እየጠሩ ወድቀው ላይሞቱ ነው የተረፉት፤ ዛሬ በደንብ አስተካክለውታል» አሉ በማፅናናት አይነት። ምን ዋጋ አለው ፈጣሪ ባይደርስላት ሞታ አልነበር። ስንት ሰው በቀን በማታ መከራውን ሲያይ ምን ሰሩ? ድሮም አንድ ሰው ሞተ፣ መኪና ተገለበጠ ካልተባሉ እንደማይሠሩ ይታወቃል፤ የህዝቡን አቤቱታ መች ሰምተውን ያውቃሉ አለች ዘመዴ ምርር ብላ። እነሱ ወሬያቸውን ቀጠሉ እኔ በሀሳብ ነጎድኩ ግን እውነት እስከ መቼ እሳት እያጠፋን እንኖራለን ?።
ተሰናብቼ ወጥቼ ከሃሳቤ ሳልላቀቅ መገናኛ አካባቢ ስደርስ ሻይ ቡና ለማለት መተባበር ህንፃ ላይ ባለ አንድ ካፌ ውስጥ ተቀመጥኩ። ቁልቁል የባቡሩን አካፋይ የቀለበት መንገድ ስመለከት ትኩረቴንም ስሜቴንም የሚስብ ተመሳሳይ ነገር አስተዋልኩና በጥሞና መከታተል ጀመርኩ። አካባቢውን በደንብ አውቀዋለሁ፤ የጎዳና ላይ ንግድ የተጧጧፈበት ነው። በተለይ አመሻሽ ላይ ያለው ገበያና የሚቀርበው ሸቀጥ «ንግድ ፈቃድ፣ ግብር፣ ቤት ኪራይ» ለምኔ የሚያሰኝ ነው። ይሄ ታዲያ ለወጣቶቹ ነጋዴዎች ከጠባቂዎች ጋር የሚደረገውን የድብብቆሽ ጨዋታ በየቀኑ ማሸነፍ ይጠይቃል። እነዚህ ነጋዴዎች አብዛኞዎቹ በወጣትነት እድሜ ክልል ያሉና ከአዲስ አበባ ውጪ የመጡ በመሆናቸው ባንድ እጃቸው ዱላ በአንደኛው ደግሞ ኮፍያቸውን ይዘው ለሚያሯሩጧቸው የሸገር ጠባቂዎች የሚረቱ አይደሉም። እንዲያውም አንዳንዶቹ ያንን ኮተት ይዘው እንደዚያ መሮጥ ከቻሉ በዱላ ቅብብል ውድድር ቢሳተፉ እላለሁ።
እንግዲህ ልብ በሉ መንግሥት የጎዳና ላይ ንግድን የሚያበረታታ ባይሆንም ወደ ህጋዊ ሥርዓት ለማስገባትና ነባራዊውን ሁኔታ ከግምት በማስገባት በመንገድ ዳርቻ እንዲሸጡ የተፈቀደላቸው ህግ አክባሪ የጎዳና ላይ ነጋዴዎች በየቦታው አሉ። በዚሁ አካባቢ እንኳ ከአደባባዩ ሁለት መቶ ሜትር ባልሞላ ርቀት አምቼ አጥር ስር በተፈቀደላቸው ቦታ ተወስነው የመኪናና የእግረኛ እንቅስቃሴ ሳያግዱ የሚሠሩ የጎዳና ላይ ነጋዴዎች ቢኖሩም እቃቸውን የሚገዛ ሸማች የሚደርሳቸው በአደባባዩ ከሚሯሯጡት ህገ ወጥ ነጋዴዎች የተረፈው ብቻ ነው። ከታች የምገልጽላችሁ ትእይንት ደግሞ እጣ ሳያወጡ፣ አቦሰም ሳይጣጣሉ ጠባቂዎቹና ነጋዴዎች እንዴት የአባሮሹን ጨዋታ እንደሚጀምሩ ነው።
አዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን እግረኛውንና አሽከርካሪውን ለመለየት በከለለው ብረት ላይ ደማቅ ሰማያዊ ቀለም ያለው ባለ አርማ ዩኒፎርም የለበሱ የቦሌ ክፍለ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች ሦስት ሆነው ተደግፈው ያወራሉ። የሚያወሩት ደግሞ ስለ ኑሮ ውድነት ነው። ፎቅ ላይ ሆነህ እንዴት ይሄን አዳመጥክ የሚለኝ ካለ ግምቴ መሆኑን በማስቀደም ለግምቴ መነሻ የሆነኝን ምክንያት አቀርባለሁ።
ከፌስ ቡክ እንደተማርኩት ከሆነ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ሰብሰብ ብለው ከታዩ ድንጋይ ውርወራ ሊጀመር በመሆኑ ከአካባቢው መራቅ አልያም ኮፍያ ብጤ ጣል ማድረግ ከተማሪዎቹ ንረታም ሆነ ሰላማዊና አጥፊን ሳይለዩ ከሚቀጡት ህግ አስከባሪዎች ራስን ለመታደግ ይረዳል። ተማሪዎቹ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ከሆኑ ስለፍቅር ጓደኛቸው እንደሚያወሩ የሚገመት ሲሆን፣ የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች ከሆኑ ስለ ፊልም እንደሚሆን እንገምት። ወደ መንግሥት ሠራተኛው ሲመጣ ጉዳዩ የሚወሰነው በእድሜ አልያም በክፍል ደረጃ ሳይሆን በደመወዝ ይሆንና ባጭሩ ዝቅተኛው ተከፋይ ስለኑሮ ውድነት መካከለኛው ተከፋይ ስለሥልጣንና እድገት ፣ ከፍተኛው አመራር የየእለት ጭውውቱ በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ያጠነጠነ መሆኑ በዚሁ ፌስ ቡክ ማየት ችያለሁ። የፖለቲካው ነገር ግን ደመወዝም ዕድሜም የሚገድበው አይደለም፤ በተለይ አሁን አሁን።
እጅና አፍ አይጠፋፉም ብዬ ከግማሽ ሰዓት ላላነሰ ጊዜ እጄን ከብርጭቆዬ አገናኝቼ ወደ አስፋልቱ ባደረግሁት ማፍጠጥ እነዚያን ስለ ኑሮ ውድነት የሚያወጉ የደንብ አስከባሪዎች የጎዳና ላይ ነጋዴዎቹ እንደ ቀልድ ባጠገባቸው ያልፏቸው ይዘዋል፤ ትንሽ መጠንቀቅ የሚመርጡት ደግሞ ጣደፍ ጣደፍ እያሉ ያልፋሉ፤ ለነገሩ ከአስፋልት ማዶ የሚያልፉ ጥንቃቄ የሚያበዙ ነጋዴዎችም አሉ።
ይህን ጉድ ሳላይ አልነሳም ብዬ ለአንድ ሰዓት ከቆየሁ በኋላ አስራ አንድ ሰዓት ተኩል ሲሆን በርከት ያሉ ደንብ አስከባሪዎች ከየአቅጣጫው በመምጣት ባጠገባቸው እያለፉ ወደ አደባባዩ ገብተው እቃቸውን ከዘረጉት የጎዳና ላይ ነጋዴዎች ጋር የዘወትር አባሮሻቸውን ቀጠሉ። አንዳንዶቹ ሊይዟቸው የሚፈልጉ አይመስሉም ፤ በፍጥነት መሮጥ ይጀምሩና ሊደርሱባቸው ሲሉ ፍጥነታቸውን ይቀንሳሉ። ለነገሩ «ከልብ ካለቀሱ» የሚለውን አባባላችን መነሻ አድርገን ካየነው ምንስ ፈጣን ቢሆን እቃ ተሸክሞ የሚሮጥን በባዶ ሮጦ መያዝ አለመቻል ተቀባይነቱ እዚህ ግባ የሚባል አይሆንም። ግን እነዚህ ደንብ አስከባሪዎች የሚሰጣቸው ሥልጠና ምንድነው? ቤት ተሠርቶ፣ አጥር ታጥሮ ሲያልቅ ማፍረስ በአጭሩ መቅጨት የሚችሉትን ለግጭትም ለንትርክም ምክንያት ሲሆን ይታያል።
ከዓመታት በፊት አንድ የመኪና ጥገና የሚሠራ ጓደኛዬ የነገረኝ « የወረዳችን አስተዳደር 21 ዓመት በጋራዥነት ሲያገለግል የነበረውን ግቢ ከስፋቱ ጀምሮ ደረጃ አያሟላም ብሎ እንዲያስፋፉ የማስተካከያ ጊዜ ይሰጣቸዋል። አስተዳደሩ ምንም እንኳ በህግ የተቀመጠ ነገር ቢናገሩም በሦስቱም አቅጣጫ በግለሰብ መኖሪያ ቤቶች የተከበበችው ቦታ ወዴትም እንደማትሰፋ በእርግጠኝነት ያውቁ ነበር። እናም ቀኑ ደርሶ ጋራዡ መስፋት ባለመቻሉ ተዘጋ» የኔ ጓደኛና ባልደረባው ከባድ መሳሪያ የማያስፈልጋቸውን ጥገናዎች በየቤታቸውና በየመንደሩ መንገድ እየዘጉ መሥራቱን ቀጠሉበት። በዛ ሰሞን እንዴት ነው ያዋጣል? ብዬ ላቀረብኩለት ጥያቄ የሰጠኝ ምላሽ እንዲህ የሚል ነበር « እኛና መንግሥት ከጋራ ተጠቃሚነት ወደ የጋራ ተጎጂነት ተሸጋግረናል፤ እኛ በጠራራ ጸሀይ በየጎዳናው እየተሽከረከርን ለመሥራት ተገደናል መንግሥት ደግሞ ብታንስም መሰብሰብ የሚችለውን ግብር አጥቷል፤ ድሮ ማወራረድ ስላለ ብዙ ነገሮችን ስንገዛ በደረሰኝ ነበር፤ አሁን ህጋዊ ነጋዴዎች ጋር የሚያስኬደን ጉዳይ የለም፣ ነገሩ ሁሉ አየር በአየር ሆኗል»። አለኝ እያዘነም ፤እየተናደደም።
ምንም እንኳ ህግ መከበር ቢኖርበት ሰው ከሰላማዊ መንገድ ተገፍቶ ሲወጣና አማራጭ ሲያጣ ወዴት እንደሚያመራ የሚያሳየን ይመስለኛል። እነዚህ በየታክሲው ላይ የምናያቸው እቤትዎ ድረስ መጥተን ፍሪጅ እናድሳለን፣ ቴፕ፣ ቴሌቪዥን እንጠግናለን የሚሉ ማስታወቂያዎችም የዚሁ ውጤት ይመስሉኛል። ይሄን ሳይ ህግና ሥርዓት አክብረው የሚንቀሳቀሱትን አለመደገፍና አለመንከባከብ ህገ ወጦችን ማበረታታት፤ ህጋዊው መንገዱንም መግፋት ይሆንብኛል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 20/2011
ራስወርቅ ሙሉጌታ