እንደምን ሰነበታችሁ! እንኳን በጤና ተገናኘን!
ስለ ስጦታ በጠቅላላው
ስጦታ በአገራችን የፍትሐብሔር ሕግ ከተደነገጉት የውል ዓይነቶች ውስጥ አንዱ ነው። በመሠረታዊው የውል ጽንሰ ሀሳብ ውል አንዱ ለሌላው የተወሰነ ነገር ሰጥቶ ወይም ፈጽሞ እርሱም በበኩሉ እንዲሁ የተወሰነ ነገር የሚቀበልበት ግንኙነት ነው።
በቀላል ምሳሌ በመኪና ሽያጭ ውል ውስጥ ሻጭ መኪናውንና ሥመ-ሀብቱን ለገዥ የማስተላለፍ ግዴታ አለበት። በአንጻሩ ገዥው የመኪናውን የሽያጭ ዋጋ ለሻጭ የማስረከብ ግዴታ አለበት። ይህም የተዋዋይ ወገኖችን ተነጻጻሪ መብትና ግዴታ (Reciprocity) ያሳያል። የዚህ ዓይነት በተዋዋይ ወገኖች ላይ ተነጻጻሪ ግዴታ የሚጥሉ ውሎች በዋጋ ላይ የተመሰረቱ ውሎች (Contracts on Onerous Title) ይሰኛሉ በሕግ አነጋገር።
ከዚህ የውል መሠረታዊ ጽንሰ ሀሳብ በተቃራኒው ግን የስጦታ ውል ተነጻጻሪ ግዴታ የሌለበት ውል ነው። በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2427 ላይ በግልጽ ሰፍሮ እንደምናነበው ስጦታ ማለት ሰጪ የተባለው አንደኛው ተዋዋይ ወገን ተቀባይ ተብሎ ለሚጠራው ለሌላ ሰው ችሮታ በማድረግ ሃሳብ ከንብረቶቹ አንዱን የሚለቅበት (ግዴታ የሚገባበት) ውል ነው።
ከዚህ የምንረዳው ስጦታ በመርህ ደረጃ ግዴታን በአንዱ ወገን ትከሻ ላይ የሚጥል፤ መብትን ደግሞ ለሌላኛው ወገን እንደሚያጎናጽፍ ነው። በሌላ አነጋገር በስጦታ ውል ውስጥ ስጦታ ሰጪው የመስጠት ግዴታ (Unilateral Obligation) ያለበት ሲሆን፤ ስጦታ ተቀባዩ ግን ከመቀበል መብት በስተቀር ተነጻጻሪ ግዴታ የለበትም።
እናም ስጦታን ጨምሮ በአንድ ወገን ላይ ግዴታ የሚጥሉ ውሎች በችሮታ ላይ የተመሰረቱ (Contracts on Gratuitous Title) ይባላሉ። ያለክፍያ የሚደረጉ የአደራ ውሎችና የውክልና ውሎችም ልክ እንደስጦታ ውል ሁሉ በችሮታ ላይ የተመሰረቱ ውሎች ምድብ ውስጥ የሚገኙ ናቸው።
እዚህ ላይ አንድ ወገን ብቻውን ተጠቅሞ ሌላው ወገን ለምን ተገዳጅ ይሆናል የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም። «የውል ግንኙነት የግለሰቦችን የፍትሐብሔር መብትና ግዴታ የሚመለከት በመሆኑ ወዶና ፈቅዶ በሕግ አግባብ እስካደረገው ድረስ አንድ ሰው በፍትሐብሔር መብቱ ላይ በመሰለው ሊያዝበት ይችላል» ይላሉ ፕሮፌሰር ጥላሁን ተሾመ «የኢትዮጵያ የውል ሕግ መሰረተ ሀሳቦች» በሚለው መጽሐፋቸው ለዚህ ጥያቄ መልስ ሲሰጡ፡፡
በመሆኑም አንድ ሰው ከሚዋዋለው ሰው ጋር ያለውን ቤተሰባዊ ግንኙነት፣ ቀደም ሲል ያደረገለትን ውለታ ወይም በጎ ሥራ፤ ወይም ሃይማኖታዊና ሰብዓዊ እሴቶቹ አስገድደውት ስጦታ ቢያደርግ የመብቱ ባለቤት እራሱ ስለሆነ ለምን ይህንን አደረክ ሊባል አይገባውም።
የስጦታ ልዩ ባህርያት
በመርህ ደረጃ ስጦታ የሰጪ የራሱ የተለየ ተግባር ወይም ጥብቅ የሆነና ራሱ የሚፈጽመው ሕጋዊ ድርጊት ነው። ያም ሆኖ የሚሰጡት ንብረቶች እንዴት ያሉ እንደሆኑና ለማን እንደሚሰጡ በግልጽ በማስታወቅ ስጦታ በተወካይ አማካኝነትም ሊፈጸም ይችላል።
የስጦታ ውል ፍጹም እንዲሆን የተቀባዩም ፈቃድ ያስፈልጋል፤ ማለትም «ልግስናውን እቀበላለሁ» ብሎ ሃሳቡን መግለጽ አለበት። ስጦታውን የስጦታ ተቀባዩ እንደራሴ ስለእርሱ ሆኖ ሊቀበልለት ይችላል። የተቀባዩ ወራሾች ግን ስለእርሱ ሆነው ስጦታን መቀበል አይችሉም።
ከዚህ የምንረዳው ታዲያ ስጦታ ውል እንደመሆኑ መጠን የግራቀኙ ሀሳብ ለሀሳብ መገናኘት የግድ አስፈላጊ መሆኑን ነው። ስጦታ ሰጪው (ውል ሰጪው) ውል የማድረግ ፍላጎቱን (የችሮታ ሀሳቡን) ለስጦታ ተቀባዩ (ለውል ተቀባዩ) በማያሻማ መልኩ መግለጽ አለበት። የውል አቀራረብ (Offer) መኖር አለበት ማለት ነው። ይህንንም ስጦታ ተቀባዩ በሙሉ ልቡና ሃሳቡ ከተቀበለው የውል አቀባበል (Acceptance) በመኖሩ በመካከላቸው ያለው የመዋዋል ፍላጎት ተቋጨ ማለት ነው፡፡
ነገር ግን ልግስናውን እንካ ተቀበል እየተባለ እቀበላለሁ ብሎ ሀሳቡን ሳይገልጽ ከቆየ ወይም ዝም ብሎ ከርሞ ሰጪው ከሞተ ወይም ችሎታ ካጣ (በሕግ ወይም በፍርድ ክልከላ ከተጣለበት አልያም አዕምሮው ከጎደለ) በኋላ ስጦታውን እቀበላለሁ ቢል በሕግ ፊት ዋጋ የለውም።
ልብ ሊባልበት የሚገባው ሌላው ጉዳይ በኑዛዜ የሚደረግ ስጦታ በሕግ እይታ ውል ሊባል እንደማይቻል ነው። እርግጥ ነው በኑዛዜ ውስጥ ሟቹ ንብረቶቹን ለኑዛዜ ስጦታ ተቀባዮች ሊሰጥ ይችላል። ነገር ግን የተቀባዩ ፈቃደኛ አለመሆን ኑዛዜውን ፈራሽ አያደርገውም። ተቀባዩ የኑዛዜውን ስጦታ አልቀበልም ካለ በሕጉ መሠረት ንብረቱ ከሟች በአደራ ለተቀበለው ሰው ይተላለፍለታል። ከዚህ ሌላ የስጦታ ውል የሚፈጸመው ወይም እንደውሉ ተቀባዩ ንብረቱን የሚወስደው ሁለቱም በሕይወት ሳሉ ሲሆን ኑዛዜ የሚፈጸመው ወይም የኑዛዜው ቃል ተግባራዊ የሚደረገው ደግሞ ተናዛዡ ከሞተ በኋላ ነው፡፡
ስጦታ ውል እንደመሆኑ መጠን የሚደረግበት ሥርዓትና ፎርም በሕጉ ተደንግጓል። በዚሁ መሠረት የማይንቀሳቀስ ንብረት ስጦታ ወይም በማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ መብትን የሚሰጥ ስጦታ (በንብረቱ መገልገል ወይም አላባውን/ፍሬውን መጠቀም) ሰጪው እየተናገረ ማናቸውም ሌላ ሰው በሚጽፍለት ወይም ራሱ ሰጪው በምስክሮች ፊት በሚጽፈው ሰነድ ላይ እንዲሰፍር ካልተደረገ ፈራሽ ነው። በመዝጋቢ አካል እንዲመዘገብ ግን አይጠበቅም።
ተንቀሳቃሽ ንብረቶችንና ለአምጪው የሚከፈሉ ሰነዶችን (እንደ ቼክ ያሉ) የተመለከቱ ስጦታዎች ደግሞ እጅ በእጅ በሚደረግ ማስተላለፍ ብቻ ይፈጸማሉ። ያም ሆኖ ስጦታ ሰጪው የማይንቀሳቀስ ንብረት ስጦታ ለማድረግ በሚያደርገው ዓይነት ፎርም ጽፎ ስጦታውን እንዳያደርግ የሚከለክለው ሕግ የለም። ከዚህ ውጪ ስጦታ ሰጪው ሌሎች መብቶቹን ወይም ከሦስተኛ ወገኖች ጋራ የተዋዋለበትን ጥቅም የሚያስገኝ የውል ሥምምነትንም ለስጦታ ተቀባይ በመስጠት ብቻ የስጦታ ውል ማድረግ ይችላል።
ስጦታን በተመለከተ በሰጪውና በተቀባዩ እንዲሁም በሦስተኛ ወገኖች መካከል አለመግባባት ተነስቶ ወደ ክርክር ቢያመሩ የማስረጃ ጉዳይ መሠረታዊ ጥያቄ ነው። በሕጋችን ስጦታ ስለመኖሩ የማስረዳት ሸክሙ ስጦታ አለ በሚለው ተከራካሪ ወገን ትከሻ ላይ ነው የወደቀው። ስጦታ አለ የሚለው ሰው ስጦታ መኖሩን ማስረዳት አለበት፡፡
ስጦታ እንዲሻር የሚጠየቅባቸው ሁኔታዎች
የስጦታ ውጤት በሰጪውና በተቀባዩ ላይ ብቻ የሚያበቃ አይሆንም። በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ የሦስተኛ ወገኖችን ጥቅም የተመለከተ ውጤት ሊኖረው ይችላል። በዚህ ረገድ ሰጪውን ጨምሮ የሰጪው ወራሾች፣ ገንዘብ ጠያቂዎችና ሕጋዊ የመብት ተጋሪዎች ስጦታውን ተከትሎ ጥያቄዎችን ማንሳታቸው አይቀሬ ነው። እናም ከሰጪውም ሆነ ከሌሎች ወገኖች ስጦታ እንዲቀነስ ወይም እንዲሻር የሚጠየቅባቸውን ጉዳዮች ማወቁ ጠቃሚ ነው።
የመጀመሪያው ጉዳይ የሰጪው አዕምሮ ትክክል አለመሆን ነው። በመርህ ደረጃ የሰጪው አዕምሮ ትክክል አልነበረም በማለት ስጦታን ማፍረስ አይቻልም። ይሁንና ሰጪው ስጦታውን ባደረገበት ጊዜ የተከለከለ ሰው እንደሆነና ስጦታውም በሞግዚቱ በኩል በደንብ ያልተደረገ ከሆነ ስጦታን ማፍረስ ይቻላል። በተጨማሪም ሰጪው በፍርድ እንዲከለከል ጥያቄ ቀርቦ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት ሰጪው ከሞተም ማፍረስ ይቻላል።
ሌላው ስጦታው የተደረገበት ምክንያት ግብረ ገብ ካልሆነ ወይም ሕገ ወጥ ከሆነ ስጦታው ፈራሽ ነው። ግብረ-ገብ የሚለው የሕጉ አገላለጽ በተለይም የማህበረሰቡን መልካም ጠባይ (ሞራል) መሠረት ያደረገ ሲሆን፤ ስጦታም ከዚህ ተቃራኒ በሆነ ምክንያት ከተደረገ ይፈርሳል። ምክንያቱም ስጦታ ውል በመሆኑ ውል ደግሞ ለሕግና ለመልካም ጠባይ የተቃረነ መሆን የለበትም። የስጦታው ምክንያት ክብረ ነክ፣ ጨዋነት የተጓደለበት፣ አሳፋሪና አስነዋሪ ድርጊትን የያዘ ከሆነ ከመልካም ጠባይ ተቃርኗል ማለት ይቻላል።
በመሠረታዊው የውል ሕግ መርህ መሠረት የተንኮል ሥራና መሳሳት ለውል መፍረስ ምክንያት ይሆናሉ። ነገር ግን ስጦታን በተመለከተ የሰጪው ወራሾች በተደረገው ስጦታ ተንኮል አለበት በማለት ስጦታው እንዲሻር መጠየቅ አይችሉም። በመሳሳት የተደረገ ስጦታ ከሆነ ግን ወራሾች እንዲሻር መጠየቅ ይችላሉ። ስህተቱም በተቀባዩ ማንነት ወይም በሚሰጠው ንብረት ላይ ከሆነ መሠረታዊ ስህተት በመሆኑ ስጦታውን ማፍረስ ይቻላል። «በችግር ሳለሁ የደረሰልኝ ወዳጄ እሱ ነው» በሚል ለሌላ ሰው ጥማድ በሬዎቹን በስጦታ የሚሰጥ ሰው መሠረታዊ ስህተት ፈጽሟል ማለት ነው። እዚህ ላይ ስጦታው ስህተት ወይም ተንኮል ያለበት ነው በማለት ሰጪው በሕይወቱ ሳለ ስጦታው እንዲሻር ክስ አቅርቦ እንደሆነ ወራሾቹ ክሱን መቀጠል እንደሚችሉ ልብ ይሏል።
ስጦታን ለማፍረስ የሚቀርበው ሌላው ምክንያት የተቀባዩ ውለታ ቢስነት ነው። ስጦታ ተቀባይ ውለታ ቢስ ነው የሚባለው ሟችን ለመውረስ የማይገባ የሚያደርግ ወንጀል ዓይነት በሰጪው ላይ የሰራ እንደሆነ ነው። በውርስ ሕጋችን እንደተመለከተው አንድ ሰው ሟችን ለመውረስ የማይገባ ነው የሚባለው ደግሞ ሟቹን ወይም የሟቹን ተወላጆች ወይም ወላጆች አንዱን ወይም የሟችን ባል ወይም ሚስት አስቦ በመግደል የተፈረደበት ወይም ለመግደል በመሞከሩ የተቀጣ ከሆነ ወይም በሐሰት በመወንጀል ወይም በሐሰት ምስክርነት ከእነዚሁ ሰዎች መካከል በአንደኛው ላይ የሞት ፍርድ ወይም ከአስር ዓመት የበለጠ የጽኑ እስራት ቅጣትን ለማስከተል የሚያሰጋ ሆኖ በዚሁ የሐሰት ሥራው የተቀጣ ሰው ከሆነ ነው። ስለዚህ ተቀባዩ ውለታ ቢስ ነው የሚባለው እንዲህ ዓይነት ድርጊት ከፈጸመ ነው።
በመሆኑም ተቀባዩ ውለታ ቢስ ሆኖ የተገኘ እንደሆነ ማናቸውም ዓይነት ተቃራኒ የውል ቃል ቢኖርም እንኳ ስጦታው ሊሻር ይችላል። ሰጪው ለውለታ ቢሱ ተቀባይ ምህረት አድርጎለት ከሆነ ግን ስጦታው አይሻርም። ሰጪው ሊያስተውል የሚገባው ሌላው ጉዳይ ስጦታውን ለመሻር ምክንያቱን ካወቀ በኋላ የመሻር ሃሳቡን በአንድ ዓመት ውስጥ ለተቀባዩ ካላስታወቀው ተቀባዩ ይቅርታ እንደተደረገለት ነው የሚቆጠረው።
ውለታ ቢስ ተቀባይን በተመለከተ የሰጪው ወራሾችም አውራሻቸው ያደረገውን ስጦታ እንዲሻር የመጠየቅ መብት አላቸው። ሰጪው በሕይወቱ ሳለ ለተቀባዩ ያደረገለትን ስጦታ የመሻር ሃሳቡን በማያሻማ አነጋገር አስታውቆት እንደሆነ፤ ተቀባዩ ሰጪውን ሆነ ብሎ እንዲሞት አድርጎ እንደሆነ፤ የውለታ ቢስነት ሥራው ሰጪው ከሞተ በኋላ ተሰርቶ እንደሆነ ወይም ሰጪው በስጦታ መሻር መብቱ እንዳይሰራበት ተቀባዩ ከልክሎት እንደሆነ ወራሾች ስጦታው እንዲፈርስ መጠየቅ ይችላሉ።
ስጦታ እንዲሻር የሚጠየቅበት ሌላው ምክንያት ክርክር ያለበትን ሀብት መስጠት ነው። ስጦታው በተደረገበት ጊዜ የተሰጠው ንብረት ክርክር ያለበት እንደሆነ በእንደዚህ ያለው ሀብት ላይ የተደረገው ስጦታ ፈራሽ ነው።
በመርህ ደረጃ ስጦታ በሰጪው ላይ ብቻ ግዴታ የሚጥል ቢሆንም በተቀባዩም ላይ ግዴታ ወይም ገደብ ሊጥል ይችላል። ይህ ግዴታ ወይም ገደብ ሕጋዊና ሞራላዊ መሆን አለበት። ሕጋዊና ሞራላዊ ካልሆነ ግን እንደሌለ ተቆጥሮ ስጦታው ይጸናል።
በሕጉ ከተቀመጡት የተቀባይ ግዴታዎች ውስጥ አንዱ ለሰጪ ቀለብ የመስጠት ግዴታ ነው። በውሉ ውስጥ ሰጪ ለተቀባዩ ቀለብ መስጠት አለበት በሚል በግልጽ የተቀመጠ የውል ቃል ባይኖርም እንኳ ሰጪው በድህነት ላይ ወድቆ ሲገኝ ተቀባዩ ለሰጪው ቀለብ የመስጠት ግዴታ አለበት። በድህነት የወደቀው ሰጪ ታዲያ ቀለቡን ሲፈልግ በሕግ ለርሱ ቀለብ የመስጠት ግዴታ ካለባቸው ሰዎች፤ ሲያሻው ደግሞ ከስጦታ ተቀባዩ መጠየቅ ይችላል። ለድሃው ስጦታ ሰጪ ቀለብ የሰጡ ሰዎች ደግሞ ቀለብ ሰጥተው ከሆነ በሰጡት ልክ ተቀባዩ እንዲሰጣቸው መጠየቅ ይችላሉ።
የሰጪን ዕዳ መክፈልም ሌላው የተቀባይ ግዴታ ነው። እዚህ ላይ ግን ተቀባዩን የሰጪውን ዕዳ እንዲከፈልለት ለመጠየቅ በመጀመሪያ በስጦታ ውሉ ውስጥ ይህ ግዴታ መስፈር አለበት። ይህ ብቻ ሳይሆን ሊከፍል የሚገባው የዕዳው ልክ በግልጽ የታወቀ መሆን አለበት በስጦታ ውሉ ውስጥ። ይህ ካልሆነ ተቀባዩን የሰጪውን ዕዳ እንዲከፍል ማስገደድ አይቻልም።
ስጦታው ለሰጪ እንዲመለስለት የሚያደርግ የውል ቃልም በተቀባዩ ላይ ግዴታ የሚጥል ሌላው ሁኔታ ነው። በዚህ ረገድ ከሰጪው አስቀድሞ ተቀባዩ የሞተ እንደሆነ ሰጪው የሰጣቸው ነገሮች እንዲመለሱለት የሚል ቃል በውሉ ውስጥ ማስገባት ይቻላል። እንዲህ ዓይነት የውል ቃል ከሌለ ግን ንብረቱ የተቀባዩ የውርስ ንብረት ይሆናል ማለት ነው።
ስጦታ እንዲሻር የሚቀርቡ ጥያቄዎች ደግሞ ስጦታው ከተደረገበት ቀን አንስቶ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ መቅረብ አለባቸው።
በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት እልባት ባገኘ አንድ ክርክር አቅመ ደካማ የሆኑት እማሆይ በደቡብ ክልል በአንድ የወረዳ ፍርድ ቤት ባቀረቡት ክርክር ባላጋራቸው የሆነው ግለሰብ ከሟች ባለቤታቸው ያገኙትን የእርሻ መሬት እጦርሻለሁ በሚል ሲጠቀምበት ከቆየ በኋላ የመሬቱን አላባ አብረን እንበላለን ልጄ ነው ብለሽ ፈርሚልኝ በማለት የስጦታ ውል አስፈርሞ ሥመ-ሀብቱን በእጁ ያደረጋል። ብዙም ሳይቆይ እማሆይን መርዳቱን ሲያቆም እሳቸውም በድህነት እጅ ወድቀው በቤተክርስቲያን ግቢ ውስጥ ተጠልለው ምጽዋት ጠባቂ ይሆናሉ፡፡
ከዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውጭ በየደረጃው ያሉ ፍርድ ቤቶች ፈርደውባቸው እስከ ፌዴራሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ክርክር አድርገው በፍጻሜው መሬታቸውን አስመልሰዋል። ስጦታ ተቀባዩ መሬቱን ሰጥተውኝ በራሴ ስም ይገኛል፤ የመጦር ግዴታህን አልተወጣህም የምባል ከሆነም ክሱ በይርጋ ይታገዳል የሚል መከራከሪያ አቅርቧል።
ይሁንና የሰበር ችሎቱ ከመጀመሪያውኑ ሰነዱን በማታለል ማስፈረሙ በማስረጃ ከመረጋገጡም በላይ በሕጉ መሠረት ሰጪው በድህነት ላይ ወድቆ ሲገኝ ስጦታ ተቀባዩ ለሰጪው ቀለብ የመስጠት ግዴታ እንዳለበት፤ ተቀባዩ ግዴታውን ባልተወጣ ጊዜ ደግሞ ሰጪው ውለታውን ለመሻር መብት እንዳለው ሕጉ ስለሚደነግግ ተቀባዩ ሰው መሬቱን ለእማሆይ ሊለቅ ይገባል ሲል የመጨረሻውን ውሳኔ አሳርፏል።
በደህና እንሰንብት!
አዲስ ዘመን ጥቅምት26/2012
(ከገብረክርስቶስ)