ኢትዮጵያ በተለያዩ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዘርፎች ዘርፈብዙ እመርታዎች አስመዝግባለች፤ አሁንም እያስመዘገበችም ትገኛለች፡፡ በተለይ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዘርፍ ትምህርትን በፍትሀዊነት ማዳረስና ማስፋፋት ችላለች፡፡ ነገር ግን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተጋረጡትን ፈተናዎች በጊዜ ካልተፈቱ የሀገሪቱ ዕድገትና ልማት ሊፈታተኑ ይችላሉ፡፡
የኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት ዕድሜው አጭር ከመሆኑ ባለፈ የተደራሽነት፣ የተገቢነት እና የጥራት ችግሮች ያሉበት ነው። በተለይ የትምህርት ጥራት መጓደል የትምህርት ዘርፉንም ሆነ ከዘርፉ የሚገኙትን ግብዓቶች በስፋት በሚጠቀሙ ተቋማት ውስጥ እየተስተዋለ ነው። በዘርፉ ብቃት ያላቸውና ለሚሰጡት የትምህርት ዓይነቶች የማይመጥኑ መምህራን፣ አንድም ከትምህርት ቤት በቀጥታ የተመረጡ፣ አልያም ከየወረዳው በፖለቲካዊ ብቃታቸው የተመለመሉ መሆናቸው የጥራቱን ጉዳይ ከመግደሉም በላይ ከታሰበው ግብ ለመድረስ የማይቻል ነው ማለት በቂ ምክንያት ሊሆን ይችላል።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ተደራሽ ለማድረግ ሰፊ ስራዎች የተሰሩ ቢሆንም ብቃት ያለው ተማሪ ለማፍራት አቅም አልተገነባላቸውም፡፡ ለዚህ ማሳያ ደግሞ ከየተቋማቱ የሚወጡትን ተማሪዎች ማየት በቂ ነው፡፡ የመምህራን ብቃት ማነስ፣ የትምህርት ግብዓት እጥረትና ተማሪዎቹ ከታች ጀምሮ በአግባቡ ተምረው አለመምጣት በምክንያትነት ይጠቀሳሉ፡፡
መንግስትም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ሲገነባ አስፈላጊ ግብዓቶችን አሟልቶ ባለመሆኑ ተማሪዎች አስላጊውን እውቀት ሳይዙ እንዲወጡ አድርጓቸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በነበሩት ዙሮች በተገነቡት ዩኒቨርሲቲዎችም የመሰረተ ልማት ችግር ቢኖርም፤ በአዲሶቹ ላይ ግን ይበረታል። ግንባታቸው እንኳን ሳይጠናቀቅ፣ አጥር ሳይኖራቸው አገልግሎት መስጠት የጀመሩት አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች ለተማሪዎች፣ ለመምህራንና በአጠቃላይ ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ፈታኝ መሆናቸው እየተገለፀ ነው። ችግሩ ይህ ብቻ አይደለም። የመሰረተ ልማት አለመሟላት የበርካታ ዩኒቨርሲቲዎችን መማር ማስተማር ሂደት እያወከ ተማሪና አስተማሪዎችንም እየፈተነ ይገኛል።
በአርሲ ዩኒቨርሲቲ የስነ ባህሪ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ዶክተር ሮብሳን ማርጎ እንደሚናገሩት፤ የአገሪቱ የትምህርት ፖሊሲና ስርዐተ ትምህርቱ በአግባቡ የተናበቡ አይደሉም፡፡ ስርዓተ ትምህርቱ የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘቡ አለመሆንና ከውጭ አገራት የተቀዳ መሆን ብቁ ሰው ሃይል ማፍራት ላይ እክል ፈጥሯል፡፡ ከመምህራን ዝግጅት አንጻርም ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በርካታ ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ምልመላው የሚካሄደው ያለአግባብና በፖለቲካ አመለካከት በመሆኑ ትምህርት አሰጣጡ ላይ ችግር ፈጥሯል፡፡ ለመምህራን የተሰጠው ትኩረት አናሳ በመሆኑ በቂ ተማሪ ማፍራት አልተቻለም፡፡
የተማሪዎች ዝግጅት ሲታይ ከመጀመሪያ ደረጃ ጀምሮ በብቃት እየተማሩ አለመምጣት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሲገቡ እራሳቸውን ለመግለፅ መቸገርና ትምህርቱን ተረድቶ ውጤታማ መሆን እንደሚያቅታቸው ይናገራሉ፡፡ ለውጥ ለማምጣት ከታች ጀምሮ መሰራት እንዳለበት በመጥቀስ፤ የተማሪዎች የትምህርት ዝግጅት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ያሳስባሉ፡፡ ሌላው ደግሞ የምዘናና ክትትል ችግር መኖር ተማሪዎች እውቀት ሳይጨብጡ ወይም እውቀት ማግኘታቸው ሳይረጋገጥ ከክፍል ክፍል እያለፉ በመምጣት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ እየገቡ እንደሚገኙ ያስረዳሉ፡፡
በእንደዚህ አይነት ሁኔታ የመጣ ተማሪን ሳይንቲስትና ስራ ፈጣሪ ይሆናል ብሎ ማሰብ አይቻልም የሚሉት ዶክተር ሮብሰን፤ የሚመለከታቸው አካላት በተለይ ቤተሰብ ክትትል ማድረግ እንዳለበት ይጠቅሳሉ። በትምህርት አካባቢ ያሉ የመንግስት ተቋማት ተናቦ ያለመስራት ችግሩን እንዳባባሰው የሚናገሩት ዶክተር ሮብሰን በአገሪቱ ፖለቲካና የትምህርት ሴክተሮች ተቀላቅለው መስራታቸው ብቁ መምህራን በየተቋማቱ እንዳይገቡ ማድረጉንና የፖለቲካ ርዕዮት አለሙን ብቻ የሚያራምድ መምህራንን እየተቀጠሩ እንደሚገኙም ይጠቁማሉ፡፡
እንደ ዶክተር ሮቢሳን ገለፃ፤ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚገኙ መምህራን በአግባቡ አያስተምሩም፡፡ መምህራኑ በሶስት ቀን ጊዜ ውስጥ አስተምረው የመፈተን ሁኔታዎች ይበዛሉ፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ማስፋፊያ ሲደረግ የቤተ መፅሀፍትና የቤተ ሙከራ ማዕከላት ግንባታ ትኩረት እየተሰጠው አለመሆኑ ብቁ ተማሪ ለማፍራት አላስቻለም፡፡ በአገሪቱ በቂ ዝግጅት ሳይደረግ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ከፍቶ ተማሪዎችን ማስገባት እየተለመደ መጥቷል። በሌላ በኩል የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው መምህራን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ማስተማር ችግሩን እያባባሰው ይገኛል፡፡
በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ኮሙንኬሽን ዳይሬክተር አቶ ደቻሳ ጉርሙ እንደሚናገሩት፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ብቃት ያለው ተማሪ ለማውጣት የትምህርት ስርዓቱን ማሻሻል እና የትምህርት ይዘቱን በመቀየር ለምርምር ስራዎች የሚያዘጋጃቸውን ትምህርቶች እየተካተቱ ይገኛሉ፡፡ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሁሉንም ትምህርት ዓይነት ከሚሰጡ ያላቸውን ሀብት ለብክነት ስለሚያጋልጡ በተወሰኑ ትምህርት አይነቶች እንዲወሰኑ ተደርጓል፡፡
ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኢንጅነሪንግ፣ በህክምና፣ በአፕላይድ ሳይንስ እና በግብርና ዙሪያ አተኩረው እየሰሩ እንደሚገኙ በመጥቀስ፤ በቀጣይ ተቋማቱን በህክምና፣ በግብርና በኢንጅነሪንግ እና በሌሎች ትምህርት አይነቶች ለየብቻ እንዲያስተምሩ ለማድረግ ዝግጅት መደረጉን ያመለክታሉ፡፡ ይህ አሰራር ተማሪዎች በተቋማት ውስጥ በአግባቡ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ እንደሚረዳ ያስረዳሉ።
እንደ አቶ ደቻሳ ገለፃ፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ቀድሞ ከነበሩ አጋር የውጭ አገራት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የነበረውን ትስስር እያሳደገ ይገኛል፡፡ በኢትዮጵያ የሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሊደገፉ በሚችሉበት መንገድ ላይ ሰሞኑንም ሰፊ ውይይቶች ተደርገዋል፡፡ በውጭ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ቀደም ብሎ የነበረውን በስልጠና፣ በሰው ሃይል ድጋፍ እና አቅም ግንባታ ስራዎች ለማስቀጠል እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት24/2012
መርድ ክፍሉ