በአሁኑ ወቅት መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር የሚያደርጋቸውን ጥረቶች ከማበረታታትና በጥብቅ ህጋዊ መስመር እንዲከናወን ከማገዝ ይልቅ ጥቃቅን ህጸፆችን በመምዘዝና ስስ ብልት በመፈለግ የተቃውሞ ድምፆችን ማስተጋባቱ አግራሞትን የሚፈጥር ትዕይንት እየሆነ ነው፡፡
ከምንም በላይ አግራሞት የሚፈጥረው ደግሞ ሰፊው ህዝብ አገሪቱ የዴሞክራሲ ጅማሮ ይበል የሚያሰኝ ነው ብሎ ይሁንታውን በሰጠበት፤ በርካታ አህጉራዊና እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ሳቀይር በኢትዮጵያ የተጀመረው ለውጥ ለምስራቅ አፍሪካ ብሎም ዴሞክራሲ እንደ ሰማይ ደመና የማይጨበጥ ለመሰላት አፍሪካ ትንሳኤ ይሆናል የሚል ተስፋ በሰነቁበት ወቅት መሆኑ አግራሞቴን የበለጠ ያንረዋል፡፡ ለውጡ በአግባቡ እየተጓዘ አይደለም ብለው የሚቃወሙት አካላት፤ ላለፉት 27 ዓመታት በዴሞክራሲ እና በፍትሃዊ ሃብት ክፍፍል እጦት ዜጎችን ሲያንገላቱና የሰቆቃ ደምጽን እንደ መዝናኛ አድርገው ሲዝናኑበት የነበሩ ጥቂት ቡድኖች መሆናቸው ደግሞ በእጅጉ ትኩረትን ይስባል፡፡
በእርግጥ ሰዎችን በጨለማ ቤቶች ሲገርፉ፣ አካል ሲያጎድሉ፣ የበርካቶችን ህይወት ምስቅልቅሉን ሲያወጡ የነበሩ፣ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለመተግበር ምላሻቸው እምቢታ የሆነና አፈሙዝ የመጀመሪያ ምርጫ ያደረጉ፣ በህዝቡ ልብ ውስጥ ሰፊ ቦታ የሚሰጣቸውን የፖለቲካ ድርጅቶች በአሸባሪነት ሲፈርጁ እና ሲያሳድዱ የነበሩ አካላት ለውጡን ባይቃወሙ ይገርም ነበር፡፡ ሁሉም በጊዜ ሂደት በፍትህ አደባባይ የእጃቸውን እንደሚያገኙ ከወዲሁ ስለተገነዘቡት ለበርካታ ዓመታት ያካበቱትን የክፋት ሴራ ዛሬ ሊጠቀሙ ላይ ታች እያሉ ነው፡፡
ለዓመታት በደህንነት፣ በፖሊስና በፀጥታ አካላት ውስጥ የተሰጣቸውን አገራዊ ተልዕኮ አሸንቀንጥረው ጥለው ለራሳቸው ፍላጎት ማስፈፀሚያ ያደራጇቸውን ቡድኖች፤ በሙስና የተጨማለቁ የእነርሱ አሸርጋጅ ባለሃብቶች፣ በጥቅም ሰንሰለት የተሳሰሩ ዘመዶቻቸውንና መሰሎቻቸውን፣ በመንግስትም ይሁን ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሰገሰጓቸውን ‹የክፉ ቀን ደራሻችን ናችሁ› ብለው ያስማሏቸውን ሁሉ ዛሬ ከጎናችን ሁኑ ለማለት ይዳዳሉ፡፡ ይህን አካሄድ በፊትም ሲጠቀሙበት ነበር፡፡
ለውጡ አልዋጥ ሲላቸው የለውጡን ማርሽ ቀያሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይን እስከ ወዲኛው እንዲያሸልብ ‹‹አለን›› የሚሉትን የእውቀት ጥግ ተጠቅመዋል፣ የጥፋት ሴራ ሸርበዋል፡፡ ከዚህም ሌላ በስልጣን ዘመናቸው ገዝቶ ለመኖር እንዲያስችላቸው ለይደር ብለው ባስቀመጧቸው የአስተዳደራዊ ወሰን ቅሬታዎችን በሁሉም ቦታ በተመሳሳይ ሠዓት በመቀስቀስ የህዝቦችን መፈናቀል እንደ አንድ የፖለቲካ ትርፍ ለመቀጠም ሲሯሯጡ ይስተዋላል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የሚታየው ይኸው ነው፡፡ ይህ ብዙም ሊያስደንቅ አይገባም፡፡ ሞት፤ ውስጣዊ ፍልሰት፣ የተደራጀ ሌብነት ከህግም ከሞራልም ልዕልና ውጭ ቢሆንም በለውጥ ወቅት የሚስተዋሉ ክስተቶች መሆናቸውን ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል፡፡
መሰል ድርጊቶች የለውጥ አደናቃፊዎች በቀብራቸው ዋዜማ ላይ ሆነው የሚያደርጉት ሽርጉድ ሲሆን፤ በርካቶች ለሚናፍቁት ለውጥ ደግሞ የንጋት ጮራ ልትፈነጥቅ መቃረቧን የሚያመላክት ነው፡፡ ሊነጋ ሲል ይጨልማል እንደተባለው ማለት ነው። በዚህ ወቅት ዋናው ነገር ከስሜታዊነት በፀዳ ሁኔታ እያስተካከሉ ወደ ተፈለገውና ለሁሉም ኢትዮጵውያን በእኩል ዓይን የሚዳኝ የዴሞክራሲ መስመር መዝለቅ ነው፡፡
አንዳንድ በእልፍኝ ጭብጨባ የሰከሩ ፖለቲከኞች፤ ወደ ሰፊው አዳራሽ ገብተው የሃሳብ ልዩነቶችን ማስተናገድ አይቻላቸውም፡፡ በመንደር አስተሳሰብ የታጠሩ ፖለቲከኞች አገር ከቁብ አይቆጥሩም፡፡ በዚህ አስተሳሰብ ውስጥ ለሁለት አስርት አመታት ሲወራጩ የነበሩ ፖለቲከኞች ዛሬም አሉ፡፡ ለውጡን መቀበል እጅ እጅ ብሏቸው የሞት የሽረት ትግል እያደረጉ ነው፡፡ በተለይም ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እየተቸረው ያለውን የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይን አስተዳደር ከእልፍኝ ወጥተው በአዳራሽ ውስጥ ሆነው ለመኮነን ብዙም የሞራል ብቃት ያላቸው አይመስለኝም፡፡ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ነፀብራቅ መታየቱም ያስደነግጣቸዋል፡፡ በመሆኑም በጉንጭ አልፋ ክርክሮች ላይ ተጥደው እሰጣ ገባ እየፈጠሩ ዛሬም ህዝብን እያታለሉ እስከ ግብዓተ መሬታቸው ቀን ድረስ በስልጣን ለመቀጠል ይዳዳቸዋል፡፡
በእርግጥ በለውጥ ማዕበል ውስጥ እየተጓዘች ያለችን አገር ፈተናዎች ቢገጥሟት አይገርምም፡፡ የትም ቦታ ቢሆን በአንድ ምሽት አገር አይገነባም፡፡ በመሆኑም ፈተናዎች የለውጡ አካል እንጂ ለውጡን ከታሰበው ቦታ የሚያስቀሩ ናቸው ብሎ ማመን የዋህነት ይሆናል፡፡ ‹‹ውድ ነገር ለቦታው ርካሽ ነው›› ይሉት ብሂል ሆኖ በአሁኑ ወቅት የተጀመረው ህዝባዊ መሠረት ያለውን ለውጥ ፀረ ለውጦች ከቁብ አይቆጥሩትም፡፡ በዚህም የተነሳ መሰረታዊ ነገሮች ከማየት ይልቅ፤ ጥቃቅን ስህተቶችን በመፈለግ ላይ ይጠመዳሉ፡፡ ከመግደል ማግስት ድል ያለ የሚመስላቸው፣ ዛሬ እንጂ ነገ የማይታያቸው ቀቢፀ ተስፋዎች አገርን የሚያከል ምስል አሳንሶ በጎራ እየተቧደኑ መጠዛጠዙ የሚበጅ ባይሆንም፤ ዛሬ ቀዳሚ ምርጫቸው አድርገዋል፡፡ እነዚህ አካላት በጥፋታቸው ልክ ይጠየቁ ሲባል ደግሞ መሸሸጊያቸውን ዘርፈ ብዙ አድርገውታል፡፡
በዚህች አገር የመደበቂያ አበዛዙ የት የየሌለ ነው፡፡ በአቅም ድክመት ሲገመገም፤ ከብሄሩ ጋር አያይዞ የተገመገመው ብቃቱ ሳይሆን ብሄሩ የሚመስለው የእውቀት እንግዳ የተበራከተበት ነች አገራችን፡፡ ወዲህ ደግሞ በበዓላት ቀን ሥራ ትቀራለህ፤ ታረፍዳለህ ስትለው መጀመሪው እሳቤው ስለማርፈድ እና መቅረት ስህተት መሆኑን ከመገንዘብ ይልቅ፤ እምነቱ የተነካበት የሚመስለው ሰው ብዙ ነው፡፡
አንድ ሌባ ሲታሰር፤ የታሰረው ሌባ ምን ሰርቆ ነው፣ እንደ አገር ምን ጉዳት አስከተለ፣ በህዝቡ ላይ የደረሰው ጫና እና ጉዳት እንዴት መመዘን አለበት የሚለው ቀርቶ የታሰረው ሰው ስሙ ማነው፣ ብሄሩና ሃይማኖቱስ እየተባለ ዝንቁልቁል አመክንዮችን ለመደርደር የሚሞክሩ በርካቶች ናቸው፡፡ እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ ደግሞ እውነተኛ የመፍትሄ አካል የሆኑ፤ ለጥቂቶች ሥርዓት ተገዥ ያልሆኑ አካላት ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ተጎጂ ይሆናሉ፡፡
ብዙ እንዳልተዋለድን፣ ተፈላልገን እንዳልተጋባን ዛሬ አንዳችን ለአንዳችን ፊት የምንነሳበት ምክንያት አለማወቅ እንጂ ደርሶ ምን ይሉታል? ለመሆኑ ሌባ፣ አክራሪ፣ ለማኝ፣ ሃብታም፣ ድሃ፣ ጎበዝ፣ ሰነፍ … የሆኑ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ መሰል ባህርያት ከግለሰቦች የሞራል ብቃትና ግለሰባዊ የልዕልና ዝቅጠት የሚመነጩ እንጂ እንዴት በብሄር ሊፈረጁ ይችላሉ?
ሌባ ብሄር የለውም፡፡ አክራሪነት መድረሻውም መነሻው ብሄር ሳይሆን በግለሰቦች የአስተሳሰብ አድማስ ሲጠብና ከእነርሱ ውጪ ያሉ አካላትን የሚያዩበት የእይታ አድማስ ሲጠብ የሚከሰት እንጂ አክራሪነት ተፈጥሮ ወይንም ለብሄር የሚሰጥ ሆኖ አይደለም፡፡ ሌብነትም እንዲሁ ሞራላዊ ግብረገብነት የጎደላቸው አካላት የአስተሳሰብ ንቃተ ህሊና የመውረድና ከምንም በላይ ራስን አብልጦ የመውደድ ደዌ ሲጠናወት የሚስተዋል የሞራል ዝቅጠት እንጂ ለብሄር የሚለጠፍ ታርጋ አይደለም፡፡ በእርግጥ የፖለቲካ ፅንፍ አገር ለማፍረስ እንደሚያደርስ ሁሉ፤ የደከመ የአስተሳሰብ ፅንፍ ግብረገብነትን ይከለክላል፡፡ ጽንፍ የነኩ ሁኔታዎች በአጭሩ በእንጭጩ ካልተቀጩ ጥፋታቸው ከጫፍ ጫፍ ነው የሚዳረሰው፡፡ አሁን በአገራችን የሚስተዋለው የጽንፈኞች ተግባርም ከላይ በጠቀስኳቸው ምክንያቶች የሚመነጩና ከእውነታው ጋር ፈፅሞ የማይጣጣሙ ናቸው፡፡
መንግስት እነዚህን ፀረ ለውጦችን አደብ ለማስገዛት የጀመራቸው ህጋዊ ጥረቶች በእጅጉ የሚበረታቱ ናቸው፡፡ ይህ ባይሆንና ችግሮች አፍጠው ቢወጡ ማጠፊያቸው አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለሆነም በአንክሮ አይቶ እንደየሁኔታው ህጋዊ እርምጃዎችን መውሰድ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ መንግስትም የሚወስዳቸው እርምጃዎችም እጅግ የተጠኑና ከእልህ አሊያም ከስሜታዊ ውሳኔ የራቁ መሆን አለባቸው፡፡ ሁሉም በሚዛኑና በልኩ መታየት አለበት፡፡ ጥፋተኞችን በሙሉ በአንድ ቀን ለህግ ማቅረብ አይቻልም፤ እንደዚያ ቢታሰብ እንኳን ደረጃው ይለያያል እንጂ በአገሪቱ ያለው ዜጋ በሙሉ ለህግ የማይቀርብበት አጋጣሚ ይኖራል የሚል እምነት አለኝ፡፡
የችግሮችን ጫፍ ብቻ ይዞ ማጋነን ተገቢ አይደለም፡፡ ችግሮቻችን እየገፉ፣ መቻቻል እያቃተንና በመነጋገር ሃሳብን በሃሳብ ማሸነፍ ሲሳነን ነገሮች ከቁጥጥር ውጭ ሊሆኑ እንደሚችሉም ቀድሞ ማሰቡ አይከፋም፡፡ በዚህ ወቅት ደግሞ በዓለም ኃያል የሆኑ አገራት በሙሉ በመጀመሪያው ደረጃ አሸማጋይ መስለው ይመጣሉ፡፡ ይሁንና እንድንሸማገልም በቅጡ አይሰሩም፤ የተንጠለጠለ ጉዳይ አስቀምጠው ይሄዳሉ፡፡ ለይደር የሚተዉት ጉዳይ እጅግ የበዛ ይሆናል፡፡ ቁልፉን ሰርተው መክፈቻውን ይዘው ይሄዳሉ፡፡ ስለዚህ በፈለጉት ሰዓት ለይደር የተዉትን ጉዳይ ይቀሰቅሳሉ፡፡
ምዕራባውያንና የሰለጠኑት ዓለማት በአፍሪካውያን ላይ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካው በማህበራዊ ጉዳችም ላይ እንደ ቤተሙከራ መጠቀማቸው ጸሀይ የሞቀው እውነት ነው፡፡ በተለይ ደግሞ በአንዴ መቶ ገዳይ የሆኑ ዘመናዊ ጦር መሳሪያዎችን በረቀቀ ሁኔታ ሰርተውት፤ ለአፍሪካውያን ረቂቅ በሆነ እና ጭካኔ በተሞላበት መንገድ እንዲገዳደሉበት በገፍ ያቀርቡላቸዋል፡፡ ግን እነርሱ የሚመጻደቁበትን ቴክኖሎጂ አያሳዩንም፤ እኛም ለማየት ያለን ጉጉት እምብዛም አይደለም፡፡ እንደ እነርሱ የረቀቀ ሃሳብ እንዲኖረን አይሹም፤ ጨርሰን ስንገዳደልም አይወዱም፡፡ ግን እኛ ስንራቆት እነርሱ ቤታቸውን ይሰራሉ፡፡ ከእነርሱ ያረጀ ያፈጀ ቴክኖሎጂ ለእኛ እንደ አዲስ ይመጣል፡፡ ሌላው ቀርቶ በእጃቸው የያዙትን ግን እኛ የምንጫረስበትን መሳሪያ እንድናመርት አይፈልጉም፡፡ በእጃቸው ላይ ካለው ቢያንስ አንድ ደረጃ ልህቀት ያለው ፈጠራ በእጃቸው አስገብተው ነው ወደ እኛ ያለፈበትን ቴክኖሎጂ የሚልኩት፡፡
እንግዲህ በሞት እንኳን ለመነገድ ብልጠት ይፈልጋል፡፡ እኛ ዕድሜ ዘመናችን በአንድ ስንዝር መሬት ስንራኮት፤ እነርሱ እኛ ካለንበት በሚሊዮን እጥፍ ርቀው በሌላ ፕላኔት ላይ ምርምር ያደርጋሉ፡፡ ስለዚህ ውስጣዊ ክፍተቶቻችን በወቅቱ ማረም ሲያቅተን፣ እርስ በእርሳችን መሸመጋገል ሲከብደን ለውጭ አካላት ፍላጎት ገበናችን አሳልፈን መስጠታችን እንደማይቀርም ከወዲሁ መታሰብ አለበት፡፡
ወንድም ወንድሙን ገሎ ጀግና ላይባል ነገር መገዳደላችንና ወንጀላችን ዘመናትን ቢሻገርም አስተሳሰባችን ድንበር አላሻገረም፡፡ እኛ ሰውን ለመግደል ስንፈላሰፍ በሰለጠነው ዓለም ከሞት አፋፍ ላይ ያለን ሕይወት እንዴት መታደግ እንደሚችሉ ይጨነቃሉ፡፡ እኛ በጦር መሳሪያ ስንገዳዳል፤ የጦር መሳሪያ አምራቾች ግን ትርፉቸውን ይቆጥራሉ፡፡ እኛ ህግ የሚፈልጋቸውን ተጠርጣሪዎችን በብሄር፣ በሃይማኖት፣ በአካባቢ ተወላጅነት… ተቧድነን ከለላ ስንሰጥ፤ ከጉያችን ደብቀን ስንቀመጥ እነርሱ ላንደርስባቸው በብዙ ርቀት ጥለውን ሄደዋል፡፡ አልተገናኝቶም! አለ የአገሬ ሰው።
እስኪ ዴሞክራሲን እንሞክረው፤ እስኪ መነጋጋር ባህላችን ይሁን፡፡ ወንጀለኞች ምሽጋቸው ብሄራቸውና ሃይማኖታቸው ሳይሆን ከእውነት አደባባይ ቆመው ንግግራቸው ከስራቸው የተስማማ ይሁን፤ ለእውነት ቆመን የፍትህ ሰዎች እንሁን፤ ዴሞክራሲን እንሞክረው፡፡ በእልፍኝ ጭብጨባ የሰከሩ ፖለቲከኞች፤ የአደባባይ ጥያቄ እንዲገባቸው እናድርግ በእልፍኝ ጭብጨባም የፍትህ አደባባይ አይፍረስ፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 20/2011
ክፍለዮሐንስ አንበርብር