ኢትዮጵያ በ2018 ዓ.ም ዝቅተኛ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ ለመሰለፍ የወጠነችውን ግብ ለማሳካት የአምስት ዓመት ግብ በመንደፍ እየተጋች ትገኛለች። የተያዘውን ግብ በተጠበቀው ልክ እውን ለማድረግም ገቢን ማሳደግ ወሳኝነት አለው። ገቢ የሌለው መንግስት እግሩ እንደተገየደ የእርሻ በሬ ይቆጠራል።
ስለዚህ የሀገሪቱን ገቢ ለማሳደግ ግብርን በዘመናዊ መንገድ፣ በትጋትና በብቃት መሰብሰብ ያስፈልጋል። ይሄንን ለማድረግ ደግሞ የማያወላዳ ውሳኔ መስጠት የሚችል ቆራጥ አመራር፤ ታማኝ፣ ብቃትና አቅም ያለው ሰራተኛ ሊኖር ይገባል። ይሄ ሲሆንና ሁሉም ኃላፊነቱን በተገቢው መልኩና ፍጥነት ሲሰራ ሀገራችንን በታሰበው ልክ በልማት ወደፊት ማራመድ ይቻላል። በዚህ ሂደት ህዝቡንም ከድህነት አረንቋ ማውጣት ቀላል ባይሆንም ከባድ አይሆንም።
የሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለማስፈጸም 2 ነጥብ 3 ትሪሊየን ብር ያስፈልጋል፤ የዚህን 75 በመቶ ገንዘብ ለመሸፈን የታቀደው ከግብር ገቢ፣ ቀሪውን ደግሞ ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች እንዲሁም ከእርዳታና ብድር ነው። ይሄ የሚያመለክተው የሀገሪቱን ዕድገት ወደፊት ለማራመድ ግብርን በወቅቱ፣ በተገቢው መንገድና በተጠናከረ መልኩ መሰብሰብ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ነው። ለዚህም ግብር ከፋዩ ህብረተሰብ በታማኝነት እና በትጋት ግብሩን እንዲከፍል ማስተማር፤ በሌላ በኩል ደግሞ በተገቢው መንገድ የውዴታ ግዴታውን እየተወጣ ያለውን ግብር ከፋይ ማበረታታት ያስፈልጋል። ለዚህም ጠንካራ ስራ መስራት፣ በኦዲት የሚገኙትን ክፍተቶች መድፈን፣ ያልተሰበሰቡና በየቦታው በምክንያትም ያለምክንያትም የተዝረከረኩ ገቢዎችን በአግባቡ እንዲሰበሰብ ማድረግ ይገባል።
የግብር አሰባሰቡን ዘመናዊ፣ አሰራሩንም ከአጭበርባሪዎችና ሙሰኞች የተጠበቀ ማድረጉ ላይ ትኩረት መስጠት ሲቻል ነው የታሰበው ግብር የሚሰበሰበውና ለታለመለት የልማት ተግባር የሚውለው። የግብር ስወራ፣ ማጭበርበር እና በሌሎችም መንገዶች የሚንቀሳቀሱና ለዚህም የሚተባበሩ ሰራተኞችና ኃላፊዎችንም መቅጣት ይገባል። ይሄ ካልሆነ አሁንም በግብር አሰባሰቡ ዙሪያ የሚታየው ችግር ከማቃለል ይልቅ ወደ ውስብስብነት የሚያድግ ይሆናል። የሚጠበቀውንም ገቢ ሀገሪቱ አታገኝም። አሁን እንደሚታየውና እንደሚሰማው ከግብር ሰብሳቢውም ሆነ ከግብር ከፋዩ አካባቢ ባለው ሸፍጥ እንዲሁም ስራን በብቃትና በቁርጠኝነት ባለመሰራቱ የገቢዎች ሚኒስቴር የሚጠበቅበትን ያክል ገቢ እየሰበሰበ አይደለም።
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት በገቢዎች ሚኒስቴር ላይ ከ2004 እስከ 2009 ዓመታት ባካሄዳቸው የክዋኔ፣ የፋይናንስና ሕጋዊነት ኦዲት ግኝቶች ነበሩ፡፡ በግኝቶቹ የተሰጡ አስተያየቶችና ማሻሻያ ሃሳቦች ያሉበትን ደረጃ አስመልክቶ የገቢዎች ሚኒስቴር የአፈጻጸሙን ሪፖርት ለተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል፡፡ በዚሁ መሰረት ከተገኙት 645 የፋይናንስ ኦዲት ግኝቶች ውስጥ የማስተካከያ እርምጃ የተወሰደባቸውና የተጠናቀቁት 101 ናቸው፤ 196ቱ ደግሞ በከፊል የተጠናቀቁና ቀሪዎቹ 348 ግኝቶች ደግሞ ገና በሂደት ላይ መሆናቸውን በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡ ይሄ በገንዘብ ሲታይ 11 ነጥብ 38 ቢሊዮን ብር ሲሆን፤ በተሠራው ሥራ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ገቢ ተደርጓል፡፡ 10 ቢሊየን ብር አሁንም አልተሰበሰበም።
የተወረሱ ንብረቶች አያያዝ፣ አጠቃቀምና አወጋገድ ላይ በኦዲት ግኝት ከተለዩት 19 ተሸከርካሪዎች ዘጠኙ ቢሸጡም፤ ቀሪዎቹ 10 ተሸከርካሪዎች ተሸጠው ገንዘቡ ገቢ አልተደረገም።
ጅንአድና አዲስ ፋና ድርጅቶች ላይ በተለየው የኦዲት ግኝትም፤ ጅንአድ በዱቤ ከገዛቸው የተወረሱ እቃዎች ሳይሰበሰብ ለረጅም ጊዜ የቆየ ብር 610 ሚሊየን 100ሺ 435.39 ዕዳ ውስጥ ወለድን ጨምሮ በአጠቃላይ 8 ሚሊየን 507 ሺ 343.79 ብር ገቢ አድርጓል፡፡ ለአዲስ ፋናም በዱቤ ከተሸጡ የተወረሱ እቃዎች ብር 10 ሚሊየን 950 ሺ 208.99 ሙሉ ለሙሉ ያልተሰበሰበ ሂሳብ መኖሩ በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡
ድርጅቶቹ በተለያየ ጊዜ ያለባቸውን ውዝፍ ገንዘብ እንዲከፍሉ ተጠይቀው ባለመክፈላቸው ጉዳዩ በህግ አግባብ ተይዞ እንዲፈታ ይደረጋል ቢባልም ይሄ ተፈፃሚ መሆን አልቻለም። ይሄ የሚያሳየው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ኃላፊዎችና ሰራተኞች ባለፉት አምስትና ስድስት ዓመታት ጠንክረው እየሰሩ ሳይሆን በምንቸገረኝነት ይንቀሳቀሱ እንደነበር ነው። ምክንያቱም ሪፖርቱ የሚያሳየው የተሰራው ስራ እጅግ ዝቅተኛ፤ ዛሬም ድረስ ያልተሰበሰበው ገቢ እና ያልተፈጸመው የማስተካከያ እርምጃ ሰፊ መሆኑን ነው።
ስለዚህ ይሄንን ኃላፊነታቸውን መወጣት በነበረባቸውና ባልተወጡ የተቋማት የስራ ኃላፊዎችና ሰራተኞች ላይ ህግን መሰረት ያደረገ ጠበቅ ያለ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል። እንዲሁም እዳ እያለባቸው የመንግስትን ገንዘብ ገቢ ባላደረጉ ተቋማት ላይም ተመሳሳይ ህግን መሰረት ያደረገ ተጠያቂነት መኖር አለበት።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 20/2011