ወተት የመሰለው የጸጉራቸው ሽበት አይን ይገባል።እሱን አጎፍረው ለተመለከታቸው መለስ ቀለስ ብሎ እንዲያያቸው ያስገድዳል። ትልቅ ሰው ትልቅ ሀሳብ አያጣምና ከእንደነዚህ አይነት ሰዎች ጋር ቆይታ ማድረግ ደግሞ የታሪክም፣ የተረትም ባለቤት ያደርጋል። እኔም ይሄንን እንደምናገኝ አስቤ የዛሬው የህይወት እንዲህናት አምዳችን እንግዳ እንዲሆኑን መርጫቸዋለሁ።
እንግዳችን አቶ መስቀሉ ባልቻ ይባላሉ። ከቀድሞዎቹ ከታዋቂ ደራሲዎች እና ጋዜጦች ከእነጳውሎስ ኞኞ፣ ብርሃኑ ዘሪሁን፣ በአሉ ግርማ ጋር የጋዜጠኝነት ህይወትን አሳልፈዋል።በመምህርነት ሰርተዋል። ከተማሪነታቸው ጀምሮ ከብዕር ጋር የተዋወቁ ናቸው። በዚህ ጥረታቸው ስምንት የግጥም መድብል በማዘጋጀት ለንባብ አብቅተዋል።
በተለይ በቅርቡ ለህትመት የበቃው” አማርኦሮ” የተሰኘ የግጥም መድብል ወቅታዊነትን የጠበቀ በመሆኑ ብዙዎች እንደወደዱላቸው ይናገራሉ።
መስቀላኮ
በ1943 ዓ.ም አርብ ጥር 21 ቀን ይህችን አለም የተቀላቀሉት አቶ መስቀሉ፤ የመጨረሻ ልጅ ሲሆኑ፤ ከሌሎች ልጆች በበለጠ በእንክብካቤ ያደጉ ነበሩ።በአርሲ ክፍለ አገር የጦሳ ወረዳ ሊጋባ ቀበሌ ተወልደው ያደጉት አቶ መስቀሉ፤ ምንም እንኳን እናት አባት ቢኖራቸውም ያሳደጋቸው የአካባቢው ማህበረሰብ ከቤተሰቡ ባልተናነሰ መልኩ እንደነበር ያስታውሳሉ።ማህበረሰቡ እውነትን ወዳድ አድርጎም ቀርጿቸዋል።
ይህ ደግሞ በቀጣይ ህይወታቸው ጭምር ሀቀኛ ሆነው እንዲኖሩ ረድቷቸዋል።ግን አንዳንዴ ውሸት የሚያሸንፍበት ጊዜ ያጋጥማልና ለውሸት ባይረቱም እንደተፈተኑበት ግን አይረሱትም። እናታቸው ሁል ጊዜ እውነት አሸናፊ ነው ይሏቸው እንደነበር የሚያነሱት አቶ መስቀሉ፤ በእውነት ውስጥ ያለውን የኦሮሞ ባህል፣ ልምድና ወግ እያዩም እንዳደጉ ይናገራሉ።
እናታቸው የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ ቢሆኑም አማርኛውን ሰምተው በኦሮምኛ በመመለስ አማርኛ በሚገባ እንዲችሉም ያበረቷቸው ነበርና አማርኛ መናገርን የለመድኩት በእናቴ ፍላጎት ነው ይላሉ።የቤተሰብ ምሰሶ እናት ስትሆን ብዙ ነገር ይቃናልና አቶ መስቀሉ በአማርኛም በኦሮምኛም የተሟላ ጸሐፊና ተናጋሪ ናቸው። አማርኛ ቋንቋን ያወቁት ኦሮምኛ ብቻ ይናገሩ የነበሩት እናታቸው በሰጧቸው ምክር መሰረት መሆኑንም አጫውተውናል።
ለአቶ መስቀሉ ይሄ ስም የወጣላቸው ከእናታቸው በመልክ ስለሚለዩ ነው።ፈረንጅ ትመስላለህ ይሏቸዋል።እናታቸው ደግሞ ጠቆር ይላሉ።ስለዚህ በኦሮምኛ “ ወገግታ፣ ፈገግ ያለ፣ ብርሃን ያለበት” ለማለት ሲፈልጉ መስቀላኮ ብለው ጠሯቸው።እንደውም ከፈረንጅ ነው የወለድሽይው ይባሉ ነበርና ይህንንም የሰጣቸውን አምላክ ለማመስገን ሲሉ ያወጡላቸው ስም መሆኑን ይናገራሉ።መስቀሉ የሚለውን ስያሜ መጠቀም የጀመሩት ደግሞ ትምህርት ቤት ከገቡ በኋላ እንደነበር ያነሳሉ።ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ለአጠራር እንዲመች በማሰባቸው ነው።
አቶ መስቀሉ በልጅነታቸው የተለያየ ቅጽል ስም ነበራቸው።ይሄውም ‹‹ነንቱ ቂና›› ይሏቸው ነበር።ይህ ማለት “አትንኩኝ ባይ” የሚል ትርጓሜን ይሰጣል።በባህሪያቸው ማንም እንዲነካቸው አይፈ ቅዱም። ከነኳቸውም አይለቁም።በእርግጥ በአቅምም ሆነ በቁመት ትንሽ ናቸው።ሆኖም ከነኳቸው ትልቅነታቸውን ያሳያሉ።እንዴት ከተባለ ጥበብ የተሞላው ንግግራቸውን በማሰማት ወይም ደግሞ አድፍጠው በማይገምቷቸው መልኩ በማጥቃት ነው።
እንዳይነኳቸው በር ይዘጋሉም።መጫወት እንኳን ቢኖርባቸው የጨዋታ ፍላጎታቸውን በመግታት እንዳይመቱ ያደርጉ እንደነበር ያስታውሳሉ።ይህንን አልፎ የመጣ ካለ ግን አያድርስ ነው።ምላሻቸው ቀላል አይሆንም።ስለዚህ ትንሽም ቢሆኑ የሚያከብራቸውና የሚወዳቸው ብዙ ነው።አቶ መስቀሉ ለአካባቢው ሰው ታዛዥ፣ ቅንና በእውነት መንገድ የሚራመዱ፤ ለሰዎችም አዛኝ ናቸው።
ሰዎች ይጎዱኛል፤ ይደበድቡኛል ብለው ስለሚያስቡ ከልጆች ጋር መጫወትን የሚፈሩ ጭምት ልጅ ናቸው።ስለዚህ ልጆች ሲጫወቱ ቁጭ ብለው ነው እነሱ የሚያዩት።ጨዋታ ካስፈለጋቸውም ከወንድሞቻቸው ጋር በቤት ውስጥ ከመጫወት ውጪ ምርጫ የላቸውም።
የእነ አቶ መስቀሉ ቤት በልጅ ብቻ ሳይሆን በልጅ ልጅም የታደለ ነው።በዚያ ላይ የአካባቢው ልጆች በእነርሱ ቤት ይቦርቃል።ስለዚህ ዘወትር ጨዋታን ሲያስቡ ቤታቸው እንጂ ውጪው አይናፍቃቸውም።በቤታቸው ማንም የሚሰድባቸውና የሚመታቸው ስለሌለም የማይሞክሩት የጨዋታ አይነት አልነበረም።ብዙ ጊዜ ግን ዘፈንን እንደሚወዱና ዘፈን ማውጣት ላይ ብቃት እንደነበራቸው ያስታውሳሉ።
በፈተና የታጠረው ትምህርት
‹‹መስቀሉ ማለት በርካታ ሰዎች ሲንከባከቡት፣ ሲገነቡትና ሲያንጹት የነበረና የበርካቶች ስሪት ነው›› የሚሉት ባለታሪኩ፤ ራሳቸው የነገሯቸውን መሰርት በማድረግ አባታቸው ይቆጣጠሯቸው እንደነበር ያነሳሉ።ምክንያቱ ደግሞ እርሳቸው አልተማሩም፤ ኤክስና ራይትንም አይለዩም።ግን ልጃቸው ጎበዝና የሚያኮራቸው እንዲሆንላቸው ይፈልጋሉ።ስለዚህም የመጀመሪያ ቀን ምልክቶቹን ይህ ምንድነው ሲሉ ጠየቁ።የትናንቱ ተማሪ የዛሬው አዛውንት አቶ መስቀሉም ኤክሱ ስህተት፣ ራይቱ ደግሞ ትክክል መሆኑን አስረዱ።አባትም ከዚያ በኋላ ያንን ይዘው ለምን ይህ ሆነ እያሉ ይጠይቁ ጀመር።በል ይህንን ቀይር፤ የሚያስፈልግህ ነገር ካለ አለሁልህ ማለታቸውን ቀጠሉ።
የአቶ መስቀሉ አባት ኤክስን መስቀል፤ ራይትን ከዘራ በማለት ከሰየሙ በኋላ ከትምህርት ቤት ሲመጡ ደብተራቸውን ገልጠው በማየት ዛሬ ጥሩ ነው፣ ዛሬ መጥፎ ነው ማለታቸው ያሳሰባቸው አቶ መስቀሉ አባታቸውን ላለማሳዘን ጠንክረው ማንበባቸውን ተያያዙት።በእያንዳንዱ ክፍልም የደረጃ ተማሪ እየሆኑ ማለፋቸውን ቀጠሉ።በዚህ ደግሞ አባታቸው ደስተኛ ናቸው።
አቶ መስቀሉ ፊደል የቆጠሩት ቄስ ትምህርት ቤት ገብተው ነው።ይህ የሆነው ደግሞ በቤት ውስጥ በእርሳቸው አቅም የሚሰራ አንዳች ነገር ስለሌለ ጊዜውን በአልባሌ ነገር ማጥፋት የለበትም በሚል እንደሆነ ይናገራሉ።ከዚያ አደግ ሲሉ ዘመናዊ ትምህርት እንደሚያስፈልጋቸው አባታቸው በማመናቸው የአንድ ሰዓት የእግር ጉዞ በማድረግ እንዲማሩ ሊጋባ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ላኳቸው።
ለትምህርት የሚላኩበት ቦታ ትልቅ ተራራ የሚወጣበትና የእግር ጉዞውም ከባድ እንደነበር ያስታውሳሉ። በአካባቢው ካሉት ልጆች ጋር አብረው ይላኩ ነበር፤ ያንን ተራራ መውጣት ስለማይችሉ በእድሜ ተለቅ ያሉ ሰዎች እየተሸከሟቸው እንደሚያግዟቸው አጫውተውናል።እስከ አራተኛ ክፍልም ይህ ድርጊት እንደቀጠለ አይረሱትም።ከአምስተኛ ክፍል በኋላ ግን አቅማቸው እየጠነከረ በመምጣቱ በራሳቸው ዳገት ወጥተው ቁልቁለት ወርደው ትምህርታቸውን ይከታተላሉ።
ዘጠነኛ ክፍል ሲገቡ ደግሞ ዳገት ቁልቁለት ማለቱ ቆመ።ሆኖም ግን ሁለት ሰዓት የሚፈጅ ጉዞ ማድረግ ተተካ። ይህን በእግር ሳይሆን በመኪና መመላለስ ግድ ይላል።እናም በክፍለ ሀገሩ ብቸኛ በሆነው አሰላ ትምህርት ቤት ከመመላለስ ለመዳን በአቅራቢያው ቤት ተከራዩ።እዛም ስንቅ የሚያቀብላቸው ወንድማቸው ሆነ።ወንድማቸው ስንቅ በማመላለስ ብዙ አልተንገላታም።ምክንያቱም በወቅቱ የአሜሪካን የሰላም ልኡካን ነበሩና እነርሱ ድጋፍ እያደረጉላቸው ምንም ሳይጎልባቸው እስከ 11ኛ ክፍል ዘለቁ።
ከዘጠኝ እስከ 11ኛ ክፍል አሰላ በራስ ዳርጌ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማሩት እንግዳችን፤ 11ኛ ክፍል ሲደርሱ ትልቅ የማይወጡት ፈተና ገጠማቸው።የተማሪ ካውንስል አባል ሆነው ሲሰሩ የስብሰባ ቀናቸው አርብ ቀን ላይ እረፍት ሰዓት በመሆኑ ይሳተፋሉ።ከእረፍት በኋላ የሚያስተምረው የውጪ ዜጋ ደግሞ ቀደም ብሎ ይገባና ሁልጊዜ ፈተና ይፈትናል።ድንገት ቶሎ ጨርሰው ሲመጡ እንኳን አርፋጅ ለማስገባት ፈቃደኛ አይደለም።ይህ የመረራቸው አቶ መስቀሉም ለዳይሬክተራቸው ተናግረው ይግባ የሚል ደብዳቤ ያጽፋሉ። መምህሩ ግን አሻፈረኝ አለ።
መልሰው ወደ ዳይሬክተሩ ቢሄዱም መልስ አጡ።በዚህም መልቀቂያ እንዲጻፍላቸው ጠየቁ።ለክስም መልቀቂያቸውን ይዘው ወደ ክፍለ ሀገሩ አስተዳዳሪ ዘንድ አመሩ።ለምን ተብሎ ተጠየቀና እንዲመለሱም ተደረገ።ሆኖም በዚያ የቆዩት ፈተና እስኪወስዱ ብቻ ነው።ምክንያቱም እርሱ ከተመለሰ አናስተምርም ብለው የውጪ ዜጋ መምህራን በሙሉ ትምህርት ቤቱን ለቀው ወጡ።
ይህ ያሳሰባቸው የትምህርት ጽህፈት ቤቱ ኃላፊውና ዳይሬክተሩም ተመካክረው የማጠቃለያ ፈተናውን ከወሰዱ በኋላ አዲስ አበባ ተማር ብለው ላኳቸው።ሆኖም እዚህም ቢሆን የሚሰማቸውና ሊያስገባቸው ፈቃደኛ የሆነ ትምህርት ቤት አጡ።በጥባጭ አንቀበልም አሏቸው።ስለዚህ አማራጭ ፍለጋ ሲዘዋወሩ የ11ኛ ክፍል ውጤታቸውን በመያዝ ለመምህርነት ተወዳደሩ።‹‹ልፋ ያለው ቢነግድ አይተርፈው›› እንዲሉ ሆነና እዚህም ሱፍ ካለበስክ አታስተምርም ተባሉ።
ተስፋ በመቁረጥ በቀጥታ ወደ ትምህርት ሚኒስቴር አምርተው በወቅቱ የነበሩትን ኃላፊ አናገሩ፤ ሥራ እንዲሰጧቸውም ጠየቁ።ማንም ግን ሊያደምጣቸው አልወደደም።ስለዚህም በተማሪነት ጊዜያቸው የጻፉት የግጥም መድብል መጸሐፋቸውን ይዘው ወደ ማስታወቂያ ሚኒስቴር አቀኑ።ይሄም ሳንሱር አስደርገው በማሳተም ገንዘብ ለማግኘት ነበር።ነገር ግን እዚያ ሲደርሱም ሌላ ነገር ገጠማቸው።ማህተም አድርጉልኝ ሲሉ በሁለት ኮፒ አምጣ ተባሉ።
በሌለ ገንዘብ ይሄንን በመባላቸው ተናደዱ። ተበሳጩም። ይህንን የተገነዘቡትና የገረማቸው የወቅቱ ኃላፊ ‹‹ማንኛውንም ስራ መስራት ትችላለህ›› ሲሉ ጠየቋቸው።ሥራ እንደሚናፍቁ ነግረውም በሀሳባቸው ተስማሙ።ኃላፊውም ከአንድ ሰራተኛ ጋር አያይዘው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ወደሚዘጋጅበት ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ተላኩ።በዚያም በተላላኪነት እንዲሰሩ እድሉ ተሰጣቸው።ይህ ደግሞ ሌላ እድል ይዞ መጣና ከመምህራን ማህበር ኃላፊው ጋር አስተዋወቃቸው።የመምህራን ማህበር ባቋቋመው ‹‹ ብርሀንህ ዛሬ›› በተሰኘ ትምህርት ቤት 12ኛ ክፍልን ለመማር ቻሉ።
12ተኛ ክፍልን በጥሩ ውጤት ያጠናቀቁት ባለታሪኩ፤ ውጤታቸውን ይዘው በኮተቤ መምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ ገቡ።በመምህርነት ሰልጥነው በዲፕሎማ ተመረቁ።ከዚያ በሙያው የተወሰነ ጊዜ ሰርተው በድጋሚ በሌላ የትምህርት መስክ ለመማር ኮተቤ መምህራን ኮሌጅን ተቀላቀሉ።የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ስነጽሑፍ ጥናት መስክም ተምረው በሙያው መስራታቸውን ቀጠሉ።ከዚያ በኋላ ግን ትምህርታቸውን አልቀጠሉም።በየአቅጣጫው የሚያጋጥማቸው ፈተና ይህንን ለማድረግ አላስቻላቸውም።ሆኖም የተለያዩ ስልጠናዎችን በመውሰድ ራሳቸውን ብቁ ለማድረግ ጥረት ማድረጋቸውን አጫውተውናል።
የሁለት ሙያዎች ፍትጊያ
መጀመሪያ ስራን “ሀ” ያሉት አዲስ ዘመን ጋዜጣ ውስጥ በተማሪነት ጊዜያቸው ነበር።በዚያም ሲሰሩ ተላላኪ ተብለው ሲሆን፤ ሆኖም ግን ከዚያ ያለፈ ሥራ በቦታው ያከናውኑ ነበር።ግጥም እየጻፉ በጋዜጣው ላይ እስከማሳተምም ደርሰዋል።የትርጉም ስራና የእርም ሥራም አንዳንዴ ይሰራሉ።ቁጭ ብሎ ማንበብም የበለጠ እውቀታቸውን ከፍ እንዳደረገላቸው ያስታውሳሉ። ከአንጋፋዎቹ በሳል ጋዜጠኞችና ደራሲያን እግር ለእግር ብለው ልምድ ቀስመዋል።
እርሳቸው አዲስ ዘመን ጋዜጣን ሲቀላቀሉ የአራተኛ ክፍሉ ጳውሎስ ኞኞን በትምህርት ደረጃ በልጠውት ነበር ።ያው ልዩነቱ የየቅል ቢሆንም።ከእርሱ ጸሐፊነቱ የልብና የጠለቀ መሆንን፣ በእውነትም ለጽሑፍ የተሰራ ሰው እንዳለ ተረድተዋል።እነርሱን መሆን ባይቻልም መምሰል ግን እንደሚቻልም አይተውበታል።ምክንያቱም በየቀን ተቀን ሥራቸው ላይ እርሳቸው አሉና።
ከእነ አቶ ብርሃኑ ዘሪሁንና ከኦሮማይ ደራሲ በአሉ ግርማ ብዙ እውቀትን መቅሰም እንደቻሉ ይናገራሉ። ስራም የጀመሩት አንጋፋው ጋዜጣ ቤት፤ ውላቸውም የእውቀት ባላባቶች ከሞሉበት ቤት ስለሆነ እጅግ ብዙ ልምድ እንዳገኙበትና ለዛሬ ህይወታቸው መለወጥ መሰረት እንደሆናቸው ያስረዳሉ።የጀማሪነት የግጥም መድብላቸውን ‹‹ የዘቢራው ወጣት››ን ለህትመት ያበቁት ስም ባላቸው ደራሲያን ዋስትና እንደነበር ያነሳሉ።
‹‹ብርሃኑ ዘሪሁን መስመር ቀዳጄና የጽሑፍ አስጀማሪዬ ነው።ገንዘብ ስለሌለኝ እውቀቴ እንዳይባክን የረዳኝ ሰው ነው።ይህን ትልቅ ሰው ሁሌም እንዳልረሳው በዚሁ የግጥም መድብሌ ላይ አንድ ግጥም አስፍሬለታለሁ›› ይላሉ።
የስራ ላይ ቆይታቸው ከአዲስ ዘመን ተላላኪነት ወደ መምህርነት ተሸጋገረ፤ ከኮተቤ መምህራን ማሰልጠኛ ልክ እንደወጡ በሲዳማ ክፍለ አገር ጌዲዎ አውራጃ ቆቲ ትምህርት ቤት ማስተማር ጀመሩ።ስድስት ዓመታትንም በዚያ አሳለፉ።ከዚያ ሲለቁ ደግሞ አርሲ ገቡና ጎቤ ትምህርት ቤት ማስተማራቸውን ቀጠሉ።በእዚያ ሦስት ዓመታትን ማሳለፍ ችለዋል።በዚህ ቆይታቸው አንቱታን ያተረፉ በመሆናቸው የብር ሜዳልያ እስከመሸለም ደርሰዋል።
አቶ መስቀሉ የእናት አገር ጥሪ ሲታወጅ ብዙ ሰው ሰንጋ እየገዛ ያቀርብ እንደነበር አንስተው፤ እነርሱ ግን ይህንን ለማድረግ የሚያስችል ገንዘብ ስለሌላቸው የፈጠራ ውጤታቸውን ይዘው መቅረብ እንደቻሉ ይናገራሉ።የፈጠራ ውጤቱም 30 ሺ ብር እንደተጫረተና ይህንን ሀሳብ ያነሳው ሰው ሌላ የሥራ አማራጭ እንደሚሰጠው ቃል እንደተገባ ያነሳሉ።ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥም ተጠርተው አርሲ ስልጠና እንደገቡና ለወረዳ አስተዳዳሪነት እንደታጩ ያስታውሳሉ።ይሄ የስልጠና እድል በዝዋይ ዱግዳ የወረዳ አስተዳዳሪ እንዲሆኑ አበቃቸው።
እንግዳችን፤ ከአንድ ዓመት በላይ በዚያ እንዳልቆዩ ያነሳሉ።ምክንያቱም ከአካባቢው ሰው ጋር በቅርበት መስራታቸውና ለህዝቡ እንጂ ለመንግስት ውግንና የሌላቸው በመሆናቸው በዚያ እንዲቆዩ አልተፈቀደላቸውም።እንዳውም አልፎ ተርፎ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ(ኢህአፓ) አስብሏቸው ነበርና ወደ ወህኒ እንደወረዱ ተደርገዋል።ለዓመት ያህልም ከእነካቢኔያቸው ከታሰሩ በኋላ ሌላ ለውጥ ሲመጣ ሌላ ሥራ ለምኔ ብለው ወደሚወዱት የመምህርነት ሙያ ተመለሱ።
‹‹መምህርነት እውቀት መጨበጫ፣ ማሳወቂያና በእውነት ተማሪዎችን ማነጺያ ነው።ስለዚህም ለእውነት ለመቆም የሚፈልግ ሁሉ ከዚህ ሙያ ሊለቅ አይገባውም›› የሚል እምነት ያላቸው ባለታሪኩ፤ ሌላ ሥራ ውስጥ ላለመግባት ወስነው ወደ ቀደመ ሙያቸው ገቡ።ኢተያ በተባለ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤትም ማስተማሩን ተያያዙት።ግን ያሉትን እንዳይጠብቁ የሚያደርግ አንድ ነገር ገጠማቸው።የልጅነት ህልማቸውን እውን የሚያደርጉበትን ሙያ የሚያሻግራቸውን መንገድ መረጡ።የሚፈልጉት ሙያ ነውና ጋዜጠኝነትን ተቀላቀሉ።
የጋዜጠኝነት ቤት
አቶ መስቀሉ ጋዜጠኛ መሆን እንደሚችሉ ያወቁት ገና ተማሪ ባሉበት ጊዜ ሰልፍ ስነ-ሥርዓት ላይ በሚያደርጉት ተሳትፎ ነበር።ከዚያ ይህንን ልምዳቸውን በአንጋፋው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ እየፃፉ አዳበሩት።ሆኖም ሁኔታዎች ገደቧቸውና ፍላጎታቸውን ገተው ሲያስተምሩ ቆዩ።ግን ውስጣቸው ዘወትር ይገፋቸው ነበርና ፍላጎታቸውን ለማርካት ትምህርት በሬዲዮ ፕሮግራም ለማዘጋጀት አዲስ አበባ ትምህርት መገናኛ ሬዲዮ በረዳት አዘጋጅነት ተቀጠሩ።በዚያም 16 ዓመታትን ሰሩ።
ከዚያም የስርዓት መቀየሩን ተከትሎ መዋቅር ለውጥ ተሰራ።እርሳቸውና አንድ የስራ ባልደረባቸው በብቃታቸው የላቁ ስለነበሩ በመዋቅሩ እንዲካተቱ ተብሎ ወደ ትምህርት ሚኒስቴር ተላኩ።ሆኖም በእነርሱ አሰራር የሚፈለገው ቦታ አልተሰጣቸውም።ስለዚህም ይህ መልካም እድል በሌሎች የመዋቅር ሰሪዎች ተቀባይነትን አጣ።በዚህም ወጣቱ ጋዜጠኛ መስቀሉ ፈተና ውስጥ ገቡ።በእናንተ መስክ ክልል ላይ እንጂ እዚህ የሚሰራ ስራ የለም ተባሉ።ስለዚህም ተንሳፋፊ ተደረጉ።ይህ ሁኔታ በጣሙን አበሳጫቸው። ሥራ ሳይቀጠሩ ለሁለት ዓመት ያህል በክርክር ማሳለፋቸውን ይናገራሉ።
በመጨረሻም በክርክሩ ሲያሸንፉ እስታትስቲክስ ላይ እንደመደቧቸው የሚናገሩት እንግዳችን፤ ከሙያቸው ጋር የማይገናኝ ስራ መስራት ስላልፈለጉ ስራቸውን ለቀው ወጡ።ከአማርኛው አዘጋጅነት ወደ ኦሮምኛ የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅነት ቀይረው ፋና ሬዲዮን ተቀላቀሉ።ከአመት በኋላ ደግሞ በኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ የሚዘጋጀውን የትምህርት ፕሮግራም ለማዘጋጀትም ተስማሙ።ስድስት ዓመታትን ካስቆጠሩ በኋላ አሁንም ይህ የመዋቅር ነገር ተከተላቸው ዳግም ተንሳፋፊ አደረጋቸው።
በሙያው ተስፋ ስለማይቆርጡ መፍትሄ ማፈላለጉን ተያያዙት።እድል ቀናቸውና በአዳማ ከተማ የኦሮሚያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ ለመስራት በፕሮዳክሽን ባለሙያነት ተቀጥረው ለሦስት ዓመታት ከሰሩ በኋላ ጡረታ ወጡ።
የድርሰት ጅማሮ
‹‹ሀሳቡ የተጸነሰው ገና በቤት ሳለሁ ነበር።ለአባቴ ግጥሜን ሳነብለት አበረታታኝና ለማህበርተኞቹ እንዳነብለት ጋበዘኝ።ከዚያ አነበብኩላቸው፤ እነር ሱም በደስታ አጨበጨቡልኝ፤ ከአባቴ በበለጠ አበረታቱኝ።ይህ ደግሞ በየቀኑ በማየው ጉዳይ ላይ ብዕሬን እንድመዝ ረዳኝ›› ይላሉ አቶ መስቀሉ፤ የድርሰት ሥራቸው ጉልበት ያገኘው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ሲሰሩ እንደነበር ግን አልሸሸጉም።
የመጀመሪያው መጽሐፋቸው ለህትመት ከበቃ በኋላ ይበልጥ እንዲሰሩ እድል ስለሰጣቸው ዛሬ ሰባት የኦሮሚኛ፣ አንድ የአማርኛ እንዲሁም አንድ ኦሮምኛና አማርኛን በጋራ የያዘ የግጥም መድብል ለአንባብያን አድርሰዋል።አሁኑ በተለይ ‹‹ አማር ኦሮ›› የሚለው የግጥም መድብላቸው ወቅቱን የዋጀ መሆኑን ይናገራሉ።
በአብዛኞቹ የግጥም መድብሎቻቸው ማህበራዊ ጉዳዮችን የሚያትቱ ናቸው።ወቅታዊነትን ይዞ መጻፍ ስለሚወዱ የህብረተሰቡን ችግር በሚያሳይና መፍትሄው ምን መሆን እንዳለበት በሚያመላክትበት ሁኔታ ይጽፏቸዋል።በተለይ መንግስትን ለማህበረሰቡ እንዲያድር ከማድረግ አንጻር ብዙ ቁምነገሮችን የሚያስጨብጡ ነገሮችን አንስተዋል።
ማህበረሰቡም የአባትና የእናቱን ባህል እንዲጠብቅ፣ ለአገሩ እንዲኖር ከማድረግ አንጻር ይመክሩበታል።ሰዎችንም ያመሰግኑበታል።ተስፋ ሰጪ ነገሮችም በግጥሞቻቸው ይካተታሉ።
ቤተሰብ
‹‹ቤተሰብ ለመመስረት ሁለት መስፈርቶች ነበሩኝ።እናቴን በጣም ስለምወድ ከእናቴ ጋር መግባባት የምትችል እንዲሁም የአካባቢዬ ሰው ብትሆን የሚለው የመጀመሪያ ምርጫዬ ነው።ሁለተኛው ደግሞ የኢኮኖሚ አቅሙ ስለሌለኝ ገንዘብ የሌላትና ራሷን በራሷ የማታስተዳድር ሴት ምርጫዬ አይደለችም።የሚል ነው። በመሆኑም የተማረችና ሥራ ለማግኘት የምትችል መሆን አለባት›› ይላሉ ባለቤታቸው በምን መስፈርት ተመርጣ እንዳገቧት ሲናገሩ።በዚህም አቶ መስቀሉና ባለቤታቸው የተገናኙት በኮሌጅ አንድ ክፍል ውስጥ በሚማሩበት ወቅት ነበር።
ከአካባቢያቸው የመጣችው የዛሬዋ ባለቤታቸው በትምህርት ክፍላቸውም ብቻ ነበረች።ስለዚህም ለእርሳቸው ብሏት ነበርና ከጎናቸው ወስዶ አስቀመጣት።ጓደኝነቱና በትምህርት መረዳዳቱ ሲጠብቅ ወደ ፍቅር ተቀየረና የትዳር አጋር ለመሆን በቁ።ዛሬ የስድስት ልጆች አባትና እናት ናቸው፤ በርከት የሚሉ ልጆች ደግሞ አያት ሆነዋል።ሁሉም ልጆቻቸው ደግሞ ተምረው በስራ ላይ ይገኛሉ።
አቶ መስቀሉ ከጋዜጠኝነቱ ሙያ ባልተናነሰ የመምህርነት ሙያንም እንደሚወዱ ለማሳየት የመጀ መሪያ ልጃቸውን መምህር ብለው እንደሰየሙትም አጫውተውናል።እርሱም አሁን ብሪቲሽ ኤምባሲ ውስጥ እየሰራ ይገኛል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ጋዜጠኝነቱን ሙያቸውን የወረሰች ልጅ እንዳለቻቸውም ነግረውናል።
መልዕክተ መስቀሉ
‹‹እኔን ብዙ ሰው አንፆኛል›› የሚሉት አቶ መስቀሉ፤ አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ በጣሙን ያሳስባቸዋል። ሰው ሰውነቱን ረስቶ ለሌሎች መጠቀሚያ ሲሆን ማየት ህመም ይፈጥርባቸዋል።ምክንያታቸው በእርሳቸው ጊዜ ሰው ለሰው ገንቢ እንጂ አፍራሽ አይደለም።ትልቅ ተራራን እንዴት መግፋት እንደሚችል ያስተምረዋል እንጂ እየዋሸ አገርን እንዲንድ አያስተምረውም።እናም የያኔው እኛ የተገነባንበት መርህ ይምጣ ባይ ናቸው።ለዚህ ደግሞ በተለይ ወጣቱ የአባቶችን ምክር ሰሚ መሆን አለበት ይላሉ።
አዕምሯዋችን እውነት ብሎ የሚቀበለው ነገር ደግመን የምንመግበውን ነው። ስለዚህም አዕምሯችንን የመልካም እና የክፋት፤ የልማት እና የጥፋት፤ የእውቀት እና የድንቁርና፤ የውድቀት እና የድል ነገሮች ተለይተው ካልተሰጡት የሚቀበለውን ያጣል።በተመሳሳይ መልካሙን ወይም መጥፎውን ለይተን ስንመግበው ደግሞ በመገብነውና ባስለመድነው መልኩ ይጓዛል። እናም መመገብ ያለብን ምን እንደሆነ መለየት ያስፈልጋል። በተለይም ሌላ እንዲመራንና ለአዕምሯችን መጥፎ ነገሮችን እንዲመግብ እድል መስጠትን ማቆም የመጀመሪያው ሥራችን መሆን አለበት።ምክንያቱም የእኛ ሳንሆን እንድንቀር ያደርገናል።ዛሬ ብዙዎች እንደበግ የሚነዱት እራሳቸውን መሆን ስላልቻሉ ነው።ለራሳቸውም መልካም ነገርን አልመገቡትም።ስለዚህ መንቃት ይገባል ይላሉ።
‹‹የሰው ልጅ ውድቀት አንደኛው መንስዔ የውሳኔ ማጣት ነው። አንድ ሰው ምንም ያህል እምቅ እውቀት ቢኖረው፤ ምንም ይህል የሚያስደንቅ ሃሳቦችን ማመንጨት ቢችልም ውሳኔ መወሰን ካልቻለ አቅሙ ሁሉ ከውስጡ አይወጣም።›› የሚሉት አቶ መስቀሉ፤ ውሳኔ አቅም እንዲያገኝ ጽናትን ማከል እንደሚያስፈልግም ይናገራሉ።
አዲስ ዘመን ጥቅምት23/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው