በእምነት አንጻር
ጥቅምት በቁሙ፤ ስመ ውርኅ (የወር ስም) ከመስከረም ቀጥሎ የሚገኝ ሁለተኛ ወር ነው። ዘይቤው የተሠራች ሥር ይላል። ጥንተ ፍጥረትን፤ ጥንተ ዓለምን ያሳያል። ጽጌውን አበባውን መደብ አድርገው ሲፈቱት የፍሬ ወቅት፤ የእሸት ሠራዊት የሚታይበት እንደማለት ነው። ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በመጽሐፈ ሰዋስዋቸው (1948፤508) እንደሚሉት ዕብራውያን ጥቅምትን አታሚንህ ወይም ኤታኒም ይሉታል። ይህም ሰባተኛ ወር ሲሆን ትርጉሙም ጥቅምት ማለት ነው። ዓለም የተፈጠረውም በጥቅምት ወር ነው።
በፀሐይ ቁጥር የመስከረም ጫፍ ይሆናል። የጥቅምት ወር ዘመነ ጽጌ በሚልም ይታወቃል። በግእዝ ጸገየ ማለት አበበ፤ ፍሬ አፈራ፤በውበት ተንቆጠቆጠ፤በደም ግባት አጌጠ፤የፍሬ ምልክት አሳየ ማለት ነው። ከዚሁ ግስ ላይ ጽጌ ጽጌያት ብሎ ስም ማውጣት ሲቻል አበባማ፤ ውበታማ፤ አበባ የያዘና የተሸከመ፤ ለማለት ደግሞ ጽጉይ ይላል።
በሀገራችን የመፀው ወቅት ምድር በልምላሜና በልዩ ልዩ ውበት የምትንቆጠቆጥበትና የምትሽቀነደርበት ጊዜ በመሆኑ በየሳምንቱ እሑድ ከመንፈቀ ሌሊት ጀምሮ በየአድባራቱና ገዳማቱ ማኅሌተ ጽጌ የሚቆሙና ሰዓታት የሚያደርሱት ካህናት እመቤታችንን ቅድስት ድንግል ማርያምን በአበባ፤ በትርንጎና በሮማን ፍሬ እየመሰሉ ለፈጣሪ መዝሙርና ምስጋና ያቀርባሉ።
የአርባ ቀኑ ዘመነ ጽጌ (ወርኃ ጽጌ) መታሰቢያነቱ ለድንግል ማርያምና ለኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እመቤታችን ልጇን ይዛ ከሰሎሜና ከዮሴፍ ጋር በምድረ ግብጽ እንደተሰደዱ የደረሰባቸውን ጭንቅና መከራ፤ ረሀብና ጥም፤ እንግልት ያመለክታል። እንደዚሁም ከምድረ ግብጽ ወደ ናዝሬት መመለሳቸውን ያስታውሳል። በጥቅምት ወር የሚከናወነው የወርኃ ጽጌ የሰንበት ማኅሌት መዝሙርና ቅዳሴ መረግድ የክብር ይዕቲውና የዕጣነ ሞገሩ ቅኔዎች ሁሉ ዘመነ ጽጌን የሚቃኙ ይሆናሉ።
በዘመነ ጽጌ በአበባው ወቅት በአገር ቤት እሑድ እሑድ በየቤቱ ወይንም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አገሬው በወረፋ እየደገሰ፤ ነጭ ጠላና ጥቁር ጠላ እያማረጠ፤ እንጀራና ወጥ እያዘጋጀ የጥቅምት ቃሪያ ከጓሮው እየቆረጠ ወይም እየገዛ የቃሪያ ስንግ፤ ክሽን ወይንም የቃሪያ ክትፎ እያዘጋጀ ማኅሌተ ጽጌ ቆመው ከአደሩ ካህናት ጋር ሲገባበዝ ይውላል። በድንገት ፀጉረ ልውጥ እንግዳ በድግሱ አካባቢ የሚያልፍ ከሆነ በሞቴ አፈር ስሆን ግባና ቀምሰህ ሂድ ተብሎ ይጋበዛል።
በተፈጥሮ ጸጋ ረገድ
በመላ ሀገራችን አስገራሚ የተፈጥሮ ትእይንት የሚታየው በጥቅምት ወር ላይ ነው። በጥቅምት ላይ የቆላውንና የደጋውን መሬት በኑግና በሱፍ አበባ፤ በጤፍ በባቄላ፤ በአተርና በማሽላ — ሰብል ተሸፍኖና አረንጓዴ.፤ ቢጫ፤ቀይ፤ጥቁር፤ገብስማ/አፈርማ መልክ በአለው ኅብረ ቀለማት አጊጦ ሲያዩት ሠዓሊ በመልክ በመልኩ እየመጠነ ያስቀመጠው ሥዕል ይመስላል። በተለይ በጥቅምት ወር ላይ ከአውሮፕላን ላይ ሆኖ የኢትዮጵያ መልክዓ ምድር ሲታይ የምድሪቱ ኅብረ ቀለም የሚሰጠው ደስታ ይህ ወሰንህ አይባልም።
አገራችን የደስታና የኩራት ምን መሆኗን በዚህ ለማረጋገጥ ይቻላል። በዚህ ወር አገር በቀል የሆኑት የበረሀና የደጋ ዛፎች ለምሳሌ ዋንዛ፤ ዋርካ፤ ዶቅማ፤ አጣጥ አምቡስ፤ ጨጮ፤ ብሳና፤ ግራር፤ ክያ፤ ለንቋጣ፤ ዋሽት፤ ሮቃ፤ እንኮይ፤ ሸምበቆ፤ ወይራ፤ ድግጣ፤ እምቧይ፤ ጫቅማ፤ እንጆሪ፤ ኮሽም፤ አጋም፤ ልምጭ፤ መድኃኒትነት ያላቸው ከሴ፤ ዳማከሴ፤…የሚታወቁት ቅጠላቸው፤ ልምላሜያቸውና ውበታቸው ይማርካል።
እንደ ሮቃ፤ ቀንጦ፤ ግራዋ፤ጥቁር እንጨት—ለምልመው ሲታዩ የበጋ ድርቅ ቅጠላቸውን የማያረግፍባቸውና የማይጠወልጉ ይመስላሉ። በጥቅምት ወር እንደ ቀጋ፤ እንጆሪ፤ እሽቃሞ፤ ሽነት፤… ፍሬያቸው የሚበላ ዛፎች በከብት እረኞች ዘንድ በእጅጉ ተወዳጆች ናቸው። ከሣር ዓይነቶች ረጃጅም ሰንበሌጥ፤ ቄጠማ፤ ትቁራጥ፤ ገፈፎ፤ ስንደዶ፤ አክርማ፤ የሚባሉት ተንቸርፍፈው ይታያሉ።
በዚህ ረገድ በጥቅምት ወር ላይ በመላ ሀገራችን ወደሚገኙ ገጠራማ ቀበሌዎችና መንደሮች የሚጓዝ ሰው በሚያየው አረንጓዴ ነገር ሁሉ ተደስቶና መንፈሱ ታድሶ እንደሚመለስ የታመነ ነው። በበኩሌ በዚህ ወር ላይ ማየት ደስ የሚለኝ በተመናመነ መልኩም ቢሆን ከጎሐ ጽዮን እስከ ደጀን ያለውን የዓባይ ሸለቆ መልክዓ ምድርና በልዩ ልዩ ዐዝርዕት የተሸፈነውን መሬትና የዐርባ ምንጭን እግዜር ሠራሽ ደን ነው።
በባህላዊ መንገድ
በሀገራችን ልክ እንደመስከረም ወር ሁሉ ለጥቅምት ይዘፈንለታል። የጨዋታ መድረክ ይዘጋጅለታል። ለምን ቢባል በመስከረም ላይ ግምቡጥ (ገና ያልበሰለ) የነበረው እሸት በትክክል የሚደርሰው፤ የፈነደቀ አበባ በትክክል የሚደምቀው፤ ለመድኃኒትነት የሚያገለግለውና በጥቅምት እስጢፋኖስ የተቆረጠ ማር፤ ከዋሻ ውስጥ፤ ከመሬት ወይም ከእንጨት ላይ የወጣ ጣዝማ ማር የሚገኘው በዚሁ ወር ላይ ስለሆነ ነው። በተጨማሪ የሰማዩና የምድሩ ቅዝቃዜ የሚረግበው፤ ምድር ከደጋ እስከወይና ደጋና እስከ ቆላ አረንጓዴ ካባ የምትለብሰው ፤ ወንዞችና ፏፏቴዎች ጠርተውና ኩል መስለው በየፏፏቴውና በየጅረቱ እየተፍለቀለቁ በእርጋታ የሚፈስሱት በጥቅምት ወር ላይ ነው።
የሜዳው ሣርና ግጦሹ የተትረፈረፈ ስለሚሆን ከብቶች የሚያምር መልክ ያወጣሉ። በክረምት ብርድና ረሀብ የተጎዱ ሰዎች በጥቅምት ወር ላይ የበቆሎ፤ የስንዴ፤ የሰመሬታ፤ የማሽላና ዘንጋዳ… እሸት እንደልብ ስለሚበሉና ወተትም እንደፈለጉ ስለሚጠጡ በደስታ ይፈነድቃሉ።
ቆለኛው የማር እሸት ቆርጦ፤ ጥመም የማሽላ እሸት ተሸክሞ ከተማ ወይም ደጋ የሚኖሩ ዘመዶቹን ይጠይቃል ። እከሌኮ ለእገሌ የማር እሸት፤ የማሽላ ጥመም (ፍሬው እንዳይደርቅ በነጠላ ተጠቅልሎ የታሠረ የማሽላ፤ ያሞራቴ እሸት)፤ የጥንቅሽ አገዳ፤ የቃሪያ እሸት አመጣለት ኑሮው ሁሉ እሸት ይሁን እየተባለ ይመረቃል።
ደገኛው በበኩሉ በጥቅምት ላይ ወተት እንደልብ ስለሚያገኝ ከተማ ለሚኖረው እና ቆላ ለሚገኘው ዘመዱ ወተቱን ቅቤውን ፤ አይቡን ወገሚቱን ጭኖ ያመጣለታል። ከተሜውም ገጠር ለሚኖረው ወገኑ ልብሱን፤ ማጭዱን መጥረቢያውን፤… በአጠቃላይም አዝመራ ለመሰብሰብ የሚረዱ የሥራ መገልገያ መሣሪያዎችን በመግዛት ያግዘዋል። በዚህም የቆለኛው፤ የደገኛውና የከተሜው ማኅበራዊ ኑሮ ምን ያህል ጠንካራ እንደሆነ ለመረዳት ይቻላል።
ሰዎች እዚህ ደረጃ ላይ የሚደርሱት ጨለማውንና ነጎድጓዳማውን የክረምት ወቅት በመላ አልፈው ነው። በግንቦትና በሰኔ ወር ላይ በየጓሮው የተዘራው ጎመን እንደልብ ስለሚበቅልና ስለሚገኝ «ታፈሰ» እየተባለ ይጠራል። የገጠር ልጆች በክረምት ወር ላይ የእህል እጥረት ስለሚገጥም እንጀራ ኩርማን ኩርማን እየሆነ ተቆርሶ፤ በኩርማኒቱ ላይ ጎመን እየተቆለለ ስለሚሰጣቸው
“እንግዲህ ጀመረ ሰኔ አቆለቆለ፤
በኩርማን እንጀራ ጎመን ተቆለለ “ እያሉ ቢያማርሩትም ጎመን ግን የረሀብተኛውን ሁሉ ነፍስ በክረምቱ ተሸክሞ እሸቱ ወደሚያፈራበት ወደ መስከረምና ጥቅምት በማድረሱ መመስገን ሲገባው ተንቆ
“ የጎመን ምንቸት ውጣ፤
የገብስ ምንቸት ግባ “ሲባል ከመበሳጨቱ የተነሣ እያዘነ በጥቅምት ወር ላይ እንዲህ እያለ ኀዘኑን ይገልጻል።
“እኔው ተቀርድጄ እኔው ተቀንጥሼ ባወጣኋት ነፍስ፤
በጥቅምት ወር ጋልቦ በሰጋር ፈረስ፤
ደረሰ በቆሎ ባለዘጠኝ ልብስ።
አትከራ ገብስ፤
ጎመን ባወጣው ነፈስ።”
በክረምት ወር ላይ በየቦታው እንደልብ በመገኘቱ ታፈሰ የተባለውና እንደ ርካሽ ነገር የተቆጠረው ጎመን በጥቅምት ወር ላይ ከነአካቴው ዘርዝሮ ጥቅም መስጠት ሲያቆም ስለሚበሳጭ
«ታፈሰ ታፈሰ ብላችሁ ስትለፉኝ፤
ራሴም ሸበተ እንግዲህ እረፉኝ ።» ብሎ ተስፋ በመቁረጥ ኀዘኑን ይገልጻል።
በጥቅምት ወር የገጠር ወጣቶች በየሰፈሩና በየመንደሩ በብዛት እየተገናኙና የበቆሎ እሸትና የማሽላ ጥመም (አሥር) እየጠበሱ እሸቱንና ውልብኙን በመብላትና ወተታቸውን በመጠጣት እንዲህ በማለት ሲዘፍኑና ሲጨፍሩ ይሰማሉ።
«አገር ቤት በጥቅምት አገር ቤት በኅዳር፤
ታብባለች ነሮ ታብባለች ትዳር።
እንጨዋት እንጂ እየጠጣን ጠላ፤
በሬ እንኳ ያናፋል ገለባ እየበላ።
የጥቅምት እሸት ነሽ የመስቀል አበባ፤
እቱ የት ሔደሻል ሳጣሽ ሆዴ ባባ።
የጥቅምት አደይ፤
ይናዳል አሉ ይናዳል ወይ።
ቆላም ሰው አለወይ በዚያ በነዳዳ፤
የምኮረሸም የጥቅምት አገዳ።
ነይልኝ ጉብሌ ልይሽ እንደልብ፤
ተናዳፊይቱ የጥቅምት ንብ።
ድረሽ በማለዳ፤
ድረሽ ከብቶቼን ስነዳ ።
አንድ ላም አለችኝ እበላለሁ በእርጎ፤
የጎረቤትን ልጅ እዚያው ኮተት አርጎ።
የጎረቤትን ልጅ የጥቅምት በርበሬ፤
እዚያው ኩርሽም ኩርሽም ሳያሰሙ ወሬ።
ቀይ ነሽ አካሌ የጥቅምት ድንግዝ፡
ከቤትሽ ልገዛ ያለደመወዝ» እያሉ ሠፈሩን ያደምቁታል።
ድንግዝ ልክ እንደ ጥንቅሽ የሚመጠጥ ቀይ መልክ ያለውና በበረሀ ውስጥ ከማሽላ ጋር አብሮ የሚበቅል ጣፋጭ አገዳ ነው። ግጥሙ የተገጠመው የወጣቷ ቅላት ከድንግዝ መልክ ጋር ስለሚመሳሰል ነው ። የተገጠመላትና የተዘፈነላት ወጣት ልክ እንደድንግዝ ትጣፍጣለሽ ለማለትም ጭምር ነው። በአካባቢው ባህል መሠረት ልጃገረድ ስትታጭ «እገሊትኮ ድንግዝ የመሰለች ቆንጆ ናት » ይባላል። በጥቅምት ወር ምሽት ወይንም በበዓል ቀን ልጃገረዶችም በወንዶች ዙሪያ ሆነውና ወንዶችን ለማናደድ ብለው ይዘፍናሉ። በተለይ በድንግዝ አገዳ ተመስላ የተዘፈነላት ወጣት የዘፈነላትን ሰው ለማናደድ ስትል እየተሽኮረመመች
“የምኔ ተማሪ ፤
ታቦት አደንቋሪ፤
የምኔ ገበሬ፤
ይሸተኛል አፉ የበላበት ጥሬ።
የቆለኛ ጎበዝ ደገኛ ደገኛ፤
የደገኛ ጎበዝ ቆለኛ ቆለኛ፤
እኔስ ደስ የሚለኝ አጓጉል ሶበኛ » እያለች ትወርፈዋለች። ከቆለኛና ከደገኛ ወጣት ይልቅ ወይና ደጋ ውስጥ የሚኖር ወንድ እንደሚበልጥባትም አስመስላ ትናገራለች። ወጣቱም ሲመልስ
«ጓያና ሽምብራ ከተደባለቀው፤
እኔ እሻልሽ ነበር ስሜ የታወቀው።» እያለ ይዘፍናል። ይህም አንቺ ያፈቀርሽው ልጅ ዘረ ቢስ ነው። በአባትና በሀብት በጉብዝና ከእኔ ጋር አይስተካከልም በሚል ያጣጥልባታል። ስትሽኮረመምበትም
«እንጨዋት እንጂ ጉብሌ ማፈርሽ፤
ያባይ ላባይ ደንጋይ ይመስላል ከንፈርሽ»
ያባይ ውኃ ሞልቶ ይዋኛል ይቃኛል፤
ኧረ ተይ ጉብሌ የሚበልጥ ይገኛል።
የዐባይ ውኃ ሞልቶ ቁም ሲከለክል፤
ትንፋሷን አመጣው ቅጠል ለቅጠል።
አልማዜ በአንቺ እዳ ጉብሌ በአንቺ እዳ፤
እገመገማለሁ ቆሜ እንደፍሪዳ።
የፈረንጅ አረቂ ብጠጣው አነቀኝ፤
መቅረት እንኳ አትቀሪም እስከዚያው ጨነቀኝ።
የፈረንጅ አረቂ ይያዛል በሹራብ፤
ግም ይዞ ከመጥገብ ሸጋ ይዞ መራብ።
ልጃገረዶቹ ሲኮሩ ብታይ ፤
የእኛም መስኮብ እግር መኩራቷ ነወይ ?
እደጊም አልልሽ ቁልቁል ያሣርርሽ፤
እስክሠራ ቤቴን ሌላ እንዳይለምንሽ።
አዳነች አማረ በጥርሷ ሰው ገድላ፤
እኛም ደረስንበት ከዝኑ ሲበላ » እያለ ስለ ጥርሷ ውበት በማድነቅ ያግባባታል ወይም እንደ መስኮብ ጠመንጃ እግርሽ ወልጋዳ ነው በሚል እያኮሰሰ ያናንቃታል። የጨዋታው ለዛም ይኸን ይመስላል። የዐባይ ድንጋይ የሚባለው ድንጋይ ሳይሆን በዐባይ ዙሪያ የሚኖሩ ሰዎች በበረሀ ውስጥ በተፈጥሮ እንደዘቃ ቅቤ በየጫካው በቅሎና አፍርቶ የሚያገኙት ቲማቲም ነው። ከንፈርሽ ቲማቲም ይመስላል ብሎ ሲክባት ነው።
በጨዋታው ወቅት ልጃገረዶች ወዳጅ ለወዳጅ ሲነጣጠቁም በተለይ ነጣቂዋ
«ለባልሽ ሰጠሁት ሲለምነኝ ባይ፤
ለውሻ ዳረጎት አይሰጥም ወይ?»
ባልሽን ጠብቂልኝ አሠርተሽ ማማ፤
እኔማ የት ልሂድ ከአባቴ ባድማ» ብላ የጓደኛዋ ወዳጅ ወስላታና የማይታመን መሆኑን በአደባባይ በመንገር ከሴት ጓደኛዋ ጋር በግጥም ትሟገታለች። ነገሩም ጨዋታ ነው። እንደውሻ የተዋረደው፤ የተናቀውና ይሁንታ የተነፈገው ወጣትም የራሱን የመልስ ግጥም እየደረደረ ያሥቃቸዋል። የጥቅምት ወር ዜማ ይህን ሲመስል ወሩን አስመልክቶ በሀገራችን የሚነገር ተረት አለ። «ትምህርት በልጅነት፤ አበባ በጥቅምት ያምራል» ልጅን በጡት፤ እኽልን በጥቅምት ካልጠበቁትና ካልቆጠቡት ከባድ ነው ይባላል። አብዛኛው ሰው ግን ሥጋ በል ስለሆነ በጥቅምት አንድ አጥንት የምትለዋን ተረት ብቻ ነው የሚያውቃት።
አዲስ ዘመን ጥቅምት23/2012
ታደለ ገድሌ ጸጋየ ዶ/ር