417 ሚሊዮን ዶላር ወረዳን ከወረዳ የሚያስተሳስር መንገድ እየተሠራ ነው

ድሬዳዋ፡- ከዓለም ባንክ በተገኘ የ417 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ወረዳን ከወረዳ የሚያስተሳስር መንገድ እየተሠራ መሆኑን የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ።የኮሪዶር ልማቱ በከተሞች ሰው እና መኪና ተለያይተው መሔድ የሚችሉበት ሁኔታ መፈጠሩን አመለከተ፡፡

የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ፤ “ስለኢትዮጵያ መሠረተ ልማት” በሚል በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አዘጋጅነት ሰሞኑን በድሬዳዋ ከተማ በተካሔደው መድረክ ላይ እንዳመለከቱት፤ ገጠር እና ከተማ ላይ የሚሠሩ የትራንስፖርት አውታሮች የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማሳለጥ የሚያስችሉ ናቸው።ይህን መሠረት በማድረግ የመንገድ ልማት ከገጠር ወደ ከተማ ለሚኖረው የዕድገት ሽግግር ትልቅ ትርጉም ስላለው በገጠር ትስስር ፕሮግራም ከክልሎች ጋር በቅንጅት እየሠራ ነው።

የከተማ ትራንስፖርት ከምንም በላይ አስፈላጊ መሆኑን አስታውሰው፤ ትራንስፖርት ከተማ ውስጥ መኖሩ ከምርታማነት እና ከኢኮኖሚ ዕድገት ጋር በቀጥታ ግንኙነት ያለው በመሆኑ በስፋት እየተሠራበት እንደሆነ አመልክተዋል።

ይሁንና በትራንስፖርት ዘርፍ በከተማ በሚሠራው ብቻ ትርፋማ መሆን እንደማይቻል አመልክተው፤ የግብርና ምርት መንገድ ኖሮ መውጣት የማይችል ከሆነ አስቸጋሪ ሁኔታ እንደሚፈጠር ጠቁመዋል፡፡

ቀድሞ የነበረው የገጠር መንገድ ተደራሽነት መሠረታዊ መዋቅር ያልተሠራለት እንደነበር አመልክተው፤ በፕሮግራሞች ታቅፈው ያልነበሩ አንዳንድ አካባቢዎች ከፍተኛ የምርት አቅም ኖሯቸው ምርታቸውን በቀጥታ ለገበያ ማድረስ የማይችሉበት ሁኔታ ተፈጥሮ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ችግሩን ለመፍታት ቀጥታ ወረዳን ከወረዳ ለማገናኘት ቢሠራም፤ አሁንም ወረዳን ከወረዳ ጋር በማስተሳሰር ሂደት ውስጥ የኢትዮጵያውያን አሠፋፈር በመሬት አቀማመጣቸው ብቻ ተነጥለው የሚኖሩ ማህበረሰቦች መኖራቸው ሥራውን ሙሉ ለሙሉ ሁሉንም ኅብረተሰብ ለማካተት እንዳይቻል እንቅፋት የሚፈጥር ነው ብለዋል።

በከተሞች ነዋሪዎች ከቤታቸው ወጥተው መንቀሳቀስ የማይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰው እንደነበር አስታውሰው፤ የኮሪዶር ልማቱ በከተሞች ሰው እና መኪና ተለያይተው መሔድ የሚችሉበት ሁኔታ መፈጠሩን አመልክተዋል።

በግለሰብ ባለሀብቶች ታጥረው የነበሩ አካባቢዎች አሁን የሕዝቡ የጋራ መጠቀሚያ መሆናቸውን አስታውሰው፤ ፍትሐዊ የሀብት አጠቃቀም የተፈጠረበት ሁኔታ መኖሩን እና ዜጎች በእግራቸው እየተራመዱ እና ቁጭ ብለው የሚያስቡበት፣ ከቤታቸው ወጥተው ልጃቸውን ይዘው የሚዝናኑበት፣ ሁሉም የከተማ ነዋሪ የሚጠቀምበት ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸዋል።

ከትራንስፖርት ልማት አኳያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ ከአመራር፣ ከአደረጃጀት ጋር ተያይዞ አስፈላጊውን ለውጥ በማድረግ ከጊዜ ወደ ጊዜ የዘርፉ ዕድገት እየተሻሻለ መምጣቱን እና የትራንስፖርት መሠረተ ልማት ላይ ትልቅ ለውጥ እየመጣ መሆኑን ተናግረዋል።

ጨምረውም አዳዲስ ዕቅዶች መኖራቸውን አመልክተው፤ በተለመደው መንገድ መንግሥትን በመጠበቅ ብቻ የሚሠሩ ሳይሆኑ፤ በግል እና በመንግሥት አጋርነት የግል ዘርፉ እንዲሳተፍ የተለያየ ጥናት ቀርቦ ሥራ ተጀምሯል ብለዋል፡፡

የግል ዘርፉ በፍጥነት መንገድም ሆነ በሌሎች የመንገድ ግንባታዎች ላይ ሊያግዝና ሊሳተፍ እንደሚገባ ጠቁመው፤ ዘርፉ ላይ መሳተፍ ትርፋማ የሚያደርግ በመሆኑ የማህበረሰቡም ተሳትፎ ማደግ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You