-በ2011 ከተቃጡ ጥቃቶች 83 ከመቶ ከሽፏል
-የመጀመሪያው ብሄራዊ የሳይበር ደህንነት ሳምንት ይከበራል
አዲስ አበባ፡- ከ2005 ዓ.ም እስከ 20011 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያ የሳይበር ጥቃት በ12 እጥፍ የጨመረ ሲሆን የጥቃቱ ብዛትና ዓይነትም እየጨመረ መሆኑ ታውቋል:: በ2011 ዓ.ም ከተቃጡ ጥቃቶች ውስጥ 83 ከመቶ የሚሆኑትን መመከት ተችሏል፡፡
በኢንፎርሜሽንና መረብ ደህንነት ኤጀንሲ መረጃ መሠረት በ2005 ዓ.ም የነበረው የሳይበር ጥቃት 59 የነበረ ሲሆን፤ በ2011 ዓ.ም ግን ጥቃቱ ወደ 791 አድጓል፡፡ በ2006 ዓ.ም 66 ጥቃቶች፣ በ2007 ዓ.ም 51፣ በ2008 ዓ.ም 214፣ በ2009 ዓ.ም 479 ጥቃቶች እንዲሁም በ2010 ዓ.ም 576 ጥቃቶች መድረሳቸው ታውቋል፡፡
የኢንፎርሜሽንና መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ወርቁ ጋቸና፤ ከጥቅምት 24 እስከ 30 ቀን 2012 ዓ.ም የሚከበረውን የመጀመሪያውን ብሄራዊ
የሳይበር ደህንነት ሳምንት አስመልክቶ ትናንት በሰጡት መግለጫ የሳይበር ጥቃት በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በኢትዮጵያ በብዛትና በዓይነት እየጨመረ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በዓለም ከተከሰቱ የሳይበር ጥቃቶች ውስጥ 90 ከመቶ የሚሆነው በሰው ልጆች የሳይበር ደህንነት ንቃተ ህሊና ማነስ የተከሰቱ ናቸው::
በመሆኑም በአገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚከበረው የብሄራዊ የሳይበር ደህንነት ሳምንት ብሄራዊ የሳይበር ንቃተ ህሊናን በመገንባት የተቀናጀ ብሄራዊ የሳይበር ደህንነት አቅምን ማጠናከር ዋንኛ ዓላማው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
እንደ ኢንጅነሩ ገለፃ፤ በ2011 ዓ.ም በኢትዮጵያ ላይ ከደረሱ 791 የሳይበር ጥቃቶች መካከል 333 የድረ ገፅ ጥቃት፣ 187 ማልዌር ጥቃት፣ 105 የመሰረተ ልማት ስለላ፣ 33 የሳይበር ትንኮሳ፣ 24 መሠረተ ልማት ሥራ ማቋረጥ፣ አንድ የሳይበር ማጭበርበር እና ወደአልተፈለገ ሲስተም ሰርጎ ለመግባት ሲባል ደግሞ 108 ጥቃቶች ተደርገዋል፡፡
ይሁንና ኤጀንሲው ባካበተው ከፍተኛ ብቃት፣ ቴክኖሎጂና የተማረ የሠው ኃይል በመታገዝ 83 ከመቶ የሚሆኑትን ጥቃቶች ማክሸፉን አስገንዝበዋል፡፡ በቀጣይም መሰል ሥራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመው ተቋሙ የሳይበር ጥቃትን ለመከላከል አቅሙን በሰፊው እያሳደገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
እንደ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ከሆነ፤ ከጥቅምት 24 እስከ 30 ቀን 2012 ዓ.ም በሚከበረው የመጀመሪያው ብሄራዊ የሳይበር ደህንነት ሳምንት የ1ሺ100 ተቋማት ከፍተኛ አመራሮችና ሠራተኞች እንዲሁም የሚዲያና ኪነጥበብ ባለሙያዎች በቀጥታ ይሳተፋሉ፡፡
የሳይበር ደህንነት ሳምንት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ16ተኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ‹‹ትኩረት ለሳይበር ደህንነት›› በሚል መሪ ሐሳብ የሚከበር መሆኑን ከኢንፎርሜሽንና መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 22/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር