– በዞኑ ለ40 ዓመታት ጥያቄ ሲቀርብበት የነበረው መንገድ ግንባታ ቢጀምርም ችግሮች ተደቅነዋል
አዲስ አበባ፡- በጋሞ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች እና ሳውላ ከተማ ባለፈው ዓመት በተደራጁ ግለሰቦችና ቡድኖች በተፈጠረ ሁከትና ብጥብጥ ተፈናቅለው የነበሩ 30ሺ ዜጎች ወደ ቀያቸው መመለሳቸው ተገለፀ፡፡
የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጅነር አክሊሉ አዳኝ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፣ በመሎ ኮዛና ባስኬቶ ልዩ ወረዳ አዋሳኝ አካባቢ በተፈጠረው አለመግባባት 30ሺ በላይ ዜጎች ተፈናቅለው ለወራት በድንኳን ውስጥ የቆዩ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ወደቀዬአቸው ተመልሰዋል፡፡
በሳውላ ከተማ በነበረው ግጭትም ከፍተኛ የሆነ የንብረት ውድመት የደረሰ ሲሆን፣ በርካታ የመንግሥት ተቋማት ላይ ጥቃት መድረሱንም ጠቁመዋል፡፡ ሆኖም ከክልል እና ፌዴራል መንግሥት ጋር በመነጋገር አካባቢውን በፍጥነት ማረጋጋት ተችሏል፡፡ በተጨማሪም ፌዴራል ፖሊስና የመከላከያ ኃይል በአካባቢው በመሰማራቱና ከህብረተሰቡ ጋር ሰፊ ውይይት በመደረጉ አስቸጋሪ ሁኔታዎች መታለፋቸውንና በአሁኑ ወቅት አስተማማኝ ሰላም መስፈኑን አረጋግጠዋል፡፡ ባለፈው ዓመት በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው የለውጥ ጉዞም በተፋጠነ ሁኔታ እየተተገበረ መሆኑን ዋና አስተዳዳሪው አስረድተዋል፡፡
እንደ ኢንጅነሩ ገለፃ፣ በአካባቢ የመሰረተ ልማቶች አለመሟላትም የቅሬታ ምንጭ ሆነው መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡ ለአብነትም ለ40 ዓመታት ጥያቄ ሲቀርብበት የነበረው ሶዶ ሳውላ መንገድ ግንባታ በአስፋልት ደረጃ እንዲሆን ሥራው ቢጀምርም አሁንም ቢሆን ችግሮች ተደቅነዋል፡፡ በተለይም ሥራው ቢጀመርም ግንባታው እየዘገየ መሆኑንና ኮንትራክተሮችም በሙሉ አቅም ወደ ሥራ እንዳልገቡ አስገንዝዋል፡፡
ዋና አስተዳዳሪው እንዳሉት፣ ዞኑ በገበያ ከፍተኛ ተፈላጊነት ያላቸው ምርቶች የሚመረቱበት ሲሆን፣ ወደማዕከላዊ ገበያ ለመውሰድ ከፍተኛ ችግር መኖሩን ጠቁመዋል፡፡ በተለይም ወደ ውጭ በመላክ ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ ሰሊጥ፣ ለውዝና በርካታ የቅባት እህሎች በአካባቢው ይመረታሉ፡፡
በተጨማሪም በርካታ የቁም እንስሳት ወደ ማዕከላዊ ገበያ ይላካሉ፡፡ ይሁንና እነዚህን ምርቶች ወደ ገበያ ለማቅረብ ከፍተኛ የመንገድ ችግር መኖሩንም ጠቁመዋል፡፡ ችግሩን ለማቃለልም በተደጋጋሚ ለሚመለከታቸው አካላት ጥያቄ ቢቀርብም እስካሁን ምላሽ እንዳልተገኘ ኢንጅነር አክሊሉ ጠቁመዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 22/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር