አዲስ አበባ፡- የቀድሞው የኦነግ መሪ የነበሩት የፖለቲካል ሳይንስ ምሁር ዶክተር ዲማ ነገዎ‹‹ኢህአዴግ በመዋሃድ ወጥ ፓርቲ ለመመስረት መንቀሳቀሱን እንደ ጥሩ አጋጣሚ እወስደዋለሁ›› ሲሉ ገለፁ፡፡
ዶክተር ዲማ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት፤በአሁኑ ወቅት በየትኛውም ፖለቲካ ውስጥ ተሳትፎ የላቸውም፡፡ነገር ግን እንደ አንድ ምሁር ማለት የሚችሉት ኢህአዴግ በውስጡ ያለውን አደረጃጀት የመወሰን የራሱ መብት ነው፡፡በመዋሃድ ወጥ ፓርቲ ለመመስረት መነሳሳቱም መልካም ተግባር ነው፡፡ በመሆኑም ሌሎችን የፖለቲካ ድርጅቶች የሚያገባቸው ነገር አይደለም፡፡
እርሳቸው እንደተረዱት፤ኢህአዴግ ወደ ውህደት ለመምጣት ከዚህ በፊት ተወያይቶ ውሳኔ ላይ ደርሷል፡፡ስለሆነም ይህንኑ ውሳኔ ተግባር ላይ ለማዋል በመታገል ላይ ያለ የፖለቲካ ድርጅት ነው፡ ፡በዚህ እንቅስቃሴው ድጋፍም ተቃውሞም መኖሩን የተረዱ ሲሆን፣ከዚያም አልፎ በግልፅ ወጥተው የተቃወሙ እንዳሉም ማስተዋል ችለዋል፡፡
ዶክተር ዲማ እንደተናገሩት፤ከዚህ በፊት የነበረው የኢህአዴግ አደረጃጀት አራት አባል ድርጅቶችና አምስት አጋር ድርጅቶች ያሉት ነው፡፡ ይህ አካሄድ በራሱ ልዩነት ያለበት ነው፡፡ አምስቱ አጋርነት እንጂ ሙሉ ተሳታፊ አይደሉም:: አካባቢያቸውን ሊያስተዳድሩ ቢችሉም፤ ኢትዮጵያን ለማስተዳደር ግን አይችሉም:: ኢትዮጵያን ሊያስተዳድር የሚችል አካል ከአራቱ ብሄራዊ ድርጅቶች ብቻ ነው፡፡ ስለዚህም አድልዎ ያለበት አካሄድ እንደሆነ ይታወቃል::
ዶክተር ዲማ አክለውም፤‹‹እንዲያም ሆኖ በአራት እህት ድርጅቶቹ መካከልም የስልጣን ተዋረዱ በግልፅ የሚታይ ነው፡፡ ከላይ በቁንጮነት ሲመራ የነበረው ህወሓት ነው፡፡አጋር የተባሉት አምስቱ ግን ከዚህም አሰላለፍ ውጭ ናቸው፡፡ ስለሆነም ይህ አደረጃት በራሱ ችግር ነበረው፡፡
በአሁኑ ወቅት ደግሞ ቆንጮ የነበረው አካል ቀርቶ ኦዲፒ ለመምራት በመፍጨርጨር ላይ ያለ ይመስለኛል፡፡እንዲያም ሆኖ የበላይ የበታች በሚል ሐሳብ ውስጥ የመቀጠል ፍላጎት ስለሌላቸው አንድ ወጥ ፓርቲ ለመመስረት እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ይህን ማድረጋቸውን እኔ እንደ ጥሩ አጋጣሚ ነው የምወስደው፡፡ ››ብለዋል፡፡
‹‹የውህደቱ ዓላማ መልካም ነው፡፡››ያሉት ዶክተሩ፣‹‹ምክንያቱም በአንድ በኩል አገሪቱን ሲያስተዳድሩ የነበረው በቅንጅት ነበር፡፡ እያንዳንዳቸው ራሳቸውን የቻሉ ፓርቲዎች ሆነው ለ27 ዓመት ያህል የቆዩ ሲሆን፣በዚህ ስሌት ማስተዳደር ራሱ የመፈጠረው ችግር አለ፡፡ስለዚህም በፓርቲው ውስጥ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ አንድ ወጥ ፓርቲ መሆን መቻሉ መልካም ነገር ይመስለኛል፡፡››ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ቀደም ሲል በራሱ እርግጠኛ የሆነ ቅንጅት አልነበረም፡፡ምክንያቱም ከላይ ቆንጮው አለ፤ሌሎቹ ደግሞ ታዛዦቹ ነበሩ፡፡አሁን ደግሞ አንድ ወጥ የሆነ ፓርቲ በአገር ደረጃ ተወዳድሮ ከተመረጠ አገር ሊያስተዳድር እንደሚችል አመልክተዋል፡፡
የኢህአዴግ መዋሃድ ፌዴራሊዝም እንዲከስም አሊያም አሃዳዊነት እንዲመጣ የሚያደርግ ነው የሚሉ አካላት አሉና ምላሽዎ ምንድን ለተባለውም ጥያቄ ሲመልሱ፣‹‹ዴሞክራሲያዊ እስከሆነ ድረስ አሃዳዊም ቢሆን እኔ ችግር የለብኝም፤ዋናው ዴሞክራሲያዊ ነው ወይ? የሚለው ነው፡፡ ››ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አክለውም፤‹‹ነገሩ ግን እሱ አይደለም፡፡
የፓርቲ አደረጃጀትና የአገር አደረጃት የተለያየ ነው፡፡አገር የምትመራው በህገመንግስት ነው፡፡ኢትዮጵያ ህብረ ብሄራዊ ፌዴራሊዝም ላይ የተመሰረተች አገር መሆኗን ህገ መንግስቱ አስምሮበታል፡ ፡ያንን ህገ መንግስት እስካለወጡ ድረስ በዛው ይቀጥላል ማለት ነው፡፡››ሲሉም አብራርተዋል፡፡
እንደ እርሳቸው ገለፃ፤እነዚህ ስጋት አለን የሚሉ አካላት የሚያነሱት ኢህአዴግ አሃዳዊ ከሆነ አገሪቱንም ወደዚያው ይወስዳታል ከሚል እሳቤ ነወ፡፡እድሜ ልካቸውንም በአንድ ፓርቲ ኢህአዴግ እንደሚመሩ የሚያስቡም ሰዎች ናቸው፡፡ የሚሰጋው አካል ከፈለገ ተፎካካሪ ፓርቲ አደራጅቶ ለምን ኢህአዴግን ከስልጣን አውርዶ ሀገሪቱን አያስተዳድሩም፡፡
‹‹እኔ እንደሚመስለኝ በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አብዛኛው ህዝብ የሚፈልገው ፌዴራላዊ ስርዓቱን ነው፡፡ ስለዚህም ይህ ባለበት አገር ውስጥ ስጋትን ምን አመጣው?፡፡ስለዚህም አንድ ፓርቲ አሊያም አንድ ግለሰብ ተነስቶ ይህንን ያፈርሳል በሚል የሚኖር ስጋት አይታየኝም፡ ፡ከሰጋትም ደግሞ በአብዛኛው በፌዴራል ስርዓት የሚያምነውን አደራጅቶና ተወዳድሮ በማሸነፍ ስርዓቱን ማራመድ ነው፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 22/2012