ርዕሴ በተሸከማቸው ሁለት ቃላት ፍቺ ልንደርደር። በሀገሬ ቋንቋ የተዘጋጁት መዛግብተ ቃላት እርስ በእርሳቸው ለሚቃረኑት ለእነዚህ ሁለት መሠረታዊ ቃላት የሠጧቸው የጽንሰ ሃሳብ ትርጉሞች የሚከተሉትን ይመስላሉ፡፡ ዳሩ ድንጋጌያቸውን በማስረጃ እናስደግፍ ለማለት ያህል ካልሆነ በስተቀር የሕይወታችን ተሞክሮዎች በራሳቸው በሁለቱ መሰል ቃላት ተቃርኖዎች የተሞሉና የተገለጡ “መዛግብተ ኑሮ” ስለሆኑ የቃላቱ ትርጉም ለአንባቢያን ይጠፋቸዋል ተብሎ አይገመትም፡፡
ለማንኛውም ከቀዳሚው ቃል አንጀምር፡፡ “ፌሽታ – የክብረ በዓላትን ቀናት ምክንያት በማድረግ የሚገለጽ ደስታና ፈንጠዝያ ነው፡፡” ቋንቋችን “ፌስቲቫል” የሚለውን የባዕድ ቃላት ቤተኛ አድርጎ በመዋስ “ፌሽታ”ን በማደጎነት ያላመደው ሳይሆን አይቀርም፡፡ ዋቢዬ የባህሩ ዘርጋው መዝገበ ቃላት ነው፡፡
ሁለተኛውና “ቱማታ” የሚለው ቃል “ፍጅት፣ መደበላለቅ፣ እርስ በእርሱ መደባደብ፣ መተረማመስ፣ ወይንም በጦር ጨበጣ መሞሻለቅ” እየተባለ የቃሉ ዘር ማንዘር ተብራርቷል፡፡ ምሥጋናችን መዛግብተ ቃላቱን በቅርስነት ላቆዩልን ለተሰማ ሀብተ ሚካኤል ይሁንልን፡፡
መሠረታዊ የጽሑፌ መነሻ በቃላቱ ፍችና በያዙት ጽንሰ ሃሳብ ላይ ትንታኔ መስጠት ብቻ ሳይሆን እንደምን ሁለቱ ቃላት “ነፍስና ሥጋ ዘርተው” በምድረ ኢትዮጵያ እየተተገበሩ እንዳሉ የብዕሬን ምልከታ ለአንባቢያን ለማጋራት ነው፡፡ ሁለቱ ቃላት እርስ በእርሳቸው የሚቃረኑ መሆናቸውን ከድንጋጌያቸው ለመረዳት አይከብድም፡፡
እርግጥ ነው ቅራኔ በሰብዓዊ ፍጡራን ውስጥም ሆነ በተፈጥሮ መስተጋብር ውስጥ ህልው ሆኖ መንፀባረቁ ያለና የነበረ ብቻ ሳይሆን ለወደፊትም ቢሆን “ይጥፋ” ተብሎ ቢዘመትበት የማይሞከር እውነታ መሆኑ ለማንም አይጠፋም፡፡ ለምን ቢሉ “ጨለማን ያለ ብርሃን”፣ “ክፋትን ያለ ደግነት”፣ “ብልፅግናን ያለ ድህነት”፣ “ጤንነትን ያለ ህመም” ነጥሎና ነጣጥሎ ማሰብ ስለማይቻል ነው፡፡
ችግሩ ተቃርኖው ተፈጠሯዊ ከመሆን ድንበር አልፎ ልክ ሀዲዱን ስቶ ለአደጋ እንደሚጋለጥ ባቡር በሕዝብና በሀገር ህልውና ላይ የከፋ መከራ በማስከተል የማይሽር ቁስል የሚያሳርፍ ከሆነ ነው፡፡ ምን ማለት እንደሆነ የርዕሴን ሸክም በውስን አብነቶች ለማብራራት ልሞክር፡፡
ሀገሬና ባህሎቻችን ድንበርና ዳርቻ አልፈው ይበረቱባቸዋል ተብለው ከሚታሙባቸው ብሔራዊ ጉዳዮቻችን መካከል አንዱ “ድህንታችን ሳይገድበን” ጥሪታችንንና አንጡራ ሀብታችንን አሟጠንና አንጠፍጥፈን ለጊዜያዊ ፌሽታና ዕልልታ መበርታታችን በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡ ያለምንም ማጋነን በርካታ የሀገራችን ሆቴሎች፣ አደባባዮች፣ ሚሊኒዬም አዳራሽን መሰል የሕዝብ መሰብሰቢያዎች በሙሉ ከዓመት ዓመት የፌሽታና የፈንጠዝያ ምችና ድርቅ ሲመታቸው መባልን ብዙዎች አይስማሙበትም፡፡
በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሰበብና ምክንያት እየተፈለገ፣ ባህልና የሕዝብ እሴቶች እንደ ምክንያት እየተጠቀሱ፣ በንግድና ባዛር እየተመካኙ፣ በሀገራዊ ጉዳዮችና በመንግስት ጠሪነት እየታቀዱ ከበሮ የሚደለቅባቸው፣ ግብዣ የሚንበሸበሽባቸውና እስክስታ የሚደለቅባቸው ኩነቶችን ማስተዋል የተለመደ “ብሔራዊና ተቀዳሚ አጀንዳችን” ከሆነ ብዙ ቀናት መሽተው ነግተዋል፡፡
ሰበብ ተፈልጎ ይደገሳል፡፡ ምክንያት እየታሰሰ ፌሽታ ይተገበራል፡፡ በሰርኩላር እየተጠራ ሕዝብ ይሰበሰባል፡፡ ለመዝናኛ እየተባለም “ዋንጫ ኖር!” ይባላል፡፡ ይበላል፡፡ ይጨፈራል፡፡ “ተልዕኮው ተሳክቶ ሲጠናቀቅም” በሃሌሉያ ማሳረጊያ በተዘጋጁ “በእኛው ኦቶብሶች” እየተጨፈረ የደርሶ መልስ ጉዞ ይደረጋል፡፡ ለብዙዎች የሚያስገርመው ጉዳይ የፌሽታው እድምተኞች እዚያም ሆነ እዚህ የተወሰኑ “የሰው ም ርጦች” ብቻ የመሆናቸው ም ሥጢር ነው፡፡
የመንግሥት ቁንጮዎች ግብር ሲያገቡ፣ ነጋዴዎች ስለ ትርፋቸው “ሴሌብሬት ሲያደርጉ”፣ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ለተማጽኖ ጥሪ ሲያስተላልፉ፣ የኪነ ጥበባት ዝግጅቶች ሲመደረኩ፣ በሀገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ውይይቶች ሲደረጉ የሸሚዛቸውን ኮሌታ በአቼቶ ገትረው፣ በከረባት ደምቀውና ቀለማቱን ሳይቀር ለይተን በተለማመድናቸው ሱፎቻቸው ተሽቀርቅረው (እህቶችም እንደዚያው ተሸሞንሙነው) ለፌሽታው ድምቀት ከሚታደሙት የመገናኛ ብዙኃን ካሜራ ፊት ደረታቸውን ነፍተው የምናስተውላቸው የተወሱኑና አንድ ዓይነት ምርጦችንና “ቅዱሳንን” ብቻ ነው፡፡ ሀገራዊ ፌሽታ ነዋ!
ከነተረቱስ “ከእንጨት መርጦ ለታቦት፤ ከሰው መርጦ ለሹመት” ይባል የለ፡፡ ይህንን እውነታ ለመፈተን የፈለገ ሰው “ክቡርነታቸው” በጀመሩት ወይይቶችና ምክክሮች፣ እረፍት አልባ ጥሪ በሚተላለፍባቸው ሀገራዊ ዝግጅቶችና ስለ ዓላማቸውና ተልዕኳቸውን በቂ ማብራሪያ በማይሰጣቸው እጅግ በርካታ ዝግጅቶች ላይ ሁሌም፣ አምናም ሆነ ካቻምና የማይጠፉትንና የማይቀሩትን “የልብ ታዳሚዎችና ሁነኛ ቤተሰቦች” መመልከቱ ብቻ በቂ ማስረጃ ሊሆን ይችላል፡፡
በአንፃሩ ግማሽ ልጩ፣ ግማሽ ጎፈሬ ክስተቶች ነጥፎባት በማታውቀው አሳረኛ ሀገሬ የሚስተዋለው ሌላኛው የፌሽታው የቱማታ ተቃራኒ ትይዕንትም ሌላው መገለጫችን ነው፡፡ እርስ በእርስ የሚያገዳድል ሤራና ቱማታ እየተጎነጎነ ሲተገበር የሚውለው በነጋ በጠባ ነው። ስመ ወጣትነት የደረበ ጀማ ምክንያታዊነት የጎደለው አጀንዳ አንግቦ አደባባዩን በድንጋይ ናዳ “ጨረቃ ሲያስመስል” መመልከት የባህላችን አንዱ ክፍል ወደ መሆኑ እየተሸጋገረ ያለ ይመስላል፡፡
ማንም ጉርባ እየተነሳ በአውራ መንገዶች ላይ አውራ ሆኖ ሲፎገላ መመልከት ብርቅ አይለም፡፡ በዘረኝነትና በጎጥ ተቧድኖ ዘራፍ ማለት የዕለት ትዕይንት ሆኗል፡፡ ንብረት ማቃጠል፣ ክብሪትና ነዳጅ እየፈለጉ ቤተ እምነቶችን ለማጋየት መጣደፍም “እውነትም ያ ስምንተኛው ሺህ” እየተባለ በአባቶች የሚነገረው የምፅዓት ቀን “ወደ ሠፈራችን” እየተቃረበ ይሆንን እያልን እንድንጠይቅ ተደፋፍረናል፡፡ መንገድ መዝጋትና ንብረት ማውደም ብቻ ሳይሆን በተዘጉት መንገዶች ላይ ሰብዓዊ ፍጡርን ቀጥቅጦ በመጣል ከበረታም ገድሎ በ“ሰልፊ ፒክቸር” ከበድን ጋር ፎቶ እየተነሱ የጀብደኛነትን ብርታት ማረጋገጥ የአደባባይ ምሥጢር ከሆነ ውሎ አድሯል ፡፡
መልካም ሥነ ምግባሮች፣ በጎ ሰብዓዊ ባህርያት፣ ሩህሩህ ሕዝብ የሚባለው አፈ ትርክትና ብሔራዊ ክብር እያልን የምናንቆለጳጵሰው ሽንገላ ከነጭራሹ ሸሽቶን “ብሔራዊ እርቃናችን” ሊገለጥ የተቃረበ ይመስላል፡፡ ትናንት የመላአክት ክንፍ ካላበቀልንለትና ካልሰገድንለት እየተባለ በአድናቆታችን የደመቀውን “ጀግናችንን” በሳጥናኤል ቱቢት ሸፍነን በቁሙ አስክሬን ሳጥን ውስጥ ካልከተትን ማለትን “ብሔራዊ ባህል” ወደ ማድረግም የተቃረብን ይመስላል፡፡
ለመሆኑ እመቤት ሆይ ፍትሕ (Lady Justice) ዓይኗን በእራፊ ጨርቅ መሸፈኗ ብቻ ሳይሆን እውነትም የዓይኗን ብርሃን ሳታጣ አልቀረችም እያልን መተከዝና ማጉተምተም ከጀመርን ውለን አድረናል፡፡ ይህቺው በግሪኮች አማልክት የተሰየመቸው እመቤት ሆይ ፍትሕ በእጇ የያዘችው ሰይፍ ስለት የሌለው ዱልዱም፣ በቀኝ አጇ የጨበጠችው ሚዛንም አድሏዊ እንደሆነ ማማት ከጀመርን ሰነባብተናል፡፡ እመቤት ሆይ ፍትሕ ማነች ብሎ የሚጠይቅ አንባቢ ካለ በሕግ ትምህርት ቤቶቻችንና በፍትሕ ተቋሞቻችን ግቢዎች ውስጥ ሐውልቷ ተገሽሮ ስለቆመ ጎራ ብሎ ሊተዋወቃት ይችላል፡፡
በሆታና በእልልታ የሰላምን ርግቦች በሀገራችን ሰማይ ላይ ለማብረር የጋራ ኪዳን ገብተናል በማለት ጨፍረው ያስጨፈሩን ቡድኖችና ግለሰቦች “አጭሰው ያስጨሱን አቧራ” ከዓየሩ ላይ ሳይገፈፍ በጠላትነት እየተፈራረጁ በቃላትም ሆነ በግብር “ይዋጣልን!” በማለት ሕዝብን ከፊት አስቀድመው እንደ ጋሻ እየተጠቀሙ ሲያቅራሩ እየተመለከተን ያለነው በዚሁ ለጉድ በጎለተው “ዐይነ ስባችን” ነው፡፡
የመዝናኛ ኮንሰርቶች፣ የመመሰጋገኛ መድረኮች፣ የመገባበዣ ማዕዶች፣ የመደናነቂያ ኩነቶች፣ የስኬት ማወጃ ስብሰባዎች እንደ አሸን ከመፍላታቸው ጎን ለጎን የበቀሉት የቱማታ አረሞች በእጅጉ የሚያሳፍሩ ብቻ ሳይሆኑ የሚያሸብሩ ክስተቶችን እየፈለፈሉብን እንዳሉ ምስክር የምንቆጥረው ያረጁ ቀናቶቻችንን ምስክር በመጥራት ብቻ ሳይሆን የዛሬዋን ጀንበር ብንጠይቅም መልሱን ማግኘት አይከብድም፡፡
“እንቱፍቱፍ ብለን የመረቅንበት” ምራቅ ሳይደርቅ “ቱፍ!” እያልን ምራቅ የምንተፋባቸውና የምናዋርዳቸው የዘመናችን አንቱዎች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ “ሃሌሉያ” እያልን በዘመርንባቸው ሜዳዎቻችን ውስጥ “የሚያጣጥር የኤሎሄ ድምጽ” ጆሯችን መስማት ከለመደ ሰነባብቷል። እዚያኛው መንደር “ላሌ ጉማ” ሲቀነቀን፣ ወዲህኛው መንደር ደግሞ በከንቱ ለተቀጠፉት ነፍሶች “ሙሾ እየተረገደ ዋይ! ዋይ” ይባላል፡፡ ለወደሙት ንብረቶች እንባ ይንዠቀዠቃል፡፡ በጋዩት የቤተ እምነት ፍርስራሾች ላይ ግፉዓን እንባቸውን እያዘሩ “የፍረድልን ድምጽ” ወደ ፀባዖት ያደርሳሉ፡፡ እነዚህ ጉዳዮች የሀገሬን ወቅታዊ የብስልና የጥሬነት ባህርያት በሚገባ ያመላክቱ ይመስለኛል፡፡
የሀገሬ ፌሽታና ቱማታ ጽንፍ ወጥተው በዓለም ማኅበረሰብ ፊት ለትዝብት ከዳረጉን ሰነባብቷል፡፡ በትንሽ ስሜት የሚፈነድቅ፣ በኢምንት ጉድለት ድንጋይ እየተወራወረና ሰይፍ እየተሞሻለቀ አለምክንያት አጥፊና ጠፊ የመሆን አባዜ ከተጠናወተን እነሆ ዓመታትን አስቆጥረናል፡፡ እኒህን መሰል የትውልዴ እፀፆች በሌላው ዓለም ስለመታየት አለመታየታቸው እርግጠኛ አደለሁም። ለካስ ሞትንም ተላምዶ ቤተኛ ማድረግ ይቻላል! ለካስ ወንድምና እህትን በአደባባይ እየወገሩ አይተኬ ነፍሶችን ከቀጠፉ በኋላ “የሰላም እንቅልፍ” ተኝቶ ማደር ይቻላል።
ለካንስ “ኢርፎን በጆሮ ላይ ሰክቶ” አሻሼ ገዳሜ እያሉ በማርገድ አብሮ የኖረን ወገን ከቀዬው አፈናቅሎ መፎከር አይከብድም፡፡ ለካንስ የንፁሐን እንባ በበደል ድርጊቶች ሲፈስ እያስተዋሉ መፈንደቅ ይቻላል፡፡ ለካንስ ተዋልዶና ተዛምዶ በኖረ ሕዝብ መካከል የውሸት ፕሮፖጋንዳ እየነዙና የውሸት ትርክት እያነበነቡ እርስ በእርስ እንዲጋጩ የሳጥናኤል መልዕክተኛ መሆን ይቻላል፡፡ አቤት የመከራችን ብርታቱ! አቤት የድንዳኔያችን ግዝፈቱ!
ከበደ ሚካኤል ወደውም አይመስለኝም ከአንድ አዛውንት ዕድሜ በማይተናነሰው አጭር ግጥማቸው እንዲህ ሲሉ የመከሩን፡
እጅግ ደስ የሚያሰኝ ነገረ በየህ ጊዜ፣
ደስታህን ትተህ ዙር ወደ ትካዜ፡፡
በዚህ ደስታ ውስጥ ላይን የተሰወረ፣
ያንኑ የሚያህል በጣም የመረረ፣
ሸክሙ የከበደ ወዮታው የጠና፣
አንድ ታላቅ ሀዘን አይታጣምና፡፡
ካቻምና በተፈጠረ ግጭት የአምስት፣ የስድስት፣ የአሥር ንፁሐንን ሞት አስተናግደን እንባችን ሳይደርቅ፣ አምና በተፈጠረ ነውጥና ቀውስ ሃያ ሰላሣ ሰው ቀብረን ከሀዘን ፍራሻችን ላይ ሳንነሳ፣ ዘንድሮ በተከሰተ ችግር ሰባ ሰማንያ ሰው ረግፎ ተመልክተን ድንጋጤ ላይ መውደቅን ባህል አድርገን እስከ መቼ መዝለቅ ይቻላል? ንፁሐን ዜጎች ተፈናቀሉ፣ ንብረቶች ወደሙ፣ ቤተ እምነቶች ተቃጠሉ የሚሉት ክፉ ዜናዎች አደንዝዘው ያፈዘዙን ይመስለኛል፡፡ ጉድ ነው ጎበዝ! ይህንን መሰል ሀገራዊ ትራዤዲ “ብሔራዊ ድንዳኔ” ብንለው ሁኔታውን አይገልጸው ይሆን?
እናስ መፍትሔው፣ መፍትሔው፣ መፍትሔው ምን ይሁን? የጸሐፊው ብዕር ብቻ ሳይሆን ነፍስያውም፣ ቀልቡም አብረው መጯጯህ ከጀመሩ ሰነባብቷል፡፡
መፍትሄ አንድ፤ በተልካሻ ሰበቦች በምንፈጥራቸው የፌሽታ ግርግሮች ላይ ማዕቀብ ጥለን ራሳችንን እንቅጣ። “ሞት በነገሰበት ሀገር ለሙሽራ ዕልል የሚባለው ዜማ አይደምቅም!” እንዲሉ ማለት ነው፡፡
መፍትሔ ሁለት፤ መከራችንና ቱማታችን የፋፉባቸው ኮሲና ክርፋታም ማሳዎች በአስቸኳይ ስለ ፍትሕ የበላይነት ሲባል ተጠርገው እንዲወገዱ የመንግሥት ወኔ ይፈርጥም፡፡
መፍትሔ ሦስት፤ በየቤታቸው በዕልልታ የታጀበ ፌሽታ፣ በአደባባይ ደግሞ በመፈክር የታጀቡ ቱማታዎችን የሚያውጁትንና የሚያሳውጁትን ራስና ዝና ወዳዶች አንገታቸውን ደፍተው እንዲሸማቀቁ ለመሠሪ ሤራቸው እምቢ በማለት እናግልላቸው፡፡
መፍትሔ አራት፤ በማኅበራዊ የትሥሥር ሰንሰለቶቻቸውና ሚዲያዎቻቸው የሚነዙትን መርዝ ለማርከስ ራሳችንን በማቀብ ለሌላውም መድህን እንሁን።መፍትሔ አምስትን፤ መፍትሔ ስድስትን፣ መፍትሔ ሰባትን አንባቢው እያከለበት ውይይቶችን በማስፋት ለሀገራዊ ህመማችን እውነተኛና ያልተቀባቡ መፍትሔዎችን በጋራ እናዋጣ የብዕረኛው የተማፅኖ ድምፅ ነው፡፡ ሰላም ይሁን!!
አዲስ ዘመን ጥቅምት22/2012