አለም ከምድር ከፍ ብሎ፤ ከውቅያኖስ ርቆ ጠፈርን መቧጠጥ፤ ህዋን መዳሰስ ከጀመረ ውሎ አድሯል። ሀገራት በሳይንሳዊ ምርምሮች በምድር ላይ ያለን ሀብት ብቻ ከመጠቀም ባለፈ የሰው ልጆች በጠፈር ላይ የሚገኝን ሀብት ለመጠቀም፤ የመኖሪያ መንደር ለመመስረት ሽሚያ ላይ ናቸው። ከምድራዊ ምርምርና ፈጠራዎች ባለፈ በጠፈር ላይ የሚደረጉ ዳሰሳዎች፤ የሚሰሩ ተግባራት ተጠናክረው የቀጠሉበትና በሀገራት መካካል ፉክክር የተገባበት ምክንያት ደግሞ የጠፈር ምርምርን ጠቀሜታ አጉልቶ ያሳያል።
በዚህ ረገድ የምዕራባዊያን ርቆ መሄድና የአፍሪካና የሌሎች ታዳጊ አገራት ወደ ኋላ መጎተት ሁለቱ ክፍለ አለማት ከዘርፉ የሚያገኙትን ፋይዳ የሰፋ ልዩነት እንዲኖረው አድርጓል። በስፔስ ሳይንስ ላይ የሚደረጉ ምርምሮች ለሀገራት ከፍተኛ ፋይዳ እያስገኘ መሆኑን ከዘርፉ ርቀው ሄደው ከተጠቀሙት ሀገራት መረዳት ይቻላል።
ኢትዮጵያ በዘርፉ፤ ማለትም በስፔስ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዘርፍ፣ በአስትሮኖሚና አስትሮ ፊዚክስ፣ በመሬት ምልከታ፣ በኤሮኖቲክስና በአስትሮኖቲክስ ጥራት ያለውና አለም አቀፍ የሆነ ምርምር፣ የሰው ሀይል ስልጠናና አለም አቀፍ ግንኙነት፣ የፈጠራና የማህበራዊ አገልግሎት ለህዝቧ በማቅረብ ኑሮውን በማሻሻልና በመስኩ ሊገኝ የሚገባውን ጥቅም ለማስጠበቅ ብዙ መስራት የሚጠበቅባት ሀገር መሆኗ እሙን ነው።
ኢትዮጵያ በመስኩ የላቀ ልምድ ባይኖራትም፤ በተለያዩ ዘመናት በመስኩ ምርምርና የተለያዩ ግኝቶችን ያደረጉ ግለሰቦች ሀገር ናት። ይሄም በራሳቸው የመጠቀ ጥበብ፤ ባህል በወለደላቸው ሀገር በቀል እውቀት ባረቀቃቸው ኢትጵያዊያን የተሰሩ የጥንት አስትሮኖሚያዊ እና ህዋዊ ምርምሮችን ሳንዘነጋ ስለነሱ ተግባርና ደርሰውበት ስለነበረው ከፍ ያለ ደረጃ በራሱ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው መሆኑን ልብ ይሏል።
የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ማህበር በ2006 ከተመሰረተ በኋላ እንደ ሀገር ንቅናቄዎች ተፈጥረው በመስኩ የሚደረጉ ምርምሮችም ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አድርጓል። እነዚህም፤ በፈርንጆች አቆጣጠር በ2012 ኢትዮጵያ የአለም አስትሮኖሚ ማህበር አባል ከሆነች በኋላ በመስኩ ያለው ተሳትፎ ተጠናክሮ ለመቀጠሉ ዋነኛ ማሳያዎች ናቸው። ሀገሪቱ አባል የሆነችበትና 80 ሀገራትን ያቀፈው የአለም አስትሮኖሚ ህብረት ከ13 ሺህ በላይ ሳይንቲስቶችን የያዘና በህዋ ምርምር ዘርፍ እጅግ የረቀቁ ምርምሮች የሚያካሂድ ከአባል ሀገራት ጋር በጋራ የሚሰራ መሆኑ ይታወቃል።
ህብረቱ ኢትዮጵያ በዘርፉ የምታካሂደውን ተሳትፎ ከፍ እንዳደረገው ይታመናል። በህዋ ሳይንስ ዘርፍ ብቸኛ ውሳኔ ሰጪ የሆነው ይህ ህብረት በሀገራት መካከል እና በስፔስ ሳይንስ ምርምር ረገድ የእርስ በርስ ልምድ ልውውጥ ያካሂዳል። ኢትዮጵያም በህብረቱ ውስጥ ባላት ሚና በቅርቡ በሚልክዌይ ጋላክሲ ውስጥ የሚገኙት HD 16175 ኮከብና HD16175b ፕላኔት ስም እንድትሰይም እድል መሰጠቱ ይታወቃል። በዚህም የኮከቡና የፕላኔቱ ስም ስያሜ ማህበረሰቡ እየተሳተፈ የቆየ ሲሆን ለስያሜው የሚሆን ስም በመለየቱና ሂደቱን በመምራት ትልቅ አስተዋፅዖ የነበረው የኢትጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ ነበር።
ህብረተሰቡ እንዲሳተፍበት በተደረገው በዚህ ሀገራዊ ስያሜ ለፕላኔቱ ስም የማውጣቱ ሂደት 275907 ስሞች በኢሜል፣ በፖስታና በስልክ መልዕክት በአማራጭነት ከህብረተሰቡ የቀረቡ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ ለኮከቡና ለፕላኔቱ ይመጥናሉ የተባሉ ስሞች በስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲው ሲለይ ቆይተዋል። በዚህም ሂደቱን በጠበቀ መልኩ አስር ገላጭ የተባሉ ስሞች ተለይተው፤ በድጋሚ ከአስሩ ውስጥ የመጨረሻ ስያሜ ሊሆን የሚችል አንድ ጥምር ስም/ኦች በህብረተሰቡ እንዲመረጥ በስፔስ ሶሳይቲው ጥሪ ተላልፏል።
ሀገሪቱ የኮከቡና የፕላኔቱ ስያሜ እንድትሰጥ በተሰጣት እድል የተመረጡ የመጨረሻ አስር ስሞች በኮድ ተለይተው ለህብረተሰቡ የተዋወቁ ሲሆን፤ በ”ኮድ 01 ቡና አቦል፤ 02 ራስ ዳሽን ዳሎል፤ 03 ኤቴል ህንዴኬ፤ 04 እንቁ ፃጉሜን፤ 05 በከልቻ ድንቅነሽ፤ 06 የሀ ዳማት፤ 07 ጣና አባይ፤ 08 ሄኖክ ኤቴል፤ 09 አቢሲኒያ ድንቅነሽ፤ 10 እንቁ እናት” የተሰኙ ጥምር ስሞች ህብረተሰቡ በስልክ አጭር መልክት፤ በሶሳይቲው ድህረ ገፅ (ኦን ላይን) በፖስታ ስያሜዎቹ ላይ እስከ ጥቅምት 28 ድረስ በመምረጥ ድምፁን እንዲሰጥ ተጋብዟል።
በዚህም ሀገሪቱ በተሰጣት እድል ተጠቅማ የኮከቡንና የፕላኔቱን ስያሜ ከመወሰን ባለፈ በስፔስ ሳይንስ የላቀ ተሳትፎ እንዲኖራትና ሀገራዊ ተጠቃሚነቷ ከፍ እንዲል እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ ዳይሬክተር ዶክተር ሰለሞን ይገልፃሉ። ከአፍሪካ ኢትጵያን ጨምሮ ስድስት አባል ሀገራት ያሉበት በአለም አቀፍ አስትሮኖሚ ህብረት በአሁኑ ወቅት መቶኛ አመቱን በማክበር ላይ ይገኛል።
ኢትጵያም በዚህ ህብረት ውስጥ ባላት ተሳትፎ የተለያዩ የማስተማሪያ ቁሳቁሶች፤ ቴሌስኮፖችና ልዩ ልዩ የስፔስ ምርምር ቁሳቁሶች በሽልማት መልክ ተበርክቶላታል። ኢትዮጵያ የኮከቡና የፕላኔቱን ስያሜ የማውጣቱ እድል የተሰጣትም አሁን እየደረገች ባለው የስፔስ ሳይንስ ጠንካራ ተሳትፎዋ መሆኑ ተገልፃል። ኢትዮጵያ በራስዋ ከምታደርገው ተሳትፎ ዘለግ ባለ በአፍሪካ ደረጃ በስፔስ ሳይንስ ልዩ ልዩ እንቅስቃሴዎች በማድረግ ላይ የምትገኝ ሲሆን፤ በምስራቅ አፍሪካም የምስራቅ አፍሪካ ስፔስ ሶሳይቲ እንዲመሰረት ባደረገችው ጥረት ሶሳይቲው እውን ሆኗል።
ከዚህ በተለየ ኢትዮጵያ የሀጉሪቱ ሳይንስቲስቶች በስፔስ ሳይንስ ዘርፍ የላቀ ሚና እንዲኖራቸው ለማድረግ አፍሪካዊ ተማሪዎችን በመጋበዝ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ስልጠና ትምህርት እንዲያገኙ እያደረገች ትገኛለች። በዚህ ልዩ ተሳትፎዋም ያገኘችው ይህ አዲሶቹን ፕላኔትና ኮከብ የመሰየም እድል ሀገሪቱን በብዙ መልክ ተጠቃሚ የሚያደርጋት መሆኑ ታምኖበታል። እርግጥ አለም ከደረሰበት የዘርፉ ምርምር አንፃር ሲታይ የሀገሪቱ የስፔስ ሳይንስ ተሳትፎ ገና የሚባል ቢሆንም፤ አሁን ላይ በዘርፉ የሚታዩ መነቃቃቶች ተስፋ ሰጪ መሆናቸው ይበል የሚያሰኝ ነው።
አዲስ ዘመን ጥቅምት21/2012
ተገኝ ብሩ