– በቱሪስት ቪዛ 559 ሶሪያውያን ገብተዋል
አዲስ አበባ፣ የኢሚግሬሽንና የዜግነት ጉዳይ መምሪያ የኢትዮጵያን ህግ ተላልፈው በልመና ላይ የተሰማሩ የሶሪያ ዜጎችን አሰሳ በማካሄድ ህጋዊ መስመር እንዲይዙ በማድረግ ላይ መሆኑንና እስካሁንም 118 ስደተኞችን መዝግቦ ለስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር ማስረከቡን አስታወቀ፡፡ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥም 559 ሶሪያውያን በቱሪስት ቪዛ ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸው ጠቅሷል፡፡
በመምሪያው የህዝብ ግንኙነት ምክትል ኃላፊ አቶ የማነ ገብረመስቀል ለጋዜጣው ሪፖርተር እንደገለጹት፣ የቁጥጥርና ክትትል ሥራ በሚያከናውነው የመምሪያው ክፍል አማካኝነት ቦሌ ሚካኤል፣ ቦሌ መድኃኒዓለም፣ መርካቶ አንዋር መስጂድ፣ በእንግዳ ማረፊያዎች፣ ሆቴሎችና በሌሎችም ይገኙባቸዋል ተብለው በተጠረጠሩ አካባቢዎች አሰሳ በማካሄድ በህዳርና ታህሳስ ወሮች ብቻ 77፣ ቀደም ሲል ደግሞ 41 ሶሪያውያንን መዝግቦ ለስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር በማስረከብ ህጋዊ ስደተኞች እንዲሆኑ ማድረግ ችሏል፡፡
መምሪያው አስፈላጊውን ግንዛቤ በመስጠት እንዲመዘገቡ ያደረገ መሆኑን የጠቆሙት አቶ የማነ፣ ግንዛቤውን ያገኙት ሌሎችንም በመቀስቀስ እንዲመዘገቡ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡ ስደተኞቹ ለምን እንዳልተመዘገቡ ተጠይቀው ‹‹በነበረባቸው የገንዘብ ችግርና የኢትዮጵያ መንግሥት ወደ ሀገራችን ይመልሰናል›› በሚል ስጋት ህጋዊ አሰራሩን እንዳልተከተሉ ምላሽ መስጠታቸውን አመልክተዋል፡፡
እንደ አቶ የማነ ገለጻ፣ ህጋዊ የስደተኞች ምዝገባ ላካሄዱት በተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ድጋፍ እየተደረገላቸው ቢሆንም ድጋፉ ለቤት ኪራይና ለምግብ በቂ ባለመሆኑ የተመዘገቡትም ቢሆኑ እየለመኑ ይገኛሉ፡፡ ችግሩን ለማቃለልና ለመንግሥት ክትትልና ቁጥጥር ሥራ እንዲያመች መጠለያ እንዲሠራላቸው መምሪያው ከስደተኞች ጋር በተያያዘ ለሚሠሩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሀሳብ አቅርቧል፡፡
መምሪያው የክትትል ሥራውን ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከጠቅላይ አቃቤ ህግ፣ ከስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደርና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት በማጠናከር አዲስ የሚገቡትንም ህጋዊ መስመር የማስያዝ ሥራ በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ የሶሪያዊያኑ በልመና መሰማራት ያልተጠበቀና ያልተለመደ በመሆኑ መምሪያው በኢ-ቪዛ አሰጣጡ ላይም ወደ ሀገር ከመግባታቸው በፊት ተገቢው ቁጥጥር መጠናከር እንዳለበት ግንዛቤ ተይዟል ብለዋል፡፡
በኢሚግሬሽን ህግ ስደተኛው ተላላፊ በሽታ ይዞ የሚገባ፣ በወንጀልና በአደዛዥ ዕጽ አዘዋዋሪነት የሚጠረጠርና የሀገሪቱ ሸክም መሆን የለበትም ያሉት ምክትል ኃላፊው፣ ኢትዮጵያውያንም ለስደተኞቹ ድጋፍ ሲያደርጉ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
አቶ የማነህ እንዳሉት፣ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ 559 ሶሪያውያን በቱሪስት ቪዛ ኢትዮጵያ ገብተው እንደነበር አስታውሰው፣ 339ኙ መመለሳቸውን ገልጸዋል፡፡ 50 ሶሪያውያን ደግሞ የመኖሪያ ፈቃድ ተሰጥቷቸው በተለያየ ሥራ መሠማራታቸው አመልክተዋል፡፡
የውጭ ዜጎች በህገወጥ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ፣ ከገቡ በኋላም ከተፈቀደላቸው ቀናት ውጭ እንዳይቆዩ፣ የሀገሪቱን ህግና ሥርዓት እንዳይጥሱ፣ ለሥራ የመጡትም ከተፈቀደላቸው የሥራ መስክ ውጪ እንዳይሰማሩ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ መምሪያው ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን ጽህፈት ቤት (ዩ ኤን ኤች ሲ አር) ቃል አቀባይ አቶ ክሱት ገብረእግዛብሄር እንደገለጹት፣ተቋማቸው ስደተኞቹ ባሉበት ቦታ ሄዶ እንዲመዘገቡ የማድረግ ኃላፊነት ባይኖርበትም ግንዛቤው ከሌላቸው በሚል መረጃ እንዲያገኙ በአረብኛ ጽሁፍ አዘጋጅቶ በማሰራጨትና በማነጋገር ባደረገው እገዛ 20 ቤተሰቦች እንዲመዘገቡ አድርጓል፡፡
የጥገኝነት ፈቃድ እስኪያገኙ ድጋፍ እያደረገላቸው መሆኑን ጠቅሰው፣ ኮሚሽኑ ሶሪያውያኑ በቱሪስት ቪዛ ገብተው ሱዳን ቆይተው ወደ ኢትዮጵያ የገቡ መሆናቸውን እንዲመዘገቡ ካደረጋቸው ስደተኞች መረጃውን ማግኘቱንም አስታውቀዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 20/2011
በለምለም መንግሥቱ