አዲስ አበባ፤ የቀረጥ ነጻ መብት በተለያዩ አካላት መፈቀዱ አገሪቱን ለዝርፊያ እየዳረገና በዓመትም 60 ቢሊዮን ብር እያሳጣ መሆኑ የፌዴራል ዋና ኦዲተር አስታወቀ።
የገቢዎች ሚኒስቴርን ከ2004 እስከ 2009 ዓመታት ያደረገው የክዋኔ፣ የፋይናንስና ሕጋዊነት ኦዲት ግኝቶች የማስተካከያ እርምጃው ውጤታማ እንዳልሆነ ተጠቆመ፡፡
የገቢዎች ሚኒስቴር በስድስት ዓመታት ኦዲት ግኝቶቹ የተሰጡ አስተያየቶችና ማሻሻያ ሃሳቦቹ ያሉበትን ደረጃ ለተቋቋመው ጥምር የኦዲት ግኝት ማሻሻል ኮሚቴና ለሚመለከታቸው አካላት ከትናንት በስቲያ ሪፖርት በቀረበበት ወቅት ዋና ኦዲተሩ አቶ ገመቹ ዱቢሶ እንደተናገሩት፤ ከቀረጥ ነጻ መብት የአገርን ጥቅም እየጎዳና በዓመትም እስከ 60 ቢሊዮን ብር እያሳጣ ነው። በመሆኑን የችግሩን ስፋት እና አሳሳቢነት በማየት መሰረታዊ መፍትሄ ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው፤ ከቀረጥ ነጻ መብቶች ለተፈቀደው አላማ መዋላቸውን የማረጋገጥ ሥራ መሥራት እንደሚገባ ገልጸው፣ በአሁኑ ወቅት ክፍተቱን ለማስተካከል እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡የቀረጥ ነጻ መብት የሚሰጡ አካላት ከ18 በላይ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ይህም በህግ አግባብ የሚስተካከል መሆኑን አረጋግጠዋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎም ከቀረጥ ነጻ መብት በተለያዩ አካላት መፈቀዱ አገሪቱን ለዝርፊያ የሚዳርግ በመሆኑ ለልማት ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ጉዳዮች ትኩረት ተደርጎ ሊተገበር ይገባል ብለዋል፡፡ የአቤቱታና ቅሬታ ሥርዓቱን ማዘመን፣ ፈጣን ምላሽ መስጠትና ጣልቃ ገብነትን ማስወገድ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
እንዲሁም ፌዴራል ዋና ኦዲተር ባካሄዳቸው የክዋኔ፣ የፋይናንስና ሕጋዊነት ኦዲት ግኝቶች ከተገኙ 645 የፋይናንስ ኦዲት ግኝቶች የማስተካከያ እርምጃ የተወሰደባቸውና የተጠናቀቁ 101ሲሆኑ፣ 196 በከፊል የተጠናቀቁ፣ 348 ግኝቶች ደግሞ በሂደት ላይ ናቸው። ይህም የፋይናንስ ግኝት መጠኑ 11 ነጥብ 38 ቢሊዮን ብር ሲሆን፤ በተሠራው ሥራ ገቢ ማድረግ የተቻለው አንድ ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ነው፡፡
በኦዲት ግኝት ከተለዩት 19 ከባድና ቀላል ተሸከርካሪዎች ዘጠኝ ተሸከርካሪዎች ቢሸጡም፤ 10 ተሸከርካሪዎች ሊሸጡ አለመቻላቸው ተገልጿል፡፡ ጅንአድ በዱቤ ከገዛቸው የተወረሱ እቃዎች ሳይሰበሰብ ለረጅም ጊዜ የቆየ ብር 610 ሚሊዮን 100ሺ 435.39 ዕዳ ውስጥ በአጠቃላይ ገቢ ያደረገው ብር 8,507,343.79 ብቻ ነው፡፡ ለአዲስ ፋናም በዱቤ ከተሸጡ የተወረሱ እቃዎች 10ሚሊዮን 950ሺ 208.99 ብር ያልተሰበሰበ ሂሳብ መኖሩ ተጠቁሟል፡፡
በአገር ውስጥ ታክስ ኦዲት ተግባር አፈጻጸም ከታዩ 18 ግኝቶች ውስጥ በ15ቱ ላይ የማስተካከያ እርምጃ በመውሰድ ተግባራዊ ሲደረግ፤ የጉምሩክ ሥነ-ሥርዓት አፈፃፀም ሂደት ላይ ከታዩት 19 ግኝቶች በ11ዱ ላይ የማስተካከያ እርምጃ በመውሰድ ተግባራዊ መደረጉ ተጠቁሟል፡፡
ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ፤ በቀድሞው የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ኦዲት ሲደረግ የታክስ መረጃ አያያዝ ሥርዓት አለመዘመን፣ ህጉንና የአሰራር ሥርዓቱን መሰረት ያደረገ የገቢ ግብር ታክስ የመሰብሰብ ክፍተት፣ ለቅሬታ ሰሚ የቀረቡ አቤቱታዎች በወቅቱ ውሳኔ አለማግኘታቸውና የተወሰነባቸውም በህግ አግባብ ማስከፈል አለመቻል ችግሮች እንደተስተዋሉ አስታውሰዋል፡፡ ጅንአድና አዲስ ፋና እዳቸውን ለማስከፈል ተቋማቱን በማደራደር መፍትሄ እንዲገኝ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡
የኮሚቴው አባላትም ችግሩን የሚመጥን ሥራ አለመሠራቱን፣ የተደረጉ እንቅስቃሴዎች የሚፈለገውን ውጤት ማስገኘት እንዳላስቻሉ በመጠቆም፤ ትኩረት ተደርጎበት ሊሠራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ሚኒስትሯ ወይዘሮ አዳነች፤ የታክስ ሥርዓቱን ማዘመን ካልተቻለ ‹‹እናስተካክላለን›› ማለት እንደሚከብድ ይጠቁማሉ፡፡ በተደረገው ግምገማም ማሻሻል የሚያስችሉ ተግባሮች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡
እንደእርሳቸው ማብራሪያ፤ ግብር ከፋይ፣ ሠራተኞችና ማህበረሰቡ ጋር የአስተሳሰብ ቀረጻ ሥራ መሠራት ይኖርበታል፡፡ ሠራተኞች ህግን መሰረት አድርገው የመሥራት ክፍተት አለባቸው፡፡ ግብር ከፋዩም ክፍተቱን ተጠቅሞ ግብር የመሰወር ችግር ይታያል፡፡ ሠራተኞችን በሥልጠና በማገዝ፣ ማትጊያዎችን በመስጠት ሠራተኞች በእኔነት ስሜት እንዲተገብሩ እየተሠራ ነው፡፡
የታክስ ሥርዓቱ ከሰው እጅ ንክኪ ማላቀቅ እንደሚገባ የሚገልጹት ወይዘሮ አዳነች፤ አዲስ ቴክኖሎጂ ለመተግበር እየተሠራ እንደሚገኝም ይናገራሉ፡፡ አቤቱታ በፍጥነት የማይወሰን፣ አሰራሩም የማይገመገም፣ ጣልቃ ገብነትም የነበረበትና በሳምንት አራት መዝገቦች ብቻ ውሳኔ ያገኙ እንደነበር በማስታወስም፤ አሁን በሳምንት እስከ 34 መዝገቦች ውሳኔ እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አፈ ጉባኤው በበኩላቸው፤ አገሪቱ ለምታደ ርጋቸው ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ፣ ለአገር ልማትና እድገት ገቢ ወሳኝ ዘርፍ እንደመሆኑ ባለድርሻዎች በንቃት እንዲሳተፉ መደረጉ ተገቢ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ባለሙያዎችን በመልካም ሥነ ምግባር መቅረጽ፣ ማበረታታት፣ ማብቃትና መገንባት እንደሚገባና ውጤታማ ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡ በተቋምም ሆነ ከተቋም ውጪ የሚያጠፋ ሰው ሲኖር ህግ ማስከበር እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 20/2011
በዘላለም ግዛው