
በታዛኒያ አዘጋጅነት ለሚካሄደው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ የሴቶች ዋንጫ(ሴካፋ) እንዲሁም ለ2020 የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በርካታ ውድድሮች የሚያደርጉት ሉሲዎቹ አሰልጣኝ ተቀጥሮላቸዋል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛውን በዋና አሰልጣኝነት የቀጠረ ሲሆን በበጀት እጥረት ሴካፋ ላይ ላይወዳደሩ ይችላሉ የተባሉት ሉሲዎቹ በቅርቡ ዝግጅታቸውን እንደሚጀምሩ ተረጋግጧል ።
አሰልጣኝ ብርሃኑ እኤአ በ2012 ኢኳቶሪያል ጊኒ ባዘጋጀችው የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ ሉሲዎቹን ማብቃት የቻለ ሲሆን በፕሪሜር ሊጉ ለሶስት ተከታታይ ዓመት ኮከብ አሰልጣኝ ሆኖ መሸለሙ ይታወሳል። የኢትዮጵያ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ በመሆን ውጤታማ ጉዞ ላይ የነበረችው አሰልጣኝ ሠላም ዘርዓይ ካፍ ባቀረበላት ጥያቄ መሰረት የሴቶች የኤሊት ኢንስትራክተር ኮርስ ለመውሰድ ወደ ግብጽ ሰሞኑን ከመጓዟ ጋር ተያይዞ ነው ፌዴሬሽኑ የአሰልጣኝ ለውጥ ያደረገው። አሰልጣኝ ሰላም ከጥቅምት 23 እስከ 27 በሚቆየው የሴት አሰልጣኞች የኤሊት ኢንስትራክተርነት በማግኘት የመጀመሪያዋ ሴት አሰልጣኝ ትሆናለች ተብሎም ይጠበቃል።
የተለያዩ ክለብ ደጋፊዎች በአዲስ አበባ መከሩ
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ክለብ የደጋፊዎች ማህበር ለመመስረት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ጥሪ የተደረገላቸው የተለያዩ ክለብ ደጋፊዎች የምክክር መድረክ አድርገዋል። ከተለያዩ ክለብ የተወጣጡ ደጋፊዎች የተገኙ ሲሆን በመድረኩም ስለ ስፖርታዊ ጨዋነትና የክለብ ደጋፊዎች ኃላፊነት፣ በቀጣይ የኢትዮጵያ ክለብ ደጋፊዎች ማሕበር አንድነት በሚቋቋምበት ሁኔታ፣ የዓመቱ የመክፈቻ ጨዋታ በሆነው የመቀለ እና ፋሲል ከነማ የአሸናፊዎች አሸናፊ ጨዋታ ዙርያ ውይይቶች ተደርገዋል። በውይይቱም በምስረታው ዙርያ መነሻ ፅሁፍ የሚያዘጋጁ ደጋፊዎች ተመርጠው ኃላፊነት የተሰጣቸው ሲሆን። ፋሲል ከመቀለ የሚያደርጉት ጨዋታ በሠላም በሚጠናቀቅበት ሁኔታ ላይ ምክክር በማድረግ አስተባባሪዎች ከተለያዩ ክለቦች ተመርጠዋል።
የደብሊን ማራቶን የሎተሪ ሲስተም
በ2020 የደብሊን ማራቶን ለመሳተፍ የሎተሪ ሲስተም መዘርጋቱን አዘጋጆቹ አሳወቁ። ቀደም ሲል በውድድሩ ለመሳተፍ በኤሌክትሮኒክስ የመመዝገቢያ ዘዴ ቀድሞ ያመለከተ ቅድሚያ የሚሰጠው ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በውድድሩ ለመሳተፍ የአመልካቾች ቁጥር ማየሉን ተከትሎ የሎተሪ ሲስተም ማስፈለጉ ተነግሯል። ይህም አመልካቾችን ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ለማገልገል ታስቦ መሆኑን የውድድሩ ዳይሬክተር ጂም ኦሕኔይ ለመገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል። በውድድሩ ለመሳተፍ አመልካቾች ከመጪው የፈረንጆች ሕዳር አንድ አንስቶ ለሰላሳ ቀናት መመዝገብ የሚችሉ ሲሆን ጥር ላይ ሎተሪውን ያሸነፉ ተሳታፊዎች በአጭር የፅሁፍ መልዕክትና በኢ ሜይል እንደሚገለፅላቸው ታውቋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 19/2012