የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች መዲና ሀዋሳ ከተማን ለቀን በዙሪያዋ ባሉ ወረዳዎች ላይ የግብርና ልማቱን መስክ ምልከታ ለማድርግ ማልደን ተነስተናል፡፡ የአስፓልቱ ዳርና ዳር ባለበሰው የበጋው ሃሩር ባልበገረው አረንጓዴ እየተደመምን ንጹህ አየርም እየሳብን፣ዋናውን መንገድ ለቀን ወደ ሸበዲኖ ወረዳ የሚያስገባውን ጥርጊያ መንገድ ይዘናል፡፡
ይህ አድናቆትና መመሰጥ ግን ብዙም አልቆየም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የአካባቢው ተፈጥሮዊ አቀማመጥ ገደላማና ኮረብታማ መሆን እንዲሁም ጥርጊያ መንገዱ በአግባቡ ያልተሰራ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የሆነ መንገራገጭ ያጋጠመን መሆኑ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ መኪናችን ለዚህ አይነት መንገድ አዲስ መሆኑን በሚያሳብቅ ሁኔታ ከወዲያ ወዲህ ስታላትመን ጥቂቶቻችን በእግራችን ወርደን መሄድን መረጥን፡፡
ከጥቂት እንግልት በኋላም የጉዛችን አላማ ከሆነው አርሶአደር ጉጃ ቤቴራ የቡና ማሳ ስንደርስ ግን ድካማችን እንድንረሳ የሚያደርግ ነገር ተመለከትን፡፡ ይኸውም አርሶአደሩ መሬታቸው ተደፋትና ለእርሻ ፈፅሞ የማይመች ቢሆንም ተፈጥሮዊ ይዘቱን ጠብቆ የቡና ልማታቸውን ያካሄዱበት ጥበብ ነው፡፡ በተጨማሪም በእርከን መልኩ የገነቡት የቡና ማድረቂያ አልጋም ለአካባቢው ልዩ ድባብ ፈጥሮለታል፡፡
አርሶአደር ጉጃ ቤቴራ በሸበዲኖ ወረዳ የሀርባ ጎና ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ ስድስት ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩት ከልጅነት እስከ እውቀታቸው በቆዩበት የቡና እርሻ ስራ ነው፡፡ አርሶአደሩ 4ነጥብ 5ሄክታር መሬታቸው ላይ ቡናን የሚያለሙት እንዲሁ ከቤተሰባቸው የወረሱት ስራ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን ለሙያው ልዩ ፍቅር ያላቸው በመሆኑ ጭምር እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡ ለዚህም ይመስላል እለት እለት ምርትና ምርታማነታቸው ያድግ ዘንድ አዳዲስ ቴክኖሎ ጂዎችንና አሰራሮችን በመቀበል ፈጥነው ወደ ስራ የሚገቡት፡፡ ይህም የስራ ባህላቸው በወረዳው የግብርና ባለሙያዎች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት አሰጥቷቸዋል፡፡ ከዚህም አልፎ በአገር አቀፍ ደረጃ ከምርጥ አርሶአደሮች አንዱ ሆነው የሜዳሊያ ተሻላሚ ሆነዋል፡፡
አርሶአደሩ ተሞክሯቸውን ለሌሎች አርሶአደሮች በማካፈልና የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን እንዲጠቀሙ ምክር በመስጠት ረገድም በግንባር ቀደምትነት ስማቸው ይጠቀሳል፡፡በአካባቢያቸው ለሚገኙ 14 ወጣቶች ጊዜያዊና ቋሚ የስራ እድል በመፍጠርም አርዓያ ሆነዋል፡፡ግለሰቡ ምንም እንኳ ከትምህርት ቤት ደጃፍ ባይደርሱም አዲስ ነገር ቶሎ ለመቀበል ፍላጎት አላቸው፡፡ አዳዲስ አሰራሮችን በመተግበር ለዘመናት ባደረጉት ብርቱ ጥረትም ሀብት ማፍራት ችለዋል፡፡ በእርሻቸው ስፍራ ከገነቧቸው መኖሪያ ቤት በተጨማሪ በለኮ ከተማ ሶስት የንግድና የመኖሪያ ቤቶች ገንብተዋል፡፡በአሁኑ ጊዜም ንብረታቸውን ጨምሮ ስምንት ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ካፒታል አፍርተዋል፡፡
አርሶአደር ጉጃ እንደሚሉት፤ እስከዛሬ ድርስ የሚያመርቱትን ቡና የሚሸጡት ለህብረት ስራ ማህበር ስለነበር ከእርሳቸው ይልቅ ተጠቃሚ የሚሆኑት ማህበራቱና ነጋዴዎቹ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን መንግስት ሰፊ እርሻ ላላቸው አርሶአደሮች በፈጠረው እድል በመጠቀም የንግድ ፍቃድ በማውጣት ያመረቱትን 15ሺ ኪሎ ግራም የቡና ምርት በራሳቸው አጥበው፣ ፈልፍለውና ቀሽረው ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ በዝግጅት ላይ ይገኛሉ፡፡
የዘንድሮ ምርት ደግሞ ከወትሮ በተለየ መልኩ ከፍተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ምርታቸውን በስፋት ለመሸጥ ጓጉተዋል፡፡በአሁኑ ወቅት ያለው የቡና ዋጋ አነስተኛ ከመሆኑ ከወጪያቸው ጋር አለመመጣጠኑ አሳስቧቸዋል፡፡እርሳቸው እንዳሉት አንድ ኪሎ ግራም እሸት ቡና በዘጠኝ ብር እየተሸጠ ነው፡፡ ዋጋው በዚሁ ከቀጠለ ትርፍ ሊያገኙበት ቀርቶ የሰራተኛ ደመወዝና የተለያየ ወጪያቸውን እንኳን አይሸ ፍንላቸውም፡፡
አርሶአደር ጉጃ ለስራ ማስኬጃ የሚሆን ገንዘብ እጥረት እንዳለባቸው ይናገራሉ፡፡የገንዘብ ችግሩ ምርቱን በጥራት ለመላክ ለሚያደርጉት ጥረት አሉታዊ ተፅእኖ እየፈጠረባቸው እንደሆነም ይገልጻሉ፡፡ በተለይ ደግሞ ለጉልበት ሰራተኞቻቸው በየሳምቱ የሚፈጽሙት ክፍያ አቅማቸውን እየተፈታተነው መሆኑን ያነሳሉ፡፡መንግስት ችግራቸውን አይቶ የብድር አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበትን እድል እንዲያመቻችላቸውም ይጠይቃሉ፡፡
ከአርሶአደሩ ማሳ ወጥተንም በዘመናዊ መንግድና በተደረጃ መልኩ እሸት ቡና ከሚደርቅበት ፥ ከሚታጠብበት፣ ከሚፈለፈልበት የአቶ ሃጂአባቱ አብደላ ጓሮ ዘልቀናል፡፡ ቁጥራቸው በርከት ያሉ ሰራተኞች በቡና ለቀማና እጥበት ላይ ተጠምደዋል፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ታጥቦ ተቀሽሮ የተዘጋጀውን ቡና ወደ መጋዘን ለማስገባት ይሯሯጣሉ፡፡ ባለሃብቱ አቶ ሃጂአባቱ ግን ከአንድ ዛፍ ስር ቁጭ ብለዋል፤ እኛም አጠገባቸው እስከምንደርስ ድርስ ሰራተኞቻቸውን የሚመለከቱ ቢመስሉንም በሃሳብ ርቀው መሄዳቸውን ታዘብን፡፡
የመጣንበትን አብይ ጉዳይ ካሳወቅናቸው በኋላም አቶ ሃጂ እንዲህ በሃሳብ ያነጎዳቸውን ምክንያት እንዲያጋሩን ጠየቅን፡፡ የሚያጓጓው የቡና ምርት ገዢ ማጣቱና ዋጋው መውረዱ ነበር ያስተከዛቸው፡፡ «እንደምታዩት በርካታ እሸት ቡና ከገበሬው ገዝቼ በጥራት እያዘጋጀሁ ነው፡፡፡ይሁንና ላኪዎቹ በጥራት ከተመረተው ይልቅ ጥራት የሌለውንና በዋጋም የወረደውን ቡና ነው የሚፈልጉት፡፡ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ምርት ገዢ አጥቶ መጋዘን ውስጥ ተከማችቷል» በማለት በቅሬታ ይገልጻሉ፡፡
ወደ ቡና ንግድ ከመግባታቸው በፊት በሸቀጣሸቀጥ ንግድ ስራ ላይ ተሰማርተው እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ ሃጂአባቱ፤ መዕዋለ ንዋያቸውን ያፈሰሱበት የቡና ንግድ ስራ ከአመት አመት ይሻሻላል በሚል ተስፋ ቢሰሩም ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆኖባቸዋል፡፡ የቡና ንግድ ተስፋ እንዲቆርጡ አድርጓቸዋል፡፡ «አንድ ኩንታል ቡና በ900 ብር ከአርሶአደሩ ተረክቤ እኔ የምሸጠው 1ሺ 200 ብር ነው፤ ይሁንና አንድ መኪና ቡና ለማስጫን እስከ መቶ ሺ ብር የሚደርስ ወጪ አወጣለሁ» ሲሉም ወጭና ገቢ አለመመጣጠኑን ይገልጻሉ፡፡
በተለይም ለ150 ሰራተኞቻቸውም ደመወዝ ለመክፈል እየተቸገሩ መሆኑን ጠቅሰው፤ በአጠቃላይ ስራው « ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ››ስለሆነባቸው በአሁኑ ወቅት ከቡና ንግድ ስራ ለመውጣት እያንገራገሩ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ በመሆኑም መንግስት መፍትሄ አንዲሰጣቸው ይፈልጋሉ፡፡ በተለይም አገሪቱ ከቡና የሚገባውን ያህል የውጭ ምንዛሬ እንድታገኝ ከተፈለገ በጥራት ላይ የሚደራደሩ ላኪዎችን ከገቢያ ውጭ ሊያደርግ እንደሚገባ ያስገነዝባሉ፡፡
እንደእርሳቸው ገለፃ፤ በአሁኑ ጊዜ ከፍታውን እጅ የሚይዝ ጥራት የሌለው ቡና ጥራት ካለው ጥቂት ቡና ጋር በመቀላቀል ለገበያ እየቀረበ ነው፡፡ መንግስት እንዲህ ያለውን ስራ የሚሰሩ ነጋዴዎች ተከታትሎ ማስቆምና ህጋዊዎቹ የሚበረታቱበትን አሰራር መዘርጋት አለበት፡፡ በጥራት ለሚያመርተውም ተመጣጣኝ ክፍያ እንዲያገኝ የማድረግና ገበያ ማፈላለግም ጎን ለጎን መስራት ይገባዋል፡፡
አቶ ተስፋዬ ሆላና ደግሞ የቴላሞና አካባቢው የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበር የሂሳብ ባለሙያ ናቸው፡፡ እንደእርሳቸው ማብራሪያ፤ ማህበሩ በ1968ዓ.ም 87 አባላት ይዞ በ 868 ብር ካፒታል የተመሰረተ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት 418 አበላትን ማፍራት ችሏል፡፡ካፒታሉንም ወደ 42 ሚሊዮን 401 ሺ ብር ማሳደግ ችሏል፡፡ ማህበሩ አራት የቡና ማጠቢያና መፈልፈያ እንዲሁም ሁለት የቡና ማበጠሪያ ማሽን ያሉት ሲሆን፣ ለኮ ከተማ ውስጥ ለተለያዩ አገልግሎቶች መስጫ የሚውል በ19ሚሊዮን ብር ወጪ ባለአራት ወለል ፎቅ ገንብቷል፡፡ በተመሳሳይም በሃዋሳ ከተማ ላይ ህንፃ ገንብቷል፡፡ ማህበሩ በአሁኑ ወቅት 44 ቋሚና 750 ጊዚያዊ ሰራተኞች አሉት፡፡
ማህበሩ በ2010 ዓ.ም1ሚሊዮን 800ሺ ኪሎ ግራም ቡና ለመሰብሰብ አቅዶ 1ሚሊዮን 341ሺ71 ኪሎ ግራም መሰብሰቡንና በ2011 ዓ.ም ደግሞ ከፍተኛ ምርት በመገኘቱ ሶስት ሚሊዮን 250ሺ ኪሎ ግራም ለመሰብሰብ መታቀዱን የገለጹት አቶ ተስፋዬ ምርቱ ከፍተኛ በመሆኑ አጥቦ ቀሽሮ ለገበያ ለማቅረብ የሚያስፈልገውን ገንዘብ በብድር ከባንክ ማግኘት አለመቻሉ ተግዳሮት እንደፈጠረበት ይናገራሉ፡፡
በሲዳማ ዞን በሸበዲኖ ወረዳ የቡና ሻይ የቅመማ ቅመም ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ኤሌያስ አየለ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ ወረዳው ቡና አብቃይና አብዛኛውም አርሶአደር ኑሮን መሰረት ያደረገው በቡና ላይ ነው፡፡ አስተዳደሩ የቡና ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ አርሶአደሩንም በሚገባ ተጠቃሚ የማድረጉ ጉዳይ ዋነኛ አጀንዳው አድርጎ እየሰራ ይገኛል፡፡
በተለይም አርሶአደሩ የተሻሻለ የቡና ዝርያ በስፋት እንዲያገኝና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀም የማድረጉ ስራ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡፡የአካባቢው ዝርያዎች ምርትማ ቢሆኑም በሽታ ከመቋቋም አንፃር ውስንነት ያለባቸው በመሆኑ በሽታን መቋቋም የሚችሉ በምርምር የተለቀቁ ዝርያዎችን እንዲተኩ የማድረግ ስራ በስፋት እየተከናወነ ነው፡፡
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ ከአገር በቀል የቡና እግር 1ነጥብ 5 ኪሎ ግራም ቡና ብቻ ነው የሚገኘው፡፡ ከተሻሻለ ዝርያ ከአንድ እግር የቡና ዛፍ እስከ ስድስት ኪሎ ግራም መሰብሰብ ተችሏል፡፡የሲዳማ ቡና በአለም ገበያ ላይ ያለውን ስም ይዞ እንዲቀጥል ተፈጥሯዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ እንዲመረት ከፍተኛ ቁጥጥር ይደረጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ እያንዳንዱ አርሶአደር በጓሮው ከእፅዋት ብስባሽ ማዳበሪያ እንዲያመርት ድጋፍ ይደረግለታል፡፡በአሁኑ ወቅት አብዛኛው አርሶአደር ቢያንስ ሁለት ሁለት የብስባሽ ማዳበሪያ ባንክ እንዲረው ተደርጓል፡፡
የወረዳው የግብርና ባለሙያዎች ለአርሶአደሩ ሙያዊ ድጋፍ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ የቡና ዛፍ በፃሃይና በውርጭ እንዳይመታና ተፈጥሯዊ ጣዕም እንዲይዝ ከፍተኛ የዛፍ ተከላና የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል የሚደረጉት ድጋፎች ለአብነት ተጠቅሰዋል፡፡
የገበያ ትስስር ለመፍጠርም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እተየሰራ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ተስፋዬ፤ በተለይም ከዚህ ቀደም የነበረውን ረጅም የገበያ ሰንሰለት በማሳጠር አርሶአደሩ የላቀ ተጠቃሚ እንዲሆን መደረጉን ይጠቁማሉ፡፡ በተደገው ልዩ ማበረታቻና ድጋፍ በአሁኑ ወቅት በወረዳው በግል ባላሃብቱ 28 የታጠበ ቡና እና ሶስት የደረቅ ቡና ኢንዱስትሪዎች መቋቋማቸውን ይጠቅሳሉ፡፡
በኢንዱስትሪዎቹ በየቀኑ በአማካኝ እስከ 30ብር ድርስ የሚከፈላቸው ከ3ሺ900 ሰራተኞች በላይ የስራ እድል መፈጠሩን ነው የሚጠቁሙት፡፡ ኢንዱስትሪዎቹ በአመት ከ10 ሚሊዮን ኪሎ ግራም እሸት ቡና በላይ እንደሚሰበስቡና ዘንድሮም እስከ 11 ሚሊዮን እሸት ቡና ለመሰብሰብ ታቅዶ እስካሁን ወደ 10 ሚሊዮን ኪሎ ግራም መሰብሰቡን ያስረዳሉ፡፡
እንደግብርና ባለሙያው ማብራሪያ፤ ምንም እንኳን ነባር ዝርያዎችን በተሻሻሉት የመተካቱ ስራ በስፋት ቢሰራም አካበቢው ግንባር ቀደም ቡና አብቃይ የመሆኑን ያህል በፍጥነትና በስፋት ተደራሽ የማድረጉ ስራ ውስንነት አለበት፡፡ አርሶአደሩም ባመረተውና ባወጣው ልክ ተጠቃሚ እንዲሆን የማድረጉ ጉዳይም ገና ብዙ ያልተሰራበትና ለቀጣይ ምርትና ምርታማነቱን ለማስቀጠል ተግዳሮት ሆኖበታል፡፡ በተለይም ደግሞ በነፃ ገበያ ሰበብ ዋጋ ላይ አሉታዊ ሚና በመጫወት አርሶአደሩን ከጥቅም ውጭ እያደረጉ ያሉ ደላሎችን በሚገባ በመቆጣጠርና በመከታተል ረገድ አሁን ቀሪ የቤት ስራዎች አሉበት፡፡
በአሁኑ ወቅት አርሶአደሩ ካመረተው ምርት ተጠቃሚ ሳይሆን፣ ጥራት ያለው ምርት እንዲያቀርብ መጠበቅ ተገቢ እንዳልሆነ የሚናገሩት የግብርና ባለሙያው በአርሶአደሩ ተጠቃሚነት ላይ መስራት እንደሚገባ ይገል ጻሉ፡፡ መንግስት በ2009ዓ.ም እንደ አማራጭ እያንዳንዱ አርሶአደር ሁለት ሄክታርና ከዚያ በላይ መሬት ካለው በራሱ ቡናውን መላክ የሚችልበትን መመሪያ ማውጣቱንም አስታው ሰው፤ ይሁንና አርሶአደሮቹ አቅም ባለመጠናከሩ ከባንክ የብድር አቅርቦት ማግኘት እንዳልቻሉ ነው የሚገልፁት፡፡
የቡና ልማት አመቱን ሙሉ የሚሰራ ስራ በመሆኑ ገበያ እስከሚወጣ ተከታታይነት ያለው ድጋፍና ክትትል እንደሚፈልግ የተናገሩት ደግሞ የሲዳማ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ቃሬ ካውቻ ናቸው፡፡ ባለፉት አመታት የዞኑ አስተዳደርም ሆነ የክልሉ መንግስት አርሶአደሩ በኤክስቴንሽን ተጠቃሚ እንዲሆን የማድረግ ስራ ሲያከናውኑ መቆየታቸውን ይገልፃሉ፡፡
አቶ ቃሬ እንደሚሉት፤ የምርቱ መጠን ከፍተኛ በመሆኑ በዞኑ ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ የቡና ማጠቢያ ማሽኖች ከወትሮው በተለየ ከሚጠበቀው ሰዓትም በላይ እንዲሰሩ ተደርጓል፡፡በሙሉ አቅም በማሽኖቹ መጠቀም ቢቻልም ከፍተኛ ምርት በመኖሩ በወቅቱ አጠናቅቆ ለገበያ ለማቅርብ ችግር እንዳያጋጥም ስጋት አሳድሯል፡፡ የማጠቢያ ማሽን ለማሟላት ማነቆ የሆነባቸው ከባንክ ብድር አለማግኘ ታቸው ሲሆን ይህም ለአርሶአደምሩም ላኪው ላይ የራሱን ጫና አሳድሯል፡፡
የፌዴሬል መንግስት ችግሩን ተገንዝቦ የመፍትሄ አቅጣጫ አስቀምጦ የነበረ ቢሆንም እስካሁን ተፈፃሚ አለመሆኑን የዞኑ አስተዳዳሪ ያመለክታሉ፡፡ ችግሩ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውስብስብ አሰራር ጋር ተያይዞ የተፈጠረ መሆኑንም ያነሳሉ፡፡ ባንኩ በሁሉም ቅርንጫፎቹ ወጥ የሆነ አሰራር ባለመዘርጋቱ መመሪያ አልተሰጠኝም የሚል ምክንያት በመስጠት ተፈጻሚ እንዳላደረገው ይገልጻሉ፡፡ የዞኑ አስተዳደር መፍትሄ ለማግኘት ቢወያይም፤ በደብዳቤ ቢያሳውቅም ከባንኩ በቂ ምላሽ ማግኘት አለመቻሉን ነው የጠቆሙት፡፡
በተንዛዛው አሰራር ምክንያት በዋናነት አቡና አምራቹ አርሶአደር ተጎጂ ቢሆንም በተዘዋዋሪ የንግዱ ማህበረሰብ እየተቸገረ መሆኑን አቶ ቃሬ ይናገራሉ፡፡ መንግስትም ከዘርፉ ማግኘት የሚገባውን ጥቅም እያሳጣ እንደሆነ አመል ክተው፤ ዘርፉ ባላደገበትና ሀገሪቷም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እያጋጠማት ትኩረት አለመሰጠቱ ተገቢ እንዳልሆነ ይገልፃሉ፡፡
በባንኩ ላይ የቀረበውን የብድር አቅርቦት ቅሬታ በተመለከተ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኮርፖሬት ኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ በልሁ ታከለ በሰጡት ምላሽ ባንኩ በመንግስት ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ዘርፎች በተለይም ለውጭ ንግድ የብድር አቅርቦት ያመቻቻል፡፡ ለሲዳማ ዞን ቡና ላኪዎችም በ2008ዓ.ም ከግል ባንኮች የተበደሩትን ገንዘብ መክፈል ባለመቻላቸው ያስያዙት ሃብት እንዳይወረስና ልማቱ እንዳይቋረጥ በመንግስት በተሰጠ አቅጣጫ ንግድ ባንክ እዳቸውን ከፍሏል፡፡ ዕዳው የተከፈለላቸው ቡና ላኪዎች ግን እስካሁን ለባንኩ ባለመክፈላቸው ተጨማሪ ብድር አልተፈቀደላቸውም፡፡
ይህ ማለት ግን ሁሉንም ላኪዎችና አርሶአደሮች ይመለከታል ማለት እንዳልሆነ አቶ በልሁ አመልከተው፤ በተለይም በቀጥታ ቡና ለመላክ ፈልገው ፍቃድ አውጥተው የመጡ አርሶአደሮች እንደሌሉ እስካሁንም በዚህ ደረጃ ባንኩ ብድር ተጠይቆ የከለከለበት አግባብ አለመኖሩን ያስረዳሉ፡፡ ከላኪዎቹ ጋር በተያየዘ ግን ከዞኑም ሆነ ከክልሉ መስተዳደር ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶች መደረጋቸውን አምነው፤ በቀጣይ የመፍትሄ አቅጣጫ ይሰጣል የሚል እምነት እንዳላቸው ነው ያስገነዘቡት፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 19/2011
ማህለሌት አብዱል