ዩኒቨርሲቲው የሠራዊቱን ጥንካሬ በትምህርትና በምርምር ከማዳበሩ ባሻገር መሪዎችን እያፈራ ነው

ቢሾፍቱ፦ የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ የሠራዊቱን ጥንካሬ በትምህርትና በምርምር ከማዳበሩ ባሻገር መሪዎችን እያፈራ ነው ሲል የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ። የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ቢሾፍቱ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሠለጠናቸውን ተማሪዎች አስመረቀ።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ የዩኒቨርሲቲው የምረቃ መርሐ ግብር ትናንት ሲካሄድ እንደገለጹት፤ የሀገራችንን ሉዓላዊነትና ሀገራዊ ጥቅም በታማኝነት የሚያስጠብቅ ሙያዊ ብቃቱ የተመሰከረለት ወታደራዊ ኃይል ለማፍራት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው። የመከላከያ ሠራዊት በላቀ ደረጃ ለመፈፀም የሚያስችለውን የፕሮፌሽናል ሠራዊት ግንባታ ሥራዎችን አጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።

የመከላከያ ሠራዊት ተልዕኮ ከጥበብ፣ ከመማር እና አዕምሮን ከመቅረጽ ውጭ ሊሳካ አይችልም ያሉት ሚኒስትሯ፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ በዚህ ተልዕኮ ውስጥ ያለው አፈፃፀም ስኬታማነት ትልቅ ተቋማዊና ሀገራዊ አንድምታዎች እንዳሉት መረዳት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ የዕውቀት በሩን ክፍት ካደረገበት ቀን ጀምሮ የሠራዊቱን አባላት በዕውቀት፣ በዓላማ እና በልህቀት እየቀረፀና እያበቃ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ዘመናዊና ብቃት ያለው ሠራዊት በመገንባት ወደ ፈጣን እድገት በመገስገስ ላይ እንደምትገኝ ጠቁመው፤ ዩኒቨርሲቲው የሠራዊቱን ጥንካሬ በትምህርት፣ በምርምርና ፈጠራ ከመቅረፁም በላይ መሪዎችንም አፍርቷል። ይህም ዩኒቨርሲቲው ከማስተማር በላይ መሥራቱን ገልፀዋል።

ዩኒቨርሲቲው ሀገራዊና ተቋማዊ ሪፎርሙን ውጤታማ ለማድረግ የመከላከያ ሠራዊቱን በዘመናዊ ሳይንስ እና በዓለም አቀፍ ወታደራዊ ፈጠራና ምርምሮች ማብቃት በማላበስ ያላሰለሰ ጥረት ማድረጉንም የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ገልፀዋል።

የመከላከያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ብርጋዲየር ጄኔራል ከበደ ረጋሣ በበኩላቸው፤ የዩኒቨርሲቲው 88 በመቶ የሚሆኑት ምሩቃን የመውጫ ፈተናውን በብቃት ያለፉ መሆናቸውን ገልፀው፤ ዩኒቨርሲቲው ለሀገሪቱ ብቁ እና በሥነምግባር የታነፁ ባለሙያዎች እያፈራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ዩኒቨርሲቲውም ለአካባቢው ማኅበረሰብ ችግር ፈቺ የሆኑ የምርምር ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረው፣ ነባር የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችም በተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊነቶች ላይ ከሙያተኝነት እስከ ከፍተኛ አመራር ደረጃ የደረሱ እንዳሉ ገልፀዋል።

የተማሪውን ብዛት እና ጥራት ለማሻሻል ዩኒቨርሲቲው ሰፊ ሥራ ተሠርቷል። ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ትምህርት እና ሥልጠና እየሰጠ እንደሚገኝ አመልክተዋል።ተመራቂዎች ኢትዮጵያ በየዘመኑ ጀግኖችን የምታፈራ ሀገር ለመሆኗ ትልቅ ማሣያ ናችሁ ያሉት ሚኒስትሯ፤ የመከላከያ ዩኒቨርሲቲ የሠለጠነ የሠራዊት አባላትንና ሲቪል አመራር በማፍራት ላይ እንደሚገኝና በዚህም በእውቀት፣ በዓላማና በሙያዊ ልህቀት የታነጹ ሙያተኞችን እያፈራ እንደሆነ ተናግረዋል።

የሠራዊቱን የወታደራዊ ቴክኖሎጂ ብቃት ለማላቅ እየሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ በተለይም ዘመናዊ የሠራዊት ግንባታን በቴክኖሎጂ ማገዝ የሚችሉ ብቁና ሥነ-ምግባር ያላቸውን ሙያተኞች እያፈራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ዩኒቨርሲቲው ለሀገርና ለመጪው ትውልድ የሚሻገር ሥራ መሥራቱን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አስገዝበው፤ ተመራቂዎች በታማኝነት፣ በቅንነትና በሥነምግባር ሀገራቸውን ማገልገል እንዳለባቸው በአፅንዖት ተናግረዋል።

ቢሾፍቱ የሚገኘው የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ትናንት የተመረቁ ተመራቂዎች ትምህርታቸውን በምሕንድስና፣ በጤና እና በሀብት አስተዳደር ዘርፍ በመጀመሪያ እና ሁለተኛ ዲግሪ መርሐ ግብር የተከታተሉ መሆናቸው ታውቋል።

በመክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን እሁድ ሐምሌ 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You