ቅዱስ አማኑኤል ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አንጋፋና በሃገሪቱ የተሟላ የአእምሮ ህክምና አገልግሎት የሚሰጥ ብቸኛ ተቋም መሆኑ ይታወቃል። በአሁኑ ወቅትም ሆስፒታሉ ከህክምናው ጎን ለጎን የአእምሮ ጤና ክብካቤን ለማጎልበት የማህበረሰብ አገልግሎቶች፣ የአጭር ጊዜና የረጅም ጊዜ ስልጠናዎችን ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመቆራኘት እየሰጠ ይገኛል።
ሆስፒታሉ ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2011 ዓ.ም ድረስ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በተቀናጀ ክሊኒካልና የህብረተሰብ አቀፍ አእምሮ ጤና አጠባበቅ በሁለተኛ ዲግሪ 200 ተማሪዎችን አሰልጥኖ ያስመረቀ ሲሆን ዘንድሮም ለ10ኛ ግዜ 25 ተማሪዎችን በዚሁ መስክ አሰልጥኖ አስመርቋል። በአእምሮ ጤና ህክምና ዘርፍ ያሉ ባለሙያዎችን በማሰልጠን ረገድ ሆስፒታሉ እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ ቢሆንም ቁጥሩ አሁንም በቂ እንዳልሆነ ብዙዎች ይስማማሉ።
አቶ ያደታ አለማየሁ በዘንድሮው ዓመት በተቀናጀ ክሊኒካልና የህብረተሰብ አቀፍ አእምሮ ጤና አጠባበቅ በሁለተኛ ዲግሪ ከተመረቁ ተማሪዎች ውስጥ አንዱ ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት 27 ከመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ በየደረጃው የአእምሮ ህመም እንዳለበት ጥናቶች ያሳያሉ። ይሁንና ለዚህ ሁሉ ታማሚ የሚመጥንና በአእምሮ ጤና ላይ የሰለጠነ የህክምና ባለሙያ የለም። የህክምና አገልግሎቱም ቢሆን ውስንነቶች ይታዩበታል። በመሆኑም በዘርፉ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን ቁጥር በየጊዜው ማሳደግና የህክምና አገልግሎቱንም ማስፋት ያስፈልጋል። ህብረተሰቡም በህክምናው ዙሪያ በቂ ግንዛቤ ስለሌለው የሕክምና አገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ግንዛቤውን ማስፋት ይገባል።
አቶ ገብረመስቀል መሳፍንትም በዘንድሮው ዓመት በዚሁ የአእምሮ ህክምና ዘርፍ የሁለተኛ ዲግሪ ተመራቂ ተማሪ ሲሆኑ የአእምሮ ጤና በማህበረሰቡ ብቻ ሳይሆን በመንግስትም ጭምር የሚሰጠው ትኩረት እጅግ ያነሰ መሆኑን ያመለክታሉ። የአእምሮ ጤና በመንግስት በኩል ልዩ ትኩረት እንዲያገኝና በዘርፉ የሰለጠኑ ባለሙያዎችም ወደ ማህበረሰቡ ሰርፀው በመግባት በአእምሮ ጤና ዙሪያ ያለውን ግንዛቤ እንዲያሰፉ ከፍተኛ ጥረት ሊደረግ እንደሚገባም ያሳስባሉ። በዘርፉ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን በማፍራት ረገድ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባም ያሰምራሉ።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር አስራት አፀደወይን እንደሚሉት በሃገሪቱ የአእምሮ ጤና ችግር ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መጥቷል። በአእምሮ ጤና የሰለጠኑ ባለሙያዎች ቁጥርም አነስተኛ ከመሆኑ አኳያ የትምህርት ተቋማትና የዘርፉ ባለሙያዎች ብዙ መስራት ይጠበቅባቸዋል። በዚህ ረገድም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከቅድመ ምረቃ እስከ ድህረ ምረቃ በዘርፉ ተማሪዎችን እያሰለጠነ ይገኛል። ከ2002 ዓ.ም ጀምሮም ከቅዱስ አማኑኤል ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ጋር በመሆን በተቀናጀ ክሊኒካልና የህብረተሰብ አቀፍ አእምሮ ጤና አጠባበቅ በሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን እያሰለጠነ ይገኛል።
በዚህ መልኩ የተወሰኑ ባለሙያዎችን ማፍራት ቢቻልም ካለው ችግር አኳያ ግን በአሁኑ ወቅት ያለው የባለሙያዎች ቁጥር በቂ አይደለም። ይህ በመሆኑም ዩኒቨርሲቲው የቅበላ አቅሙን በማሳደግ በዘርፉ ሰልጥነው የሚወጡ ባለሙያዎችን ቁጥር ማሳደግ ይጠበቅበታል። ሌሎች አቻ የትምህርት ተቋማትም ባላቸው ሃብትና የሰው ሃይል ልክ የዘርፉን ችግር በመገንዘብ ባለሙያዎችን የመፍራቱን ስራ መቀጠል ይኖርባቸዋል።
እንደ ፕሬዝዳንቱ ገለፃ ካለው የሀብት ውስንነት አኳያና ትምህርቱ ከንድፈ ሃሳብ በተጨማሪ የተግባር ልምምድንም የሚጠይቅ በመሆኑና ተማሪዎች ለሚሰሩት ጥናት የአማካሪዎች ቁጥር አናሳ መሆን የዩኒቨርሲቲው የቅበላ አቅም በዓመት ከሃያ ተማሪዎች አይበልጥም። ይሁንና በየዓመቱ ዩኒቨርሲቲውን የሚቀላቀሉ ተማሪዎችን በእውቀት፣ በክህሎትና በአመለካከት ቀርፆ የማውጣት ስራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል።
የቅዱስ አማኑኤል ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር ኢዳኦ ፈጆ በበኩላቸው እንደሚገልፁት ሆስፒታሉ ከ1979 ዓ.ም ጀምሮ ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር በመተባበር 469 የሚሆኑ የአእምሮ ህክምና ነርሶችን በአድቫንስድ ዲፕሎማ ፕሮግራም አስተምሮ በማስመረቅ በመላው ሀገሪቱ በሚገኙ ከ57 በላይ የጤና ተቋማት ውስጥ ተመድበው አገልግሎት እንዲሰጥ አድርጓል። ከ2002 ዓ.ም እስካሁን ድረስ ደግሞ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በአስር ዙር በተቀናጀ የክሊኒካልና ህብረተሰብ አቀፍ አእምሮ ጤና በሁለተኛ ዲግሪ 245 ተማሪዎችን አስመርቋል። በተመሳሳይም ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋርም እየሰራ ይገኛል።
እንደ ዋና ስራ አስኪያጁ ገለፃ ሆስፒታሉ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያስመረቃቸው ባለሙያዎች በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የአእምሮ ህክምና ትምህርት ዲፓርትመንቶችን ከፍተው በማሰልጠን በዘርፉ በርካታ የሰለጠነ የሰው ሃይል እንዲኖር የራሳቸውን አስተዋፅኦ በማበርከት ላይ ናቸው። ይሁንና በአሁኑ ወቅት ከሚታየው የአእምሮ ጤና ችግር አኳያ ባለሙያዎችን በብዛትና በጥራት የማፍራቱ ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። ሌሎች የህክምና ትምህርት ተቋማትም ከሌሎች የጤና ዘርፍ ትምህርት ክፍሎች እኩል ለአእምሮ ጤናም ትኩረት በመስጠት ባለሙያዎችን ሊያፈሩ ይገባል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 18/2012
አስናቀ ፀጋዬ