ዛሬ ዛሬ ከስርዓተ ፆታ ጋር በተያያዘ የብዥታ ችግር እንደሌለ ይታወቃል። ይህ ርዕሰ ጉዳይ በተለያዩ አጋጣሚዎች ይነሳል። በመሆኑም በጉዳዮቹ ላይ ምን እየተሰራ እንደሆነ ከመግለፅ ውጪ ጉዳዮቹን የማብራራት አካሄድ አንከተልም ማለት ነው።
መንግስት በትምህርት ሚኒስቴር አማካኝነት በሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የስርዓተ ፆታን ጉዳይ ጉዳዬ ብሎ የሚሰራ ዳይሬክቶሬት እንዲቋቋም በወሰነው መሰረት ተቋቁመው በዳይሬክተር የሀላፊነት ደረጃ በመመራት የተለያዩና ስርዓተ ፆታን፤ በተለይም ሴት ተማሪዎችን የተመለከቱ ስራዎችን መስራት ከጀመሩ ሰነባብተዋል።
የስርዓተ-ፆታ ጉዳይ በአንድ ወቅት የአንድ ወገን ጉዳይ ብቻ ተደርጎ የሚወሰድበት አተያይ ነበር። ይህም መነሻው የሴቶች የ“መብታችን ይከበር” ንቅናቄ (Feminism) ይዞት የተነሳው አላማ ሲሆን አሁን አሁን ግን ሁለቱንም ስርዓተ-ፆታ አባላት የሚያካትት መሆኑ ግንዛቤን ላይ የተደረሰበት ጉዳይ ነው። በመሆኑም በአራችን የዩኒቨርሲቲዎች እየተሰሩ ያሉ ስርዓተ ፆታን የተመለከቱ ተግባራት ሁለቱንም ፆታዎች ባካተተ መልኩ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።
በየትኛውም አቅጣጫ ብንመለከተው ከስርዓተ ፆታ ጋር በተያያዙ የሚፈፀሙ በርካታ ኢፍትሀዊና ኢሰብአዊ ድርጊቶች መኖራቸውን እንመለከታለን። ፆታዊ ጥቃት/ትንኮሳ፣ አስገድዶ መድፈር፣ የኢኮኖሚ የበላይ/የበታችነት፣ ያለ እድሜ ጋብቻ፣ የትምህርት እድል ማግኘት/ማጣት፣ የፖለቲካ ተሳትፎና የስልጣን ክፍፍል . . . ጥቂቶቹ ናቸው። በመሆኑም ነው እነዚህን ለማስቀረት በአለም አቀፍ ደረጃ እየተሰራ ያለው። እኛም ጋር ይሄው አሰራር (የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ ካቢኔን 50/50 ያስቧል) ያለ ሲሆን በየተቋማትና ማህበራዊ ዘርፎች ተገቢው ቦታ፣ ጊዜ፣ በጀትና የሰው ሀይል ተመድቦለት እየተሰራ ይገኛል።
ከእነዚህ ተቋማት አንዱ በአገራችን ያሉት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት (ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች) ሲሆኑ በእነዚህ ተቋማት ስርዓተ-ፆታን፤ በተለይም የስርዓተ ፆታ እኩልነትን ከማስፈን አኳያ ምን እየተሰራ ነው? ምንስ ይቀራል? ችግሮቹስ ምን ምንድን ናቸው? የሚሉትን በተመለከተ ጅማ እና ደብረ ብርሀን ዩኒቨርሲቲዎችን ማሳያ በማድረግ እንመለከታለን።
ቅኝታችንን የጀመርነው ከጂማ ዩኒቨርሲቲ ሲሆን ያነጋገርናቸውም በዩኒቨርሲቲው የፎክለር መምህርና የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ዳይሬክተር የሆኑትን ዶ/ር አስናቀች ደምሴን ነበር። ዶ/ር አስናቀች እንደሚናገሩት በትምህርት ሚኒስቴር አማካኝነት በየዩኒቨርሲቲዎች የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት እንዲቋቋም መወሰኑን ተከትሎ በጂማ ዩኒቨርሲቲ የተቋቋመው ይህ ዳይሬክቶሬት በርካታ ስራዎችን ያከናወነ ሲሆን አሁንም በእቅድ ይዞ ልዩ ልዩ ስራዎችን እየሰራና ተማሪዎችን እያገለገለ ይገኛል።
እንደ ዳይሬክተሯ ገለፃ ከሆነ በዩኒቨርሲቲ ሴት ተማሪዎች በኩል የሚስተዋሉ በርካታ ችግሮች ያሉ ሲሆን ከኤች.አይቪ/ኤድስ ስርጭትና ጥቃት አኳያ የግንዛቤ ክፍተት መኖሩ፣ የአንዳንድ ሴት ተማሪዎች የኢኮኖሚ አቅም ዝቅተኛ መሆን፣ ከሴትነት ተፈጥሯዊነት አኳያ የሚከሰቱና የወር አበባን የመሳሰሉ ክስተቶችን ለማስተናገድ ያለው ሁኔታ ምቹ አለመሆን ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
ዶክተር አስናቀች እንደሚሉት ድሮም የነበረው አድሎኣዊ ስርአት አሁንም አለ። ይህ ደግሞ በሴቶች ላይ የራሱ ተፅእኖ ሲፈጥር መቆየቱ ይታወቃል። በመሆኑም ይህንን በታሪክ አጋጣሚ የተፈጠረን ለወንድ ያደላና ሴቶችን ሲጨቁን የነበረ ሁኔታ መቀየር አስፈላጊ መሆኑ ስለታመነበት በዚያው አኳያ እየተሰራ ይገኛል።
ሴት ተማሪዎች በርካታ ችግሮች አሉባቸው የሚሉት ደክተር አስናቀች አንዱ በተለያዩ ምክንያቶች የግንዛቤ ችግር መኖሩ እንደሆነ ይናገራሉ። በተለይ ከገጠር አካባቢ የሚመጡ ተማሪዎች ለብዙ ነገር እንግዳ ስለሚሆኑ ግርታ ሲፈጠር ይታያል። ከጊዜ አጠቃቀም፣ አጠናን ዘዴ፣ ትምህርት አቀባበልና በመሳሰሉት አካባቢዎች ችግሮች አሉባቸው። በመሆኑም እነዚህን ሁሉ ለመፍታት እየተሰራ ነው።
በተለይ የሴት ተማሪዎች ቁጥር ከወንዶች ጋር ሲነፃፀር በጣም አነስተኛ የነበረ ሲሆን አሁን ግን እየተሻለ በመምጣት ላይ እንደሆነ የሚናገሩት ዶ/ር አስናቀች ከአራት አመት በፊት 25 በመቶ የነበረው በ2011ዓ.ም 32 በመቶ መድረሱን፤ በዩኒቨርሲቲው የሴት መምህራን ቁጥርም ከነበረበት 13 በመቶ ወደ 18 በመቶ ማደጉን ገልፀዋል።
የሴት ተማሪዎች አካዳሚያዊ ጥንካሬን በተመለከተም እየተሻሻለ በመምጣት ላይ እንደሆነና ሴቶች ከወንዶች እኩል እየተወዳደሩ የሚያሸንፉበትና ወደ ስራ አለም የሚቀላቀሉበት፣ በተለያዩ ዘርፎችም በቀዳሚነት ተሸላሚ የሚሆኑበት ጊዜ በርካታ መሆኑን የሚናገሩት ዳይሬክተሯ በ2010 ዓ.ም በተደረገ ውድድር የ19 ሴት ተማሪዎችን ስኬት በምሳሌነት አቅርበዋል።
እንደስርዓተ ፆታ ዳይሬክቶሬትነቱ ወንዶችንም ያገለግላል የሚሉት ዶ/ር አስናቀች በተለይ ለፎቶኮፒ፣ ማባዥና ለመሳሰሉት እጥረት ላለባቸው የፋይናንስ ድጎማ፤ የግንዛቤም ሆነ አካባቢያዊ እንግድነት የሚያጋጥማቸው ተማሪዎች አስፈላጊውን ምክርና አገልግሎት ሁሉ እንደሚያገኙም ተናግረዋል።
እንደ ዶ/ር አስናቀች ማብራሪያ በጅማ ዩኒቨርሲቲ እየተደረገ ያለው በተለይ የሴት ተማሪዎችን ችግሮች የመፍታት እንቅስቃሴ አበረታች ሲሆን ከኤች.አይቪ/ኤድስ ጀምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ወቅታዊ ግንዛቤን እንዲጨብጡ በተለያዩ መድረኮች ውይይት ይደረጋል፤ ስልጠናዎች ይሰጣሉ፤ በግል (በቢሮ) በመወያየት አስፈለጊው የምክርና ድጋፍ አገልግሎት ይሰጣል።
የደብረ ብርሀን ዩኒቨርሲቲ የሴቶችና ህፃናት ዘርፍ ቡድን መሪ ወይዘሮ አስቴር በበኩላቸው ዳይሬክቶሬቱ አደረጃጀቱን ቀይሮ በአዲስ መልክ የተደራጀው ከ2011 አ.ም ጀምሮ ሲሆን በርካታ ተግባራትንም አከናውኗል። በተለይ ሴት ተማሪዎች ከተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች ስለሚመጡ ግር የሚላቸውና የሚደናገጡ፣ የሚፈሩና ላልተፈለገ ነገር የሚጋለጡባቸው ሁኔታዎች እንዳይከሰቱ ገና ከመምጫቸው ጀምሮ የእንኳን ደህና መጣችሁ ፕሮግራም ይዘጋጃል። በዝግጅቱ አማካኝነትም የተለያዩ ግንዛቤ የማስጨበጫ ስራዎች ይሰራሉ።
በደብረ ብርሀን ዩኒቨርሲቲ የህይወት ክሂሎት (Life skill) ለሁሉም ተማሪዎች ይሰጣል የሚሉት ወይዘሮ አስቴር ይህም ተማሪዎችን እንዴት ከሌላው ተማሪ ጋር አብረው መኖር፣ መስራት፣ መማር ወዘተ እንዳለባቸው፤ በትምህርታቸው እንዴት ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ፤ የአጠናን ዘዴን እና የመሳሰሉትን በተመለከተ ግንዛቤያቸውን በማዳበር ተጠቃሚ እያደረጋቸው ይገኛል ብለዋል።
ለሴት ተማሪዎች ከንፅህና መጠበቂያ ጀምሮ የገንዘብ ድጋፍና የምክር አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን ኤች.አይቪ/ኤድስ፣ የስነተዋልዶ (አልፎ አልፎ እርግዝና ስለሚያጋጥማቸውና ህገወጥ ውርጃም ስለሚከሰት)፣ የጊዜ አጠቃቀምና አጠናን ዘዴንና ተዛማጅ ጉዳዮችን በተመለከተ የስነፅሁፍና ሌሎች የተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀት ግንዛቤን የማስጨበጥ ስራዎች አካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን ጨምሮ እንደሚሰጥ ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።
የሴት ተማሪዎችን የትምህርት ተሳትፎ በተመለከተም ገና ሲገቡ 50 በመቶ (አካል ጉዳተኞች 100 ፐርሰንት) ምርጫቸው እንደሚጠበቅላቸው፣ በተለይ ከ2009 አ.ም ጀምሮ ሴቶች 4 ነጥብ በማምጣት የዋንጫ ባለቤት እየሆኑ መምጣት መቻላቸው፣ በሰቃይነት በዩኒቨርሲቲው ለመምህርነት በመቅረት ላይ መሆናቸውን ቡድን መሪዋ የተናገሩ ሲሆን የበለጠ እንዲሰሩ የማጠናከሪያ ትምህርት/ክፍለ ጊዜ እንዳላቸውና “የሴቶች ላይብረሪ”ም እንዳላቸው ገልፀዋል።
ሴት ተማሪዎች ከሚያጋጥሟቸው ችግሮች መካከል የአቻ ግፊት፣ ፆታዊ ትንኮሳና ተያያዥ ጉዳዮች መኖራቸው የጠቀሱት ወይዘሮ አስቴር በችግሮቹ ዙሪያ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው የማድረግ ስራ ያለማቋረጥ እንደሚሰራና ወንድ ተማሪዎችንም በጋራ የማወያየት አሰራር መኖሩንም አስረድተዋል።
አልፎ አልፎ በአጠቃላይ ተማሪዎች በኩል የሚታዩ የስነ ምግባር ችግሮች መኖራቸውን የሚናገሩት ወይዘሮ አስቴር በዳዳ ተማሪዎች ከዚህ አይነቱ ተግባር እንዲቆጠቡ፣ ስራቸው መማር በመሆኑ ትኩረታቸውን ሙሉ ለሙሉ ትምህርታቸው ላይ እንዲያደርጉ፣ ካልተፈለገ አመፅና ረብሻ እንዲርቁ፣ ተምረው እራሳቸውን፣ ቤተሰባቸውንና አገራቸውን የማገዝ አላማቸውን ማሳካት ላይ በርትተው እንዲሰሩ ምክራቸውን ለግሰዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 17/2012
ግርማ መንግሥቴ