አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ይፋ ያደረገው አዲሱ የኢንቨስትመንት መመሪያ ቴክኖሎጂ (‹‹አይ ጋይድ››) ባለሀብቶች ባሉበት ቦታ መረጃ ተደራሽ በማድረግ የኢንቨስትመንት ፍሰቱን ለመጨመር ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ኮሚሽኑ አስታወቀ፡፡
በኮሚሽኑ የኢንፎርሜሸን ቴክኖ ሎጂና መረጃ አስተዳደር ዳይሬክተር ወይዘሮ ሐረገወይን ምሮታው ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፣ አዲሱ መመሪያ ከዚህ ቀደም ለባለሀብቶች በወረቀት ላይ ተፅፎ ሲሰጥ የነበረውን መመሪያ በድረ-ገጽ በኩል መስጠት የሚያስችል በመሆኑ ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ ለመሰማራት የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ለማቀላጠፍ ይረዳል፡፡ ቴክኖሎጂው ከዚህ ቀደም የነበረውን አሠራር በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ በመቀየር ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት መረጃዎችን በቀላሉ እንዲያገኙ ለማድረግ ያግዛል፡፡
እንደርሳቸው ገለፃ፣ አዲሱ ቴክኖሎጂ ባለሀብቶች ወደ ኢንቨስትመንት ከመሰማ ራታቸው አስቀድመው በአገሪቱ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችን፣ ስለሚ ያገኟቸው አገልግሎቶች ምንነት፣ ማሟላት የሚጠበቅባቸውን መስፈርቶች እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ የኢንቨስትመንት መረጃዎችን እንዲያገኙ የሚያስችል ነው፡፡
‹‹ቴክኖሎጂው በኮሚሽኑ፣ በተባ በሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንና በድርጅቱ የንግድና ልማት ኮንፈረንስ ትብብር የተሠራ ነው›› ያሉት ዳይሬክተሯ፣ ከዚህ ቀደም በሰባት የአፍሪካ አገራት ተሞክሮ ውጤታማ ስለመሆኑም ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ አስተ ዳደር እየወሰዳቸው ባሉት የለውጥ እርምጃዎች ምክንያት የኢንቨስትመንት ፍሰቱ እየጨመረ እንደሆነም ወይዘሮ ሐረገወይን ጠቁመዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 19/2011
በአንተነህ ቸሬ