ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም ቢባልም ይህው መስከረም ጠብቶ ጥቅምትን አጋምሰናል፡፡ ጥቅምት አጋማሽ ላይ ግን እጅን አፍ ላይ የሚያስከድን እንዴት ሊሆን ይችላል የሚያስብል ነገር ሰማሁ:: በተለይም ይህ አስገራሚ ነገር እዚሁ ኢትዮጵያ ብሎም አዲስ አበባ መሆኑ ደግሞ ጉዳዩን የበለጠ ለማወቅ ጉጉት አሳደረብኝ፡፡ ስለዚህም ይህ አስደናቂ ጉዳይ ወደ አለበት ወደ ቂርቆስ አካባቢ አመራሁ፡፡
ጉድ የሚያሰኘውን ጉዳይ በአይኔ በብረቱ አየሁት፡፡ ብዙዎቻችን ፎቶ ለመነሳት አዲስ አይደለንም፡፡ ለመታወቂያ፤ ለልደት፤ለሰርግ፤ ለት/ቤት ለስራ ወ.ዘ.ተ ፎቶ ከአንድም ብዙ ጊዜ ተነስተን ይሆናል:: ሆኖም ግን ፎቶውን ያነሱን ባለሙያዎች በአትኩሮት በአይናቸው እየተመለከቱን ፤ ከራስህ አዘንብለሃል፤አንገትህ ተጣሟል፤ ከረቫትህ ተዛንፏል፤ የሸሚዝህ ኮሌታ አልተስተካከለም፤ ፈገግ በል ወዘተ በሚሉ ትዕዛዞች እየታጀብን እኛም እየታዘዝን በፎቶ አማካኝነት አይናችንን በአይናችን አይተናል:: በተነሳናቸውም ፎቶዎች ተደስተናል ፤ ተበሳጭተናል፡፡ ያነሱንንም ባለሙያዎች እንደችሎታቸው አመስግነናል፤ ወቅሰናል፡፡
የዛሬው ፎቶ አንሺያችን ግን ከነዚህ ሁሉ የተለየ ነው፡፡ በአይኑ ሳይመለከተን ፤ፊት ለፊትም ሳያየን፤ ቀይ እንሁን ጠይም ሳይለየን፤ የሸሚዛችን ኮሌታ ሳይጣመም፤ ከረቫታችን ሳይዛነፍ ፤ አንገታችን ሳይንጋደድ ፤ውብና በፈገግታ የተሞላ ፎቶ በእጃችን እንዲደርስ ያደርጋል፡፡ ይህን የሚያደርገው ጥበበኛ ማነው ካላችሁ በኢትዮጵያም ሆነ በተቀረረው ዓለም ብቸኛው አይነስውር ፎቶ አንሺ አብዱ ሀሰን ነው፡፡
አብዱ ሀሰን የዛሬ 30 ዓመት ገደማ ይህችን ዓለም ሲቀላቀል ሁለቱም አይኖቹ አያዩም ነበር፡፡ ሆኖም ተፈጥሮ ብርሃንን ብትነፍገውም ጥበብን ግን አብዝታ ሰጥታዋለች፡፡ አይነ ስውሩ ፎቶ አንሺ አብዱ ሀሰን ሳያይና ሳይመለከት ያልጠቆረ፤ ያልነጣ፤ ያልተዛነፈን ያልተንጋደደ ፎቶ የሚያነሳ ጥበበኛ ነው፡፡ አብዱ ከልጅነቱ ጀምሮ ለፎቶ ጥበብ ልዩ ፍቅር አለው፡፡ ገና በትምህርት ቤት እያለ ጓደኞቹን ፤ ቤተሰቦቹንና የቅርብ ሰዎቹን ባገኘው ካሜራ ሁሉ ያነሳ ነበር::
ገና ከልጅነቱ ካሜራ ፍቅር ጠርቶት ፤ ካሜራ ህይወቴ ብሎ እርሱነቱን ከካሜራ ጋር አቆራኝቷል፡፡ብዙዎችም ቆመው፤ ተቀምጠው፤ ስቀው፤ አኩርፈው፤ ተቃቅፈው ፤ ተለያይተው በአብዱ ካሜራ እራሳቸውን አይተዋል፡፡ ሁሉም ሊባል በሚችል መልኩ በተነሷቸው ፎቶዎች ተደምመዋል፡፡ በተለይም ሰበታ በሚገኘው አይነስውራን ት/ ቤት እያለ የተለያዩ ዝግጅቶችን ፎቶ እያነሳ የትምህርት ቤቱ ቅርስ እንዲሆኑ አድርጓል:: በዚህም በርካታ አድናቆትና ምስጋና ተችሮታል፡፡
‹‹አካል ጉዳተኝነት ከምንም ተግባር አያግድም፤ ካሰቡበት ቦታ መድረስ ይቻላል፤ ዋናው ጥረት ብቻ ነው›› የሚል ብሂል ያለው አብዱ የፎቶ ጥበብ አይናማዎች ብቻ ሳይሆኑ አይነስውራንም ሊጠበቡበት የሚችሉት ሙያ ነው ይላል፡፡ እንዴት ሰው ሳያይና በሚያነሳው ነገር ላይ ሳያነጣጥር ፎቶ በምን መልኩ ሊያነሳ ይችላል የሚለው የብዙዎቻችን ጥያቄ መሆኑ አይቀርም፡፡ አብዱ ግን ለዚህ መልስ አለው፡፡ ‹ልክ አይነ ስውር ያልሆነ ሰው አይኑን ተጠቅሞ ነገሮችን እንደሚያመጣጥን ሁሉ አይነስውራንም ምጣኔ የሚያደርጉት በጆርዋቸው ነው:: በድምጽ አማካኝነት የነገሩን ሁኔታ ይረዱታል፡፡
የነገሩን አመጣጥ፤ አቀማመጥ፤ አረማመድ፤ በአጠቃላይ መሉ ገጽታውን በድምጽ አማካኝነት ይገነዘቡታል:: ፎቶ የሚነሳውን ሰው አቀማመጥ፤ አቋቋም፤ አጠቃላይ ሁኔታና ገጽታ ከሰውዩው ድምጽ መረዳት ይቻላል፡፡ ለዚህ ደግሞ ለአይነ ስውራን ተፈጥሯዊ ሁኔታቸው ይረዳቸዋል:: ጆሯቸው አይን ሆኖ ያገለግላቸዋል፡፡ በድምጽ አማካኝነት ወደ ግራም ሆነ ወደ ፊት ወይም መሃል ላይ ይሁን ሚዛኑን ጠብቆ ማንሳት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ከፍተኛ የሆነ ልምምድና ጥረት ይጠይቃል፡፡ ዝም ብሎ የሚገኝ አይደለም፡፡›› ይለናል ጥበበኛው አብዱ ሀሰን::
አንድ ሰው ፎቶ ሊነሳ ሲመጣ በመጀመሪያ ከሰውየው ጋር በጨዋታ መልክ የሃሳብ ልውውጥ ስለሚደረግ ተነሺው ሰው በሚያወጣው ድምጽ አቅጣጫ አማካኝነት የሰውየውን አቀማመጥም ሆነ አቋቋም ሙሉ ስዕል በአእምሮ ውስጥ እንደሚቀረጽ አብዱ ይናገራል፡፡ አብዱም ሰውየውን አጠቃላይ ሁኔታ በዚህ መልኩ አዕምሮው ውስጥ ከሳለ በኋላ ካሜራውን ወደ ሰውየው በማነጣጠር እና በተገቢው ሁኔታ የካሜራው ፍሬም ውስጥ በማስገባት ፎቶውን ያነሳል፡፡ ይህ ለብዙዎች አደናጋሪና የማይቻል የሚመስለው ነገር ለአብዱ ግን በየቀኑ የሚተገብረው የህይወቱ አካል ከሆነ ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡
አብዱ ሀሰን ዛሬ የ30 ዓመት ወጣትና የሁለት ልጆች አባት ነው፡፡ ከፎቶ ጥበቡ ጎን ለጎንም ትምህርቱን በርትቶ በመማሩ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቋንቋና ስነ ጽሁፍ የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል:: በአሁኑ ወቅትም በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት የሶሻል ሚዲያ በለሙያ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ሙያም የተማረውን ትምህርት ከፎቶ ሙያው ጋር ለማስተሳሰር እንዳስቻለው ይናገራል፡፡ ሶሻል ሚዲያ ፎቶንና ጽሁፍን አንድ ላይ አስተሳስሮ መረጃ የሚሰጥ ሙያ በመሆኑ ለአብዱ ተመችቶታል:: ፎቶዎችን አንስቶ እና ከጽሁፍ ጋር አዋህዶ በየቀኑ ለህብረተሰቡ መረጃ ይሰጣል፡፡
አብዱ ከፎቶ አንሺነቱ በተጨማሪ እንደማንኛውም አይናማ ሰው በኮምፒ ውተር በፍጥነት የመጻፍ ችሎታን አዳብሯል:: በኮፒውተር ላይ መጻፍ ዕይታን የሚጠይቅ ቢሆንም ለአብዱ ግን ይህ ችግር አልሆነበትም:: ጣቶቹን ከኮምፒውተሩ ጋር አዋህዶ በአእምሮ የመጡለትን ሃሳቦች ያፈሳቸዋል፡፡ ሀሳቡ እስካልተገታ ድረስ ማንኛውንም ሀሳብ በፍጥነት መጻፍ ይችላል:: እንዲያውም አይናማ ከሆኑ ሰዎች ይልቅ በፍጥናትና በጥራት ይጽፋል:: ፎቶ የማንሳትና በኮምፒውተር የመጻፍ ችሎታው ተደምረው በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮችን በሶሻል ሚዲያው ላይ ፖስት እንዲያደርግ ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥረውለታል፡፡
ለአይናሞች ብቻ የተተወ የሚመ ስለውንና እና የቴክኖሎጂ ዕውቀትንና የጽሁፍ ክህሎትን አጣምሮ የሚጠይቀውን የሶሻል ሚዲያ ሙያን በውጤታማነት እየከወነው ይገኛል:: በየቀኑም የተለያዩ ሀሳቦችን፤ ድርጊቶችንና ሁነቶችን ከነፎቷቸው ፖስት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ በፌስ ቡክ አማካኝነት ብዙ ተከታዮችን በማፍራቱም ሀሳቡን የሚጋሩት ብዙዎች ናቸው፡፡
ሌላው የአብዱ አስገራሚ ችሎታ ደግሞ በቢሮው ውስጥ ሆነ ቤት ውስጥ የሚበላሹ ኮምፒተሮችን ፤ስቶቭ፤ አሌክትሪክ፤ ኤሌትሪክ ምጣድ፤ የልብስ ማጠቢያ ማሽን ወዘት የመጠገን ብቃቱ ነው፡፡ ማንኛውም የተበላሸ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃ በአብዱ ጥበባዊ ዕጆች ይጠገናሉ፡፡ የአብዱ እጆች ያረፈባቸው የተበላሹ ማሽኖች አፍታም ሳይቆዩ ህይወት ይዘራሉ፡፡ የተበላሹ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች በምን ምክንያት እንደተበላሹ እንከናቸውን መርምሮ፤ ሽቦ ቀጥሎ፤ ኤሌክትሪክ አገናኝቶ፤ ማሽን ፈቶ፤ በታትኖና ገጥሞ ህይወት ይዘራባቸዋል:: ይህን በአይናቸው በብረቱ ያዩ ሰዎች አጃኢብ በማለት በአብዱ ነገር ይገረማሉ ፡፡
ተካልኝ ጌታቸው የአብዱ ስራ ባልደረባ ነው፡፡ እናም የአብዱን ችሎታና ተሰጥዖ ትንግርት ነው ሲል ይገልጸዋል:: ‹‹ኮምፒተር ላይ ሲጽፍ አይናሞችን ያስንቃል:: ፎቶ ከማንሳት አልፎ ካሜራዎች ሲበላሹ ይጠግናል፡፡ የቢሮ ኮምፒተሮች ሲበላሹ የሚጠግናቸው እሱ ነው፡፡ ድምጽህን ሰምቶ ጥሩ ፎቶ ያነሳል፡፡ ብቻ አብዱ የማይሰራው ስራ የለም ፡፡ ለዚህ ነው አብዱ ትንግርት የሆነ ሰው ነው ያልኩት›› ሲል ተካልኝ ምስክርነቱን ይሰጣል፡፡
አብዱ ሀሳቡና ርዕዩ ሩቅ ነው፡፡ ከራስ አልፎ ሀገርን የሚያስጠራ ትልቅ ህልም ሰንቋል፡፡ እስካሁንም አይነ ስውር ሆኖ ፎቶ የሚያነሳ ሰው እንደሌለ አውቃለሁ የሚለው አብዱ በቀጣይ በአይነስውራን ብቻ የታጀበ የፎቶና የቪዲዮ ስቲዲዮ እንዲኖረው ይመኛል፡፡ የቪዲዮና የፎቶግራፍ ሙያዎችን አጣምሮ የያዘ፤ በአይነቱ ዘመናዊ ስቱዲዮ በመገንባት አይነ ስውራን ታሪክ መስራት እንደሚችሉ ለቀሪው አለም የማሳየት ህልም አለው፡፡
በተለይም ይህንን ሀሳብ የሚደግፉ መልካም ሰዎች ከተገኙ ይህንን ሀሳብ ወደ መሬት ለማውረድ የሚከብድ አይደለም ሲል ይደመጣል፡፡ ‹‹ይህንን አስተሳሰብ መደገፍ ማለት በመላው ዓለም የኢትዮጵያን ስም እንዲጠራ የሚያደርግና የመጀመሪያውና በአይነቱ አዲስ የሆነ በአይነ ስውራን ብቻ የሚመራ ስቱዲዮ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ እንዲኖር የሚያደርግ ነው፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ የአለም ሚዲያዎችን ቀልብ የሚስብ በመሆኑ የኢትዮጵያን ስም በበጎ የሚያስነሳና ጎብኝዎችም በስፋት ወደ ሀገራችን እንዲመጡ የሚያደርግ ነው›› ሲል የሃሳቡን ስፋት አጋርቶናል፡፡
አካል ጉዳተኞች ስራ ከማግኘት ጀምሮ ከፍተኛ እንግልት ይደርስባቸዋል፡፡ አካል ጉዳተኞች ሁሉንም ነገር ማድረግ ይችላሉ፤ ከራሳቸውም አልፎ ለሌሎች ይተርፋሉ የሚለው አስተሳሰብ በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ በርካታ ተሰጥዖና ችሎታ ያላቸው አካል ጉዳተኞች ወደ አደባባይ ሳይወጡ ቤታቸው እንዲቀሩ አድርጓል፡፡ አብዱ ሀሰን ግን ይህንን አመለካከት ሰብሮ ተሰጥዖውን ለአደባባይ ማብቃት ችሏል፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 15/2012
እስማኤል አበበ