መደመር ከክስተትነቱ ይልቅ ሂደትነቱ ያመዘነ፣ ከንግግር ይልቅ ተግባር ላይ ያተኮረ፣ ከእኔነት ይልቅ እኛነት ላይ የተመሰረተ ጽነሰ ሃሳብ ነው። ከመደመር የምንጠብቀው ብዙ መልካም ፍሬ እንዳለ ሁሉ የሚያስከፍለንም ዋጋ ቀላል ላይሆን ይችላል። መደመር በግፊት ያለፈቃዳችን የሚጫንበን ቀንበር ሳይሆን በፈቃደኝነትና በደስታ የምንወስደው የኃላፊነት ሸክም ነው። የመደመርን ጽንሰ ሃሳብ በትክክል ለመረዳትና ለመተግበር በመጀመሪያ ትክክለኛ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ተገቢውን መልስ ልናገኝ ይገባል። አለበለዚያ ጭፍን ተደማሪዎች ወይም ድፍን ተቃዋሚዎች ከመሆን ውጪ አማራጭ አይኖረንም። በሁለቱ መካከል ደግሞ እምብዛም ልዩነት ሊኖር አይችልም። መደመርን ከሥር መሠረቱ በመረዳት ቀላል የአተገባበር አቅጣጫን ለመያዝ ከሚረዱን ጥያቄዎች መካከል የሚከተሉት መሠረታዊ ተደርገው ሊወሰዱ ይገባል።
በምን እንደመር (Possibilities) – መደመር በዋናነት የጭማሪ ስሌት ነው። ይህም ምኔን እምኑ ላይ ልደምር የሚለውን ሃሳብ ያጭራል። የመደመር አስተሳሰብ የመጀመሪያው እሳቤ ሁሉም ሰው ለሌላው ሊሰጥና ሊያበረክት የሚችለው ነገር አለው የሚል ነው። ሰው ከበጎ ፈቃዱ፣ በመልካም ቃሉና በሰናይ ግብሩ ሊደመር ይችላል። በጎ ፈቃዱ ካለን መናገርና ማድረግ በማንችልበት ሁኔታ ውስጥ ብንሆን እንኳ ቢያንስ አሉታዊና አፍራሽ ነገሮችን ላለመናገር፣ ላለማድረግና ላለመተባበር መወሰን እንችላለን። ይህ የመደመር ጽንሰ መነሻ መሠረት ነው። የአቋም ድማሮ ባለበት የአቅም መደመርን መፍጠር አያዳግትም።
እንዴት እንደመር (Process) – መደመር አንድም የከፋፈለንንና ያራራቀንን ያለፈ ሰንኮፍ አውጦቶ ለመጣል የሚደረግ ትግል ነው፤ ደግሞም የወደፊቱን ህልውናችንንና ማንነታችንን ወደ ተሻለ ቦታ ለማድረስ አብሮነታችንን መኮትኮትና በግለሰቦች ነፃነትና የሰብእና ልቀት ላይ የተመሰረተን ህብሩን ያለቀቀ ጽኑ ማህበረሰባዊ አንድነትን ለመፍጠር የሚደረግ የእመርታ ሂደት ነው።
ያለፈ ክፉ ፋይሎቻችንን ለአንዴኛ ለመጨረሻ ጊዜ ዘግተን ወደ ሥልጣኔ ከፍታ በእመርታ ለመውጣት የሚረዱንን ተግባሮች ከራስ ወደ ቤተሰብ፣ ከአካባቢ ወደ ሀገር በማስፋፋት፣ ከአህጉራችን ተርፈን ለዓለም ሕዝቦች የምናበረክተውን ስጦታ ወደ ማፍራት በመገስገስ ነው።
ለምን እንደመር (Purpose) – የመደመር ግብና ፍሬው ብዙ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ ባለመደመር ጦስ ከሚመጣ መከፋፈልና ለመጠፋፋት መነሳት፣ ከበቀልና ማለቂያ ከሌለው ግጭት የምንድነው በመደመር ነው። በመደመራችን ትልልቅ ችግሮቻችን ይፈረካከሳሉ፣ ተግዳሮቶቻችን ወደ ዕድል ይቀየራሉ።
በመደመር የናቁንና ለውድቀታችን የሰሩ ኃይሎች ሊያከብሩንና እንደ እኩያ ባልንጀራ ሊያዩን ይጀምራሉ። በመደመር ለየብቻ ሆነን ልንሆንና ልንሰራ ያልቻልናቸውን ነገሮች ባጭር ጊዜና በተሻለ ፍጥነት እንሰራቸዋለን። ብንደመር ሁላችንም እንደተረት ስንሰማት የነበረችውንና የሁላችንም ሕልም የሆነችውን አንዲት የታፈረችና የተከበረች ሰላማዊ ኢትዮጵያ እንገነባለን።
ማን ይደመር (Person) – መደመር ማንንም የሚያገልል ማንንም የሚያስገድድ ሂደት አይደለም። እርቅና ሰላምን የመረጠ፣ ፍቅርና አንድነትን የወደደ ብሎም ለነፃነትና እኩልነት፣ ለብልጽግናና ሰብዓዊነት የቆመና የቆረጠ ሁሉ ተደማሪ ሊሆን ይችላል። የመደመር ሜዳው ሰፊ፣ ዕድሉ ብዙ መንገዱም ልዩ ልዩ ነው። ስለዚህም አልፈልግም አሻፈረኝ ከሚልና ለግል ጥቅሙና አላማው ማስፈጸሚያ ፈልጎ ልደመር ከሚል በቀር የመደመር በር ለሁሉ ክፍት ነው።
መቼ እንደመር (Program) – የመደመር ሃሳብ በክስተትነቱ ያስደመመንን ያህል ተግባራዊነቱ ሂደትና አንዳንዴም እልህ አስጨራሽ መሆኑን መዘንጋት የለብንም። ፈጥኖ በመደመር ስሌት ውስጥ በጭፍን ከመቀላቀል ተረድቶና ሁለንተናን ሰጥቶ ጊዜን ወስዶ መደመር የተሻለ ውጤት ሊኖረው ይችላል። የተደመሩ ሲበዙ መደመሩ እየቀለለ ይመጣል። መደመርን የግዴታ ፖለቲካ ሳይሆን የውዴታ እንቅስቃሴ ብናደርገው ተደማሪዎች በፍጥነትም በቁጥርም ሊበዙ ይችላሉ። ከላይ በመሪዎች ደረጃ፣ ከታችም በማህበረሰብ ደረጃ የመደመር ጽንሰ ሃሳብና ተግባራዊ መንገዶቹ እየተብራሩ ሲመጡ መደመር ሁሉንም የሚስብ ማግኔት ይሆናል። ዛሬ ያለው የመደመር ጅረቶች ተዋህደው ትልቁን ወንዝ የሚፈጥሩበት ጊዜ እስኪመጣ ግን ትዕግስትና የማያቋርጥ ጥረት ይጠይቃል።
የት እንደመር (Platform) – ከሌብነትና ከዘቀጠ ሥራ ጋር መደመር መቀነስ ነው። ከጥላቻና ከጥፋት ጋር መደመር መውረድ ነው። ይቅርታና እርቅ፣ ሰላምና አንድነት፣ በጎነትና ቅንነት፣ መልካም ሥራና ልማት፣ ፍቅርና እኩልነት መግባቢያ ቋንቋና የመደመር ልኬቶች በሆኑበት ቦታ ሁሉ መደመር ያስፈልጋል። በሀገራችን የተፈጠሩትን የመከፋፈል ሰው ሰራሽ ድንበሮች ለማፍረስ፣ በቡድን አስተሳሰብና በስማ በለው የተፈጠሩ የጀማ ጥላቻና ፍረጃን ለማስቀረት በተጀመሩ እንቅስቃሴዎችና ጅማሮዎች ሁሉ መተባበር ትክክለኛው የመደመር ቦታ ነው።
ባንደመርስ (Problems) – መደመር የግልም ሆነ የቡድን ምርጫችን መሆኑ እሙን ነው። ሌላው አማራጭ ደግሞ አለመደመር ሲሆን ያለመደመርን ዳፋና ሰቆቃ በመፍረስ አፋፍ ላይ ሆነን ስላየነው መደመርን አማራጭ የሌለው ምርጫ አድርገን ማየቱ ተገቢ ነው። ከይቅርታ ይልቅ ቂም፣ ከእርቅ ይልቅ በቀል፣ ከፍቅር ይልቅ ጥላቻና ፍርሃት፣ ከሰላምም ይልቅ ጠብ፣ ግጭትና ጦርነት በመደመርና ባለመደመር መሀል ያለውን ልዩነት የሚያሳዩ የምርጫዎቻችን መንገዶች ናቸው።
ውጤታቸውም እንደመንገዱ ሁሉ ብርሃን ከጨለማ እንደሚለይ የተለያዩ ናቸው። ይህም ያለመደመር ውጤቶች ከነፃነት ይልቅ የሰብአዊ መብት ጥሰትና የፍርሃት ኑሮና ሽሽት፣ ከብልጽግና ይልቅ ድህነትና ጉስቁልና፣ ከእኩልነት ይልቅ ኢፍትሃዊነት፣ አድልዎና ቡድንተኝነት ይሆናል። ይህም ወደማያቋጥ መከፋፈልና መፈራረስ የሚያመጣ ጎዳና ሊሆን ይችላል። የመምረጥን ነፃነትና መብትን ባለመደመር ለመግለጽ መሞከር ሌላውን ሳይሆን ራስንም ወደ ጥፋት የሚወስድ አፍራሽ ጎዳና ነው። ይህንን የመደመር ጽንሰ ሃሳብ ከግለሰብ እስከማህበረሰብ፣ ከቤተሰብ እስከሀገር ብሎም አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ አውድና ትርጉም ልንሰጠው እንችላለን።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 15/2012
አብርሃም ተወልደ